በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመሬት መንቀጥቀጥ!

የመሬት መንቀጥቀጥ!

የመሬት መንቀጥቀጥ!

ታይዋን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

“መብራቱ እየደበዘዘ ሲሄድ ታይፔ በሚገኝ አፓርታማ ዘጠነኛ ፎቅ ላይ ጋደም ብዬ አነብ ነበር። ከዚያም ያለሁበት ክፍል በኃይል መነቃነቅ ጀመረ። አንድ ግዙፍ የሆነ ፍጡር ሕንፃውን ወዲያና ወዲህ የሚያወዛውዘው ይመስል ነበር። ከላይኛው ፎቅ ዕቃዎች ወለሉ ላይ ሲከሰከሱ የሚሰማው ድምፅ ኮርኒሱ ይደረመሳል የሚል ፍርሃት ስላሳደረብኝ ተወርውሬ ጠረጴዛ ሥር ገባሁ። ንቅናቄው ማቆሚያ ያለው አይመስልም ነበር።” ​—⁠በታይዋን የሚኖር ጋዜጠኛ

የመሬት መንቀጥቀጥ። ቃሉ መጠቀሱ ብቻ እንኳ ፍርሃት ያሳድራል። በቅርቡ ደግሞ ቃሉን አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ በተደጋጋሚ ሳትሰማው አትቀርም። የዩናይትድ ስቴትስ ስነመሬታዊ ጥናት እንዳለው ከሆነ በ1999 ከተለመደው ቁጥር በላይ ታላላቅ የመሬት መንቀጥቀጦች የተከሰቱ ሲሆን በዚያ ሳቢያ የሞቱት ሰዎች ቁጥርም ከዓመታዊው አማካኝ አኃዝ በእጥፍ ይበልጥ ነበር።

በ1999 ከደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ሁሉ ከፍተኛው በሁለት ትላልቅ አሕጉራዊ ስፍሃኖች (plates) መጋጠሚያ ላይ በምትገኘው በታይዋን የተከሰተው ነው። በድምሩ ታይዋንን አቋርጠው የሚያልፉ 51 ዝንፈት መስመሮች (fault lines) አሉ። በመሆኑም በዚህች አገር በየዓመቱ 15, 000 የሚሆኑ የመሬት መንቀጥቀጦች የሚከሰቱ መሆኑ ምንም አያስገርምም። ሆኖም የአብዛኞቹ ንቅናቄ በጣም አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ክስተቱ ሳይስተዋል ያልፋል።

በመስከረም 21, 1999 የደረሰው ግን ለየት ያለ ነው። ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ47 ደቂቃ ላይ ታይዋን ኃይለኛ በሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ከመናወጥዋ የተነሳ ፕሬዚዳንት ሊ ደንግ ኋ “በመቶ ዓመት ጊዜ ውስጥ በደሴቲቱ ላይ ከደረሰው ሁሉ የከፋው” ሲሉ ገልጸውታል። የቆየው ለ30 ሴኮንድ ብቻ ቢሆንም በሬክተር መለኪያ 7.6 ተመዝግቧል። * የመሬት መንቀጥቀጡ ጥልቀት 1 ኪሎ ሜትር ብቻ መሆኑ ንቅናቄው ኃይለኛ እንዲሆን አድርጎታል። የመሬት መንቀጥቀጡ እንቅጥቅጣፍ (epicenter) አቅራቢያ የሚኖረው ሊዩ ሱ ሳ “ንቅናቄው ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ከእንቅልፌ ነቃሁ” ሲል ተናግሯል። “የቤት ዕቃዎች፣ ኮርኒሱ ላይ ያለው መብራት ሳይቀር ወድቀው ተሰባበሩ። መሬት ላይ የወዳደቁ ዕቃዎችና የተሰባበሩ ጠርሙሶች በሩን እንዳይከፈት ስላደረጉት መውጫ ቀዳዳ አጣሁ።” ንቅናቄው ከአልጋ ላይ አስፈንጥሮ የጣላት ኋንግ ሹ ሆንግ የገጠማት ችግር ደግሞ የተለየ ነበር። “መብራት ወዲያው በመጥፋቱ አካባቢው ሁሉ ጨለማ ሆነ። እየተደነቃቀፍኩ ወደ ውጭ ወጣሁና ከጎረቤቶቼ ጋር መንገድ ዳር ተቀምጬ ሌሊቱን አነጋሁ። የመሬቱ ንቅናቄ ማቆሚያ ያለው አይመስልም ነበር” ስትል ተናግራለች።

የነፍስ አድን ጥረት

ጎሕ ሲቀድ የመሬት መንቀጥቀጡ ያስከተለው ጥፋት ግልጽ ሆነ። ባለ አንድ ፎቅ ከሆኑ መኖሪያ ቤቶች አንስቶ ብዙ ፎቅ ያላቸው አፓርትመንቶች ድረስ በጥቅሉ 12, 000 የሚያህሉ ሕንፃዎች ፈራርሰዋል። አደጋውን አስመልክቶ ዜና ሲሰራጭ ከ23 አገሮች የተውጣጡ የነፍስ አድን ሥራ ባለሙያዎች በአገሪቱ ያሉ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ለመርዳት ወደ ታይዋን መጡ። በርካታ የአደጋው ሰለባዎች መውጫ አጥተው በፍርስራሾች ክምር ተውጠው ነበር።

የተፈጥሮ አደጋ ከተከሰተ በኋላ የሚኖሩት የመጀመሪያዎቹ 72 ሰዓታት በሕይወት የሚተርፉ ሰዎችን በማግኘት ረገድ ወሳኝ የሆኑ ጊዜያት ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ግን የነፍስ አድን ሠራተኞች አንዳንድ አስገራሚ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል አንድ የስድስት ዓመት ልጅ የነፍስ አድን ሠራተኞች እስኪደርሱለት ድረስ ለ87 ሰዓታት መውጫ አጥቶ ቆይቷል። በታይፔ ደግሞ የነፍስ አድን ሠራተኞች ግዙፍ መሣሪያ ተጠቅመው አንድ ባለ 12 ፎቅ የመኖሪያ ሕንፃ ፍርስራሽ እያጸዱ በነበረበት ወቅት ሳይታሰብ አንድ ወጣት ከፍርስራሹ ውስጥ ብቅ አለ። እሱና ወንድሙ ከአምስት ቀናት በላይ መውጫ አጥተው ፍርስራሽ ውስጥ ከቆዩ በኋላ ከሥቃዩ በሕይወት መትረፍ ችለዋል!

የሚያሳዝነው ግን እያንዳንዱን ሰው ማግኘት ያልተቻለ ከመሆኑም በላይ የነፍስ አድን ሠራተኞች አንዳንድ አሳዛኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል አንድ የቡድን መሪ “ከስምንት ሰዓት በፊት አንድ ልጅ ሲያለቅስ ይሰማን ነበር። በኋላ ላይ ግን ድምፁ ጠፋ” ሲል የተሰማውን ሐዘን ገልጿል። በመጨረሻ ታይዋን ውስጥ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ2, 300 ያለፈ ሲሆን ከ8, 500 የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

አደጋው ያስከተለውን ጉዳት መጋፈጥ

የመሬት መንቀጥቀጡ ቤት አልባ ላደረጋቸው በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች መጠለያ ለመስጠት ከፍተኛ ርብርቦሽ ማድረግ ተጀመረ። መጀመሪያ ላይ አንዳንድ የአደጋው ሰለባዎች ወደ ቤት ለመግባት አመንትተው ነበር። የመጀመሪያው የመሬት መንቀጥቀጥ ከደረሰ በኋላ በነበሩት አሥር ቀናት ውስጥ ወደ 10, 000 የሚጠጉ አነስተኛ ንቅናቄዎች ተመዝግበው ስለነበር አንዳንድ ሰዎች ለምን ወደ ቤት መግባት እንደፈሩ ሊገባን ይችላል! ከደረሱት ንቅናቄዎች መካከል አንደኛው በሬክተር መለኪያ 6.8 የተመዘገበ ሲሆን አስቀድሞ ተናግተው የነበሩትን በርካታ ሕንፃዎች አፈራርሷል።

የሆነ ሆኖ የመልሶ ማቋቋሙ ሥራ አልተቋረጠም። ከውጭ አገር የመጡ የነፍስ አድን ሠራተኞች፣ ቼ ጄ የሚባለው የቡዲስት ቡድን እና የእሳት አደጋ መከላከያ አባላትን ጨምሮ በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጊዜያቸውንና ችሎታቸውን ሥራው ላይ አውለዋል። በመልሶ ማቋቋሙ ሥራ ከተሳተፉት መካከል የይሖዋ ምሥክሮችም ይገኙበታል። ገላትያ 6:​10 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መንፈስ በመከተል ሁለት ግቦችን አወጡ። (1) በእምነት ለሚዛመዷቸው ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማሟላት እና (2) እምነታቸውን የማይጋሯቸውን ሰዎች ጨምሮ ለሁሉም ሰው መልካም ማድረግ ፈልገው ነበር።

በመጀመሪያው ቀን ማብቂያ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ምግብ፣ ውኃ፣ ድንኳንና ከቤት ውጭ ለምግብ ማብሰያ የሚያገለግሉ ዕቃዎችን በጭነት መኪና ያጓጉዙ ነበር። ማንኛውም ዓይነት የመገናኛ መስመር ተቋርጦ ስለነበር አደጋው በደረሰበት አካባቢ ከሚገኙ ስድስት ጉባኤዎች የተው⁠ጣጡ ሽማግሌዎች የእምነት ጓደኞቻቸውንና ዘመዶቻቸውን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችንና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ለማግኘት የተቀናጀ ጥረት አደረጉ። ቤታቸው ለፈረሰባቸው የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ጥሩ ክትትል ለማድረግና ከሁሉም ጋር በቀላሉ መገናኘት እንዲቻል አንድ ላይ ተሰባስበው እንዲቀመጡ ማበረታቻ ተሰጣቸው። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና የታይዋን ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት ማበረታቻ ለመስጠት እያንዳንዱን ቡድንና ጉባኤ እየዞሩ ጎበኙ።

ቀጣዩ እርምጃ ጉዳት የደረሰባቸውን መኖሪያ ቤቶችና የመንግሥት አዳራሾች መጠገን ነበር። እያንዳንዱ ጉባኤ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወንድሞች ስም ዝርዝር አዘጋጀ። ከዚያም የአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴ በሚሰጠው አመራር አስፈላጊውን ጥገና ለማድረግ የፈቃደኛ ሠራተኛ ቡድኖች ተላኩ። የመሬት መንቀጥቀጡ ከደረሰ በኋላ በነበረው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሥራው ሁሉ ተጠናቀቀ።

የይሖዋ ምሥክሮች በእምነት ለማይጋሯቸው ጎረቤቶቻቸውም የእርዳታ እጃቸውን ዘርግተዋል። ለምሳሌ ያህል ምሥክሮቹ ማጽናኛ ለመስጠት ሆስፒታሎችና ሠፈራ ጣቢያዎችን ጎብኝተዋል። በተጨማሪም “የተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም እንዲችል ልጃችሁን መርዳት” በሚል ርዕስ የወጣውን የሰኔ 22, 1996 ንቁ! (እንግሊዝኛ) እትም ፎቶ ኮፒ አድርገው አሰራጭተዋል። ብዙ ሰዎች ይህን ጽሑፍ በማግኘታቸው የተደሰቱ ሲሆን እንደደረሳቸው ወዲያው ማንበብ ጀምረዋል። የይሖዋ ምሥክሮች መንገዶች ሲከፈቱ በመሬት መንቀጥቀጡ ክፉኛ ወደተጎዱ ገለልተኛ ተራራማ አካባቢዎች ቁሳ ቁሶች የያዙ የጭነት መኪናዎችን ልከዋል።

መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ ሰዎች የዚህ የነገሮች ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ‘በልዩ ልዩ ስፍራ’ በሚከሰቱ ‘የምድር መናወጦች’ ተለይተው እንደሚታወቁ ከረጅም ጊዜ በፊት መተንበዩን ይገነዘባሉ። (ማቴዎስ 24:​7) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ ሰላም በሰፈነበት በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሚኖሩ የሰው ልጆች የተፈጥሮ አደጋዎች እንደማያስፈሯቸው ማረጋገጫ ይሰጠናል። በዚያን ጊዜ ምድር ገነት ትሆናለች።​—⁠ኢሳይያስ 65:​17, 21, 23፤ ሉቃስ 23:​43

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 በአንጻሩ በነሐሴ 1999 በቱርክ የደረሰው አሳዛኝ የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር መለኪያ 7.4 የተመዘገበ ሲሆን በሕይወት ላይ ያስከተለው ጉዳት ግን በታይዋን ከደረሰው ቢያንስ በሰባት እጥፍ እንደሚበልጥ ይነገርለታል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች ካምፖች ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ስብሰባዎቻቸውን ያካሂዱ ነበር

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመሬት መንቀጥቀጡ በርካታ መንገዶችን አፈራርሷል

[ምንጭ]

San Hong R-C Picture Company

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

San Hong R-C Picture Company

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Seismogram on pages 2, 23-25: Figure courtesy of the Berkeley Seismological Laboratory