በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጠቃሚ የሆነ ማሰላሰል

ጠቃሚ የሆነ ማሰላሰል

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ጠቃሚ የሆነ ማሰላሰል

“አቤቱ፣ ረድኤቴ መድኃኒቴም፣ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ [“በልቤ የማሰላስለው ነገር፣” NW ] በፊትህ ያማረ ይሁን።”​—⁠መዝሙር 19:​14

“ማሰላሰል” ለአንተ ምን ትርጉም አለው? አንዳንድ የምሥራቃውያን ሃይማኖቶች የሚያስተምሩትን ነገር የምትከተል ከሆነ ማሰላሰል ሐሳብ ወለል ብሎ እንዲታይህ ወይም ልዩ የሆነ የእውቀት ብርሃን እንዲገለጥልህ የሚያደርግ እንደሆነ ታምን ይሆናል። በቡዲዝም እምነት ውስጥ የሚደረገው ማሰላሰል አእምሮን ከማንኛውም ሃሳብ ነጻ ማድረግን ያበረታታል። ሌሎች የማሰላሰል ዓይነቶች ደግሞ አእምሮን “ሁሉን አቀፍ በሆኑት የጥበብ እውነቶች” መሙላትን የሚያበረታቱ እንደሆኑ ይነገራል።

ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማሰላሰል ያለው አመለካከት ከዚህ የተለየ ነው። በምን መንገድ? መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የሚያሰላስልባቸው ነገሮች ስለነበሩት ይስሐቅ ስለተባለ አንድ የ40 ዓመት ሰው የሚናገረውን ታሪክ ተመልከት። ዘፍጥረት 24:​63 “ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር” በማለት ይናገራል። እዚህ ላይ ይስሐቅ አእምሮውን ከማንኛውም ሐሳብ ነጻ አድርጎ ነበር ወይም ለመረዳት በሚከብዱት ‘ሁሉን አቀፍ የጥበብ እውነቶች’ ላይ በማሰላሰል ተመስጦ ነበር የምንልበት ምንም ምክንያት የለም። ይስሐቅ የሚያስብባቸው አንዳንድ ጉዳዮች ነበሩት። ለምሳሌ፣ ስለ ወደፊት ሁኔታው፣ እናቱን ስለማጣቱ ወይም ሚስቱ ማን ልትሆን እንደምትችልና ስለመሳሰሉት ነገሮች እንደሚያስብ እሙን ነው። በጣም አስፈላጊ በሆኑት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ለማሰላሰል የምሽቱን የተወሰነ ጊዜ የተጠቀመ ይመስላል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ማሰላሰል ከቀን ሕልም የበለጠ ነገርን ያመለክታል።

ማሰላሰል ሌላም የሚጨምረው ነገር አለ

የመዝሙራዊውን ዳዊት ምሳሌ ተመልከት። ዳዊት ለመወጣት በጣም አስቸጋሪ የሚመስሉ ችግሮች አጋጥመውት ነበር። ፍጽምና የሌለው ሰው እንደመሆኑ መጠን በትክክለኛው መንገድ ለመጓዝ የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ ነበር። ዳዊት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ጠንካራ እንዲሆን ያስቻለው ምን ነበር? በመዝሙር 19:​14 ላይ እንደተመዘገበው ዳዊት እንዲህ ብሏል:- “አቤቱ፣ ረድኤቴ መድኃኒቴም፣ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ [“በልቤ የማሰላስለው ነገር፣” NW ] በፊትህ ያማረ ይሁን።” እዚህ ላይ “ማሰላሰል” ተብሎ ለተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል መገኛ የሆነው “ከራስ ጋር መነጋገር” የሚል ጥሬ ፍቺ ያለው ቃል ነው። አዎን፣ ዳዊት ስለ ይሖዋ ሥራዎች፣ ተግባሮች፣ ሕጎች እንዲሁም ስለ ጽድቁ ‘ከራሱ ጋር ይነጋገር’ ነበር።​—⁠መዝሙር 143:​5

በተመሳሳይም የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መመደብ የእውነተኛው አምልኮ አንዱ ክፍል እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል አሳስቦአቸዋል:- “እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ።” (ፊልጵስዩስ 4:​8) እርግጥ፣ የሚያንጹ ነገሮችን ለማሰብ ጳውሎስ የተናገራቸው ‘እነዚህ ነገሮች’ ወደ አእምሮአችን የሚገቡበት አጋጣሚ ሊኖር ይገባል። እንዴት?

መዝሙራዊው መልሱን ይሰጠናል። መዝሙር 1:​1, 2 እንዲህ ይላል:- “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፣ . . . በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል።” አዎን፣ መዝሙራዊው የአምላክን ቃል አዘውትሮ ያነብብ ነበር። ከዚህም የተነሣ ስለ ፈጣሪ በተማራቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰል ችሏል።

ማሰላሰል​—⁠በዛሬው ጊዜ

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያለው ዋጋ ከፍተኛ ቢሆንም ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል፣ በጥልቅ ማሰብ ወይም ስላነበብነው ነገር “ከራሳችን ጋር መነጋገር” ይኖርብናል። ከምንመገበው ምግብ ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ምግቡ ከሰውነታችን ጋር መዋሐድ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንም ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ማሰላሰል ይኖርብናል። ትክክለኛው ዓይነት ማሰላሰል አሉታዊ አስተሳሰቦችን ከማስወገድ አልፎ ለችግሮቻችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የመፍትሔ ሐሳቦችን እንድናስተውል ያደርገናል። እንዲህ ያለው ማሰላሰል በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ጭንቀቶች ውጤታማ በሆነ መንገድ መቋቋም እንድንችል ይረዳናል።​—⁠ማቴዎስ 6:​25-32

መዝሙራዊው ዳዊት ማሰላሰል አምላክን በማስደሰት በኩል የሚጫወተውን ሚና ተገንዝቦ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጻድቅ ከንፈሩን እያንቀሳቀሰ ጥበብን ለራሱ ይናገራል።” (መዝሙር 37:​30 NW ) አዎን፣ ማሰላሰል የአንድ ታማኝ አምላኪ መለያ ምልክት ነው። በአምላክ ዓይን እንደ ጻድቅ መቆጠር ትልቅ በረከት ከመሆኑም በላይ መንፈሳዊ ጥቅሞች ያስገኛል። ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 4:​18) ስለሆነም ‘ከንፈሩን እያንቀሳቀሰ ጥበብን ለራሱ የሚናገር’ ታዛዥ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን በማስተዋል ረገድ እድገት እንደሚያደርግ ሊጠብቅ ይችላል።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች በቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶቻቸው ላይ እንዲያሰላስሉ አጥብቆ ይመክራቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ብሎት ነበር:- “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር። ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፣ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።” (1 ጢሞቴዎስ 4:​15, 16) አዎን፣ የምንናገራቸውና የምናደርጋቸው ነገሮች በሌሎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።

ሁላችንም አስፈላጊ ስለሆኑ ጉዳዮች በጥልቅና በትኩረት እንድናስብ የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች እንዳሉን ግልጽ ነው። ቀደም ሲል ስላሳለፍነው ነገር፣ አሁን ስላሉት ጉዳዮችና ስለ ወደፊቱ ሁኔታችን ማሰላሰላችን በጣም አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ከሁሉም በላይ ሐሳባችን ፈጣሪያችን በሆነው በይሖዋ አምላክ ጥበብ ላይ ያተኮረ ከሆነ ማሰላሰላችን ከፍተኛ ደስታ ያመጣልናል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በሐሳብ የተዋጠው ሰው” በሮዲን የተቀረጸ