ጥንታዊው ዛፍ ቆራጭ ዛሬም ከሥራው አልቦዘነም
ጥንታዊው ዛፍ ቆራጭ ዛሬም ከሥራው አልቦዘነም
የሰው ልጅ ምሳርን፣ ሽብልቅንና መጋዝን ጨምሮ እንጨት ለመቁረጥ የሚያገለግሉ ብዙ መሣሪያዎች ሠርቷል። ከዚህም በተጨማሪ ግዙፍ የዛፍ ግንዶችን ሊቆርጥ የሚችል ስለታም የብረት መጋፊያ ያላቸው ትራክተሮችም አሉ። ከሁሉም ጥንታዊ የሆነው መቁረጫ ግን ሰው ሠራሽ መሣሪያ አይደለም። እነዚህ የጥንታዊው ዛፍ ቆራጮች ማለትም ቢቨር የተባለው እንስሳ ስለታም ጥርሶች ናቸው።
አንድ እድገቱን የጨረሰ ቢቨር ርዝመቱ 1.3 ሜትር ሊደርስና እስከ 27 ኪሎ ግራም ድረስ ሊመዝን ይችላል። ከላይና ከታች ያሉት የፊት ጥርሶቹ ያለማቋረጥ ስለሚያድጉ ያገኘውን ሁሉ ዘወትር መጋጥ ግድ ይሆንበታል። የፊት ጥርሶቹን የሸፈነው ጠንካራ ጥሩር [enamel] ጥርሶቹን ስለታም እንዲሆኑ ያደርጋል። እነዚህ ተፈጥሯዊ መሮዎች ወደ ውስጥ አጠፍ ያሉና በጠንካራ የመንገጭላ ጡንቻዎች የሚደገፉ በመሆናቸው ጠንካራ የሚባለውን እንጨት ሳይቀር በቀላሉ ይቆርጣሉ።
የሚሞቅ ልብስና ብዙ አገልግሎት ያለው ጅራት
ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ባለበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ሙቀት የሚሰጥና ውኃ የማያስገባ ካፖርት ያለውን ዋጋማነት ይገነዘባሉ። ቢቨሮች በተፈጥሮ ወፍራምና ፀጉራም ካባ ስለለበሱ እንዲህ ዓይነት ልብስ መሸመት አያስፈልጋቸውም። ፈዘዝ ካለው እስከ ደማቁ ቡናማ ድረስ የተለያየ ቀለም ያለው የቢቨሮች ፀጉራማ ልብስ ባለ ሁለት ድርብ ነው። ከታች የሚገኙት ጥቅጥቅ ያሉ ፀጉሮች በጣም ስስ የሆኑና እንስሳውን ከውኃና ከቅዝቃዜ ለማስጣል በሚችል መንገድ እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ ብናኞች አሉት። ረዘም ያሉት ወፋፍራሞቹ ፀጉሮች ደግሞ የታችኞቹን ፀጉሮች በመሸፈን ቢቨሩን ከውኃ ለማስጣል ያገለግላሉ። ፀጉሮቹ የሚያብረቀርቅ መልክና ልስላሴ ስላላቸው ከቢቨር ቆዳ የተሠሩ ልብሶች በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ መሆናቸው ምንም አያስገርምም! እንዲያውም በአንድ ወቅት ከቢቨር ቆዳ የተሠሩ አጎዛዎች ካናዳ ውስጥ እንደ ገንዘብ አገልግለዋል!
ሁሉም ቢቨሮች ከጅራታቸው ሥር አስገራሚ ተግባር የሚያከናውኑ ሁለት ጥንድ ዕጢዎች አሏቸው። አንደኛው ጥንድ ለየት ያለ ቅባት ሲያመነጭ ሌላኛው ደግሞ ካስቶሪየም የተባለ ጠንካራ መዓዛ ያለው ነገር ያመነጫል። ቢቨሩ ይህንን ፈሳሽ ለብዙ አገልግሎት የሚጠቀምበት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ፀጉሩን ከውኃ ለመከላከልና ሌሎች ቢቨሮችን ለመሳብ ይጠቀምበታል። ካስቶሪየም ለሰዎችም የሚሰጠው ጥቅም አለ። ሽቱ ቀማሚዎች ለአንዳንድ ዓይነት መዓዛ ይጠቀሙበታል።
የቢቨር ጅራት ለየት ያለ ነው። እንደ መቅዘፊያ ያለ ቅርጽ ያለውና ርዝማኔው እስከ 0.3 ሜትር የሚደርስ ሲሆን የተለያዩ አገልግሎቶች ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል የቢቨር ጅራት በውኃ ውስጥ ለጉዞ የሚረዳ መቅዘፊያ ሆኖ ያገለግላል።
መሬት ላይ ደግሞ ቢቨሩ ዛፎችን በሚገዘግዝበት ጊዜ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ይረዳዋል። አደጋ በሚያንዣብብበት ጊዜ ቢቨሩ ውኃውን በጅራቱ በመምታት በአቅራቢያው የሚገኙ ቢቨሮች በሙሉ እንዲጠነቀቁ ያነቃቸዋል። አንድ መወገድ ያለበት የተሳሳተ አመለካከት ግን አለ። ቢቨሮች ግድብ ሲሠሩ ጅራታቸውን ጭቃ ለመለጠፍ እንደ ግንበኛ መለሰኛ ማንኪያ አይጠቀሙበትም።ምግብና ውኃ
ቢቨሮች የሚመገቡት ምንድን ነው? ዋነኛ ምግባቸው ፖፕላር እና ዊሎው የተባሉት ዛፎች የውስጠኛ ለስላሳ ቅርፊትና ቀንበጥ ነው። ቢቨር ለአንድ የግንባታ ፕሮጄክት ዛፍ በሚቆርጥበት ጊዜ እግረ መንገዱንም ተወዳጅ ምግቡን ያጣጥማል። አንዳንድ ጊዜ አንዱ ቢቨር ግንዱን ለመቁረጥ ሲቦረቡር ሌላው ቢቨር ሳይታይ ቀስ ብሎ መጥቶ ጣፋጭ ከሆነው የእንጨት ፍርፋሪ ይሠርቀዋል።
በክረምት ወቅት ቢቨሮች ምግባቸውን ለማከማቸት ልዩ የሆነ ዘዴ ይጠቀማሉ። በመጀመሪያ ከውኃው በታች ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ይቆፍራሉ። ቢቨሮች ለ15 ደቂቃ ያህል ውኃ ውስጥ ጠልቀው መቆየት ስለሚችሉ ይህ ለእነርሱ በጣም አስቸጋሪ ሥራ አይደለም። ከዚያም ቢቨሮች ከጉድጓዱ ቀዳዳ በላይ ባለው የውኃው ወለል ላይ የአስፐን እና የዊሎው እንዲሁም የሌሎችን ዛፎች ቅርንጫፍ ይረበርባሉ። ብዙ እንጨት በተከመረ ቁጥር ክምሩ ወደታች ወደ ጉድጓዱ መጨረሻ እየወረደ ይሄዳል። ከጊዜ በኋላ ኩሬውን በረዶ ሲከድነውና በውኃው ወለል ላይ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሲገታ ቢቨሮቹ ከውኃ በታች ባለው “ጓዳ” ውስጥ በቂ ምግብ ይኖራቸዋል።
ስለ ውኃ ከተነሣ የቢቨሮችን ያህል በውኃ ውስጥ ተመችቶት የሚኖር የየብስ እንስሳ የለም ለማለት ይቻላል። በቅባት አማካኝነት ውኃ ከማያርሰውና ጥቅጥቅ ካለው ፀጉራቸው በተጨማሪ በጣም ቀዝቃዛ በሆነው ውኃ ውስጥ ከብርድ የሚከላከልላቸው ታህተ-ቆዳይ ስብ (subcutaneous fat) አላቸው። እንዲያውም ቢቨሮች እንስቶቻቸውን የሚገናኙት ከውኃ በታች ነው! ውኃ በቢቨሮች ሕይወት ውስጥ ይህን ያህል ከፍተኛ ሚና ስለሚጫወት ቢቨሮችን ከሐይቅ ወይም ከወንዞች አካባቢ ርቀው አታገኛቸውም።
ቢቨሮችና የሰው ልጅ
ቢቨሮች በቀላሉ የሚለምዱ ሲሆን በደግነት የሚቀርቧቸውን ሰዎች በቀላሉ ጓደኛ የሚያደርጉ እንስሳት ናቸው። እነዚሁ እንስሳት ዘወትር ንጽሕናቸውን ይጠብቃሉ። የጥንቶቹ የምድረ አሜሪካ ነዋሪዎች ቢቨሮችን በመኖሪያ አካባቢያቸው እንደ ቤት እንስሳት ይንከባከቡ ነበር። ይሁንና አንድ ቢቨር ወደ ቤትህ ለማምጣት ከመወሰንህ በፊት ደግመህ ደጋግመህ ማሰብ ይኖርብሃል። ችግሩ ግንባታ ከማካሄድ አለመቦዘናቸው ነው። ኢንቫይሮሜንታል ኢንጂነር የሆኑት ኤሊስ አውትዋተር እንደጻፉት ከሆነ “በቤት ውስጥ ካስገቧቸው የጠረጴዛዎችንና የወንበሮችን እግሮች በመቁረጥ በየዕቃው መሃል የራሳቸውን ትናንሽ ግድቦች ይገነባሉ።” በጓሮህ ውስጥ ያሉ ዛፎችና የአጥር ቋሚዎችም ተመሳሳይ ዕጣ ሊገጥማቸው ይችላል።
ይሁን እንጂ በቢቨሮችና በሰዎች መካከል ከዚህም የከፉ ችግሮች ተነሥተዋል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ የመሬት ባለ ይዞታዎች ግድቦቹ ጅረቱ እንዲሞላና ከዚያ የሚፈስሰው ውኃ በንብረት ላይ ጉዳት እንዲያደርስ ምክንያት ይሆናሉ በማለት ያማርራሉ። ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ቢቨሮች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ያለውን ጠቀሜታ በመጠቆም እንዲህ ያለውን ምሬት ያስተባብላሉ። ለምሳሌ ያህል ውኃው በአንድ ወገን እንዲከማች የሚያደርገው የቢቨሮች ግንባታ ውኃው እንዲጠበቅና እንዲጣራ የሚረዳ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ዓይነት ዝርያዎች ሕልውናቸው እንዲጠበቅ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። እንዲያውም አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ ቢቨሮች ያሉባቸው ኩሬዎች ድርቅ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ያስችላሉ።
ስለ ተፈጥሮ የሚያጠኑ አንዳንድ ሊቃውንት በአሕጉራዊው የዩናይትድ ስቴትስ ግዛት ውስጥ 10, 000, 000 የሚደርሱ ቢቨሮች እንዳሉ ይገምታሉ። ይሁን እንጂ ከዛሬ 500 ዓመታት በፊት ከ200, 000, 000 የሚበልጡ ቢቨሮች በዚሁ አካባቢ ይኖሩ እንደነበር አንዳንድ ግምቶች ይጠቁማሉ። እስቲ አስበው:- የመጀመሪያዎቹ አውሮፓውያን ወደዚህ አካባቢ ከመምጣታቸው በፊት በሰሜን አሜሪካ ደኖች ውስጥ የተሠማሩ በአሥር ሚልዮኖች የሚቆጠሩ “ዛፍ ቆራጮች” ነበሩ። ይሁን እንጂ እነዚያ የመጀመሪያ ሰፋሪዎች ወደ አካባቢው ሲደርሱ ያገኙት ዛፍ የሚባል ነገር የሌለበት ጠፍ ምድር ሳይሆን በጣም ሰፊና ጥቅጥቅ ያለ ደን ነበር። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ቢቨሮች የምድራችንን ስነ ምሕዳር በማስጠበቅ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። እንግዲያውስ ጥንታዊው ዛፍ ቆራጭ ዛሬም ከሥራው ባለ መቦዘኑ አመስጋኝ ልንሆን ይገባናል!
[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
“ሲሠሩ እንደ ቢቨር”
ይህን አባባል ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረው ሰው ቢቨሮች የውኃ ግድብ ሲሠሩ ወይም መኖሪያቸውን ሲገነቡ ተመልክቶ መሆን አለበት። በእርግጥም እነዚህ እንስሳት ዛፍ ሲቆርጡና ቁርጥራጮቹን ወደ ግንባታው ቦታ ሲያጓጉዙ ለተመለከተ ድካም የሚባል ነገር የሚያውቁ አይመስልም። አንዳንድ ጊዜ የግንባታ ዕቃዎችን ወደ ተገቢው ቦታ ለማጓጓዝ ሲሉ ብቻ መተላለፊያ ቦይ ይሠራሉ።
ይሁን እንጂ ቢቨሮች ግድባቸውን የሚሠሩት እንዴት ነው? በመጀመሪያ የግንባታውን መሠረት ለመጣል ከውኃው በታች ቅርንጫፎችን ያስቀምጣሉ። ጅረቱ ስፋት ካለው ግድቡ የውኃውን ግፊት መቋቋም እንዲችል ከውኃ አቅጣጫ በተቃራኒ እንደ ቅስት አድርገው ይሠሩታል። ተጨማሪ እንጨት በማምጣት በመሃል ያለውን ክፍተት ይሞሉና ቀዳዳዎቹን በድንጋይና በጭቃ ይመርጓቸዋል። ቢቨሮች ግድቡ ጥንካሬ እንዲኖረው ለማድረግ ሲሉ ውኃው በሚፈስበት አቅጣጫ ቅርንጫፎችን ከወንዙ ዳር በመትከል ያጠናክሩታል። እነዚህ ታታሪ ፍጥረታት ለዚህ የእጅ ሥራቸው በየጊዜው እድሳት ያደርጉለታል!
ፀጥ ያለው ኩሬ ብዙም ሳይቆይ ነውጥ ይጀምራል። እዚህ ውስጥ ቢቨሮች አስተማማኝ የመኖሪያ ቦታ ይገነባሉ። በመጀመሪያ ግድቡ በግንባታ ላይ እያለ በወንዙ ዳርቻ ጉድጓድ ቢጤ ይቆፍራሉ። ከዚያም ከዳርቻው ራቅ ብሎ በእንጨትና በጭቃ የተገነባ መሬት ላይ ጉብ ብሎ የሚታይ ቤት ይሠራሉ። ቢቨሮች ራሳቸውን ከአዳኝ አውሬ ለመጠበቅ ሲሉ መግቢያቸውን የሚያደርጉት ከውኃ በታች ነው። ይህም አስተማማኝ ማረፊያና ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት ቦታ ይሆንላቸዋል!
ቢቨሮች በእርግጥም ታታሪ ሠራተኞች ናቸው። በዋዮሚን ዩ ኤስ ኤ የሚገኙ ሳይንቲስቶች ለረጅም ጊዜ አንድም ቢቨር ታይቶበት በማያውቅ አካባቢ አምስት ተባዕትና አምስት እንስት ቢቨሮችን አሠማሩ። ከአንድ ዓመት በኋላ ተመራማሪዎቹ ተመልሰው ሲሄዱ አምስት ራሳቸውን የቻሉ ኩይዋሶች (colonies) ተመሥርተውና 55 ግድቦች ተሠርተው አግኝተዋል!
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቢቨር በሥራ ላይ፤ የቢቨር ማረፊያና ግድብ፤ ግልገል ቢቨር