በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ከዕድሜ ልክ ሥራዬ” እንድፈናቀል የሚያደርግ ምን ነገር ተከሰተ?

“ከዕድሜ ልክ ሥራዬ” እንድፈናቀል የሚያደርግ ምን ነገር ተከሰተ?

“ከዕድሜ ልክ ሥራዬ” እንድፈናቀል የሚያደርግ ምን ነገር ተከሰተ?

ግሬሃም * በአንድ ትልቅ የአውስትራሊያ ኩባንያ ውስጥ ለ37 ዓመታት ሠርቷል። በ50ዎቹ ዕድሜው መጨረሻ ላይ እያለ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሥራ እንዲያቆም የሚገልጽ ደብዳቤ ተሰጠው። ግራ እንደሚጋባ፣ በጣም እንደሚገረምና የወደፊት ሕይወቱ በእጅጉ እንደሚያሳስበው የታወቀ ነው። ግሬሃም ‘የጡረታ ዕድሜዬ እስኪደርስ ድረስ ችግር አያጋጥመኝም ካልኩት “ከዕድሜ ልክ ሥራዬ” እንድፈናቀል የሚያደርግ ምን ነገር ተከሰተ?’ ሲል በመገረም ጠይቋል።

እርግጥ ነው፣ ከሥራ መፈናቀል እንግዳ ወይም አዲስ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣው ከሥራ የመባረር ሁኔታ በወቅቱ ላለው ሠራተኛ አዲስ ነው። ሰዎች ከሥራ የሚባረሩባቸው የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ሆኖም ዋነኛው ምክንያት ቅነሳ የሚባለው ነው። ቅነሳ ምንድን ነው? እንዴትስ ተጀመረ?

የሥራ ቦታ መለዋወጥ

በአሁኑ ጊዜ ያለው ኢኮኖሚ ዓለም አቀፋዊ መልክ እየያዘ መጥቷል። ይህ ሁኔታ በተለይ በዩናይትድ ስቴትስ ግንዛቤ እያገኘ የመጣው በአገሪቱ የሚገኙ ኩባንያዎች ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎች በሌላ አገር የተመረቱ መኪናዎችን፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን፣ እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ ሸቀጦችን እንደሚገዙ ባስተዋሉበት በ1970ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ላይ ነው።

የአሜሪካ ኩባንያዎች በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቅረብና የምርት ወጪያቸውን ለመቀነስ የሠራተኞቻቸውን ቁጥር መቀነስ እንዲሁም የአሠራር ዘዴውንና የዕቃውን ጥራት ማሻሻል ጀመሩ። የሠራተኛውን ኃይል ለመቀነስ የተጠቀሙበት ዘዴ ቅነሳ ተባለ። ሂደቱ “በአብዛኛው በቅነሳ፣ ያለ ዕድሜያቸው ጡረታ እንዲወጡ በማበረታታትና በዝውውር አማካኝነት የአንድን ድርጅት የሠራተኛ ኃይል መቀነስ” ተብሎ ይገለጻል።

ለተወሰኑ ዓመታት በአብዛኛው የሚቀነሱት የጉልበት ሠራተኞች ነበሩ። ሆኖም በ1980ዎቹ መጨረሻና በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ቅነሳው ቁጥሩ እየጨመረ ያለውን የቢሮ ሠራተኛ ያካትት ጀመር። ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁሉንም በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮች ነክቷል። የፋይናንስ አቅም እየተዳከመ ሲሄድ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ቀጣሪ ኩባንያዎች ተጨማሪ ቅነሳ በማድረግ ወጪያቸውን ዝቅ የሚያደርጉበትን ዘዴ ይፈልጋሉ።

ብዙ ሠራተኞች የሥራ ዋስትና የሚባል ነገር የላቸውም። አንድ የሠራተኛ ማኅበር ባለሥልጣን እንደተናገሩት “ለ10, ለ15, ለ20 ዓመታት በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩ ሰዎች የኮንትራት ውላቸው ተቀዶ እንደ አሮጌ ዕቃ ይወረወራሉ” ሲሉ ተናግረዋል። ደሎሪዝ አምብሮሴ ሂሊንግ ዘ ዳውንሳይዝድ ኦርጋናይዜሽን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “የድርጅቱ ሰው” የሚለው አጠራር በ1956 አንድን ሠራተኛ ለማመልከት ይሠራበት እንደነበረ ገልጸዋል። አክለውም “በሠራተኛ ማኅበር የታቀፈ ሠራተኛም ይሁን ሥራ አስኪያጅ ኢኮኖሚያዊ ደህንነቱን፣ ማኅበራዊ ሕይወቱን ለዕድሜ ልክ ሥራው ሲል መሥዋዕት አድርጓል። ድርጅቱንም በታማኝነት ሲያገለግል ኖሯል። በዘመኑ ድርጅቶች ውስጥ ይህ ዓይነቱ ነገር እንደማይታይ ግልጽ ነው።”

በዓለም ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሠራተኞች በቅነሳ ሳቢያ ሥራቸውን ያጡ ሲሆን በዚህ ሁኔታ ያልተነካ ሠራተኛ አይገኝም። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ እንኳ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከቋሚ ሥራቸው ተሰናብተዋል። በሌሎች ብዙ አገሮችም ተመሳሳይ ቅነሳ ተደርጓል። ይህ አሃዛዊ መረጃ ብቻ ከሥራ መቀነስ ምን ያክል ከባድ እንደሆነ አይገልጽም።

የሚያስከትለው ተጽዕኖ

በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ግሬሃም “ከፍተኛ ሥነ ልቡናዊ ጉዳት ያስከትልብሃል” ሲል ተናግሯል። ከሥራ መባረሩን “ከበሽታ ወይም ድብደባ ከሚያስከትለው ጉዳት” ጋር አመሳስሎታል።

ሰዎች ላሳዩት ታማኝነት ወሮታ ሳይከፈላቸው ሲቀር ክህደት እንደተፈጸመባቸው ይሰማቸዋል፤ ምክንያቱም ለኩባንያው ሲሉ የከፈሉት መሥዋዕትነት ሁሉ መና ቀረ ማለት ነው። በተለይ ብዙ ከፍተኛ የአስተዳደር ባለሥልጣናት የሠራተኛ ቁጥር በመቀነሳቸው ምክንያት ዳጎስ ያለ ድጎማ ሲሰጣቸው ማየት ሰዎች እምነት እንዲያጡ ያደርጋል። በተጨማሪ ከሥራ የተባረረው ሰው ገቢው ድንገት ስለሚቋረጥ የባንክና ሌሎች ዕዳዎችን፣ የቤተሰቡን አባላት የሕክምና ወጪና የትምህርት ቤት ክፍያዎችን መክፈል ይሳነዋል። እንዲሁም የለመደው የአኗኗር ዘይቤ ይስተጓጎላል፣ በትርፍ ጊዜ ያደርጋቸው የነበሩትን ነገሮች ለማቋረጥ ይገደድ ይሆናል፣ ያሉትን ንብረቶች የማጣት አደጋም ይጋረጥበታል። ይህ ደግሞ የተስፋ መቁረጥና የከንቱነት ስሜት ያሳድርበታል።

ቋሚና ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት አንድ ሰው ተፈላጊ እንደሆነ እንዲሰማው ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያበረክት ከሆነ ከሥራ መፈናቀል በአካል ጉዳተኞች፣ ሙያ በሌላቸው ወይም በዕድሜ በገፉ ሰዎች ላይ የሚያስከትለውን ቅስም የሚሰብር ሁኔታ አስብ። በአውስትራሊያ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በአብዛኛው ከሥራ የመባረር ዕጣ የሚገጥማቸው ከ45 እስከ 59 ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ናቸው። ራሳቸውን ከሁኔታው ጋር ማስማማት የሚቸግራቸው ደግሞ በዚህ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ናቸው።

ሌላ ምርጫ ይኖር ይሆን? ሥራ ከመፍታት የከፊል ጊዜ ሥራ መሥራት ወይም በዝቅተኛ ደመወዝ መቀጠር ይሻላል። ይሁን እንጂ ይህ የኑሮው ደረጃ ዝቅ እንዲል ያደርግ ይሆናል። ከሥራ ከተባረሩት ሰዎች መካከል የቀድሞ ሥራቸው ከሚያስገኝላቸው ደሞዝ ጋር የሚመጣጠን ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ የሚያገኙት አንድ ሦስተኛ የሚያክሉት ብቻ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል። ይህ ደግሞ በቤተሰብ ሕይወት ላይ ጭንቀት ይፈጥራል።

ሥራ ብትይዝም እንኳ የአእምሮ ሰላም ላታገኝ ትችላለህ። ምክንያቱም ከሥራ እባረር ይሆናል የሚለው ስጋት ሳታውቀው ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትልብህ ስለሚችል ነው። ፓርቲንግ ካምፓኒ የተባለው መጽሐፍ እንደሚከተለው ብሏል:- “ከሥራ እባረር ይሆን ብሎ ማሰብ መኪና በዚህኛው ጎኔ ቢገጨኝ ይሻላል ብሎ ከመምረጥ ጋር ይመሳሰላል። አብዛኛውን ጊዜ መኪና የሚገጭህ ድንገት ስለሆነ በዚህ ጎን ብገጭ ይሻለኛል ብለህ ለመምረጥ ዕድሉም አይኖርህም። ከሥራ መባረርም ተመሳሳይ ነው።”

ሥራ ማጣት በወጣቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንድን ነው? የትምህርትና የሳይንስ መምሪያ አንድ ጥናት ካደረገ በኋላ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “አንድ ሰው ከልጅነት ወደ ዐዋቂነት መሸጋገሩን ከሚያሳይባቸው ውጪያዊ ማስረጃዎች መካከል ዋነኛው ቋሚ ሥራ መያዝ ነው፤ ይህ ደግሞ በገንዘብ ረገድ የማንም ሰው ጥገኛ ሳይሆን በዐዋቂዎች ጎራ ‘እውነተኛውን’ የዐዋቂነት ሕይወት መምራት እንደጀመረ የሚያሳይ ምልክት ነው።” ሥራ ማግኘት ወደ ዐዋቂነት ሕይወት መሸጋገርን የሚያሳይ ምልክት ተደርጎ ከታየ ሥራ አጥነት በወጣቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

ሥራ አጥነትን መቋቋም

ከሥራ መባረር ከሚያስከትለው ስሜት ጋር መታገል ፈንጂ በተቀበረበት መስክ ላይ ከመራመድ ጋር ይመሳሰላል። ፓርቲንግ ካምፓኒ የተባለው መጽሐፍ እንደሚናገረው ብዙውን ጊዜ እንደ ቁጣ፣ እፍረት፣ ፍርሃት፣ ሐዘንና ትካዜ ያሉ ስሜቶች እንደሚያጋጥሙ ጠቁሟል። እነዚህን ስሜቶች ማሸነፍ በጣም አስቸጋሪ ነው። ደራሲው ቀጥሎ “የወደፊት ዕጣህን የመወሰን ከባድ ሥራ ተሰጥቶሃል። ይህ ጠይቀህ የተሰጠህ ሥራ አይደለም፤ እንዴት ብለህ መጀመር እንዳለብህ አታውቅ ይሆናል፤ ብቻ ድንገት ያለ አጋር ሜዳ ላይ የቀረህ ሆኖ ይሰማሃል” ብሏል። ከሥራ የተባረሩ ሰዎች ከሚገጥሟቸው ችግሮች መካከል ከባዱ ከሥራ መባረራቸውን ለቤተሰባቸው ማስረዳት ነው።

ይሁን እንጂ ከሥራ መቀነስ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚረዱ አንዳንድ ተግባራዊ ዘዴዎች አሉ። የመጀመሪያው እርምጃ አኗኗርን በመመጠንና ቀድሞ ከለመድከው አኗኗር ቀለል ያለ ኑሮ ለመኖር ጥረት ማድረግ ነው።

ችግሩን ሙሉ በሙሉ ባያስወግዱትም ከአቅምህ በላይ እንዳይሆን ሊረዱህ የሚችሉ ጥቂት ሐሳቦች ቀጥሎ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ደረጃ ድንገት ከሥራ መባረር በዚህ ዘመን ያለ ነገር መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ስለዚህ ዕድሜህም ሆነ ያለህ የሥራ ልምድ ምንም ይሁን ምን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ እንዴት አድርገህ ሕይወትህን መምራት እንደምትችል አስቀድመህ ዕቅድ አውጣ።

በሁለተኛ ደረጃ ለኑሮ የግድ አስፈላጊ ላልሆኑ ነገሮች ከባድ ዕዳ ውስጥ እንዳትዘፈቅ ተጠንቀቅ። እንደ አቅምህ ኑር፤ እንዲሁም የሥራ እድገት ወይም የደሞዝ ጭማሪ ሳገኝ እከፍላለሁ ብለህ በማሰብ ዕዳ ውስጥ አትግባ። ዛሬ ያለው የኢኮኖሚው ሁኔታ የሚጠቁመው የወደፊቱ ጊዜ ፈጽሞ አስተማማኝ አለመሆኑን ነው።

በሦስተኛ ደረጃ ቀላል ሕይወት ለመምራት የሚያስችልህን ዘዴ ቀይስ እንዲሁም በገንዘብ ረገድ ያሉብህን ኃላፊነቶች ቀንስ። ይህም ቀላልና ደህና ለሚባለው አኗኗር የግድ አስፈላጊ ላልሆኑ ነገሮች የምታወጣውን ወጪ መቀነስን ይጨምራል።

በአራተኛ ደረጃ፣ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ለወደፊቱ ጊዜ ያወጣኸውን ግብ መለስ ብለህ ከልስና ማሻሻያዎችን አድርግ። ካወጣኸው ግብ ጋር የማይጣጣሙ ውሳኔዎችን ሁሉ እንደገና አመዛዝነህ በሕይወትህ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ አስብ።

በመጨረሻም በአካባቢህ ያሉ ሰዎች ያላቸውን ነገር ወደ መመኘትና የአኗኗር መንገዳቸውን ወደ መከተል እንዳትሳብ ገንዘብ እንደልባቸው የሚበትኑ ሰዎች የአኗኗር ዘይቤ አያጓጓህ።

ከላይ የተጠቀሱት አንተና ቤተሰብህ አስተማማኝ ባልሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ በሚገኝ የማይጨበጥ ሃብት ተማምናችሁ በወጥመድ እንዳትያዙ እንዲሁም የዘመኑ የአኗኗር ዘይቤ በሚያመጣው ጭንቀት እንዳትዋጡ የሚረዱ ሐሳቦች ናቸው።

ቀድሞ የኢንቨስትመንት ባንክ ባለ ንብረት የነበሩት ፊሊክስ ሮኻተን እንዲህ ሲሉ ጠቅሰዋል:- “የአንዱ ከሥራ መፈናቀል ለሌላው መበልጸግ ምክንያት የሚሆን ከሆነ በማኅበረሰባችን ውስጥ አንድ መሠረታዊ ችግር አለ ማለት ነው።” እዚህ ላይ የተጠቀሰው መሠረታዊው ችግር በቅርቡ በአዲስ ዓለም የሚተካው ይህ ሥርዓት ነው። በዚያን ጊዜ “የዕድሜ ልክ ሥራ” የሚለው አነጋገር አሁን ከምናስበው በላይ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል።​—⁠ኢሳይያስ 65:​17-24፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ስሙ ተቀይሯል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘የአንዱ ከሥራ መፈናቀል ለሌላው መበልጸግ ምክንያት የሚሆን ከሆነ አንድ ችግር አለ ማለት ነው’

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አኗኗርህን ቀላል የምታደርግበትን ዘዴ ቀይስ