በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቤተሰቦች ሥር የሰደደ በሽታን መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?

ቤተሰቦች ሥር የሰደደ በሽታን መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?

ቤተሰቦች ሥር የሰደደ በሽታን መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?

መቋቋም የሚለው ቃል “ውጥረትን ውጤታማ በሆነ መንገድ የመወጣትና የማሸነፍ ችሎታ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። (ቴበርስ ሳይክሎፔዲክ ሜዲካል ዲክሽነሪ ) ይህም በተወሰነ መጠን ራስን መቆጣጠርና የአእምሮ ሰላም ማግኘት በሚያስችል መንገድ ሥር የሰደደ በሽታ የሚያስከትላቸውን ችግሮች መጋፈጥን ይጨምራል። ሥር የሰደደ በሽታ መላውን ቤተሰብ የሚነካ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ቤተሰቡ በተሳካ ሁኔታ ችግሩን መቋቋም እንዲችል እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል በታማኝነት ፍቅራዊ ድጋፍ መስጠቱ አስፈላጊ ነው። ቤተሰቦች ሥር የሰደደ በሽታን መቋቋም የሚችሉባቸውን አንዳንድ መንገዶች ከዚህ በታች እንመርምር።

እውቀት የሚያስገኘው ጥቅም

አንድን ሥር የሰደደ በሽታ ማዳን አይቻል ይሆናል፤ ሆኖም እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ማወቁ በሽታው በአእምሮና በስሜት ላይ የሚያሳድራቸውን ተጽዕኖዎች ለመቀነስ ይረዳል። ይህም “አዋቂም ሰው ኃይሉን ያበዛል” ከሚለው አንድ ጥንታዊ ምሳሌ ጋር ይስማማል። (ምሳሌ 24:​5) አንድ ቤተሰብ እንዴት መቋቋም እንደሚችል ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው?

የመጀመሪያው እርምጃ ጊዜ ወስዶ ለበሽተኛውና ለቤተሰቡ ሁሉንም ነገር በሚገባ ለማብራራት ፈቃደኛ የሆነ ተግባቢና ጥሩ ድጋፍ የሚሰጥ ሐኪም ማግኘት ነው። “ጥሩ ሐኪም የሚባለው” ይላል ኤ ስፔሽያል ቻይልድ ኢን ዘ ፋሚሊ የተባለው መጽሐፍ “ለመላው ቤተሰብ የሚያስብና ጥሩ የሕክምና ችሎታ ያለው ነው።”

ቀጣዩ እርምጃ ደግሞ ሁኔታው በተቻለ መጠን ሙሉ በሙሉ እስኪገባህ ድረስ ጥያቄዎችን መጠየቅ ነው። ይሁን እንጂ ከሐኪሙ ጋር በምትሆንበት ጊዜ ግራ ልትጋባና ልትጠይቅ ያሰብከው ጥያቄ ሁሉ በቀላሉ ሊጠፋብህ እንደሚችል አስታውስ። ልትጠይቅ ያሰብካቸውን ጥያቄዎች ቀደም ብሎ መጻፉ ለዚህ መፍትሔ ሊሆን ይችላል። በተለይ ደግሞ ሕመሙ ሊያስከትል ስለሚችለው ነገር እና ስለ ሕክምናው እንዲሁም መደረግ ስላለበት ነገር ማወቅ ያስፈልግሃል።​—⁠“አንድ ቤተሰብ ለሐኪሙ ሊያቀርባቸው የሚችላቸው ጥያቄዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

በበሽታው ለተያዘው ልጅ ወንድሞችና እህቶች ጉዳዩን በሚገባ ማስረዳቱም በጣም አስፈላጊ ነው። “ገና ከጅምሩ ምን ነገር እንደተከሰተ ንገሯቸው” በማለት አንዲት እናት ትመክራለች። “ስለ ተከሰተው ነገር ምንም የማያውቁ ከሆነ ከቤተሰቡ እንደተገለሉ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል።”

አንዳንድ ቤተሰቦች በአካባቢያቸው ወደሚገኝ ቤተ መጻሕፍት ወይም የመጽሐፍ መደብር በመሄድ አለዚያም ደግሞ በኢንተርኔት አማካኝነት ምርምር በማድረግ ጠቃሚ መረጃዎችን አልፎ ተርፎም ስለ በሽታው ዝርዝር ማብራሪያዎችን ማግኘት ችለዋል።

በተቻለ መጠን ደስተኛ ሕይወት ለመምራት መጣር

የቤተሰብ አባላት በሽተኛው በተቻለ መጠን ሕይወቱ አስደሳች እንዲሆን እንደሚፈልጉ የታወቀ ነው። በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰውን ኒል ደ ቶይን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የማመንመን ጠባይ ያለው በሽታው አሁንም ድረስ ያበሳጨዋል። የሆነ ሆኖ ከሁሉ ይበልጥ ደስታ የሚሰጠውን ነገር በማድረግ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋውን በአካባቢው ለሚኖሩ ሰዎች በመናገር በወር 70 የሚያክል ሰዓት ያሳልፋል። “በጉባኤ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መስጠትም ውስጣዊ እርካታ ይሰጠኛል” በማለት ይናገራል።

ደስተኛ ሕይወት ፍቅር የማሳየትና የመፈቀር፣ በሚያስደስቱ እንቅስቃሴዎች የመካፈልና ተስፋን ጠብቆ የማቆየት ችሎታን ያጠቃልላል። በሽተኞች ሕመማቸውና የሚደረግላቸው ሕክምና የሚፈቅድላቸውን ያህል ከሕይወታቸው ደስታ ማግኘት ይፈልጋሉ። ሥር የሰደደ በሽታን ለ25 ዓመታት የተቋቋመ ቤተሰብ ያለው አንድ አባት ሲናገር “ወደ አንድ ቦታ ወጣ ማለት እንወዳለን። ይሁን እንጂ ልጃችን አቅሙ ውስን በመሆኑ የእግር ጉዞ አናደርግም። ከዚህ ይልቅ ከባድ እንቅስቃሴ ማድረግ ወደማይጠይቁ አካባቢዎች እንሄዳለን።”

አዎን፣ ሥር የሰደደ በሽታ ያለባቸው ሰዎች በተወሰነ ደረጃ ከሕይወት እርካታ ማግኘት የሚያስችሏቸው ችሎታዎች ይኖሯቸዋል። እንደ ሕመማቸው ሁኔታ ብዙዎቹ የተዋቡ ቦታዎችን በማየትና ማራኪ ድምፆችን በመስማት ሊደሰቱ ይችላሉ። በተለያዩ የሕይወት ዘርፎቻቸው መጠቀም እንደሚችሉ ሆኖ በተሰማቸው መጠን ደስታ የማግኘታቸው አጋጣሚም የዚያኑ ያህል ከፍ እያለ ይሄዳል።

ጎጂ ስሜቶችን መቋቋም

ሥር የሰደደ በሽታን መቋቋም ጎጂ ስሜቶችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ማወቅንም ይጨምራል። ከእነዚህ ስሜቶች መካከል አንዱ ቁጣ ነው። አንድ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች ሊበሳጭ እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ሆኖም ‘ለቁጣ የዘገየን’ እንድንሆንም ይመክረናል። (ምሳሌ 14:​29 NW ) እንዲህ ማድረጉ ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚለው ቁጣ “ውስጥ ውስጡን ሊበላህና እንድታማርር ወይም በኋላ ላይ እንድትጸጸት የሚያደርግ ጎጂ ቃላትን እንድትናገር ሊያደርግህ ይችላል።” ሌላው ቀርቶ አንድ ጊዜ እንኳ በቁጣ መገንፈል የሚያስከትለው ጉዳት እስኪጠገን ድረስ ረዥም ጊዜ ሊወስድ ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ “በቊጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ” የሚል ምክር ይሰጣል። (ኤፌሶን 4:​27) ፀሐይ የምትጠልቅበትን ጊዜ ማዘግየት እንደማንችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በራሳችንና በሌሎች ላይ ጉዳት ማድረሳችን እንዳይራዘም ‘ቁጣችንን’ በቶሎ ለማብረድ እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን። እንዲሁም ቁጣህ መብረዱ ሁኔታውን በተሻለ መንገድ ለመያዝ ይረዳሃል።

እንደ ማንኛውም ቤተሰብ ሁሉ የአንተም ቤተሰብ ከፍተኛ ውጣ ውረድ እንደሚገጥመው ምንም ጥርጥር የለውም። ብዙዎች እርስ በርስ መመካከራቸው ወይም ሩኅሩኅ ለሆነና የሌሎችን ችግር እንደራሱ አድርጎ ለሚመለከት ሰው ምሥጢራቸውን ማካፈላቸው ችግሮቻቸውን በተሻለ መንገድ እንዲቋቋሙ እንደረዳቸው ይናገራሉ። የካትሊን ተሞክሮ ለዚህ ማረጋገጫ ይሆናል። በመጀመሪያ ካንሰር ያለባትን እናቷን፣ ከዚያም ሥር የሰደደ የመንፈስ ጭንቀትና በኋላም የአልዛይመር በሽታ የያዘውን ባለቤቷን ታስታምም ነበር። “ችግሬን ለሚረዱልኝ ወዳጆቼ ሐሳቤን ማካፈሌ እፎይታና መጽናኛ አስገኝቶልኛል” በማለት ተናግራለች። እናቷን ለሁለት ዓመት ያስታመመችው ሮዝሜሪም ከዚህ አባባል ጋር ትስማማለች። “ሁነኛ ለሆነ ወዳጄ የልቤን ማካፈሌ ሚዛኔን እንድጠብቅ ረድቶኛል።”

በምትናገሩበት ጊዜ እንባችሁን መቆጣጠር ቢያቅታችሁ አትደነቁ። “ማልቀሳችሁ የሚሰማችሁን ውጥረትና ሥቃይ የሚያስታግስላችሁ ሲሆን ሐዘናችሁንም እንድትቋቋሙ ይረዳችኋል” በማለት ኤ ስፔሽያል ቻይልድ ኢን ዘ ፋሚሊ የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። *

አዎንታዊ አመለካከት ያዙ

“በሕይወት ለመኖር ያለህ ተስፋ ሕመምህን እንድትታገሥ ይረዳሃል” በማለት ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ጽፏል። (ምሳሌ 18:​14 የ1980 ትርጉም ) በዘመናችን ያሉት ተመራማሪዎች በሽተኞች የሚኖራቸው አስተሳሰብ አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ በሆነ መንገድ በሕክምና በሚያገኙት ውጤት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተገንዝበዋል። ታዲያ አንድ ቤተሰብ የቤተሰቡ አባል ለረዥም ጊዜ በሚቆይ ሕመም እየተሠቃየ እያለ ብሩሕ አመለካከት ሊይዝ የሚችለው እንዴት ነው?

ቤተሰቦች በሽታውን ከናካቴው ችላ ባይሉትም ሊያደርጉ በሚችሏቸው ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ችግሩን በተሻለ መንገድ እንዲቋቋሙ ያስችላቸዋል። “ሁኔታው ሙሉ በሙሉ አሉታዊ አመለካከት ሊያሳድርብህ ይችላል። ሆኖም ያሉህን በርካታ ነገሮች መዘንጋት አይኖርብህም። ሕይወት፣ ቤተሰብና ወዳጆች አሉህ” በማለት አንድ አባት ተናግሯል።

ሥር የሰደደ በሽታ እንደ ቀላል ነገር የሚታይ ባይሆንም እንኳ ጤናማ የሆነ ቀልድ አፍራሽ የሆነ አመለካከትን ለማስወገድ ይረዳናል። ተጨዋች የሆነው ደ ቶይ ለዚህ አባባል ጥሩ ማስረጃ ይሆናል። የኒል ደ ቶይ ታናሽ እህት ኮሌት እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “አንዳንድ ሁኔታዎችን እንዴት መቋቋም እንደምንችል የተማርን በመሆናችን ሌሎችን በጣም ሊያበሳጩ የሚችሉ ነገሮች በእኛ ላይ ሲደርሱ በመሳቅ ማሳለፍ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን ያለውን ውጥረት ለማርገብ ይረዳናል።” መጽሐፍ ቅዱስ “ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል።​—⁠ምሳሌ 17:​22

መንፈሳዊ እሴቶች ወሳኝ ናቸው

ለእውነተኛ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ደህንነት አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ ‘በጸሎትና በምልጃ በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናን ማቅረብ’ ነው። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል የተገባውን የሚከተለውን ውጤት ያስገኛል:- “የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:​6, 7) ሥር የሰደደ በሽታ ያለባቸውን ሁለት ልጆችዋን ለ30 ዓመታት ያህል ያስታመመች አንዲት እናት “ይሖዋ ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጥ ተምረናል። በእርግጥም ደግፎ ያቆማችኋል” በማለት ተናግራለች።

ከዚህም በላይ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ውስጥ ሕመምና ሥቃይ እንደማይኖር በሚናገረው ተስፋ ተጠናክረዋል። (ራእይ 21:​3, 4) “በቤተሰባችን ውስጥ ሥር የሰደደ በሽታ በመከሰቱ ምክንያት ‘አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል’ የሚለው አምላክ የገባው ተስፋ ይበልጥ ትርጉም ያለው ሆኖልናል” በማለት ብራም ይናገራል። እንደ ሌሎች ብዙ ሰዎች ሁሉ የደ ቶይ ቤተሰብም በገነት ውስጥ “የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም” የሚለው ተስፋ ፍጻሜውን የሚያገኝበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃል።​—⁠ኢሳይያስ 33:​24፤ 35:​6

አይዟችሁ። በአሁኑ ጊዜ የሰው ዘሮችን እያንገላታ ያለው ሕመምና ሥቃይ ራሱ በቅርቡ የተሻሉ ሁኔታዎች እንደሚመጡ ከሚያረጋግጡት ማስረጃዎች መካከል የሚመደብ ነው። (ሉቃስ 21:​7, 10, 11) እስከዚያው ድረስ ግን በአሁኑ ጊዜ በርካታ አስታማሚዎችና ሕሙማን በእርግጥም ይሖዋ ‘በመከራችን ሁሉ የሚያጽናናን የርኅራኄ አባትና የመጽናናትም ሁሉ አምላክ’ እንደሆነ ሊመሠክሩ ይችላሉ።​—⁠2 ቆሮንቶስ 1:​3, 4

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 በሽታ በስሜት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ይበልጥ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የየካቲት 8, 1997 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 3-13 ላይ የሚገኘውን “እንክብካቤ ማድረግ የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ መቋቋም” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንድ ቤተሰብ ለሐኪሙ ሊያቀርባቸው የሚችላቸው ጥያቄዎች

• ሕመሙ የሚባባሰው እንዴት ነው? የሚያስከትለው ጉዳትስ ምንድን ነው?

• ምልክቶቹ ምንድን ናቸው? መቆጣጠርስ የሚቻለው እንዴት ነው?

• አማራጭ ሕክምናዎች አሉ?

• የተለያዩ የሕክምና ዘዴዎች ሊያስከትሉ የሚችሉት የጎንዮሽ ጉዳትና አደጋ እንዲሁም የሚያስገኙት ጥቅም ምንድን ነው?

• ሁኔታውን ለማሻሻል ምን ሊደረግ ይቻላል? ምን ነገርስ መወገድ ይኖርበታል?

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጥሩ ድጋፍ መስጠት የምትችለው እንዴት ነው?

አንዳንድ ሰዎች ምን መናገር ወይም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ስለማያውቁ የታመሙ ሰዎችን ከመጠየቅ ወይም እርዳታ ከመስጠት ይታቀባሉ። ሌሎች ደግሞ ጥሩ ነው ብለው ያሰቡትን ነገር ሁሉ በመናገር ቤተሰቡን ከልክ በላይ ሊጫኑና ውጥረቱን ሊያባብሱበት ይችላሉ። ታዲያ አንድ ሰው በግል ጉዳዮቻቸው ውስጥ ሳይገባ ሥር የሰደደ በሽተኛን ለሚንከባከቡ ቤተሰቦች ድጋፍ ሊሰጥ የሚችለው እንዴት ነው?

እንደ ራስህ ችግር አድርገህ አዳምጥ። ያዕቆብ 1:​19 ‘ለመስማት የፈጠናችሁ ሁኑ’ በማለት ይና⁠ገራል። ጥሩ አድማጭ በመሆንና የቤተሰቡ አባላት መናገር ሲፈልጉ እንዲወጣላቸው በማድረግ አሳቢነት አሳይ። ‘የሌላውን ሰው ችግር እንደ ራስህ አድርገህ እንደምትመለከት’ ከተገነዘቡ እንደዚያ ለማድረግ አይከብዳቸውም። (1 ጴጥሮስ 3:​8 NW ) ሁለት ሰዎች ወይም ቤተሰቦች ሥር የሰደደ በሽታ ለሚፈጥረው ሁኔታ አንድ ዓይነት ስሜት እንደማይኖራቸው አስታውስ። ስለዚህ “ስለ በሽታው ወይም ስለ ሁኔታው የተሟላ እውቀት ከሌለህ ምክር ለመስጠት አትሞክር” በማለት እናቷንና በኋላም ሥር የሰደደ በሽታ የያዘውን ባለቤቷን ታስታምም የነበረችው ካትሪን ትናገራለች። (ምሳሌ 10:​19) ስለ ጉዳዩ የምታውቅ ቢሆንም እንኳ በሽተኛውና ቤተሰቡ ምክር እንድትለግሳቸው ላይፈልጉ ወይም የምትሰጣቸውን ምክር ላይቀበሉ ይችላሉ።

ተግባራዊ የሆነ እርዳታ ስጥ። በቤተሰቡ የግል ጉዳይ ውስጥ እንዳትገባ ጥንቃቄ በማድረግ በሚፈልጉህ ጊዜ ሁሉ ከአጠገባቸው አትጥፋ። (1 ቆሮንቶስ 10:​24) በእነዚህ ርዕሶች ላይ የተጠቀሰው ብራም እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ክርስቲያን ወዳጆቻችን ከፍተኛ እርዳታ አድርገውልናል። ለምሳሌ ያህል የሚሼል ጤንነት በመባባሱ ምክንያት ሐኪም ቤት እናድር በነበረበት ጊዜ ከአራት እስከ ስድስት የሚጠጉ ወዳ­ጆቻችን ሌሊቱን ሙሉ አብረውን ያሳልፉ ነበር። እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ ተለይተውን አያውቁም።” የብራም ባለቤት አንም በመጨመር እንዲህ ትላለች:- “ጊዜው ከባድ ቅዝቃዜ የነበረበት የክረምት ወቅት ነበር፤ ለሁለት ሳምንት ያህል በየቀኑ የተለያየ ትኩስ ሾርባ ይመጣልን ነበር። ትኩስ ሾርባና ሞቅ ያለ ፍቅር ተመግበናል።”

አብረሃቸው ጸልይ። አንዳንድ ጊዜ ልታደርግ የምትችለው ነገር እንደሌለ ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ለበሽተኛውና ለቤተሰቦቹ አንድ ዓይነት ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ ማካፈል ወይም ከልብ አብሮ መጸለይ እጅግ ሊያበረታታ ይችላል። (ያዕቆብ 5:​16) “ሥር የሰደደ በሽታ ለያዘው ሰውና ለቤተሰቦቹ በግላችንም ሆነ አብረናቸው መጸለያችን ያለውን ኃይል አቅልሎ መመልከት አይገባም” በማለት በከባድ የመንፈስ ጭንቀት የምትሠቃይ እናት ያለችው የ18 ዓመቱ ኒኮላስ ተናግሯል።

አዎን፣ ትክክለኛ በሆነ መንገድ የተሰጠ ድጋፍ ቤተሰቦች ሥር የሰደደ በሽታ የሚያስከትለውን ውጥረት እንዲቋቋሙ ከፍተኛ እርዳታ ያበረክታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ [“ችግርን ለመጋራት፣” ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ] ይወለዳል” በማለት ሁኔታውን ይገልጸዋል።​—⁠ምሳሌ 17:​17

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በሽተኛው ለሞት በሚቃረብበት ጊዜ

አንዳንድ ቤተሰቦች ሞት አፋፍ ላይ የደረሰውን የቤተሰባቸውን አባል አስመልክተው መነጋገር አይፈልጉም። ይሁን እንጂ ኬሪንግ​—⁠ሃው ቱ ኮፕ የተባለው መጽሐፍ “ምን ነገር ሊከሰት እንደሚችልና ምን ማድረግ እንዳለብህ አስቀድመህ የምታውቅ ከሆነ የሚደርስብህን የድንጋጤ ስሜት ማቅለል ትችላለህ” በማለት ይናገራል። የሚወሰዱት እርምጃዎች እንደየአካባቢው ሕግና ልማድ የሚለያዩ ቢሆኑም ሊሞት የተቃረበን በሽተኛ የሚያስታምም ቤተሰብ ሊያስብባቸው የሚችላቸው አንዳንድ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

አስቀድሞ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች

1. በሽተኛው የሚሞትበት ቀንና ሰዓት እየተቃረበ ሲሄድ ምን ነገር ሊከሰት እንደሚችልና በሌሊት ቢሞት ምን ማድረግ እንደሚገባ ሐኪሙን ጠይቁ።

2. ስለ በሽተኛው ሞት ማወቅ የሚገባቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ያዙ።

3. የተለያዩ የቀብር ሥነ ሥርዓት አማራጮችን ቆም ብላችሁ አስቡ:-

• የበሽተኛው ፍላጎት ምንድን ነው?

• አስከሬኑ እንዲቀበር ነው የሚፈልገው ወይስ እንዲቃጠል? የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚያስፈጽሙ የተለያዩ አካላት የሚያስከፍሉትን ዋጋና የሚሰጡትን አገልግሎት አነፃፅሩ።

• የቀብር ሥነ ሥርዓቱ መፈጸም ያለበት መቼ ነው? ራቅ ካለ ሥፍራ የሚመጡ ሰዎች ለቀብሩ እንዲደርሱ በቂ ጊዜ ስጡ።

• የቀብር ሥነ ሥርዓቱን የሚያስፈጽመው ወይም የቀብር ንግግሩን የሚሰጠው ማን ነው?

• ይህስ የሚከናወነው የት ነው?

4. በሽተኛው በማደንዘዣ ተኝቶ ባለበት ሰዓትም እንኳ ቢሆን በአካባቢው እየተወራ ወይም እየተካሄደ ስላለው ነገር ሊያውቅ ይችላል። እንዲሰማ የማትፈልጉትን ነገር እሱ ፊት እንዳትናገሩ መጠንቀቅ አለባችሁ። ለስለስ ባለ መንገድ በማነጋገርና እጁን ያዝ በማድረግ ልታጽናኑት ትችላላችሁ።

በሽተኛው ሲሞት

ሌሎች ሰዎች ቤተሰቡን ለመርዳት የሚከተሉትን ሊያደርጉ ይችላሉ:-

1. የቤተሰቡ አባላት አስከሬኑ አጠገብ ሆነው ማልቀስ ቢፈልጉ አትከልክሏቸው።

2. ከቤተሰቡ ጋር ሆናችሁ ጸልዩ።

3. ቤተሰቦቹ የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ የሚሯሯጥላቸው ሰው ይፈልጉ ይሆናል:-

• ከሞቱ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ማስረጃዎችን ከሐኪሙ ለማግኘት።

• የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ለሚያስፈጽመው ሰው፣ ለሬሳ ማቆያ ክፍል ወይም ሬሳውን ለሚያቃጥለው አካል ለመንገር።

• ለዘመድ አዝማድና ለወዳጆች ለመንገር። (እንዲህ ብለህ ልትነግር ትችላለህ:- “ስለ [የበሽተኛውን ስም ጠቅሰህ ] ልነግራችሁ ነበር የደወልኩት። እንደምታውቁት [በእንዲህ ዓይነት በሽታ ] ለረጅም ጊዜ ሲሰቃይ ነበር። ሆኖም አሁን [ቦታውንና ጊዜውን ] ጠቅሰህ አርፏል።”)

• መርዶውን በጋዜጣ ማሳወቅ የሚፈልጉ ከሆነ።

4. ቤተሰቡ ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስፈጸም የሚረዳቸው አንድ ሰው አብሯቸው እንዲሆን ይፈልጉ ይሆናል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቤተሰብ አባላት በተቻለ መጠን አስደሳች ሕይወት ለመምራት የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከቤተሰቡ ጋር አብሮ መጸለይ ችግሩን እንዲቋቋሙ ሊረዳቸው ይችላል