በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኬሚካሎች ጤናህን ሲያውኩት

ኬሚካሎች ጤናህን ሲያውኩት

ኬሚካሎች ጤናህን ሲያውኩት

ብዙዎቹ የመልቲፕል ኬሚካል ሴንሲቲቪቲ (ኤም ሲ ኤስ) ገጽታዎች ግራ የሚያጋቡ ናቸው። በመሆኑም የበሽታውን ባሕርይ በተመለከተ በሕክምናው ማኅበረሰብ መካከል ትልቅ አለመግባባት ይታያል። አንዳንድ ዶክተሮች የኤም ሲ ኤስ መንስኤ አካላዊ ነው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ሥነ ልቦናዊ ነው ይላሉ። አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ምክንያቶችን የሚጠቅሱም አሉ። አንዳንድ ዶክተሮች ደግሞ ኤም ሲ ኤስ የጋራ ባሕርይ ያላቸውን በርከት ያሉ በሽታዎች የሚወክል ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ። *

የኤም ሲ ኤስ ምልክቶች የሚታዩባቸው ብዙ በሽተኞች ለበሽታው መንስኤ የሆነባቸው ነገር መጀመሪያ ላይ እንደ ተባይ ማጥፊያ ላለ መርዝ በከፍተኛ ሁኔታ መጋለጣቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ዝቅተኛ መጠን ላለው መርዝ በተደጋጋሚ ወይም ረዘም ላለ ጊዜ መጋለጣቸው የበሽታው ተጠቂ እንዳደረጋቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ። በሽተኞቹ አንዴ በኤም ሲ ኤስ ከተያዙ በኋላ እንደ ሽቶና የጽዳት መገልገያ ኬሚካሎች ያሉ ቀደም ሲል ይቋቋሟቸው የነበሩና ምንም ዓይነት ዝምድና ያላቸው የማይመስሉ የተለያዩ ኬሚካሎች የተለያዩ የበሽታ ምልክቶች ያስከትሉባቸዋል። በሽታው “በተለያዩ ኬሚካሎች በቀላሉ መጠቃት” የሚል ስያሜ የተሰጠውም ለዚህ ነው። የጆይስን ሁኔታ እንውሰድ።

ጆይስ ተማሪ እያለች የፀጉር ቅማል ይዟት ነበር። በመሆኑም ጭንቅላቷ ላይ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒት ነፉባት። የጆይስ ጤና እየተቃወሰ ከመሄዱም በላይ ቀደም ሲል ምንም የማይረብሿት ብዙ ኬሚካሎች ችግር ይፈጥሩባት ጀመር። ከእነዚህ ኬሚካሎች መካከል ቤት ለማጽዳት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች፣ የቤትን ጠረን ለመለወጥ የሚነፉ ፍሊቶች፣ ሽቶዎች፣ ሻምፖዎችና ቤንዚን ይገኙበታል። “ዓይኖቼ በጣም ያብጣሉ” ትላለች ጆይስ፣ “በተጨማሪም ሳይነሶቼ ይመረዙና በርከት ላሉ ቀናት የሚቆይ ከባድ ራስ ምታትና የማቅለሽለሽ ስሜት ይሰማኛል። . . . በተደጋጋሚ ጊዜያት በሳንባምች በመያዜ ሲጋራ አጭሼ የማላውቅ ቢሆንም እንኳ ለ40 ዓመታት እንዳጨሰ ሰው ሳንባዬ ጠባሳ አውጥቷል!”

አንድ ሰው ከቤት ውጪም ሆነ በቤት ውስጥ ዝቅተኛ መጠን ላለው መርዝ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጋለጥ ይችላል። ይህም ኤም ሲ ኤስ ሊያስከትል እንደሚችል ተገልጿል። እንዲያውም ባለፉት አሥርተ ዓመታት በቤት ውስጥ የሚከሰት የአየር ብክለት የሚያስከትላቸው ተደራራቢ በሽታዎች “የቤት ውስጥ የተበከለ አየር ድምረህመም” የሚል ስያሜ ወጥቶላቸዋል።

የቤት ውስጥ የተበከለ አየር ድምረህመም

የቤት ውስጥ የተበከለ አየር ድምረህመም የተከሰተው በ1970ዎቹ ዓመታት ተፈጥሯዊ የሆነ ንጹሕ አየር ያገኙ የነበሩ ብዙ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችና ቢሮዎች ኃይል ለመቆጠብ ሲባል ምንም አየር በማያስገቡና አየር ማቀዝቀዣ መሣሪያ በተገጠሙላቸው ሕንፃዎች ሲተኩ ነበር። ብዙውን ጊዜ በእነዚህ ሕንፃዎች ውስጥ ለክየታ (Insulation) የሚያገለግሉ ነገሮች፣ በኬሚካላዊ ሂደት ውስጥ ያለፈ እንጨት፣ በቀላሉ የመትነን ባሕርይ ያላቸው ማጣበቂያዎች፣ ሰው ሠራሽ በሆኑ ነገሮች የተሠሩ ጨርቆችና ምንጣፎች ይኖራሉ።

ከእነዚህ ነገሮች መካከል ብዙዎቹ በተለይ አዲስ በሚሆኑበት ጊዜ አነስተኛ መጠን ያላቸው እንደ ፎርማልዴሃይድ ያሉ ሊጎዱ የሚችሉ ኬሚካሎች በቤቱ ውስጥ ካለው አየር ጋር እንዲቀላቀሉ ያደርጋሉ። ምንጣፎች ለጽዳት የሚያገለግሉ የተለያዩ ኬሚካሎችንና አሟሚ ንጥረ ነገሮችን እየመጠጡ ለረጅም ጊዜ እንዲበንኑ በማድረግ ችግሩን ያባብሱታል። “በቤት ውስጥ ያለውን አየር ይበልጥ የሚበክለው ከተለያዩ አሟሚ ንጥረ ነገሮች የሚወጣው ተን ነው” ሲል ኬሚካል ኤክስፖዠርስ​—⁠ሎው ሌቭልስ ኤንድ ሃይ ስቴክስ የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል። “አሟሚ ንጥረ ነገሮች” ደግሞ ይላል መጽሐፉ፣ “በኬሚካሎች በቀላሉ የሚጠቁ ሕሙማን ለበሽታቸው መንስኤ አድርገው በተደጋጋሚ ከሚጠቅሷቸው ነገሮች መካከል ይገኙበታል።”

አብዛኞቹ ሰዎች በእንዲህ ዓይነት ሕንፃዎች ውስጥ ያለውን ሁኔታ መቋቋም የሚችሉ መስለው ቢታዩም እንኳ አንዳንድ ሰዎች ከአስምና ከሌሎች የመተንፈሻ አካላት ችግሮች አንስቶ እስከ ራስ ምታትና አካላዊ ልፍስፍስነት ድረስ የተለያዩ የበሽታ ምልክቶች ይታዩባቸዋል። በጥቅሉ ሲታይ ሰዎቹ አካባቢውን ለቅቀው ሲሄዱ እነዚህ የበሽታ ምልክቶች ይጠፋሉ። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ “ሕሙማኑ በተለያዩ ኬሚካሎች በቀላሉ የመጠቃት በሽታ ሊይዛቸው ይችላል” ሲል ዘ ላንሴት የተሰኘው የብሪታንያ የሕክምና መጽሔት ገልጿል። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ኬሚካሎች በሚፈጥሩባቸው ችግር ሳቢያ ሲታመሙ ሌሎቹ የማይታመሙት ለምንድን ነው? ኬሚካሎች ምንም ዓይነት ችግር ሲፈጥሩባቸው የማይታዩ አንዳንድ ሰዎች ኬሚካሎች ባስከተሉባቸው መዘዝ የታመሙ ሰዎችን ችግር መረዳት አዳጋች ሊሆንባቸው ስለሚችል ይህን ጥያቄ ማንሳቱ አስፈላጊ ነው።

አንዳችን ከሌላው የተለየን ነን

ሁላችንም ለኬሚካሎች፣ ለጀርሞችም ሆነ ለቫይረሶች የምንሰጠው ምላሽ የተለያየ መሆኑን ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። በዚህ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በራሂያዊ ቅንብር፣ ዕድሜ፣ ጾታ፣ የጤና ሁኔታ፣ እየወሰድናቸው ያለናቸው መድኃኒቶች፣ ቀደም ሲል ይዞን የነበረ በሽታ፣ እንዲሁም እንደ አልኮል፣ ትምባሆ ወይም አደገኛ ዕፆች ያሉ ልማዶች ይገኙባቸዋል።

ለምሳሌ ያህል የሕክምና መድኃኒቶችን በተመለከተ “አንድ መድኃኒት የተፈለገውን ውጤት ማስገኘት አለማስገኘቱና ሊያስከትለው የሚችለው የጎንዮሽ ጉዳት” በዓይነቱ ልዩ በሆነው ተፈጥሮህ ላይ በእጅጉ የተመካ ነው ሲል ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ይገልጻል። ከእነዚህ የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል አንዳንዶቹ በጣም አደገኛ ሊሆኑ አልፎ ተርፎም ለሞት ሊዳርጉ ይችላሉ። ኤንዛይም የሚባሉት ፕሮቲኖች ሰውነታችንን በመድኃኒቶች ውስጥ ካሉት ኬሚካሎችና በዕለታዊ እንቅስቃሴያችን ወደ ሰውነታችን ከሚገቡ በካይ ነገሮች ያጠራሉ። ሆኖም ይህን “የማጽዳት” ሥራ የሚያከናውኑት እነዚህ ኤንዛይሞች ምናልባትም በዘር ውርስ፣ ቀደም ሲል መርዛማ በሆኑ ነገሮች በደረሰባቸው ጉዳት ወይም በአመጋገብ ጉድለት ሳቢያ እንከን ያለባቸው ከሆኑ ወደ ሰውነታችን የሚገቡት ኬሚካሎች በአደገኛ ሁኔታ ሊከማቹ ይችላሉ። *

ኤም ሲ ኤስ ከኤንዛይም ጋር ዝምድና ካላቸው ፖርፊሪያስ ተብለው ከሚጠሩ የደም በሽታዎች ጋር በሚመሳሰል መንገድ ተገልጿል። ብዙውን ጊዜ ከተሽከርካሪዎች ጭስ አንስቶ እስከ ሽቶ ድረስ የተለያዩ ኬሚካሎች የፖርፊሪያስ ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚያስከትሉት ሁኔታ ኤም ሲ ኤስ ባለባቸው ሰዎች ላይ ከሚያስከትሉት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው።

በአእምሮም ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል

አንዲት የኤም ሲ ኤስ ምልክቶች የሚታዩባት ሴት አንዳንድ የተለመዱ ዓይነት ኬሚካሎች እንደሚያፈዝዟት ለንቁ! ዘጋቢ ገልጻለች። “ባሕሪዬ ይለዋወጣል። እቆጣለሁ፣ መንፈሴ ይረበሻል፣ እነጫነጫለሁ፣ ፍርሃት ፍርሃት ይለኛል፣ እንዲሁም ሰውነቴ ይልፈሰፈሳል። . . . እነዚህ ምልክቶች ለጥቂት ሰዓታት እንዲያም ሲል በርከት ላሉ ቀናት ሊቆዩ ይችላሉ” ስትል ተናግራለች። ከዚያ በኋላ ደግሞ አንጎበርና ደረጃው የተለያየ የመንፈስ ጭንቀት ይሰማታል።

እነዚህ ነገሮች ኤም ሲ ኤስ ላለባቸው ሰዎች እንግዳ አይደሉም። ዶክተር ክላውዲያ ሚለር እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ሰዎች እንደ ተባይ ማጥፊያ ላሉ ኬሚካሎች ሲጋለጡም ይሁን የቤት ውስጥ የተበከለ አየር [ድምረህመም] ሲይዛቸው ሥነ ልቦናዊ ችግር እንደሚገጥማቸው ከደርዘን በላይ የሚሆኑ አገሮች ሪፖርት አድርገዋል። . . . አሟሚ ለሆኑ ንጥረ ነገሮች የተጋለጡ ሠራተኞች በከባድ የፍርሃት ስሜት ወይም በመንፈስ ጭንቀት የመዋጣቸው አጋጣሚ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ተገንዝበናል። . . . ስለዚህ ለሌሎች በጣም የምናስብና በሰውነት ውስጥ ካሉት ሥርዓተ አባላት ሁሉ በኬሚካል በቀላሉ የሚጎዳው አንጎል ሊሆን እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል።”

ለኬሚካል መጋለጥ ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ሊያስከትል ቢችልም እንኳ የዚህ ተገላቢጦሽ ሊከሰት እንደሚችል ማለትም ሥነ ልቦናዊ ችግሮች አንድ ሰው በቀላሉ በኬሚካሎች እንዲጠቃ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ብዙ ዶክተሮች ያምናሉ። አካላዊ ችግሮች ኤም ሲ ኤስን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አጥብቀው የሚያምኑት ከላይ የተጠቀሱት ዶክተር ሚለር እና ዶክተር ኒኮላስ አሽፎርድ “የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣትን ወይም ፍቺን የመሰሉ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ገጽታዎች ያሏቸው ክስተቶች በሰውነት የበሽታ መከላከያ ሥርዓት ላይ ቀውስ ሊያስከትሉ እንደሚችሉና አንዳንድ ሰዎችን ዝቅተኛ መጠን ባላቸው ኬሚካሎች በቀላሉ እንዲጠቁ ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ” ያምናሉ። “በሥነ ልቦናዊና በግብራካላዊ [physiological] ሥርዓቶች መካከል ያለው ዝምድና በእርግጥም በጣም ውስብስብ ነው።” ኤም ሲ ኤስ በአካላዊ ችግሮች ሳቢያ ሊከሰት እንደሚችል የሚያምኑት ሌላዋ ዶክተር ሼሪ ሮጀርስ “ውጥረት አንድ ሰው ይበልጥ በኬሚካሎች እንዲጠቃ ያደርገዋል” ሲሉ ገልጸዋል።

የኤም ሲ ኤስ በሽተኞች ጤንነታቸውን ለማሻሻል ወይም ቢያንስ ቢያንስ የሚታዩባቸውን የበሽታ ምልክቶች ለመቀነስ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ይኖራል?

ኤም ሲ ኤስ ለያዛቸው ሰዎች የሚሆን እርዳታ

ምንም እንኳ ኤም ሲ ኤስ ይህ ነው የሚባል ፈውስ ባይገኝለትም ብዙዎቹ ሕሙማን የሚታዩባቸውን የበሽታ ምልክቶች መቀነስ የቻሉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ጤናማ ሕይወት መምራት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ችግሩን እንዲቋቋሙ የረዳቸው ነገር ምንድን ነው? አንዳንዶቹ ሕመማቸውን የሚቀሰቅሱባቸውን ኬሚካሎች በተቻለ መጠን እንዲያስወግዱ ሐኪም የሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው እንደጠቀማቸው ይናገራሉ። * የኤም ሲ ኤስ ሕመምተኛ የሆነችው ጁዲ ኬሚካሎችን ማስወገዷ በእጅጉ ረድቷታል። ጁዲ ኤፕስታይን-ባር በተሰኘ ቫይረስ ሳቢያ ታማ በነበረበት ወቅት ቤቷ ውስጥ ለተረጨ ተባይ ማጥፊያ በእጅጉ በመጋለጧ ከጊዜ በኋላ የኤም ሲ ኤስ በሽተኛ ሆነች።

እንደ ብዙዎቹ የኤም ሲ ኤስ በሽተኞች ጁዲም በቤት ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ብዙ ኬሚካሎች ይረብሿታል። በመሆኑም የጽዳት ሥራዋን የምታከናውነውና ልብስ የምታጥበው ከኬሚካሎች በጠሩ ሳሙናዎችና በቤኪንግ ሶዳ ነው። ኮምጣጤ ልብስን በማለስለስ ረገድ በጣም ውጤታማ ሆኖ አግኝታዋለች። ቁም ሳጥኗ ውስጥና መኝታ ቤቷ ውስጥ ያሉት ልብሶችና ጨርቆች ከተፈጥሮ ክሮች የተሠሩ ብቻ ናቸው። ባለቤቷ በደረቅ እጥበት የታጠቡ ልብሶቹን ቁም ሳጥን ውስጥ ከማስገባቱ በፊት ልብሶቹ ላይ ያለው ጠረን እስኪለቅ ድረስ ለሳምንታት ጥሩ አየር ባለበት ቦታ ላይ ያቆያቸዋል።

እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ባለው ዓለም ውስጥ የኤም ሲ ኤስ በሽተኞች ችግር ከሚፈጥሩባቸው ኬሚካሎች ሙሉ በሙሉ መራቅ አዳጋች ሊሆንባቸው ይችላል። አሜሪካን ፋሚሊ ፊዚሺያን “ብዙውን ጊዜ ኤም ሲ ኤስ የሚያስከትለው ትልቁ ጉዳት በሽተኛው ከኬሚካሎች ራሱን ለመጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ከሌሎች ሰዎች የሚገለልና የሚርቅ መሆኑ ነው” ሲል ይገልጻል። ሕሙማኑ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንቅስቃሴያቸውን ቀስ በቀስ በማስፋት መሥራታቸውና ማኅበራዊ ግንኙነት ማድረጋቸው ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ጽሑፉ ይጠቁማል። ከዚሁ ጋር ጎን ለጎን ደግሞ ዘና ማለትና አተነፋፈስን መቆጣጠር የሚቻልባቸውን ዘዴዎች በመማር የሚሰማቸውን የድንጋጤና የመሸበር ስሜት ለማስወገድ እንዲሁም የልብ ትርታቸው ሥርዓቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ መጣር አለባቸው። ዋናው ዓላማ ሕሙማኑ ኬሚካሎችን ጨርሶ ከሕይወታቸው ውስጥ እንዲያስወግዱ ማድረግ ሳይሆን ቀስ በቀስ ከኬሚካሎች ጋር እንዲላመዱ መርዳት ነው።

ሌላው በጣም ጠቃሚ ሕክምና ሌሊት ጥሩ እንቅልፍ ማግኘት ነው። በኤም ሲ ኤስ በሽታ የተጠቃውና በአሁኑ ጊዜ ከበሽታው ምልክቶች ነፃ ወደመሆን ደረጃ የደረሰው ዴቪድ ለማገገም የረዳው አንዱ ነገር ንጹሕ አየር እንደ ልብ በሚያገኝበት መኝታ ክፍል ውስጥ መተኛቱ እንደሆነ ተናግሯል። የኤም ሲ ኤስ ተጠቂ የሆኑት ኧርነስት እና ባለቤቱ ሎሬንም “ሌሊት ጥሩ እንቅልፍ መተኛት ቀን ቀን ልናስወግዳቸው ለማንችላቸው ኬሚካሎች መጋለጣችን ሊያስከትልብን የሚችለውን ችግር ለመቋቋም በእጅጉ” እንደሚረዳ ተገንዝበዋል።

ጥሩ የአመጋገብ ልማድም ጤንነትን ለመጠበቅም ሆነ በሽታን ለማሸነፍ ምንጊዜም አስፈላጊ እንደሆነ የታወቀ ነው። እንዲያውም “በሽታን ለመከላከል ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር” ጥሩ የአመጋገብ ልማድ ማዳበር እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል። ሰውነት ዳግም ጤነኛ እንዲሆን ከተፈለገ ቢያንስ ቢያንስ የሰውነት ሥርዓቶች በተቻለ መጠን በብቃት መሥራት አለባቸው። እንደ ቫይታሚን ያሉ ተጨማሪ ንጥረ ነገሮችን መውሰድ ሊጠቅም ይችላል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግም ለጤና ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም ሲያልባችሁ በሰውነታችሁ ውስጥ ያሉ መርዘኛ የሆኑ ንጥረ ነገሮች በቆዳችሁ በኩል ይወጣሉ። ከዚህም ሌላ ጥሩ የአእምሮ ዝንባሌ ማዳበርና ተጫዋች መሆን እንዲሁም በሌሎች መወደድና ለሌሎች ፍቅር ማሳየት በእጅጉ ይጠቅማል። እንዲያውም አንዲት ዶክተር ለኤም ሲ ኤስ ታካሚዎቻቸው በሙሉ የሚያዝዙት መድኃኒት “ፍቅርና ሳቅ” ነው። አዎን፣ “ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት።”​—⁠ምሳሌ 17:​22

ይሁን እንጂ እንደ ሽቶዎች፣ ለጽዳት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች፣ ጠረን ለመለወጥ የሚነፉ ፍሊቶችና ሌሎች ኬሚካሎች ያሉትን አብዛኞቻችን በዕለታዊ እንቅስቃሴያችን የሚያጋጥሙንን ነገሮች መቋቋም የማይችሉት የኤም ሲ ኤስ በሽተኞች ፍቅር የሰፈነበት አስደሳች ወዳጅነት መመሥረት በጣም አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። ኤም ሲ ኤስ ያለባቸው ሰዎች እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በተሳካ ሁኔታ መወጣት የሚችሉት እንዴት ነው? ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ሰዎች ኤም ሲ ኤስ ያለባቸውን ሰዎች ለመርዳት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጉዳዮች ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ንቁ! የሕክምና መጽሔት አይደለም፤ በመሆኑም ስለ ኤም ሲ ኤስ የሚያትቱት እነዚህ ርዕሶች የወጡት የትኛውንም የሕክምና አመለካከት ለማራመድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በቅርቡ የተደረሰባቸውን ግኝቶችና አንዳንድ ዶክተሮችና ሕሙማን በሽታውን ለመቋቋም የሚረዳ ሆኖ ያገኙትን ነገር የሚያትቱ ናቸው። የንቁ! መጽሔት የኤም ሲ ኤስን መንስኤ፣ የበሽታውን ባሕርይ ወይም ለበሽታው ተጠቂዎች የሚሰጡትን ወይም በሽተኞቹ የሚጠቀሙባቸውን በርካታ ሕክምናዎችና ፕሮግራሞች በተመለከተ በሐኪሞች መካከል ዓለም አቀፋዊ ስምምነት እንደሌለ ያምናል።

^ አን.12 ላክቴስ የተሰኘው ኤንዛይም፣ የኤንዛይም ጉድለት ለሚያስከትለው ሁኔታ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። የላክቴስ ችግር ያለባቸው ሰዎች በወተት ውስጥ የሚገኘው ላክቶስ ከሰውነታቸው ጋር መዋሃድ ስለማይችል ወተት ሲጠጡ ይታመማሉ። ሌሎች ሰዎች ደግሞ በፎርማጆና በሌሎች ምግቦች ውስጥ የሚገኘውን ታይራሚን የተባለ ኬሚካል ወደ ጉልበት የሚለውጠው ኤንዛይም ጉድለት አለባቸው። በዚህም ሳቢያ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ዓይነቶቹን ምግቦች ሲመገቡ ገሚስ ራስምታት ሊይዛቸው ይችላል።

^ አን.20 ኤም ሲ ኤስ እንደያዛቸው የሚሰማቸው ሰዎች ጥሩ ስም ካተረፈ ሐኪም ሙያዊ እርዳታ ለማግኘት መጣር ይኖርባቸዋል። መጀመሪያ ላይ የተሟላ ምርመራ ሳታደርጉ በአኗኗራችሁ ላይ ሥር ነቀል፣ ምናልባትም ደግሞ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ለውጥ ማድረግ አግባብ አይደለም። የምርመራው ውጤት በአመጋገባችሁ ወይም በአኗኗራችሁ ላይ ጥቂት ማስተካከያዎች ብቻ በማድረግ የበሽታ ምልክቶቻችሁን መቀነስ አልፎ ተርፎም ማስወገድ እንደምትችሉ የሚጠቁም ሆኖ ሊገኝ ይችላል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ብዙ ዓይነት ኬሚካሎች ያስፈልጉሃልን?

ሁላችንም መርዘኛ ሊሆኑ ለሚችሉ ኬሚካሎች የምንጋለጥበትን አጋጣሚ በተቻለ መጠን መቀነስ አለብን። ይህም በቤት ውስጥ የምናስቀምጣቸውን ኬሚካሎች ይጨምራል። ኬሚካል ኤክስፖዠርስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በቤት ውስጥ የምንጠቀምባቸው አየር የሚበክሉ ንጥረ ነገሮች በኬሚካሎች በቀላሉ እንድንጠቃ ከሚያደርጉ ዋና ዋና ነገሮች መካከል የሚደመሩ ናቸው። ዝቅተኛ መጠን ያላቸውን በቀላሉ የሚተንኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ካርቦናማ ኬሚካሎች የያዙ ውስብስብ ድብልቆች ቤት ውስጥ ይገኛሉ።” *

ስለዚህ አሁን የምትጠቀምባቸውን ያህል ብዙ ኬሚካሎች፣ በተለይ ደግሞ የተባይ ማጥፊያዎችና በቀላሉ የሚተኑ አሟሚ ንጥረ ነገሮችን የያዙ የምርት ውጤቶች በእርግጥ ያስፈልጉህ እንደሆነና እንዳልሆነ ራስህን ጠይቅ። መርዝነት የሌላቸውን ሌሎች አማራጮች ለመጠቀም ሞክረሃል? ይሁን እንጂ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ኬሚካል ለመጠቀም የምትገደድ ከሆነ ኬሚካሉን ከመጠቀምህ በፊት አስፈላጊ የሆኑትን ጥንቃቄዎች በሙሉ ማድረግ ይኖርብሃል። በተጨማሪም ልጆች ሊደርሱ በማይችሉበትና ከኬሚካሉ ሊወጣ የሚችለው ተን ጉዳት በማያደርስበት ቦታ አስቀምጠው። በደንብ በተገጠሙ አንዳንድ ዕቃዎች ውስጥ ያለ ኬሚካልም እንኳ ሊተን እንደሚችል አስታውስ።

በተጨማሪም ኬሚካሎችን ጠንቅቀን ማወቃችን በቆዳችን ላይ በምናደርገው ወይም በምናፈስሰው ነገር ላይ ጥንቃቄ እንድናደርግ ይረዳናል። ሽቶዎችን ጨምሮ ብዙ ኬሚካሎች በቆዳችን በኩል ዘልቀው በመግባት ከደማችን ጋር ይቀላቀላሉ። ቆዳ ላይ የሚቀቡ መድኃኒቶች የሚታዘዙትም ለዚህ ነው። ስለዚህ መርዘኛ የሆነ ኬሚካል ቆዳህ ላይ ከፈሰሰ “የመጀመሪያውና አፋጣኙ የሕክምና ዘዴ በደንብ በመታጠብ ኬሚካሉን ከቆዳህ ላይ ማስወገድ ነው” ይላል ታየርድ ኦር ቶክሲክ? የተሰኘው መጽሐፍ።

በኬሚካሎች በቀላሉ የመጠቃት ችግር ያለባቸው ብዙ ሰዎች ሽቶዎች ያስቸግሯቸዋል። ወደ 95 በመቶ የሚጠጉት ሽቶዎች ከነዳጅ የተገኙ ሰው ሠራሽ ውሁዶችን የያዙ ናቸው። እነዚህም አሴቶን፣ ካምፎር፣ ቤንዛልዴሃድ፣ ኤታኖል፣ ጂ-ቴርፒኒን የተባሉትንና ሌሎች ብዙ ውሁዶችንም ይጨምራሉ። እነዚህ ንጥረ ነገሮች በጤና ላይ ሊያስከትሉት የሚችሉት አደገኛ ሁኔታ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአካባቢ ጥበቃ ድርጅት ታትሞ ወጥቷል። ጠረንን ለመለወጥ በሚነፉ ፍሊቶች ውስጥ ያሉት ኬሚካሎችም እንዲሁ ናቸው። በአካባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ ጥናት የሚያካሂዱ ሳይንቲስቶች ጠረንን ለመለወጥ በሚነፉ ፍሊቶች ላይ ጥናት የሚያካሂዱት “በቤት ውስጥ ያለውን አየር እንደሚበክሉት እንጂ ወደተሻለ ሁኔታ እንደሚለውጡት አድርገው በመመልከት አይደለም” ሲል ዩኒቨርሲቲ ኦቭ ካሊፎርንያ አት በርክሌይ ዌልነስ ሌተር ገልጿል። ጠረንን ለመለወጥ ተብለው የሚነፉ ፍሊቶች መጥፎውን ሽታ ይደብቁታል እንጂ አያስወግዱትም።

ካልኩሌትድ ሪስክስ የተባለው መጽሐፍ “በጣም ጠቃሚ ከሆኑት የሥነ መርዝ ሳይንስ ጽንሰ ሐሳቦች አንዱ ሁሉም ዓይነት ኬሚካሎች እንደየሁኔታው መርዝ ሊሆኑብን ይችላሉ [የሚለው ነው]” ሲል ይገልጻል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.33 ቤትህ መርዘኛ ሊሆኑ በሚችሉ የተለያዩ ኬሚካሎች እንዳይበከል መከላከል የምትችልባቸው መንገዶች በታኅሣሥ 22, 1998 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ ተዘርዝረዋል።