በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ብሪታንያውያንና መዝናኛ

በ1999 ለመጀመሪያ ጊዜ ብሪታንያውያን “ለምግብ፣ ለመኖሪያ ወይም ደግሞ በሳምንታዊው የቤተሰብ በጀት ውስጥ ለሚካተት ለሌላ ለማንኛውም ነገር ካዋሉት ገንዘብ” የበለጠ ለመዝናኛ ቁሳቁሶችና ግልጋሎቶች አውጥተዋል ሲል ታይምስ የተሰኘው የለንደን ጋዜጣ ዘግቧል። በ1968 እያንዳንዱ ቤተሰብ ከሚያወጣው ጠቅላላ ገንዘብ ውስጥ ለመዝናኛ ይውል የነበረው 9 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን በዛሬው ጊዜ ግን 17 በመቶ ደርሷል። ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ ሙያዊ ምክር የሚሰጡት ማርቲን ሄይዎርድ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “በአሁኑ ጊዜ የደረስንበት ብልጽግና፣ እንበልና ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ከነበረው በእጅጉ የላቀ በመሆኑ በአንድ ወቅት እንደ ቅንጦት ተደርገው ይታዩ የነበሩ ነገሮች ዛሬ በአብዛኞቹ ሰዎች ዘንድ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮች ተደርገው ይታያሉ። በዛሬው ጊዜ ለአብዛኞቹ ሰዎች ዕረፍት መውሰድ ‘በፍላጎት’ ላይ የተመሠረተ ነገር ሳይሆን ‘የግድ አስፈላጊ’ የሆነ ነገር ሆኗል። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች በዓመት ሦስት ጊዜ ዕረፍት መውጣት የግድ አስፈላጊ የሆነ መሠረታዊ ነገር ነው የሚል እምነት አላቸው።” ቤተሰቦች በአሁኑ ጊዜ ለቪዲዮና ለኦዲዮ መሣሪያዎች፣ ለቴሌቪዥን እንዲሁም ለኮምፒዩተሮች የሚያወጡት ወጪ በ1968 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በአራት እጥፍ ይበልጣል። እንዲያውም ከ10 ቤተሰቦች አንዱ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ሲሆን ከ3 ቤተሰቦች አንዱ ደግሞ ኮምፒዩተር አለው።

ሲጋራ ማጨስ ዕድሜ ያሳጥራል

“የሰው ልጅ አንድ ሲጋራ ባጨሰ ቁጥር ዕድሜውን በ11 ደቂቃ ያሳጥረዋል” ይላል ዩኒቨርሲቲ ኦቭ ካሊፎርንያ በርክሌይ ዌልነስ ሌተር ያወጣው ዘገባ። በመሆኑም አንድ ስቴካ ሲጋራ ሲያጨስ ዕድሜውን በአንድ ቀን ተኩል የሚያሳጥረው ሲሆን በቀን አንድ ፓኬት ሲጋራ የሚያጨስ ከሆነ በየዓመቱ ዕድሜውን በሁለት ወር ገደማ እንደሚያሳጥረው በእንግሊዝ ብሪስትል ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ተመራማሪዎች አመልክተዋል። ሳይንቲስቶች እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት የሚያጨሱና የማያጨሱ ሰዎችን የሕይወት ዘመን በማነጻጸር ነው። ተመራማሪዎቹ “ይህ አገላለጽ ማጨስ የሚያስከትለውን ኪሳራ እያንዳንዱ ሰው ሊረዳው በሚችል መንገድ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ጥጥ የሚበቅለው በበጎች ላይ ነው?

በቅርቡ በአውሮፓ ወጣት ገበሬዎች ምክር ቤት አማካኝነት የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “በኢ ዩ [የአውሮፓ ኅብረት] አባል አገሮች ውስጥ ካሉት ልጆች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት ስኳር ከየት እንደሚገኝ አያውቁም፤ ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ደግሞ . . . ጥጥ ከየት እንደሚገኝ የማያውቁ ሲሆን ከአንድ አራተኛ በላይ የሚሆኑት ጥጥ የሚበቅለው በበጎች ላይ ነው ብለው የሚያስቡ ናቸው።” ከዚህም በተጨማሪ በብሪታንያና በኔዘርላንድ ከሚገኙት በዘጠኝና በአሥር ዓመት የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ልጆች መካከል 25 በመቶዎቹ ብርቱካንና ወይራ በአገራቸው እንደሚበቅል አድርገው ያስባሉ። ልጆቹ በአብዛኛው የእርሻ ውጤቶችን የሚመለከቱት በግብርና ቦታዎች ሳይሆን በገበያ አዳራሾች ከመሆኑም በላይ ስለ ግብርና የሚማሩት በትምህርት ቤት ነው። እነዚህ ሁኔታዎች በዛሬው ጊዜ ብዙዎቹ አውሮፓውያን ልጆች በግብርና ሙያ የመሠማራት ፍላጎት እንዳይኖራቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገው ሊሆን ይችላል። “በአማካይ” ይላል ምክር ቤቱ፣ “በኢ ዩ አባል አገራት ውስጥ ከሚገኙት ልጆች መካከል ወደፊት ገበሬ የመሆን ‘ከፍተኛ ፍላጎት’ ያላቸው 10 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው።”

ጓደኝነት አደጋ ላይ ወድቋል

ለረጅም ሰዓት መሥራት፣ ለሥራ ጉዳይ በብዛት ከቦታ ወደ ቦታ መጓዝ፣ እንዲሁም “ከሰው አራርቀው ከሌሎች ነገሮች ሁሉ ጋር የሚያገናኙት የኤሌክትሮኒክ መዝናኛዎች” በግለሰቦች መካከል በሚኖረው ወዳጅነት ላይ ከባድ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው ሲል ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል። “ከጓደኞች ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደ አስፈላጊ ነገር ሳይሆን በፕሮግራም የተጣበበውን ውድ ጊዜ የሚሰርቅ ራስን ለማስደሰት ተብሎ የሚደረግ ትርፍ ነገር ተደርጎ ይታያል” ይላል ጋዜጣው። ይሁን እንጂ ለጓደኝነት ብዙም ትኩረት የማይሰጡ ሰዎች በቤተሰባቸው ላይ አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ሲደርስ “ሊረዳቸው የሚችል ሰው አጠገባቸው አለመኖሩን” ሊገነዘቡ ይችላሉ በማለት የማኅበራዊ ጉዳይ አጥኚ የሆኑት ኢያን ዬገር ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ጥሩ ጓደኞች ያሏቸው ሰዎች በአብዛኛው ብዙ ውጥረትና ሕመም እንደማይገጥማቸውና ረዘም ያለ ዕድሜ ሊኖሩ እንደሚችሉ ጥናቶች አመልክተዋል። “ቁልፉ” ይላል ጆርናል፣ “ቤተሰብን ችላ ሳይሉ ሥራን ማከናወን ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ ሁሉ ወዳጅነትን ጠብቆ ማቆየትም ተጨማሪ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅ መገንዘብ ነው።”

ከልክ በላይ የመወፈር ችግር በልጆች ላይ

“የእስያ ወጣቶች ከገጠሟቸው እጅግ አሳሳቢ የጤና ችግሮች አንዱ ከልክ ያለፈ ውፍረት ነው” ሲሉ በታይዋን የታይፔ የአመጋገብ ሥርዓት ጠበብት ማኅበር ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ቹዋንግ ለ-ቺ አስጠንቅቀዋል። በብዙዎቹ የእስያ ክፍሎች በተለይ ደግሞ በከተሞች ከልክ ያለፈ ውፍረት የሚታይባቸው በአብዛኛው ወንዶች የሆኑ ልጆች እየተበራከቱ መጥተዋል ይላል ኤሽያዊክ ያወጣው ዘገባ። በቤጂንግ በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሰውነታቸው ክብደት ከልክ ያለፈ መሆኑን አመልክቷል። የእስያ ወጣቶች ቴሌቪዥን በማየትና የቪዲዮ ጨዋታዎች በመጫወት የሚያሳልፉት ጊዜ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ይመስላል ሲል ዘገባው ይገልጻል። መፍትሔው ምንድን ነው? ኤሽያዊክ እንደሚለው ከሆነ መፍትሔው በአብዛኛው የተመካው ልጆች የሚበሉትን ምግብ መጠን በመመጠን ላይ ሳይሆን ቋሚ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እያደረጉ ብዙ ስብ ባላቸው ምግቦች ፋንታ እንደ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ያሉ ምግቦችን እንዲመገቡ በማድረጉ ላይ ነው። ዶክተር ቹዋንግ በዚህ ረገድ ስኬታማ ለመሆን የአካል እንቅስቃሴው አስደሳች እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አክለው ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ልማዳቸው ካልተለወጠ ይላል ሪፖርቱ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ልጆች የደም ግፊት፣ የጉበት በሽታ፣ የስኳር በሽታና የሥነ ልቦና ችግሮች ሊገጥሟቸው ይችላሉ።

በወጣላቸው ፕሮግራም የሚወለዱ ሕፃናት

“ሕፃናት ሆስፒታሎች በሚፈልጉት ጊዜ ላይ መወለድ ተምረዋል” ይላል ኮሪየሬ ዴላ ሴራ የተሰኘው የኢጣሊያ ጋዜጣ። ወሊድን በተመለከተ በቅርቡ በኢጣሊያ ፍሎረንስ ከተማ በተካሄደ አንድ ኮንፈረንስ ላይ የማኅፀን ሐኪም የሆኑት ስዊዘርላንዳዊው ፍሬድ ፓኮድ እንዲህ ብለዋል:- “ከ19ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ በምዕራቡ ዓለም ቅዳሜና እሁድ ቀናት ላይ የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር 95 በመቶ ቀንሷል። ከዚህም በተጨማሪ አብዛኞቹ ሕፃናት የሚወለዱት የሠራተኞች ማኅበር በወሰነው የሥራ ሰዓት ላይ ማለትም አብዛኞቹ ዶክተሮችና ነርሶች ሥራ ላይ በሚሆኑባቸው ፈረቃዎች ላይ ነው።” ሕፃናቱ እንዲወለዱ የሚደረገው አንድም በመድኃኒት አለዚያም ደግሞ በቀዶ ሕክምና አማካኝነት ነው። “እናቶች በመድኃኒቶች አማካኝነት አለዚያም በቀዶ ሕክምና እንዲወልዱ እያደረግን ነው” ሲሉ በፍሎረንስ የማኅፀን ሐኪም የሆኑት አንጄሎ ስኩዴሪ ተናግረዋል። “በቀዶ ሕክምና የማዋለዱ ተግባር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሕፃናት [የሚወለዱት] በዚህ መንገድ ነው።” ይሁን እንጂ የኢጣሊያ የማኅፀንና የፅንስ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ካርሎ ሮማኒኒ “ሕፃናት ‘በወጣላቸው ፕሮግራም’ እንዲወለዱ የሚደረገው አመቺ ሁኔታ ስለሚፈጥር ተብሎ ሳይሆን” እናቶችም ሆኑ የሚወለዱት ሕፃናት ካልታሰቡ የጤና እክሎች እንዲጠበቁ የሚያደርግ ስለሆነ ነው። “የሆስፒታል ሠራተኞች በተሟላ ሁኔታ በሥራ ገበታቸው ላይ በሚገኙበትና በተቻለ መጠን የተሻለ እንክብካቤ መስጠት በሚቻልበት ጊዜ ላይ [ማዋለዱ] እጅግ ይመረጣል” ብለዋል።

“አርቲስት” ዝሆኖች

በሕንድ አገር ኦታፓላም ውስጥ የዝሆን ግልገሎች በኩንቢያቸው ብሩሽ ይዘው ሥዕል እንዲስሉ ሥልጠና እየተሰጣቸው ነው። የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ተሟጋቾች ዝሆኖች የሳሏቸውን ሥዕሎች በመሸጥ ለዝሆኖች ጥበቃ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ የእስያ የዝሆን ሥዕልና ጥበቃ ፕሮጄክት ማቋቋማቸውን ዚ ኢንዲያን ኤክስፕረስ ዘግቧል። ገኔሰን የተሰኘ አንድ የስድስት ዓመት ዝሆን “ሥዕል” መሞነጫጨር የሚያስደስተው ይመስላል። መሣል ሲፈልግ ጆሮዎቹን ያርገበግብና ከአሠልጣኙ ብሩሽ ይቀበላል። ገኔሰን በሚስልበት ጊዜ ሌላው ቀርቶ ወፎች ወይም ሙጭጭላዎች እንኳ እንዲረብሹት አይፈልግም። የተለያዩ ቀለማትን ከሞነጫጨረ በኋላ የሠራውን ቆም ብሎ ሲያጤን ይስተዋላል። ይሁን እንጂ የእንስሳት “ሠዓሊዎች” እንዲሆኑ ለማድረግ እየተደረገ ላለው ጥረት አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ያሉት ሁሉም የዝሆን ግልገሎች አይደሉም። አንዳንዶቹ የሥዕል ብሩሾቹን በመስበር በሁኔታው አለመደሰታቸውን ያሳያሉ።

ፊልሞችና ቤተ ክርስቲያን

“በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ከባሕላዊዎቹ ቤተ ክርስቲያናት ይልቅ እንደ ተርምኔተር 2፣ ታይታኒክ እና ስታር ዎርስ ያሉት ፊልሞች ይበልጥ ጥልቀት ያለው ሃይማኖታዊ ግንዛቤ ያስጨብጧቸዋል” ሲል የለንደኑ ዚ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ዘግቧል። በኮሎራዶ ዩኒቨርሲቲ የመገናኛ ብዙሃን ጥናት ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሊን ክላርክ ከሃይማኖታዊ እምነቶቻቸው ጋር ይበልጥ የሚሄደው የትኛው ፊልም እንደሆነ ለ200 ወጣቶች ጥያቄ አቅርበው ነበር። ብዙዎቹ በበጎነትና በክፋት መካከል የሚካሄደውን ትግል እንዲሁም ዋናው ገጸ ባሕርይ በጊዜ ሂደት ወደ ኋላ ተመልሶ እንደ መሲሕ የሚቆጠርን አንድ ሕፃን ለማዳን የሚያደርገውን ጥረት የሚያሳየውን ተርምኔተር 2 የተሰኘውን ፊልም ጠቅሰዋል። ስኮትላንድ፣ ኤድንበርግ ውስጥ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ ዶክተር ክላርክ የሰጡትን ንግግር እንዲህ ሲሉ አጠቃልለዋል:- “በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች ስለ ሕይወት ምንነት ላሏቸው ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት እየጣሩ ያሉት ዳርት ቬደር ከተሰኘው ገጸ ባሕርይና ኤክስ-ፋይልስ ከተሰኘው ፊልም ነው። ኤክስ-ፋይልስ አጽናፈ ዓለምን ስለሚቆጣጠር አንድ የማይታወቅ ኃይል ምንነት ለማወቅ የሚደረግን ጥረት የሚያሳይ ፊልም በመሆኑ የመማረክ ኃይል አለው። ሳይንስ መልስ ያላገኘላቸው ጉዳዮች አሉ የሚለውን ነጥብ ያነሳል። ይህ ሃይማኖታዊ ጉዳይ ቢሆንም ሃይማኖት በቅጡ ሊፈታው አልቻለም።”

ትንሽ ማሸለብ መንፈስን ያድሳል

ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ባወጣው ዘገባ መሠረት ቀትር ላይ የሚፈጠረውን የሚጫጫን ስሜት በካፌይን ኃይል ለማሸነፍ መሞከር ምርታማነትን ሊቀንስ ይችላል። “ካፌይን ከወሰድን በኋላ ድክምክም ይለናል” ሲሉ በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ በእንቅልፍ ጥናት ኤክስፐርት የሆኑት ዶክተር ጄምስ ማስ ተናግረዋል። “የእንቅልፍ ዕዳህ በሰው ሠራሽ ማነቃቂዎች ሊቃለል አይችልም።” የቡና ዕረፍት ከመውሰድ ይልቅ “ዝርዝር ጉዳዮችን በትኩረት የመከታተልና ከባድ ውሳኔዎችን የመወሰን ችሎታችን በእጅጉ መጠናከር ይችል ዘንድ” ለተወሰኑ ደቂቃዎች ማሸለብ የተሻለ እንደሚሆን በመግለጽ ማስ ምክራቸውን ለግሰዋል። አንድ ሰው እኩለ ቀን ላይ 30 ደቂቃ ለማይሞላ ጊዜ ማሸለቡ ኃይሉን ሊያድስለት የሚችል ከመሆኑም በላይ ለመነሳት አይቸገርም፣ የሌሊት እንቅልፉንም አያስተጓጉልበትም ይላል ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ። “እንዲህ ዓይነቱ እንቅልፍ ችላ መባል የለበትም” ሲሉ ማስ ተናግረዋል። “የዕለታዊ እንቅስቃሴ ክፍል ተደርጎ መታየት አለበት።”