በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳስበኝ ታማኝነቴን መጠበቄ ነበር

ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳስበኝ ታማኝነቴን መጠበቄ ነበር

ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳስበኝ ታማኝነቴን መጠበቄ ነበር

ኦሌክሲይ ዴቪድዩክ እንደተናገረው

በ1947 ከፖላንድ ጠረፍ አጠገብ ከሚገኘውና ዩክሬን ላስኬፍ ከተባለው መንደራችን ትንሽ ራቅ ብሎ በዕድሜ የሚበልጠኝ ስቴፓን የተባለው ጓደኛዬ ከፖላንድ ወደ ዩክሬን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በድብቅ ያስገባ ነበር። ሆኖም አንድ ቀን ምሽት ጠረፍ ጠባቂ አገኘውና አሳድዶ በጥይት መትታው። የስቴፓን ሞት ከ12 ዓመታት በኋላ በሕይወቴ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ከፍተኛ ነበር። ይህንን ጉዳይ በኋላ እመለስበታለሁ።

በ1932 ላስኬፍ ውስጥ ስወለድ የመንደራችን አሥር ቤተሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነበሩ። በዚያን ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች የሚታወቁት በዚህ ስም ነበር። ከእነዚህ ቤተሰቦች መካከል የእኔ ወላጆች የሚገኙበት ሲሆን በ1970ዎቹ አጋማሽ ላይ እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ ለይሖዋ ታማኝ በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተዋል። እኔም በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ሲያሳስበኝ የኖረው ዋነኛ ነገር ለአምላክ ታማኝ መሆን ነበር።​—⁠መዝሙር 18:​25

በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀምር እኛ እንኖርበት የነበረው ምሥራቃዊ ፖላንድ ከሶቭየት ሕብረት ጋር ተዋሃደ። ሰኔ 1941 ጀርመኖች ቦታውን እስከተቆጣጠሩበት ጊዜ ድረስ በሶቭየት አገዛዝ ሥር ነበርን።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በትምህርት ቤት አስቸጋሪ ጊዜያት አሳልፌያለሁ። ልጆቹ ብሔራዊ ስሜት የሚቀሰቅሱ መዝሙሮች ይማሩና ወታደራዊ ልምምድ ያደርጉ ነበር። እንዲያውም አንዱ ሥልጠና የእጅ ቦንብ መወርወርን መማር ነበር። ሆኖም እኔ ብሔራዊ መዝሙሮች ለመዘመርም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበርኩም። ገና በልጅነቴ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለተመሠረተው እምነቴ ጥብቅ አቋም መውሰዴ በቀጣዮቹ ዓመታት ለአምላክ ታማኝነቴን እንድጠብቅ ረድቶኛል።

በጉባኤያችን የአገልግሎት ክልል ውስጥ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ያሳዩ በጣም ብዙ ሰዎች ስለነበሩ እነርሱን ለመርዳት ሁለት አቅኚዎች (የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሚጠሩበት ስም ነው) እኛ ጋር ተመደቡ። ኢልያ ፌዶሮቪች የተባለው አንደኛው አቅኚ እኔን መጽሐፍ ቅዱስ ከማስጠናቱም በተጨማሪ ለአገልግሎት አሰልጥኖኛል። ጀርመን አገሪቷን በተቆጣጠረችበት ወቅት ኢልያ ከአገር እንዲወጣ ተደርጎ በአንድ የናዚ የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በመጣሉ እዚያው እንዳለ ሞቷል።

አባቴ ገለልተኛ ሆኖ ለመቆየት ያደረገው ትግል

በ1941 የሶቭየት ባለ ሥልጣናት ጦርነቱን በገንዘብ እደግፋለሁ የሚል አንድ ውል አባቴን ለማስፈረም ሞከሩ። በጦርነት ሁለቱንም ወገኖች መደገፍ እንደማይችልና የአምላክ አገልጋይ እንደመሆኑ መጠን ገለልተኛ አቋም እንዳለው ነገራቸው። አባቴ ጠላት ነው ተብሎ የ4 ዓመት እስራት ተፈረደበት። ሆኖም እስር ቤት የቆየው ለ4 ቀናት ብቻ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ከታሰረ በኋላ በዋለው የመጀመሪያ እሁድ የጀርመን ወታደሮች የምንኖርበትን አካባቢ ተቆጣጠሩ።

የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ጀርመኖች ወደ እነርሱ እንደቀረቡ ሲሰሙ የእስር ቤቱን በሮች ከፍተው ሸሹ። አብዛኞቹ እስረኞች ከውጭ በኩል በሶቭየት ወታደሮች ተተኩሶባቸዋል። አባቴ እስር ቤቱን ወዲያው አልለቀቀም። በኋላ ግን ወደ ጓደኞቹ ቤት ሸሸ። እዚያም ሆኖ ሶቭየቶችን በጦርነቱ ባለመደገፉ ምክንያት ታስሮ እንደነበር የሚገልጹ ማስረጃዎቹን እንድትልክለት ለእናቴ ላከባት። አባቴ እነዚህን ማስረጃዎች ለጀርመን ባለ ሥልጣናት በማሳየቱ ሕይወቱ ሊተርፍ ችሏል።

ጀርመኖች ከሶቭየቶች ጋር የተባበሩትን የሁሉንም ሰዎች ስም ለማወቅ ፈልገው ነበር። አባቴ እንዲያጋልጥ ከፍተኛ ግፊት ቢያደርጉበትም እርሱ ግን ፈቃደኛ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የገለልተኝነት አቋሙን አብራራላቸው። አባቴ የአንዳቸውን ስም ሰጥቶ ቢሆን ኖሮ እርሱ ወይም እርሷ ይገደሉ ነበር። አባቴ ያሳየው የገለልተኝነት አቋም የሌሎች ሰዎችን ሕይወት አትርፏል። ለዚህም በጣም አመስጋኞች ነበሩ።

በድብቅ መሥራት

ሶቭየቶች ነሐሴ 1944 ወደ ዩክሬን ተመልሰው በአውሮፓ ይካሄድ የነበረው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በግንቦት 1945 አበቃ። ከዚያ በኋላ የብረት መጋረጃ ተብሎ የሚጠራው እገዳ በሶቭየት ሕብረት የምንገኘውን ከተቀረው ዓለም አቆራረጠን። በፖላንድ ጠረፍ አቅራቢያ ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ግንኙነት ማድረግ እንኳ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ደፋር የሆኑ ምሥክሮች ወደ ጠረፉ ሾልከው በመግባት ውድ የሆኑ ጥቂት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችን ይዘው ይመለሱ ነበር። ጠረፉ ላስኬፍ ከሚገኘው ቤታችን ስምንት ኪሎ ሜትር ብቻ ይርቅ ስለነበር እነዚህ መልእክተኞች የሚያጋጥሟቸውን አደጋዎች እሰማ ነበር።

ለምሳሌ፣ ሲልቬስተር የተባለ አንድ ምሥክር ሁለቴ ወደ ጠረፉ ሄዶ ሁለቱንም ጊዜ ምንም አደጋ ሳያጋጥመው ተመለሰ። ለሦስተኛ ጊዜ በሄደበት ወቅት ግን የጠረፉ ጠባቂዎችና አነፍናፊ ውሾቻቸው አገኙት። ወታደሮቹ እንዲቆም ቢጮኹም ሲልቬስተር ሕይወቱን ለማትረፍ እግሬ አውጭኝ አለ። ከውሾቹ ለማምለጥ የነበረው ብቸኛ አማራጭ አቅራቢያው ባለው ሐይቅ ውስጥ ዘሎ መግባት ነበር። ሙሉውን ሌሊት ረጃጅም ሣሮች በበቀሉበት ሐይቅ ውስጥ እስከ አንገቱ ተነክሮ አደረ። በመጨረሻም ጠባቂዎቹ ተስፋ ቆርጠው ፍለጋቸውን ሲያቆሙ ሲልቬስተር በጣም ደክሞ እየተንገዳገደ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

አስቀድሜ እንደጠቀስኩት የሲልቬስተር የወንድም ልጅ የሆነው ስቴፓን የተገደለው እንዲሁ ጠረፉን ለማቋረጥ ሲሞክር ነበር። ያም ሆኖ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ግንኙነት ማድረጋችንን መቀጠላችን የግድ ነበር። ደፋር መልእክተኞች ባደረጉት ጥረት መንፈሳዊ ምግብና ጠቃሚ መመሪያ ማግኘት ችለናል።

በሚቀጥለው ዓመት ማለትም በ1948 አንድ ምሽት ከቤታችን አጠገብ በሚገኝ አንድ ትንሽ ሐይቅ ውስጥ ተጠመቅሁ። ተጠማቂዎች የተገናኙት ቤታችን ሲሆን ጨለማ በመሆኑና ሁሉም ነገር የተከናወነው በጸጥታ ስለነበር ተጠማቂዎች እነማን እንደነበሩ አላወቅሁም። እኛ እጩ ተጠማቂዎችም ብንሆን እርስ በርሳችን አልተነጋገርንም። የጥምቀት ንግግሩን ማን እንደሰጠ፣ ከሐይቁ አጠገብ ቆመን የጥምቀት ጥያቄዎቹን ማን እንደጠየቀኝ ወይም ውኃ ውስጥ ማን እንዳጠለቀኝ አላውቅም። ዓመታት ካለፉ በኋላ ከአንድ ጥሩ ጓደኛዬ ጋር የግል ማስታወሻችንን ስናስተያይ ሁለታችንም በዚያ ምሽት ከተጠመቁት መካከል እንደሆንን ተገነዘብን!

በ1949 በዩክሬን የሚገኙት ምሥክሮች የስብከቱ ሥራ በሶቭየት ሕብረት ሕጋዊ እውቅና ያገኝ ዘንድ ሞስኮን እንዲጠይቁ ከብሩክሊን ማበረታቻ ተሰጣቸው። ይህንን መመሪያ በመከተል ጥያቄያቸው በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኩል ለሶቭየት ሕብረት ጠቅላይ የመንግሥት ምክር ቤት ፕሬዚዲየም አባላት ቀረበ። ከዚያም ሚኮላ ፓያቶካ እና ኢልያ ባቢቹክ ሞስኮ ሄደው መንግሥት የሰጠውን መልስ እንዲያመጡ ተጠየቁ። እነርሱም በነገሩ በመስማማት በዚያ በጋ ወደ ሞስኮ ተጓዙ።

ልዑኩን የተቀበሉት ባለሥልጣን ለሥራችን ድጋፍ የሚሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶችን አዳመጡ። ወንድሞች ሥራችን የሚከናወነው “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” በሚለው የኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት እንደሆነ አብራሩ። (ማቴዎስ 24:​14) ይሁን እንጂ መንግሥት ለሥራችን ሕጋዊ እውቅና ፈጽሞ እንደማይሰጥ ባለ ሥልጣኑ ተናገሩ።

ምሥክሮቹ ከሞስኮ ከተመለሱ በኋላ በዩክሬን ሥራው ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ወደ ዋና ከተማዋ ወደ ኪዬቭ ሄዱ። ባለ ሥልጣኖቹ ጥያቄውን በድጋሚ ውድቅ አደረጉት። የይሖዋ ምሥክሮች በሰላም መኖር የሚችሉት መንግሥትን ከደገፉ ብቻ እንደሆነ ተናገሩ። ምሥክሮቹ በጦር ኃይሎች ውስጥ ማገልገልና በምርጫዎች መሳተፍ አለባቸው አሉ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል የዓለም ክፍል መሆን እንደማይገባን በመግለጽ የገለልተኝነት አቋማችንን እንደገና ማብራራት አስፈልጎ ነበር።​—⁠ዮሐንስ 17:​14-16

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወንድም ፓያቶካ እና ወንድም ባቢቹክ ተይዘው የ25 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው። በዚሁ ጊዜ ገደማ ማለትም በ1950 አባቴን ጨምሮ ብዙ ምሥክሮች በባለ ሥልጣናት ተይዘው ወደ ሌላ ቦታ ተወሰዱ። አባቴ የ25 ዓመት እስራት ተፈርዶበት ከሶቭየት ሕብረት ምሥራቃዊ ጠረፍ 7, 000 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ካባሮቭስክ ተላከ!

የሳይቤሪያ ግዞት

ከዚያም በሚያዝያ 1951 የሶቭየት መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ላትቪያ፣ ኢስቶኒያ፣ ሊቱዋንያ፣ ሞልዶቫ፣ ቤላሩስ እና ዩክሬን እየተባሉ በሚጠሩት ምዕራባዊ ግዛቶቹ ውስጥ በሚኖሩት ምሥክሮች ላይ የተደራጀ ጥቃት ሰነዘረ። በዚያ ወር እናቴንና እኔን ጨምሮ ወደ 7,000 የምንሆነው ወደ ሳይቤሪያ ተጋዝን። ወታደሮቹ በምሽት ቤታችን መጥተው ወደ ባቡር ጣቢያው ይዘውን ሄዱ። ከብቶችን ለማጓጓዝ በሚጠቀሙባቸው የባቡር ፉርጎ ውስጥ አስገብተው ከቆለፉብን በኋላ ጉዞ ጀመርን። እያንዳንዱ ፉርጎ 50 የምንሆነውን ይዞ ነበር። ከሁለት ሳምንት በኋላ ኢርኩትሲክ ግዛት ውስጥ ወደሚገኘውና ከባይካል ሐይቅ ብዙም ወደማይርቀው ዛላሪ የተባለ ቦታ ስንደርስ አወረዱን።

በጣም በሚቀዘቅዘው አየር በረዶ ላይ ቆመንና በታጠቁ ወታደሮች ተከብበን ባለበት ወቅት ከአሁን በኋላ ምን ይጠብቀን ይሆን እያልኩ አስብ ነበር። እዚህ ለይሖዋ ታማኝ ሆኜ መቆየት የምችለው እንዴት ነው? ብርዱ እንዲለቅቀን የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመር ጀመርን። ብዙም ሳይቆይ መንግሥታዊ የሆኑ ድርጅቶች ሥራ አስኪያጆች ደረሱ። አንዳንዶቹ ከባድ የጉልበት ሥራ የሚሠሩ ወንዶች ያስፈልጓቸው ነበር። ሌሎቹ ደግሞ እንስሶችን መንከባከብ የመሳሰሉ ሥራዎች ማከናወን የሚችሉ ሴቶች ይፈልጉ ነበር። እኔና እናቴ የታግኒንስካያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እየተገነባ ወደነበረበት ቦታ ተወሰድን።

እዚያም እንደደረስን ለግዞተኞች መኖሪያ ተብለው በመደዳ የተሠሩ የእንጨት ቤቶች ተመለከትን። እኔ የትልቅ መኪና ሾፌርና የኤሌክትሪክ ሠራተኛ ሆኜ እንድሠራ ስመደብ እናቴ ደግሞ በእርሻ ላይ እንድትሠራ ተመደበች። በይፋ የምንታወቀው እስረኞች ተብለን ሳይሆን ከአገር የተባረሩ ተብለን ነበር። ስለዚህ ከኃይል ማመንጫ ጣቢያው ብዙም ሳንርቅ ወዲያ ወዲህ ማለት እንችል ነበር። ይሁን እንጂ 50 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ሁለተኛ የሰፈራ ጣቢያ እንዳንሄድ ተከለከልን። ባለ ሥልጣኖቹ እስከ መጨረሻው እዚያ እንቆያለን የሚል ሰነድ እንድንፈርም ግፊት አሳድረውብን ነበር። ለአሥራ ዘጠኝ ዓመት ወጣት ይህ በጣም ረጅም ጊዜ ስለነበር አልፈርምም አልኩ። ሆኖም ለ15 ዓመታት እዚያው ቆይተናል።

ሳይቤሪያ ከገባን በኋላ ከፖላንድ ጠረፍ የራቅነው 8 ኪሎ ሜትር ብቻ ሳይሆን ከ6,000 ኪሎ ሜትር በላይ ነበር! እዚያ የነበርነው ምሥክሮች የመሪነቱን ቦታ የሚይዙ ወንዶች በመሾም ራሳችንን እንደገና በጉባኤ መልክ ለማደራጀት የቻልነውን ሁሉ አድርገናል። መጀመሪያ ላይ አንዳንድ ምሥክሮች ከዩክሬን ካመጧቸው ጥቂት ጽሑፎች በስተቀር ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አልነበሩንም። እነዚህን ጽሑፎች በእጅ ከገለበጥናቸው በኋላ አንዳችን አንብበን ለሌላው እናስተላልፍ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ስብሰባዎች ማድረግ ጀመርን። ብዙዎቻችን ሰብሰብ ብለን በአንድ አካባቢ እንኖር ስለነበር አብዛኞቹን ምሽቶች አንድ ላይ ሆነን አናሳልፋለን። ጉባኤያችን ወደ 50 የሚጠጉ አባላት ያሉት ሲሆን እኔ ደግሞ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እንድመራ ተመደብኩ። በጉባኤያችን ውስጥ ያሉት ወንድሞች ጥቂት በመሆናቸው እህቶች የተማሪ ንግግሮች ያቀርቡ ነበር። ይህ አሠራር በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የተጀመረው በ1958 ነበር። ሁሉም እህቶች ትምህርት ቤቱ ይሖዋን ለማወደስና ሌሎቹን የጉባኤ አባላት ለማበረታታት የሚጠቅም መሣሪያ እንደሆነ በመገንዘብ ክፍላቸውን በጥሩ ሁኔታ ይዘጋጁ ነበር።

አገልግሎታችን ተባረከ

ምሥክር ካልሆኑ ሰዎች ጋር በአንድ መንደር ውስጥ እንኖር ስለነበር ምንም እንኳ በጥብቅ የተከለከለ ቢሆንም ከሌሎች ጋር ስለ እምነታችን ሳንነጋገር አንድም ቀን አልፎብን አያውቅም። የሶቭየት ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ስታሊን በ1953 ከሞተ በኋላ ሁኔታዎች ተሻሻሉ። ከሌሎች ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ስላለው እምነታችን በግልጽ መነጋገር ችለን ነበር። ዩክሬን ከሚገኙ ጓደኞቻችን ጋር ባደረግነው የደብዳቤ ልውውጥ በአቅራቢያችን ሌሎች ምሥክሮች የት እንደሚገኙ ስለተረዳን ፈልገን አገኘናቸው። ይህም ጉባኤዎቻችንን በወረዳ ለማደራጀት አስችሎናል።

በ1954 ከዩክሬን በግዞት የመጣችውን ኦልጋን አገባሁ። በይሖዋ አገልግሎት ባሳለፍኳቸው ዓመታት ሁሉ ከፍተኛ የድጋፍ ምንጭ ሆናልኛለች። በ1947 ፖላንድን ከዩክሬን በሚያዋስናት ጠረፍ ላይ የተገደለው ስቴፓን የእርሷ ወንድም ነበር። በኋላም ቫለንቲና የተባለች ሴት ልጅ ወለድን።

ኦልጋና እኔ በሳይቤሪያ ባከናወንነው ክርስቲያናዊ አገልግሎት ብዙ በረከት በማግኘታችን ተደስተናል። ለምሳሌ፣ ጆርጅ የተባለ የባፕቲስት ቡድን መሪ አግኝተን ነበር። አዘውትረን እናነጋግረውና በእጃችን ያለውን ማንኛውንም የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት እናስጠናው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ጆርጅ የይሖዋ አገልጋዮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰብኩት ነገር እውነት መሆኑን ተገነዘበ። በተጨማሪም ብዙ ባፕቲስት ጓደኞቹን ማስጠናት ጀመርን። ጆርጅና አንዳንድ ጓደኞቹ ተጠምቀው መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ሲሆኑ ማየቱ ምንኛ የሚያስደስት ነበር!

በ1956 ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። ይህም በየሳምንቱ በአካባቢያችን ከሚገኙት ጉባኤዎች አንዱን መጎብኘት ይጠይቅብኝ ነበር። ቀኑን ሙሉ ስሠራ ከዋልኩ በኋላ አመሻሹ ላይ ከጉባኤው ጋር ለመሰብሰብ በሞተር ብስክሌቴ እጓዛለሁ። በሚቀጥለው ቀን ቀደም ብዬ በጠዋት እነሳና ተመልሼ ወደ ሥራ እሄዳለሁ። በተጓዥነት ሥራ እንዲረዳኝ ተሹሞ የነበረው ሚካይሎ ሰርዲንስኪ በ1958 በደረሰበት አደጋ ሕይወቱን አጣ። የሞተው ረቡዕ ቀን ነበር። ሆኖም በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ የተቻለውን ያህል ብዙ ምሥክሮች የመገኘት አጋጣሚ እንዲያገኙ ስንል ቀብሩን እስከ እሁድ አዘገየነው።

ብዙ ሆነን ወደ መካነ መቃብሩ መጓዝ ስንጀምር የአገሪቱ የደህንነት አባላት ተከተሉን። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የትንሣኤ ተስፋችንን የሚያብራራ ንግግር መስጠት ማለት ለመታሰር መቁረጥ ማለት ነበር። ሆኖም ስለ ሚካይሎና እርሱ ስለሚጠብቀው አስደናቂ ተስፋ ለመናገር ከውስጥ ተገፋፍቼ ነበር። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እያወጣሁ ብናገርም የደህንነት ሠራተኞቹ አላሠሩኝም። እንዲህ ማድረጉ እንደማይጠቅማቸው ተሰምቷቸው ይሆናል። ደግሞም ብዙ ጊዜ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ለጥያቄ የምጠራ የዘወትር “እንግዳቸው” ስለነበርኩ አሳምረው ያውቁኛል።

አንድ ጆሮ ጠቢ አሳልፎ ሰጣቸው

በ1959 የአገሪቱ የደህንነት ሠራተኞች በስብከቱ ሥራ የመሪነቱን ቦታ የያዙትን 12 ምሥክሮች አሰሩ። ሌሎች ብዙዎች ደግሞ ለጥያቄ የተጠሩ ሲሆን ከእነርሱ መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ። ተራዬ ደርሶ ስለ ሥራችን የሚገልጹ አንዳንድ ምስጢራዊ ጉዳዮችን ከባለ ሥልጣኖቹ አፍ በዝርዝር ስሰማ በጣም ደነገጥኩ። እነዚህን ነገሮች እንዴት ሊያውቁ ቻሉ? ስለ እኛ በደንብ የሚያውቅና ለተወሰነ ጊዜ ለመንግሥት የሠራ አንድ ጆሮ ጠቢ እንደሚኖር ግልጽ ነበር።

አሥራ ሁለቱም ወንድሞች የታሰሩት በተከታታይ ክፍሎች ውስጥ ስለነበር ለባለ ሥልጣኖቹ አንድም ቃል ላለመተንፈስ ተስማሙ። በዚህ መንገድ ወሬውን ያቀበለው ሰው ራሱ ቀርቦ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል። ተከሳሽ ባልሆንም እንኳ ሁኔታውን ለማየት ስል ወደ ፍርድ ቤት ሄድኩ። ዳኛው ጥያቄዎች ጠየቁ። ሆኖም 12ቱም ምንም መልስ አልሰጡም። ከዚያም ለብዙ ዓመታት የማውቀው ኬንስታንቲን ፖሊሽቹክ የተባለ ምሥክር በ12ቱም ላይ የምሥክርነት ቃሉን ሰጠ። በአንዳንዶቹ ላይ እስራት ከተፈረደባቸው በኋላ ችሎቱ ተዘጋ። ከፍርድ ቤቱ ሕንጻ ውጪ ባለው መንገድ ላይ ከፖሊሽቹክ ጋር ፊት ለፊት ተገጣጠምን።

“ለምን አሳልፈህ ሰጠኸን?” ስል ጠየቅኩት።

“ከአሁን በኋላ ስለማላምን” ሲል መለሰልኝ።

“ከአሁን በኋላ የማታምነው ምንድን ነው?” ስል ጠየቅኩት።

“ከአሁን በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ማመን አልችልም” ሲል መለሰ።

ፖሊሽቹክ እኔንም አሳልፎ መስጠት ይችል የነበረ ቢሆንም ስሜን አልሰጠም። ስለዚህ ለምን እንዲህ እንዳደረገ ጠየቅኩት።

“እስር ቤት እንድትገባ አልፈልግም” ሲል መለሰልኝ። “ስቴፓን ስለሚባለው የሚስትህ ወንድም አሁን ድረስ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል። በዚያ ምሽት ጠረፉን እንዲሻገር የላክሁት እኔ ነኝ። በእውነት በጣም አዝናለሁ።”

የተናገራቸው ቃላት እንቆቅልሽ ሆኑብኝ። ሕሊናው እንዴት ተዛብቷል! የስቴፓን ሞት ጸጸተው። የይሖዋን አገልጋዮች አሳልፎ ሲሰጥ ግን ቅንጣት ታህል እንኳ አልተሰማውም። ከዚያ በኋላ ፖሊሽቹክን አይቼው አላውቅም። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ሞተ። ለዓመታት የማምነው ሰው ወንድሞቻችንን አሳልፎ ሲሰጥ ማየቱ የማይሽር ጠባሳ ትቶብኝ አልፏል። ሆኖም በዚህ አጋጣሚ አንድ ጠቃሚ ትምህርት አግኝቻለሁ:- ፖሊሽቹክ ታማኝነቱን ሊያጎድል የቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቡንም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ማመኑን ስላቆመ ነው።

በእርግጥም ይህንን ትምህርት ሁልጊዜ ማስታወስ ያስፈልገናል:- ለይሖዋ ታማኝነታችንን ጠብቀን መቆየት ከፈለግን ቅዱሳን ጽሑፎችን አዘውትረን ማጥናት ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና” በማለት ይናገራል። ከዚህም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች እንዲጠነቀቁ ነግሯቸዋል። ለምን? “ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር።”​—⁠ምሳሌ 4:​23፤ ዕብራውያን 3:​12

ወደ ዩክሬን መመለስ

የሳይቤሪያ ግዞታችን በ1966 ሲያበቃ ኦልጋና እኔ ከላሺፍ 80 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝና ሶካል ወደተባለ የዩክሬን ከተማ ተመለስን። በሶካልና በአካባቢው ባሉት የቼርቮኖግራድና የሶስኒቭካ ከተሞች ያሉት ምሥክሮች 34 ብቻ በመሆናቸው ብዙ ሥራ ነበር። በዚህ አካባቢ በዛሬው ጊዜ 11 ጉባኤዎች አሉ!

ኦልጋ ታማኝነቷን እንደጠበቀች በ1993 ሞተች። ከሦስት ዓመት በኋላ ሊዲያን ያገባሁ ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥታኛለች። ቫለንቲና የተባለችው ልጄና ቤተሰቧ የይሖዋ ቀናተኛ አገልጋዮች ሲሆኑ ለእኔም የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል። ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን ከፍተኛ ደስታ የሚሰጠኝ ነገር ታማኝ ለሆነው አምላክ ለይሖዋ ታማኝነቴን ጠብቄ መቆየቴ ነው።​—⁠2 ሳሙኤል 22:​26

አሌክሲ ዴቪድዩክ ይህ ጽሑፍ በመዘጋጀት ላይ እንዳለ የካቲት 18, 2000 ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት እንደጠበቀ ሞቷል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1952 ምሥራቃዊ ሳይቤሪያ ባሉት መንደሮች ውስጥ የሚሰበሰበው ጉባኤያችን

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1953 የነበረው የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤታችን

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1958 የተካሄደው የሚካይሎ ሰርዲንስኪ ቀብር

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከሊዲያ ጋር