በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በተለያዩ ኬሚካሎች በቀላሉ መጠቃት—እንግዳ የሆነ በሽታ

በተለያዩ ኬሚካሎች በቀላሉ መጠቃት—እንግዳ የሆነ በሽታ

በተለያዩ ኬሚካሎች በቀላሉ መጠቃት—እንግዳ የሆነ በሽታ

ፓም የምትኖርበት አካባቢ በጥጥ ማሳዎች የተከበበ ነው። አውሮፕላኖች አዘውትረው በማሳዎቹ ላይ የሚረጯቸው ፀረ አረም እና ተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች ብዙውን ጊዜ በነፋስ እየተወሰዱ ወደ ፓም ቤትና በአካባቢው ወደሚገኙ ሌሎች ቤቶች ይገባሉ።

ፓም ከባድ ራስ ምታትና የማቅለሽለሽ ስሜት ይሰማት ጀመር። ጤንነቷ እየተቃወሰ ሄደ። እያደር ከተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች ጋር ምንም ዝምድና የሌላቸው የሚመስሉ ንጥረ ነገሮች ማለትም ሽቶ፣ ዲዮደራንት፣ የሰውነት ቅባቶች፣ ለጽዳት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች፣ ቀለም፣ አዲስ ምንጣፍ፣ የትምባሆ ጭስ፣ የቤትን ጠረን ለመለወጥ የሚነፉ ፍሊቶችና ሌሎች ንጥረ ነገሮች ያሳምሟት ጀመር። በፓም ላይ መታየት የጀመሩት ምልክቶች መልቲፕል ኬሚካል ሴንሲቲቪቲ (በተለያዩ ኬሚካሎች በቀላሉ መጠቃት (ኤም ሲ ኤስ)) በተባለው ግራ የሚያጋባ በሽታ የተያዙ ሰዎች ከሚታዩባቸው ምልክቶች መካከል የሚደመሩ ናቸው። *

“ዕለት ተዕለት የምንገለገልባቸውን ኬሚካሎች ስጠቀም በጣም ይደክመኛል። በተጨማሪም ግራ የመጋባት፣ የማዞርና የማቅለሽለሽ ስሜት ይሰማኛል” ስትል ፓም ለንቁ! መጽሔት ዘጋቢ ገልጻለች። “ሰውነቴ ያብጣል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ትንፋሼ ቁርጥ ቁርጥ ይላል፣ የፍርሃት ስሜት ውርር ያደርገኛል፣ ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ አለቅሳለሁ፣ የልብ ትርታዬ ይጨምራል፣ እንዲሁም ሳንባዬ ውኃ ይቋጥራል። ይህ ደግሞ ለሳንባምች ዳርጎኝ ነበር።”

ኤም ሲ ኤስ የሚያስከትላቸው ምልክቶች ከሰው ወደ ሰው ሊለያዩ ቢችሉም ራስ ምታትን፣ ሥር የሰደደ ድካምን፣ የጡንቻ ሕመምን፣ የአንጓ ሕመምን፣ ችፌን፣ ሽፍታን፣ የጉንፋን ዓይነት ምልክቶችን፣ አስምን፣ የሳይነስ ችግሮችን፣ የመረበሽ ስሜትን፣ የመንፈስ ጭንቀትን፣ የማስታወስ ችግርን፣ ሐሳብን የማሰባሰብ ችግርን፣ እንቅልፍ ማጣትን፣ የልብ ምት መለዋወጥን፣ የሰውነት ማበጥን፣ ማቅለሽለሽን፣ ማስመለስን፣ የአንጀት ችግሮችንና እንፍርፍሪትን (seizure) ሊያጠቃልሉ ይችላሉ። እርግጥ ከእነዚህ ምልክቶች መካከል ብዙዎቹ በሌሎች በሽታዎችም ሳቢያ ሊከሰቱ ይችላሉ።

ኤም ሲ ኤስ​—⁠በመስፋፋት ላይ ያለ ችግር

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የተካሄዱት ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከ15 እስከ 37 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ እንደ መኪና ጭስ፣ የትምባሆ ጭስ፣ አዲስ ቀለም፣ አዲስ ምንጣፍና ሽቶዎች ባሉ የተለመዱ ኬሚካሎችና የኬሚካል ጠረኖች በቀላሉ እንደሚጠቁ ወይም ለእነዚህ ነገሮች አለርጂክ እንደሆኑ ተናግረዋል። ጥናቱ የተካሄደው በዕድሜ ክልል ተከፍሎ ሲሆን እንደየዕድሜ ክልሉ ኤም ሲ ኤስ እንደያዛቸው የገለጹት 5 በመቶዎቹ ብቻ ወይም ከዚያ ያነሱ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ሦስት አራተኛ ገደማ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

በኤም ሲ ኤስ የሚሠቃዩ ብዙ ሰዎች ለችግራቸው መንስኤ የሆኑት ነገሮች የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶችና አሟሚ ንጥረ ነገሮች እንደሆኑ ይናገራሉ። ሁለቱም ውጤቶች በተለይ ደግሞ አሟሚ ንጥረ ነገሮች በየአካባቢያችን በብዛት የሚገኙ ናቸው። አሟሚ ንጥረ ነገሮች ሌሎች ንጥረ ነገሮችን የሚበትኑ ወይም የሚያሟሙ ከመሆናቸውም በላይ በቀላሉ ይተናሉ። በቀለም፣ በቫርኒሽ፣ በማጣበቂያ፣ በተባይ ማጥፊያና ለጽዳት በሚያገለግሉ ድብልቆች ውስጥ ይገኛሉ።

በሚቀጥሉት ርዕሶች ላይ ኤም ሲ ኤስን ይበልጥ ጠለቅ ብለን እንመረምራለን፤ እንዲሁም በዚህ ችግር የሚሠቃዩ ሰዎች ምን ነገር ሊረዳቸው እንደሚችልና እነሱም ሆኑ ይህ ችግር የሌላቸው ሰዎች ተባብረው እንዴት ችግሩን ማቅለል እንደሚችሉ እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 “መልቲፕል ኬሚካል ሴንሲቲቪቲ” የሚለውን መጠሪያ የተጠቀምነው በስፋት የሚሠራበት በመሆኑ ነው። ይሁን እንጂ “ኢንቫይሮመንታል ኢልነስ (አካባቢያዊ በሽታ)” እና “ኬሚካል ሃይፐርሴንሲቲቪቲ ሲንድሮም (በኬሚካል በቀላሉ መጠቃት የሚያስከትለው ድምረህመም)” የሚሉትን ጨምሮ ሌሎች ብዙ መጠሪያዎች አሉ። እዚህ ላይ የገባው “ሴንሲቲቪቲ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል አብዛኞቹን ሰዎች ምንም በማይጎዳ የኬሚካል መጠን በቀላሉ መጎዳትን የሚያመለክት ነው።