በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለተሻለ ጤና—አዲስ የመፍትሔ አቅጣጫ ነውን?

ለተሻለ ጤና—አዲስ የመፍትሔ አቅጣጫ ነውን?

ለተሻለ ጤና—አዲስ የመፍትሔ አቅጣጫ ነውን?

ከጤና ይበልጥ ሰዎችን የሚያሳስብ ርዕሰ ጉዳይ የለም ለማለት ይቻላል። አንዳንድ ጊዜ የሚሰጠው አስተያየት ብዛት በሕክምና ሰዎቹ ቁጥር ልክ ነው። ንቁ! መጽሔት ለየትኛውም የሕክምና ዓይነት ሳይወግን ቀጥሎ በሚቀርቡት ተከታታይ ርዕሶች አማካኝነት በአብዛኛው አማራጭ ሕክምና በመባል ስለሚታወቁት እየተበራከቱ የመጡ የሕክምና ዓይነቶች ይዘግባል። በውይይታችን የምንጠቅሳቸውንም ሆነ ሌሎቹን የሕክምና ዓይነቶች አናበላልጥም። ያልተጠቀሱም የሕክምና ዓይነቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በሰፊው የታወቁ ሌሎቹ ደግሞ አጠያያቂ የሆኑ ናቸው። በጥቅሉ ሲታይ ስለ ጤና ጉዳይ የሚሰጥ ትምህርት ጠቃሚ ነው የሚል እምነት ቢኖረንም አንድ ሰው ጤንነትን በተመለከተ የሚያደርገው ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ለግለሰቡ የተተወ ነው።

ሉም ሰው ጤነኛ መሆን ይፈልጋል። ይሁንና የጤና እክል ባላቸው ብዙ ሰዎች ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው ጥሩ ጤና በቀላሉ ሊገኝ የሚችል ነገር ላይሆን ይችላል። የዛሬውን ያህል ብዙ ሰዎች በበሽታ የተጠቁበት ጊዜ እንደሌለ የሚሰማቸው ሰዎች አሉ።

ብዙ ዶክተሮች በሽታን ለመከላከል በእጅጉ የሚተማመኑት የመድኃኒት ፋብሪካዎች በሚያመርቷቸውና አጋንነው በሚያስተዋውቋቸው መድኃኒቶች ነው። የሚያስገርመው በቅርብ አሥርተ ዓመታት ውስጥ የእነዚህ መድኃኒቶች ሽያጭ በዓለም ገበያ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ በዓመት ጥቂት ቢልዮኖች የነበረው ወጪ ወደ መቶ ቢልዮኖች ከፍ ብሏል። ውጤቱስ?

በሐኪሞች የሚታዘዙ መድኃኒቶች ብዙ ሰዎችን ረድተዋል። ይሁንና መድኃኒት የሚወስዱ የአንዳንድ ሰዎች ጤንነት ምንም መሻሻል አላሳየም ወይም ጭራሽ የከፋ ሆኗል። በመሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንዶች ሌሎች የሕክምና ዘዴዎችን ወደ መጠቀም ዘወር ብለዋል።

ብዙዎች ፊታቸውን ያዞሩት ወዴት ነው?

መደበኛዎቹ ዘመናዊ መድኃኒቶች ዋነኛ የበሽታ መከላከያ ሆነው በቆዩባቸው አገሮች ብዙ ሰዎች አማራጭ ወይም ተጨማሪ ሕክምና ወደሚባሉት የሕክምና ዓይነቶች ዘወር እያሉ ነው። “አማራጭ ሕክምናዎችንና መደበኛውን ሕክምና አለያይቶ የቆየው የበርሊን ግንብ እየፈራረሰ ያለ ይመስላል” ሲል የግንቦት 2000 ኮንሱመር ሪፖርትስ ዘግቧል።

ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን (ጃማ) በኅዳር 11, 1998 እትሙ እንዲህ የሚል አስተያየት አስፍሮ ነበር:- “በአሠራራቸው እንደ ጣልቃ ገብ ተደርገው የሚገለጹት አማራጭ ሕክምናዎች በሕክምና ትምህርት ተቋማት በሰፊው የማይወሱና በዩናይትድ ስቴትስ ባሉት ሆስፒታሎች በብዛት የማይገኙ ቢሆንም በአገር አቀፍ ደረጃ ከመገናኛ ብዙሐን፣ ከሕክምናው ማኅበረሰብ፣ ከመንግሥት ድርጅቶችና ከሕዝቡም ጭምር የሚሰጣቸው ትኩረት እያደገ መጥቷል።”

ይሁን እንጂ ጆርናል ኦቭ ማኔጅድ ኬር ፋርማሲ አሁን ያለውን አዝማሚያ በማስተዋል በ1997 እንዲህ ብሎ ነበር:- “ቀደም ባሉት ጊዜያት የመደበኛው ሕክምና ባለሙያዎች አማራጭ የሕክምና ልማዶችን የሚያዩአቸው በጥርጣሬ ዓይን ነበር። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ግን የሃርቫርድ፣ የስታንፎርድ እንዲሁም የአሪዞና እና የያሌ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ 27 የሕክምና ትምህርት ተቋማት [በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት 75 ናቸው ይላል] ስለ አማራጭ ሕክምናዎች በምርጫ የሚወሰዱ ኮርሶችን በመስጠት ላይ ናቸው።”

ጃማ ብዙ ታማሚዎች ጤናቸውን ለማሻሻል በማሰብ ምን እያደረጉ እንዳለ ጠቅሷል። እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “በ1990 ከበድ ባለ የጤና ችግር ምክንያት ዶክተር ጋር ከቀረቡት ሰዎች መካከል ከአምስት አንዱ (19.9%) አማራጭ ሕክምናዎችንም ተጠቅሟል። በ1997 ደግሞ ይህ አኃዝ ከፍ ብሎ ከሦስት አንድ (31.8%) ደርሷል።” ይኸው ጽሑፍ ጨምሮ እንዳለው ከሆነ “ከዩናይትድ ስቴትስ ውጭ የተካሄዱ አገር አቀፍ ጥናቶች አማራጭ ሕክምና በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገራት በእጅጉ መስፋፋቱን ይጠቁማሉ።”

እንደ ጃማ አገላለጽ ከሆነ በቅርቡ በ12 ወራት ውስጥ በአማራጭ ሕክምናዎች የተጠቀሙ ሰዎች ብዛት በካናዳ 15 በመቶ፣ በፊንላንድ 33 በመቶ እንዲሁም በአውስትራሊያ 49 በመቶ ነበር። “የአማራጭ ሕክምና ፈላጊዎች ቁጥር መጨመር በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ሲል ጄ ኤ ኤም ኤ አስታውቋል። በተለይ ይህን ያህል ጭማሪ የኖረው አማራጭ ሕክምናዎች በኢንሹራንስ ክፍያ በማይሸፈኑበት ሁኔታ ሥር መሆኑ ለሁኔታው የበለጠ ክብደት ይሰጠዋል። በመሆኑም ጃማ ያዘጋጀው ጽሑፍ “ወደፊት ለአማራጭ ሕክምናዎች የሚሰጠው የኢንሹራንስ ሽፋን እያደገ ቢመጣ በአሁኑ ጊዜ ያለው የአማራጭ ሕክምናዎች ተጠቃሚ ቁጥር ወደፊት የሚኖረውን ተጠቃሚ ብዛት ከወዲሁ የሚያመላክት ሊሆን ይችላል” በማለት ደምድሟል።

አማራጭ ሕክምናዎችን ከመደበኛው ሕክምና ጋር የማቀናጀቱ አዝማሚያ በብዙ አገሮች የተለመደ አሠራር መሆን ከጀመረ ቆይቷል። የሮያል ለንደን ሆሚዮፓቲክ ሆስፒታል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ፒተር ፊሸር ተጨማሪ ሕክምና የሚባሉት ዋነኛ የሕክምና ዓይነቶች “በብዙ ቦታዎች የመደበኛነት ደረጃ አግኝተዋል ለማለት ይቻላል። የሕክምና ዓይነቶችን መደበኛና መደበኛ ያልሆነ ብሎ መክፈል እየቀረ ነው” ብለዋል። “አሁን ያለው ሁለት ዓይነት ሕክምና ማለትም ጥሩና መጥፎ ሕክምና ብቻ ነው።”

በመሆኑም ዛሬ ብዙ የሕክምና ባለሙያዎች መደበኛዎቹም ሆኑ በአማራጭነት የተፈረጁት ሕክምናዎች ያላቸውን ጠቀሜታ እየተገነዘቡ መጥተዋል። አንድን ታካሚ ይህንን አለዚያም ያንን ዓይነት ሕክምና ምረጥ ብሎ ከመጫን ይልቅ ከተለያዩት ሕክምናዎች መካከል ታካሚው የተሻለ ሆኖ ያገኘውን ዓይነት እንዲመርጥ ሐሳብ ይሰጣሉ።

አማራጭ ወይም ተጨማሪ ሕክምናዎች የሚባሉት የሕክምና ዓይነቶች የሚጠቀሙባቸው የመፈወሻ ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው? ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የተጀመሩት መቼና የት ነው? የእነዚህ ሕክምናዎች ተጠቃሚ የተበራከተውስ ለምንድን ነው?