ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
“ስብሰባ ላይ ናቸው”
ለትላልቅ ኩባንያዎች ሥራ አስኪያጆች በሚሠሩ 148 ጸሐፊዎች ላይ በተደረገ ጥናት 47 በመቶ የሚሆኑት አለቆቻቸው እንዲዋሹላቸው ጠይቀዋቸው እንደነበረ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል። የቴክሳስ ግዛት የሽያጭ ረዳት ኃላፊ የሆነች ጸሐፊ ለ30 ዓመታት ሥራዋ ላይ ልትቆይ የቻለችው በስልክ ለሚጠይቃት ሰዎች አለቃዋ ቢሮው ውስጥ እያለ “ስብሰባ ላይ ናቸው” ብላ እየዋሸች እንደሆነ ተናግራለች። በተለይ ባልዋ የት እንደሄደ ለምትጠይቅ ሚስት አላውቅም ብሎ መመለስን የመሰለው ውሸት ከባድ ችግር ውስጥ ሊከት ይችላል። አንዲት ጸሐፊ በስልክ ለጠየቃት ሰው ሊላክለት የሚገባው ቼክ ገና እንዳልተላከለት በሐቀኝነት በመናገሯ ከሥራ ተባርራለች።
ወላጆች ግድ ሲኖራቸው
“በአሁኑ ጊዜ ለአንድ ሕፃን የተሳካ የትምህርት ውጤት ማግኘት ቁልፉ ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ትምህርት ግድ ያላቸው መሆኑና ይህንንም በተግባር ማሳየታቸው እንደሆነ የሳይንስ ሊቃውንት ይናገራሉ” ሲል ዘ ቶሮንቶ ስታር አስታወቀ። ስታትስቲክስ ካናዳ እና ሂውማን ሪሶርስስ ደቨሎፕመንት ካናዳ የተባሉት ተቋሞች ዕድሜያቸው ከ4 እስከ 11 የሚደርሱ 23, 000 ካናዳውያን ልጆችን ዕድገትና ጤንነት ከ1994 ጀምሮ ተከታትለዋል። አብዛኞቹ ካናዳውያን ወላጆች በልጆቻቸው ትምህርት፣ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ክፍሎች ንቁ ክትትል እንደሚያደርጉ ሊታወቅ ተችሏል። ዘገባው እንዳመለከተው “በ10 እና በ11 ዓመት ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙ ልጆች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት ወላጆቻቸው ሁልጊዜ ወይም አብዛኛውን ጊዜ በትምህርታቸው ጎበዝ እንዲሆኑ እንደሚያበረታቷቸው” ሲናገሩ 87 በመቶ የሚሆኑት ወላጆች ደግሞ “ከ1ኛ እስከ 3ኛ ክፍል ካሉ ልጆቻቸው ጋር በየቀኑ ቁጭ ብለው ያነብባሉ።” በቶሮንቶ አውራጃ የትምህርት ቦርድ የወላጆች ፕሮግራም አስተዳዳሪ የሆኑት ሜሪ ጎርደን “ባሁኑ ጊዜ ጥሩ ወላጅ ለመሆን የሚያስፈልገው የተማሩ ወይም ሀብታም መሆን ሳይሆን ሁልጊዜ መገኘት፣ ንቁ መሆንና ፍላጎት ማሳየት እንደሆነ አውቀናል።” አክለው ሲናገሩ “አእምሮን የሚያሳድገው እንክብካቤ የተሞላበት ዝምድና ሲሆን ይህ ደግሞ የሚጀምረው ከቤት ነው” ብለዋል።
በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችና ስልክ
በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በስልክ ለረጅም ጊዜ በማውራት የታወቁ ሆነዋል። ፕቺያቹካ የተባለው የፖላንድ መጽሔት እንዳስተዋለው “ለቀልድ ሲሉ ብቻ ወይም ሲሰለቻቸው ስልክ ያነሳሉ።” ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ለምን ያህል ጊዜ ስልኩን እንደያዙ ወይም ምን ያህል ወጪ እንደሚያስከትል አይገነዘቡም። ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? ወጣቱ ቢያንስ ከቴሌፎን ሒሳብ ላይ የተወሰነውን መጠን እንዲከፍል ማድረግ ጥሩ እንደሚሆን መጽሔቱ ሐሳብ ይሰጣል። “ቴሌፎኑ የጋራ መገልገያ መሆኑንና ሌሎች ሰዎችም ሊጠቀሙበት ሊፈልጉ እንደሚችሉ” ለወጣቶቹ ማሳሰብ ጥሩ ሊሆን እንደሚችል መጽሔቱ ያስገነዝባል።
ተኳሽ ጥንዚዛ
“ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸው የፎቶግራፍ መሣሪያዎች ቦምባርዲየር ቢትል የተባለችው የጥንዚዛ ዓይነት በሦስት አጽቄዎች ዓለም ተወዳዳሪ የማይገኝላት ተኳሽ እንድትሆን ያስቻላትን ነገር ሳይንቲስቶች እንዲረዱ እንዳስቻሉ” የለንደኑ ኢንዲፔንደት ጋዜጣ ዘግቧል። ጥንዚዛው በሆዷ ጫፍ ላይ በሚገኙ ጥንድ ጋሻ መሰል ማነጣጠሪያዎች በመጠቀም አነጣጥራ በባለጋራዋ ላይ አሲድ ትወነጭፍና አንድ ሰኮንድ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ታወድመዋለች። በተጨማሪም ይህ ፈሳሽ በራሷ ሰውነት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ስለማያደርስ እንደ ጉንዳን ያሉ አነስተኛ ነፍሳት በሚያጠቋት ጊዜ ጀርባዋን ጨምሮ በአንዳንድ የአካሎቿ ክፍል ላይ በመርጨት ራሷን ከጥቃት ትከላከላለች። በኢታካ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ኮርነል ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ሳይንቲስቶች ጥንዚዛ በእንቅስቃሴ ላይ እያለች ካነሷቸው ፎቶግራፎች የሚከተለውን ተገንዝበዋል:- “የምቢምባርዲየር ጥንዚዛዎች የሆዳቸውን ጫፍ በማዟዟር ማነጣጠር እንደሚችሉ ቢታወቅም ዒላማቸውን አስተካክለው የመምታት ችሎታቸው ይህን ያህል የረቀቀ መሆኑ አልታወቀም ነበር።”
የባሕር ውኃን ከጨው ማጥራት
በደቡብ አውስትራሊያ በአንዲት አነስተኛ ደሴት በሚገኝ የውኃ ማጣሪያ የባሕር ውኃ ወደ መጠጥ ውኃነት በመለወጥ ላይ እንደሆነ ዚ አውስትራሊያን የተባለ ጋዜጣ ዘግቧል። ጨዋማ ውኃ አጣርቶ ለመጠጥነት መገልገል አዲስ ነገር ባይሆንም “ይህ ቴክኖሎጂ ኬሚካል የማይፈልግ በመሆኑ ልዩ እመርታ” እንደሆነ ዘገባው ይገልጻል። በካንጋሮ ደሴት በፔንሽ ለሚገኘው 400 አባላት ያሉት ማኅበረሰብ “የሚያስፈልገውን ውኃ ለማቅረብ የውቅያኖሱ ውኃ ይቀዳና በከፍተኛ ግፊት በብራና መሳይ ነገር እንዲያልፍ ይደረጋል። ያልተጣራው ጨዋማ ውኃ ወደ ባሕር ተመልሶ እንዲገባ ይደረጋል።” በዚህ አዲስ ዘዴ የመጠቀም ከፍተኛ ጉጉት ቢኖርም እስካሁን የታወቀው ውኃን ከጨው የማጣራትን ዘዴ ያህል ባይሆንም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ዘዴ ነው ሲል ዚ አውስትራሊያን ዘግቧል።
ያልበሰለ በቆልት አደገኛነት
የዩናይትድ ስቴትስ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ምግብ ወለድ በሽታዎች
እየጨመሩ እንደመጡ የሚገልጹ ሪፖርቶች ከደረሱት በኋላ ከምግብ ወለድ በሽታዎች ራሱን ለመጠበቅ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ያልበሰለ በቆልት መመገብ እንደሌለበት ማስጠንቀቁን ኤፍ ዲ ኤ ኮንሲውመር ሪፖርት አድርጓል። ብዙ ሰዎች የአልፋልፋ ወይም የማገጥ ወይም የባቄላ በቆልት በጥሬው መብላት ይወዳሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ምግቦች በብዙ አገሮች በባክቴሪያዎች ለመመረዝ ምክንያት እንደሆኑ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ አስታውቋል። በተለይ ትናንሽ ልጆች አረጋውያንና በሽታ የመከላከል አቅማቸው የተዳከመባቸው ሰዎች ለዚህ አደጋ የተጋለጡ ናቸው። ሳይንቲስቶች ለችግሩ መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውን የተለያዩ ዘዴዎች ቢሞክሩም አንዳቸውም ቢሆኑ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ አልሆኑም። ከነዚህ ዘዴዎች መካከል በቆልትን በክሎሪን ወይም በአልኮል ማጠብ ይገኙበታል። ለዚህም ምክንያቱ “ዘሮቹ ለመብቀል በሂደት ላይ በሚሆኑበት ጊዜ የሚፈጠረው እርጥበትና ሙቀት ለባክቴሪያዎቹ መራባት አመቺ ሁኔታ ስለሚፈጥር” እንደሆነ ታይምስ ገልጿል።የለንደን ቋንቋዎች
በእንግሊዝ ዋና ከተማ በለንደን የሚኖሩ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚናገሯቸው ቋንቋዎች ቢያንስ 307 እንደሚደርስ ዘ ታይምስ የተባለው የዚህችው ከተማ ጋዜጣ አስታውቋል። ባሁኑ ጊዜ በለንደን ከተማ በሚነገሩት ቋንቋዎች ላይ የተደረገውን የመጀመሪያ ጥናት ሪፖርት ካዘጋጁት ሰዎች አንዱ የሆኑት ዶክተር ፊሊፕ ቤከር በቋንቋዎቹ ብዛት ተገርመዋል። “ባሁኑ ጊዜ ለንደን በቋንቋዎች ብዛት ከኒው ዮርክ እንኳን እንደምትበልጥና ከዓለም የአንደኛነቱን ቦታ እንደያዘች እርግጠኛ ለመሆን ችለናል።” የቋንቋዎቹ ብዛት ቢያንስ 307 ሲሆን ይህ አኃዝ በመቶ የሚቆጠሩ ቀበሌኛዎችን አይጨምርም። በከተማይቱ ውስጥ ከሚገኙት 850, 000 ተማሪዎች መካከል እቤታቸው በእንግሊዝኛ የሚናገሩት ሁለት ሦስተኛው የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ከውጭ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል በቁጥር የሚበዙት ከሕንድ ንዑስ አሕጉር የመጡ ናቸው። ቢያንስ 100 የሚደርሱ የአፍሪካ ቋንቋዎች ይነገራሉ። በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ብቻ ተማሪዎች 58 ቋንቋዎች ይናገራሉ።
የፈንገስ ጥቃት!
በእግር ጣቶችና በውስጥ እግር ላይ በሚፈጠር የፈንገስ ኢንፌክሽን ምክንያት የሚፈጠረው ጮቅ በጀርመን አገር በከፍተኛ ፍጥነት በመዛመት ላይ እንደሚገኝ ዳር ስፒገል የተባለው የዜና መጽሔት ዘግቧል። በጀርመን አገር ከ5 ሰዎች አንዱ ጮቅ እንደሚኖርበት ሲገመት በሌሎች አገሮች ያለው ሁኔታ ከዚህ ሊከፋ እንደሚችል ይታሰባል። በፈንገሱ የመለከፍ አጋጣሚ የሚበዛው እንደ ሳውና፣ መዋኛና ሃይማኖታዊ ሕንፃዎች ባሉ የተከለሉና ሰዎች ባዶ እግራቸውን በሚሄዱባቸው ቦታዎች ነው። የፈንገሶቹ ውጪያዊ ሽፋን በጣም ጠንካራ በመሆኑ የእግር ማጽጃ መሣሪያዎች ወይም ረዥም ጊዜ የማይቆይባቸው የኬሚካል መታጠቢያ ሳህኖች አብዛኛውን ጊዜ በሽታውን ከማስወገድ ይልቅ ያሰራጩታል። ታዲያ እንዴት እግርህን መጠበቅ ትችላለህ? የፈንገስ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሃንስ ዮርገን ቲየትዝ ሰዎች ባዶ እግራቸውን መሄድ በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ሁሉ ነጠላ ጫማ አድርጎ መሄድን ይመክራሉ። ከሁሉም በላይ የሚጠቅመው ደግሞ እግርን በደንብ አድርጎ ማድረቅ ነው። እግሮችን በተለይም በጣቶች መካከል ያለውን ቦታ በደንብ ማድረቅ ፈንገሶቹ ሥር ሰድደው እንዳይራቡ ይረዳል።
ብስጭት በወጥ ቤት
“የረቀቀና የተወሳሰበ ቴክኖሎጂ ያፈራቸው የወጥ ቤት መሣሪያዎች እየበዙ በመምጣታቸው ለወጥ ቤት ብስጭት መንስኤ” መሆኑን ዚ ኢንዲፔንደንት የተባለው የለንደን ጋዜጣ ዘግቧል። የቤት እመቤቶች “ለበርካታ ሰዓት የመሣሪያውን መመሪያ ካላነበቡ አንድ ኩባያ ሾርባ በማይክሮዌቭ ምድጃቸው ሊያሞቁ እንደማይችሉ፣ አንድ ጥንድ የእግር ሹራብ ሊያጥቡ እንደማይችሉ ወይም በእንቁላል መምቻ መሣሪያዎች ሊጠቀሙ እንደማይችሉ ሲያውቁ ይበሳጫሉ።” የሥነ ልቦና ሊቃውንት እንደጠቆሙት ዘመናዊው ቴክኖሎጂ የመሣሪያ ፈልሳፊዎች በአንድ ጊዜ ብዙ ዓይነት ተግባር የሚያከናውን መሣሪያ እንዲሠሩ የሚፈቅድላቸው ሲሆን ለዚህም የቪዲዮ ማጫዎችን እንደ ምሳሌ አድርገው ይጠቅሳሉ። በማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ካሪ ኩፐር እንደሚከተለው በማለት ያብራራሉ:- “ሰዎች በየሥራ ቦታቸውና በሌሎች ቦታዎች ከአዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር ተፋጥጠው ስለሚውሉ እቤታቸው ሲደርሱ በሥራ ቦታቸው ያሳለፉትን የማያስታውሳቸው ቀላል ኑሮ ይፈልጋሉ።”
የዓለማችን ግንባር ቀደም ትንባሆ ተጠቃሚ
ቻይና “በትንባሆ ምርትም ሆነ ፍጆታ ከዓለም አንደኛ መሆኗን” ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን ሪፖርት አድርጓል። “1.2 ቢልዮን ከሚደርሰው የቻይና ሕዝብ መካከል 300 ሚልዮን ወንዶችና 20 ሚልዮን ሴቶች ያጨሳሉ።” ከቻይና የበሽታዎች መከላከያ አካዳሚና ቤጂንግ ከሚገኘው የቻይና ማጨስ እና ጤና ማኅበር የተውጣጡ ዶክተሮች ከምዕራባውያን ዶክተሮች ጋር ተቀናጅተው 120, 000 በሚያክሉ ሰዎች ላይ ባካሄዱት ብሔራት አቀፍ ጥናት ያገኙትን ውጤት ይፋ አውጥተዋል። ምን መደምደሚያ ላይ ደረሱ? “ቻይና በትንባሆ ወረርሽኝ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ካሉት ቢያንስ 50 ሚልዮን ቻይናውያን በአጭሩ ይቀጫሉ።” ማጨስ የጀመሩ ቻይናውያን ዕድሜ ከ1984 ወዲህ በሦስት ዓመት በመቀነስ ከ28 ወደ 25 እንደወረደ ሪፖርቱ ያመለክታል። ማጨስ የሳንባ ካንሰርና የልብ በሽታ ሊያስከትል እንደሚችል የሚያውቁት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።