በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መልካም በረራ!

መልካም በረራ!

መልካም በረራ!

“መንገደኞች አውሮፕላኑን ለቅ​ቀው እንዲወጡ የሚያስገድድ ሁኔታ በሳምንት አንድ ጊዜ ይከሰታል” ሲል ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ ዘግቧል። ምንም እንኳ አብዛኞቹ በቀላል አደጋዎች ወይም በተሳሳተ የማስጠንቀቂያ ደወል ምክንያት የሚከሰቱ ቢሆኑም ቀጥሎ የቀረቡትን ማሳሰቢያዎች ከተከተልክ አውሮፕላኑን ለቅቆ መውጣት ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል:-

ተገቢ ልብስ ልበስ። ምቹ እና እንደልብ መንቀሳቀስ የሚያስችልህን ልብስ ልበስ። ልብሱ በተቻለ መጠን ገላህን በሙሉ የሚሸፍን ሊሆን ይገባል። ሱሪና እጅጌ ሙሉ ልብስ ብትለብስ ጥሩ ነው። ከጥጥ፣ ከሱፍ፣ ከቆዳና ከመሳሰሉት የተፈጥሮ ውጤቶች የተሠሩ ልብሶች ልበስ። እንደ ሬዮን፣ ፖሊስተርና ናይለን ያሉ (በተለይ ሻማ ነክ የሆኑ) ሰው ሠራሽ ጨርቆች በቀላሉ ስለሚቀልጡ በሰውነትህና በእግርህ ላይ ከባድ ቃጠሎ ሊያስከትሉ ይችላሉ።

የአእምሮ ዝግጅት አድርግ። ድንገት አደጋ ቢፈጠር ምን እንደምታደርግ ቀደም ብለህ አስብ። መቀመጫህን ከያዝክ በኋላ ከፊትህም ሆነ ከኋላህ ለአንተ ቅርብ የሆኑትን የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች በዓይንህ ፈልግ። አውሮፕላኑ ከመነሳቱ በፊት ከበረራ አስተናጋጅ የሚሰጠውን መግለጫ አዳምጥ። በአደጋ ጊዜ ከአውሮፕላኑ እንዴት መውጣት እንደሚቻል የሚገልጸውን መመሪያ ከልስ።

አትደናገጥ። ድንገተኛ አደጋ ከተከሰተ ረጋ ብለህ የአውሮፕላኑ ሠራተኞች የሚሰጡትን መመሪያ ተከተል። አውሮፕላኑን ለቅቆ መውጣት አስፈላጊ ከሆነ ንብረትህን ትተህ በጣም ቅርብህ ወደሆነው በአደጋ ጊዜ ወደሚወጣበት በር ሂድ።

ከአውሮፕላኑ በጥንቃቄ ውጣ። ቁጢጥ ብለህ ለመንሸራተት ከመሞከር ይልቅ መጀመሪያ እግርህን ቀጥ አድርገህ ዘርጋ። እጆችህን አጣምር። እግርህን ግጠም። ሹል ተረከዝ ያለው ጫማ አድርገህ ከሆነ አውልቅ። መሬት እንደደረስክ ከአውሮፕላኑ ራቅ፤ ከዚያም ለእርዳታ የሚመጡ ተሽከርካሪዎችን በንቃት ተጠባበቅ።

እነዚህን መመሪያዎች በጥብቅ መከተል የሞት አደጋ ሊቀንስ ይችላል? አዎን! የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር የሚያዘጋጀው ኢንተርኮም የተባለው ጽሑፍ “በአየር መንገዶች ላይ የሚያጋጥሙት አደጋዎች ሞት የሚያስከትሉት ሁሉም አይደሉም” ይላል። አክሎም “በንግድ አየር መንገዶች ላይ ከሚደርሱት የሞት አደጋዎች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት መትረፍ ሲቻል የሚከሰቱ ናቸው” በማለት ገልጿል።