በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጾታዊ ትንኮላን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ጾታዊ ትንኮላን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .

ጾታዊ ትንኮላን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

“ወንዶቹ በፉጨትና በመጮህ ይተናኮላሉ።”—ካርላ፣ አየርላንድ

“ልጃገረዶች አሁንም አሁንም ስልክ ይደውላሉ። ወኔህን ለማዳከም ነው የሚሞክሩት።”—ጄሰን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“እጄን ይነካካኛል፤ እንዲሁም በእጁ ለመያዝ ይሞክራል።” ​—⁠ዮኬኮ፣ ጃፓን

“ልጃገረዶች ብልግና አዘል አስተያየቶች ይሰነዝሩልኛል።”​—⁠አሌክሳንደር፣ አየርላንድ

“ከትምህርት ቤት አውቶቡስ ላይ ሆኖ የሚጮህብኝ አንድ ልጅ አለ። ከእኔ ጋር ተቀጣጥሮ የመጫወት ፍላጎት ኖሮት አይደለም። እንዲሁ ሊተናኮለኝ ፈልጎ ነው።”—ሮዝሊን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በማሽኮርመም ዓይን መመልከት፣ ጾታዊ መልእክት ያለው “ሙገሳ፣” ጸያፍ ቀልድ፣ በግልጽ የሚፈጸም ጾታዊ ጉንተላና የመሳሰለው ነገር በሌላኛው ወገን የማይፈለግ ከሆነና ከተደጋገመ ብዙውን ጊዜ ጾታዊ ትንኮላ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ዓለም አቀፋዊ የሆነ የአኃዝ መረጃ ማግኘት አዳጋች ቢሆንም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱት ልጆች መካከል አብዛኞቹ ጾታዊ ትንኮላ እንደሚደርስባቸው ጥናቶች ያሳያሉ።

ታዲያ ጾታዊ ትንኮላ ምንድን ነው? ኮፒንግ ዊዝ ሴክሹዋል ሃራስመንት ኤንድ ጀንደር ባያስ በሚል ርዕስ በዶክተር ቪክቶሪያ ሻው የተዘጋጀው መጽሐፍ እንዲህ የሚል ፍቺ ሰጥቶታል:- “አንድን ሰው በጾታ ስሜት ማስቸገር . . . በድርጊት (አንድን ሰው በጾታ ስሜት መነካካትን የመሰለ)፣ በቃል (ስለ አንድ ሰው ቁመና ተገቢ ያልሆኑ አስተያየቶች መስጠትን የመሰለ)፣ ወይም አለ ቃል ሊሆን ይችላል።” አንዳንድ ጊዜ ትንኮላው የብልግና ሐሳቦች መሰንዘርንም ይጨምራል።

በትምህርት ቤት የሚያጋጥማችሁ አብዛኛው ትንኮላ የሚመጣው ምናልባት ከዕድሜ እኩዮቻችሁ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በአንዳንድ ሁኔታዎች እንደታየው እንዲህ ያለው አሳፋሪ ባሕርይ መምህራንን ከመሳሰሉት ትልልቅ ሰዎችም ይመጣል። ሬድቡክ በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ የሚባለው በጾታ ትንኮላ ወንጀል የተከሰሱት መምህራን ቁጥር “የሚወክለው የወንጀሉን ፈጻሚዎች እጅግ ጥቂቱን ቁጥር ብቻ ሳይሆን አይቀርም” የሚል ግምት ሰጥቷል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሳይቀር ሴቶችንና አንዳንዴ ደግሞ ወንዶችንም በጾታ መተናኮል የተለመደ ነበር። (ዘፍጥረት 39:​7፤ ሩት 2:​8, 9, 15) መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ሁኔታ እንደሚደርስ አስቀድሞ ተናግሮአል። “የመጨረሻው ቀን አስጨናቂ ይሆናል። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ስስታሞች፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞችና ተሳዳቢዎች ይሆናሉ፤ . . . ክፉዎች፣ ምህረት የሌላቸው፣ ሐሜተኞች፣ ጠበኞችና ጨካኞች ይሆናሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-3ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን) ስለዚህ ጾታዊ ትንኮላ በእናንተም ላይ ሊደርስ የሚችልበት አጋጣሚ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።

አምላክ እንዴት ያየዋል?

እርግጥ ይህን በመሰለው ጾታዊ ጥቃት የሚበሳጩት ሁሉም ወጣቶች አይደሉም። አንዳንዶችን ሊያስደስታቸው እንዲያውም ሙገሳ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደና አስደንጋጭ ውጤት ይዞ የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው የዚህ ጥቃት ሰለባ ከሆኑት መካከል 75 በመቶዎቹ ራሳቸውም ጭምር በሌሎች ላይ ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸማቸውን አምነዋል። አንዳንድ ትላልቅ ሰዎች በጾታ የመተናኮስን ባሕርይ አሳሳቢነት ልጅነት ነው በሚል ፈሊጥ አቃልለው በመመልከት ተገቢውን ትኩረት መንፈጋቸው ችግሩን ያባብሰው ይሆናል። ይሁን እንጂ አምላክ ይህን ነገር እንዴት ይመለከተዋል?

የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ዓይነት ጾታዊ ትንኮላዎች በግልጽ ያወግዛል። ጾታዊ ገደቦችን ጥሰን በመሄድ የሌሎችን ‘መብት እንዳንጋፋ’ [NW ] ተመክረናል። (1 ተሰሎንቄ 4:​3-8) እንዲያውም ወጣት ወንዶች በተለይ “ቈነጃጅቱን እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና” እንዲይዙ በግልጽ ታዝዘዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​1, 2) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዋዛን’ ያወግዛል። (ኤፌሶን 5:​3, 4) ስለዚህ ሌሎች በጾታ ስሜት ሲተናኮሏችሁ ብትቆጡ፣ ብትበሳጩ፣ ግራ ቢገባችሁና እንዲያውም እንደተዋረዳችሁ ሆኖ ቢሰማችሁ ምንም ስህተት የለበትም!

ምን እላለሁ?

ታዲያ አንድ ሰው በዚህ መንገድ የሚያስቸግራችሁ ከሆነ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይኖርባችኋል? አንዳንድ ጊዜ ደካማ ወይም ግልጽ ያልሆነ ምላሽ ተንኳዩ ይበልጥ በድርጊቱ እንዲገፋበት ከማድረግ በስተቀር ምንም የሚያስገኘው ጥቅም የለም። ዮሴፍ በአሠሪው ሚስት የብልግና ሐሳብ በቀረበለት ጊዜ ጥያቄውን እንዲያው ችላ ብሎ ከማለፍ ይልቅ ይህንን ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ግብዣ በጽኑ እንደተቃወመ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ዘፍጥረት 39:​8, 9, 12) ዛሬም ቢሆን ጥብቅና ቀጥተኛ መሆን ጾታዊ ትንኮላን ለመከላከል ከሁሉ የተሻለ አማራጭ ነው።

እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ በጾታ ስሜት የሚተናኮላችሁ ሰው እንዲህ የሚያደርገው ሆን ብሎ እናንተን ለማናደድ ላይሆን ይችላል። ጾታዊ ትንኮላ እንደሆነ አድርጋችሁ የወሰዳችሁት ነገር ምናልባትም የእናንተን ትኩረት ለመሳብ ተብሎ ብቻ የተደረገ የቂልነት ሙከራ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የማትፈልጓቸውን ትንኮላዎች ለማስወገድ ስትሉ ብቻ ያልታረመ ጠባይ ማሳየትን እንደ አማራጭ አድርጋችሁ አትውሰዱት። ከዚህ ይልቅ ‘እንዲህ ያለ ንግግር መስማት አልፈልግም፣’ ወይም ‘እባክህ፣ እጅህን ሰብስብ’ እንደሚሉ ያሉ አነጋገሮችን መጠቀሙ ብቻ ስሜታችሁን ለመግለጽ በቂ ሊሆን ይችላል። የምትጠቀሙባቸው ቃላት ምንም ዓይነት ይሁኑ መልእክታችሁን አታድበስብሱት። ቃላችሁ አይደለም ከሆነ አይደለም ይሁን! ወጣቷ አንድሪያ እንዲህ በማለት አስቀምጣዋለች:- “በደግነት ምላሽ ስትሰጧቸው ካልገባቸው በቀጥታ መንገር ያስፈልጋችኋል። ብዙውን ጊዜ ደግሞ የሚያስፈልገው ይህ ነው።” ፈርጠም ባለ አነጋገር ‘እረፍ ብዬሃለሁ እረፍ!’ ብሎ መናገር ውጤታማ ሊሆን ይችላል።

ሁኔታው እየከፋ ከሄደ ብቻችሁን መፍትሄ ለማግኘት አትሞክሩ። በጉዳዩ ላይ ከወላጆቻችሁ ወይም ከሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር ለመወያየት ሞክሩ። ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራዊ ሐሳቦች ይኖሯቸው ይሆናል። መላ ከጠፋ ሁኔታውን ለትምህርት ቤት ባለ ሥልጣናት ማሳወቁን አማራጭ አድርገው ይወስዱትም ይሆናል። እንዲህ ማድረጉ የቱንም ያህል ላያስደስታችሁ ቢችል ወደፊት ተመሳሳይ ነገር እንዳይደርስባችሁ ሊከላከልላችሁ ይችላል።

ትንኮላን መከላከል

እርግጥ፣ ገና ከመጀመሪያው የጥቃቱ ሰለባ ላለመሆን ጥረት ማድረጉ ከሁሉ የተሻለ ነው። በዚህ ረገድ ምን ሊረዳችሁ ይችላል? አንድሪያ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥታለች:- “ሌሎች ምናልባት ልቧ ይፈልጋል ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ ፍንጭ አትስጡ። ስለ ሁኔታው ሌሎችም መስማታቸው ስለማይቀር ተጽእኖውም በዚያው መጠን ይቀጥላል።” በዚህ ረገድ አለባበሳችሁ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ወጣቷ ማራ “በአለባበሴ አሮጊት መምሰል አልፈልግም። ሆኖም ወደ ሰውነቴ ትኩረት የሚስቡ ልብሶችንም አልለብስም” በማለት ተናግራለች። ጾታዊ ትንኮላን እየተቃወሙ የሌሎችን ስሜት የሚያነሳሱ ልብሶች መልበስ እርስ በርሱ የሚጋጭ መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ አለባበሳችን ‘ልከኝነትና ጤናማ አስተሳሰብ’ የሚንጸባረቅበት እንዲሆን ይመክረናል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:​9 NW 

የጓደኛ ምርጫችሁም ሌሎች እናንተን በሚይዙበት መንገድ ላይ ተጽእኖ ያደርጋል። (ምሳሌ 13:​20) ሮዝሊን የሚከተለውን አስተውላለች:- “በአንድ ቡድን ውስጥ የወንዶችን ትኩረት ማግኘት የሚፈልጉ አንዳንድ ሴቶች ካሉ ወንዶቹ እዚያ ያሉት ሁሉ ተመሳሳይ ስሜት ያላቸው ይመስላቸዋል።” ካርላም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሐሳብ ሰጥታለች:- “ሌሎች የሚሰነዝሯቸውን አስተያየቶች በደስታ ከሚቀበሉ ወይም የሌሎችን ትኩረት ማግኘት ከሚያስደስታቸው ልጆች ጋር አብራችሁ የምትሆኑ ከሆነ እናንተም የጥቃቱ ሰለባ ትሆናላችሁ።”

መጽሐፍ ቅዱስ በልቅ ጠባያቸው ከሚታወቁት የከነዓን ሴቶች ጋር ጓደኝነት ስለመሠረተች ዲና የተባለች ወጣት ይነግረናል። ይህ ድርጊቷ ለጾታ ጥቃት አጋለጣት። (ዘፍጥረት 34:​1, 2) መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ” የሚልበት ጥሩ ምክንያት አለው። (ኤፌሶን 5:​15) አዎን፣ በአለባበሳችሁ፣ በአነጋገራችሁና በጓደኛ ምርጫችሁ ‘ጠንቃቆች’ መሆናችሁ ጥቃቱን በመከላከል ረገድ ብዙ ሊረዳችሁ ይችላል።

ይሁን እንጂ ክርስቲያን ወጣቶች ከሆናችሁ ጾታዊ ትንኮላን ለመከላከል የሚያስችላችሁ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ሃይማኖታዊ አቋማችሁን ማሳወቅ ነው። የይሖዋ ምሥክር የሆነው ወጣቱ ቲሞን እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “ልጆቹ ምሥክር መሆኔን ሲያውቁ ሁሉም ዓይነት ትንኮላ ማለት እችላለሁ ቆመ።” አንድሪያ “ምሥክር መሆናችሁን ማሳወቃችሁ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። በብዙ መንገዶች ከእነርሱ እንደምትለዩና ጥብቅ የሆኑ የሥነ ምግባር አቋሞች እንዳሏችሁ እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል” በማለት ያስተዋለችውን ተናግራለች።​—⁠ማቴዎስ 5:​15, 16

ትንኮላ ሲደርስባችሁ

የቱንም ያህል ጥረት ብታደርጉ ባለጌ ወይም ሥርዓት አልባ ከሆኑ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ማምለጥ አትችሉም። ይሁን እንጂ ክርስቲያናዊ ጠባይ አሳይታችሁም የጥቃቱ ሰለባ ከሆናችሁ ራሳችሁን በጥፋተኝነት ስሜት የምታሰቃዩበት ምንም ምክንያት የለም። (1 ጴጥሮስ 3:​16, 17) ሁኔታው የስሜት ውጥረት ካስከተለባችሁ ከወላጆቻችሁ ወይም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ካሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር በመወያየት እርዳታ ለማግኘት ሞክሩ። ጥቃቱ የደረሰበት አንድ ሰው ስለራሱ ጥሩ ስሜት እንደማይሰማው ሮዝሊን ሳትሸሽግ ተናግራለች። “አንድ ልታነጋግሩት የምትችሉት ሰው ማግኘቱ ብቻ በጣም ይረዳል።” ከዚህም በላይ ይሖዋ “ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ” እንደሆነ አስታውሱ።​—⁠መዝሙር 145:​18, 19

የማትፈልጉት ነገር ሲፈጸም መቃወም ቀላል ባይሆንም ጥቅም አለው። ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሱነማይቱ ልጃገረድ የሚናገረውን ታሪክ ተመልከቱ። ቃሉ በዛሬው ጊዜ ከሚያስተላልፈው ትርጉም አንጻር ይህች ሴት በትክክል ጾታዊ ትንኮላ ደርሶባታል ማለት ባይቻልም ሰሎሞን ከተባለው ሃብታምና ኃያል የይሁዳ ንጉሥ የማትፈልገው ማባበያ ቀርቦላት ነበር። ሌላ የምትወድደው ሰው ስለነበር እነዚያን ማባበያዎች አልተቀበለቻቸውም። ስለዚህ “እኔ ቅጥር ነኝ” በማለት ስለራሷ በኩራት መናገር ችላለች።​—⁠መኃልየ መኃልይ 8:​4, 10

እናንተም ተመሳሳይ የሆነ የሥነ ምግባር ጥንካሬና ቆራጥነት አሳዩ። የማትፈልጓቸው ማባበያዎች ሲቀርቡላችሁ እንደ “ቅጥር” ሁኑ። በዙሪያችሁ ላለው ሰው ሁሉ ክርስቲያናዊ አቋማችሁን በግልጽ አሳውቁ። እንዲህ በማድረግ ‘ያለነቀፋ የዋሆችም’ ሆናችሁ ለመቆየት ከመቻላችሁም በላይ አምላክን እንዳስደሰታችሁ እርግጠኞች ልትሆኑ ትችላላችሁ።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​14 *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.27 ጾታዊ ትንኮላን የሚመለከት ተጨማሪ ምክር በግንቦት 22, 1996 ንቁ! (እንግሊዝኛ)፣ ሚያዝያ-ሰኔ 1996 ንቁ! እንዲሁም ግንቦት 22, 1991 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔቶች ላይ ወጥቷል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያናዊ እምነታችሁን በግልጽ ማሳወቃችሁ ጥበቃ ሊሆንላችሁ ይችላል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአጉል ሰዎች ጋር ጓደኝነት ባለመፍጠር ጾታዊ ትንኮላን መከላከል ትችሉ ይሆናል