“ሬሳው” ነፍስ ዘራ
“ሬሳው” ነፍስ ዘራ
ኢንዶኔዥያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ሐምሌ 17, 1997 በኢንዶኔዥያ የምሽት ዜና ላይ አንድ ለየት ያለ ነገር ተነገረ። በዓለም ትልቅ ከሚባሉት የአበባ ዝርያዎች መካከል አንዱ ማበቡን የሚገልጽ ነበር። የአንድ ተክል ማበብ ይህን ያህል በዜና እስከ መነገር ያደረሰው ምንድን ነው? ተክሉን ልዩ የሚያደርገው በ40 ዓመት ዕድሜው የሚያብበው ለሦስት ወይም ለአራት ጊዜያት ለዚያውም ለሁለት ወይም ለሦስት ቀናት ብቻ መሆኑ ነው። ዜናው ከተነገረ በኋላ ተክሉ በሚገኝበት ቦጎር ቦታኒካል ጋርደን በተባለ ቦታ የጎብኚዎች ቁጥር 50 በመቶ ጨምሯል። እንዲያውም ተክሉን በአንድ ቀን ውስጥ ከ20, 000 የሚበልጡ ሰዎች ጎብኝተውታል!
የዚህ ተክል ስነ እፃዊ ሙሉ ስም አሞርፎፋሉስ ቲታኑም (Amorphophallus titanum) ነው። አንዳንዶች በአጭሩ ቲታን አሩም በማለት የሚጠሩት ሲሆን የአበባው ጠረን የሸተተ ዓሣ ወይም የሞተ አይጥ ስለሚያስታውሳቸው አብዛኞቹ ኢንዶኔዥያውያን ሬሳው አበባ የሚል ስም አውጥተውለታል። ዘር አስተላላፊ የሆኑ ንቦች አበባው ማበቡን የሚያውቁት በዚህ መጥፎ ጠረን አማካኝነት ነው።
ቲታን አሩምን ከሌሎች አበባዎች ልዩ የሚያደርገው ጠረኑ ብቻ ሳይሆን ግዝፈቱም ነው። እድገቱን የጨረሰ ቲታን በጣም ረጅም ከሚባለው የሰው ቁመት ትንሽ መለስ ቢል ነው። ቦጎር ቦታኒካል ጋርደን በተባለው ቦታ የሚገኘው ይህ ተክል ጠቅላላ ቁመቱ 2.5 ሜትር ሲሆን ትልቅ የአበባ ማስቀመጫ የሚመስል 2.6 ሜትር ስፋት ያለው ጥሩምቤ አበባ አውጥቷል። ይህ ግዙፍ አበባ የወጣው 100 ኪሎ ግራም ከሚመዝን ስሬ ግንድ (tuber) ነው!
ቲታን አሩም አንድ ዓይነት አበባ ብቻ ሳይሆን ብዙ ትናንሽ አበባዎች ስለሚያወጣ መጠኑ በጣም ግዙፍ ቢሆንም የዓለም ትልቁ አበባ የሚል ስም ማትረፍ አልቻለም።
ቲታን አሩም መዝሙራዊው “አቤቱ አምላኬ፣ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፣ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም” ሲል የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸውን የሚያሳይ አንድ ማስረጃ ነው።—መዝሙር 40:5