ፍጥሞ—የአፖካሊፕስ ደሴት
ፍጥሞ—የአፖካሊፕስ ደሴት
ግሪክ የሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ከዕለታት አንድ ቀን የፍጥሞ ደሴት ነዋሪዎች ከኤጂያን ባሕር ባሻገር በሳሞስ ደሴት አቅራቢያ በሚገኝ ተራራ ላይ ብልጭ ድርግም የሚል ብርሃን ተመለከቱ። አንዳንዶች ይህ እንግዳ ነገር እስታቲክ ኤሌክትሪክ እንደሆነ ሲናገሩ በፍጥሞ የሚኖሩ የሃይማኖት ሰዎች ግን በፍጹም አይደለም ብለው ድርቅ አሉ። ሰዎቹ ከ1, 900 ዓመታት ገደማ በፊት በትንሿ እስያ የባሕር ዳርቻ በምትገኘው በዚህች ትንሽ የግሪክ ደሴት ላይ እንደኖረ በሰፊው የሚታወቀው ሰው ሌላ ምልክት እንዳሳያቸው በማመን ይህን ለጎረቤቶቻቸው ለመንገር ሮጡ።
ይህ ታዋቂ ሰው ‘ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ስለ መሠከረ’ የሮማ ንጉሠ ነገሥት ዶሚሺያን ሳይሆን አይቀርም ፍጥሞ ላይ እንዲታሰር ፈረደበት። እዚያም “አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ . . . የምታየውን በመጽሐፍ [ጻፍ]” የሚለውን “የመለከትን ድምፅ የሚመስል” የአምላክን ድምፅ ሰማ።—ራእይ 1:8-11
ይህ ጥቅልል ወይም መጽሐፍ በስርጭቱ እስከ ዛሬ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መጽሐፍ የመጨረሻ ክፍል ሆኗል። አንዳንዶች እስከ አሁን ከቀረቡ የጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ ለመረዳት የሚያስቸግር መጽሐፍ እንደሆነ ይናገራሉ። መጽሐፉ ራእይ ወይም አፖካሊፕስ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ ነው። ጸሐፊው የኢየሱስ ሐዋርያ የነበረው ዮሐንስ ነው። ዮሐንስ የተቀበለው ይህ ራእይ ስለ ክፉው ዓለም የመጨረሻ ጥፋት ስለሚናገር በየዘመናቱ የኖሩ አንባብያንን ትኩረት ስቧል። *
የዛሬይቱ ፍጥሞ
በዶዲክኒስ ደሴቶች ሰሜናዊ ክፍል ራቅ ብላ የምትገኘው ፍጥሞ ይህን መጽሐፍ ለመጻፍ አመቺ ስፍራ እንደሆነች ብዙ ጎብኚዎች ይስማማሉ። እንደ እሳት የሚለበልብ የፀሐይ ሙቀት ባለበት በዚያ የኤጂያን አካባቢ በእሳተ ገሞራ የተፈጠሩ ተረተሮችና አስፈሪ ገደላ ገደሎች እንዲሁም አረንጓዴ የተላበሱ ሸንተረሮችና በአበባ ያሸበረቁ ሜዳዎችን ያካተተ መልክዓ ምድር ይገኛል።
ዛሬ ፍጥሞ ምን እንደምትመስል ለማየት የግሪክ ዋነኛ ወደብ ከሆነው ከፒሪዬቭስ በጀልባ ተሳፈርኩ። ከእኩለ ሌሊት በኋላ ጀልባችን የፍጥሞ ደሴት ወደብና ትልቋ ከተማ ወደሆነችው ስኮላ ባሕረ ሰላጤ ስትደርስ ደመናው እየገፈፈ ሲሄድ ፍንትው ብላ የወጣችው ሙሉ ጨረቃ በፈነጠቀችው ብርሃን ደሴቲቱ ወለል ብላ ታየችን።
በሚቀጥለው ቀን ጠዋት መረር የሚለውን የግሪክ ቡና ፉት እያልኩ ደሴቲቱን ለመጎብኘት ዝግጅቴን አጠናቀቅሁ። ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍራቸው ጥቁር የለበሱ ሴት አያቶች ድክድክ ከሚሉ ሕፃናት ጋር ሲሯሯጡ መመልከት ገና በማለዳው ትኩረቴን የሳበው ትዕይንት ነበር። በአቅራቢያው አንድ ሪዛም ዓሣ አጥማጅ ተቀምጦ ያጠመደውን ዓሣ ለምሳ ለማዘጋጀት ዓሣውን በድንጋይ ላይ ይፈጠፍጣል።
ጀልባ ከመሳፈር ይልቅ ደሴቲቱ ሙሉ በሙሉ እንድትታየኝ ከስኮላ በስተጀርባ ያለው ተራራው ላይ ለመውጣት ወሰንኩ። እጅግ የሚያስደንቅ እይታ ነበር። ባሕሩ ላይ እንደሚንሳፈፍ ትልቅ የመልክዓ ምድር ካርታ ደሴቲቱ ተንጣልላ ትታያለች። ፍጥሞ እንደሰንሰለት እርስ በርስ የተያያዙ ሦስት ትንንሽ ደሴቶች የሚገኙባት ደሴት ናት። እነዚህን ደሴቶች ከሚያገናኙት ጠባብ ልሳነ ምድር አንዱ ስኮላ አጠገብ ይገኛል። ሌላው ደግሞ ሰው በማይኖርበት ዚያኮፍቲ በሚባለው የደሴቲቱ ደቡባዊ ክፍል ይገኛል። “ለሁለት መክፈል” የሚል ትርጉም ያለው ይህ ስም ለዚህ ቦታ መሰጠቱ ተስማሚ ነው። ፍጥሞ 13 ኪሎ ሜትር ያህል ርዝመት ሲኖራት በአንድ ቦታ ላይ ያላት ስፋት ደግሞ የድንጋይ ውርወራ ያህል ነው።
ፈታኝ በሆኑ ጊዜያት ውስጥ ማለፍ
ፍጥሞ ከ4, 000 ዓመት ገደማ በፊት ከትንሿ እስያ የመጡ ሰፋሪዎች በዚያ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እንደ ቅዱስ ቦታ ትታያለች። የመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች በደሴቲቱ በከፍታው ሁለተኛ በሆነው ቦታ ላይ የአደን ሴት አምላክ ለሆነችው ለአርጤምስ ቤተ መቅደስ ሠሩ።
ሐዋርያው ዮሐንስ በፍጥሞ እንደታሰረ በሚታሰብበት በ96 እዘአ ገደማ ደሴቲቱ በሮም ንጉሠ ነገሥት አገዛዝ ሥር ነበረች። በአራተኛው መቶ ዘመን “በክርስቲያናዊው” የባይዛንታይን ንጉሠ ነገሥት ሥር ተጠቃለለች። ከዚያም በሰባተኛውና በአሥረኛው መቶ ዘመን መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ በእስልምና ተጽዕኖ ሥር ወደቀች።
ከጊዜ በኋላ ፍጥሞ ሰው አልባ ጠፍ ሥፍራ ሆነች። ከዚያም በ11ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ አንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ መነኩሴ የአርጤምስ ቤተ መቅደስ በነበረበት ቦታ ላይ “የቅዱስ” ዮሐንስን ገዳም መገንባት ጀመረ። ሰፋሪዎች ቀስ በቀስ ተመልሰው አሁን ድረስ በሆውሮ በገዳሙ ዙሪያ ግጥግጥ ብለው የሚገኙትን ነጫጭ ሾጣጣ ቤቶችን ገነቡ።
በ1800ዎቹ ማብቂያ ላይ አንዳንድ የደሴቲቱ ዜጎች በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ በጣም ውድ ከሆኑት የንግድ መርከቦች መካከል አንዷን ሲገዙ ለአጭር ጊዜ የላቀ ክብር ተቀዳጅታ ነበር። ይህች መርከብ አዲስ ለተከሰተው ወረራ በተዘዋዋሪ መንገድ ምክንያት ሆናለች። በ1970ዎቹ አንዳንድ የዓለም ሃብታሞች በአንድ ወቅት ተረስታ በነበረችው በዚህች ደሴት ላይ ባሉ የሚያማምሩ ግን ርካሽ የመኖሪያ ቤቶች ላይ ዓይናቸውን ጣሉ። እነዚህ ሃብታሞች የባሕር ላይ ነጋዴዎች ንብረት የሆኑትን የድሮ ቤቶች በአዲስ ሞዴል የሠሩላቸው ሲሆን ይህ ሁኔታ ከአዲሱ ወደብ ጋር ተዳምሮ ፍጥሞን የቱሪስት መስህብ አድርጓታል።
ፍጥሞ የቱሪስት እግር የሚበዛባቸው ሌሎች የግሪክ ደሴቶች ከደረሰባቸው ውድመት አምልጣለች። ለዚህ በዋነኛነት የሚጠቀሱት ምክንያቶች የአውሮፕላን ማረፊያ አለመኖሩና መነኮሳት ደሴቲቱ የቅዱሳን መናኸሪያ እንድትሆን በእጅጉ መፈለጋቸው ነው።
ታሪክንና አፈ ታሪክን ማደባለቅ
ባረፍኩበት ሆቴል ያስተናገደኝ ሰው ደሴቲቱን በደንብ እንድጎበኝ በማሰብ ከስኮላ ከተማ ጀርባ የሚያልፍ 400 ዓመታት ያስቆጠረ ኮረኮንች መንገድ እንዳለ ጠቆመኝ። መንገዱ ጥሩ መዓዛ ያለውን የጥድ ደን አቋርጦ የዮሐንስ ዋሻ እንደሆነ ወደሚታመነው ስፍራ እንዲሁም ወደ “ቅዱስ” ዮሐንስ ገዳም ይወስዳል። በከተማው መውጫ በድንጋይ ተሠርቶ በተለሰነ ግድግዳ ላይ በቀይ ቀለም “ኦሂ ስቶ 666” (666ን ፈልጋችሁ አግኙ) የሚል ተጽፎ አየሁ። ይህ ቁጥር በራእይ ውስጥ ከሚገኙ የተሳሳተ ትርጉም ከሚሰጣቸው ምልክቶች አንዱ ነው።
“የቅድስት” አንን ትንሽ የጸሎት ቤት የያዘው የአፖካሊፕሱ ገዳም ዮሐንስ ራእዩን የተቀበለበት እንደሆነ በአፈ ታሪክ የሚነገርለትን ዋሻ መግቢያ እንዲያጠቃልል ተደርጎ የተሠራው በ1090 ነው። ብቻዋን ያለች አንዲት ሴት ተንበርክካ “በቅዱስ” ዮሐንስ ምስል ላይ ቶሞ (ስእለት) ስታገባ አየሁ። ታማኝ ኦርቶዶክሶች ምስሉ ተአምር ሊሠራ ይችላል ብለው ስለሚያምኑ ከብረት የተሠሩ የሰው ምስሎች፣ የሰውነት አካላት፣ ቤቶች ሌላው ቀርቶ መኪናዎችንና ጀልባዎችን ቶሞታ ያገባሉ። በቆሮንቶስ አቅራቢያ በጥንቱ የግሪክ ፈዋሽ አምላክ በአስክሊፐስ ቤተ መቅደስ ውስጥ ከሸክላ የተሠሩ ተመሳሳይ የስእለት ዕቃዎችን ማየቴን አስታውሳለሁ። ይህ እንዲሁ አጋጣሚ ነውን?
ባሕላዊ ቅርሶችና የብራና ጽሑፎች
ወደ “ቅዱስ” ዮሐንስ ገዳም አደባባይ እንደገባሁ ጭልምልም ካለው መተላለፊያ ውስጥ አንድ ተግባቢ ሰው ብቅ አሉ። “ፓፓ ኒኮስ” (አባ ኒክ) ለእኔና ለሌሎች ጥቂት ቱሪስቶች የገዳሙን ንዋየ ቅድሳት በሚያስጎበኙበት ጊዜ በእነዚህ ቅርሶች እንደሚኮሩ ከፊታቸው ይታይ ነበር። የፍጥሞን ሰፊ ቦታ የያዘው ይህ ገዳም በግሪክ ከሚገኙ ገዳማት ሁሉ በጣም ውድ የሆኑ ቅርሳ ቅርሶችን የያዘና በሰፊው የሚታወቅ ቦታ ነው።
ቀዝቀዝ ያለውንና ሻማ ጭል ጭል የሚልበትን የጸሎት ቤት በዝግታ አልፈን የገዳሙ መሥራች ዐጽም ወደ ተቀመጠበት ቦታ ደረስን፤ ከዚያም ከፊሉ በአርጤምስ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ የተገነባው የደናግል ጸሎት ቤት ደረስን። በሙዚየሙ ውስጥ ከዛር ንጉሠ ነገሥት በስጦታ የተገኙ እጅግ ብዙ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮች፤ የባይዛንታይን ንጉሠ ነገሥት አሌክሲስ ቀዳማዊ ኮምኒኑስ የፈረመበት መነኩሴው በ11ኛው መቶ ዘመን ለደሴቲቱ ያበረከቱትን ሥራ፣ የወይን ጠጅ መልክ ባለው ብራና ላይ በቀለም ሳይሆን በብር የተጻፈ የማርቆስ ወንጌል ቁርጥራጭ አየን። ገዳሙ ከዚህ ከቁርጥራጭ በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች ሃይማኖታዊ የብራና ጽሑፎች በብዛት ይገኝበታል።
የደሴቲቱ ልዩ ልዩ ቦታዎች
ደሴቲቱ ተፈጥሯዊ ውበትም ተጎናጽፋለች። ከስኮላ በስተደቡብ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ወጣ ብሎ የተከለለ የባሕር ዳርቻ ይገኛል። የባሕሩ ዳርቻ አምስት ወይም ስድስት ፎቅ ያህል ከፍታ ካለው ትልቅ ቋጥኝ በስተቀር ለጥ ያለ ነው። ካሊካትሱ ማለትም “ዓሣ አውጪ” የሚል ትርጉም ያለው ይህ ቋጥኝ ዋሻዎች የሞሉበት ነው።
ፍጥሞን በደንብ ለማወቅ በጣም ጥሩው መንገድ በውስጧ ብዙ መዘዋወር ነው። ጥናት ባልተደረገበት በካስቴሊ ፍርስራሽ መካከል አናት በምትበሳው ፀሐይ ላይ ተቀምጠህ ከሩቅ የሚሰማውን የበጎች ቃጭልና የእረኞች ዋሽንት ማዳመጥ ትፈልግ ይሆናል። ወይም አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ሻሽ የመሰለ የኤጂያን ባሕር ጭጋግ ሽቅብ ወደ ላይ ሲወጣ በባሕሩ ዳርቻ ተቀምጠህ ጀልባዎች በሚተነው ጭጋግ መካከል ከዓይን ሲሰወሩ ማየት ትፈልግ ይሆናል።
በቆይታዬ የመጨረሻው ቀን ላይ ያየኋት ደም የመሰለችው ጀምበር ስትጠልቅ ከታች የሚታየውን ከተማ ትልቅ አስመሰለችው። መብራት የያዙት ዓሣ አጥማጆች ግሪ ግሪ ተብለው የሚጠሩትን ጀልባዎች እየቀዘፉ በመደዳ ሆነው ከፊት የሚመራቸውን መርከብ ይከተላሉ።
መላዋ ደሴት ደም መስላለች። ቀዝቃዛው ነፋስና ከፍተኛ ማዕበል ግሪ ግሪ የሚባሉትን እነዚህን ጀልባዎች ከወዲያ ወዲህ ያንገላቷቸዋል። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ከባሕሩ የወዲያኛው ጫፍ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ላይ ጀልባዎቹ ዓሣ ከሚያጠምዱበት አካባቢ ተነስተው በፍጥነት እየቀዘፉ ወደ ፓይሬቭስ ሲመጡ አየኋቸው። ሰዎቹ ዓሣዎቹን ለመሳብ ጭል ጭል የሚል ብርሃን ያለውን መብራት ያበራሉ። የዚያን ዕለት ምሽት እነርሱም ሆኑ ከጀርባቸው ያለችው ደሴት ከእይታዬ ቢሰወሩም ግዞተኛው ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት ሆኖ ራእዩን ሲጽፍ የሚያሳየው ስዕል ከአእምሮዬ አልጠፋም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ራእይ —ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የሚለውን መጽሐፍ ተመልከት።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Miranda 2000
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የቅዱስ” ዮሐንስ ገዳም