በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አማራጭ ሕክምናዎችን ስንቃኛቸው

አማራጭ ሕክምናዎችን ስንቃኛቸው

አማራጭ ሕክምናዎችን ስንቃኛቸው

“አማራጭ ሕክምናዎችን ለሚመርጡ ሰዎች የተሻለ የጤና እንክብካቤ በመስጠት ረገድ በሕክምና ዶክተሮችና በአማራጭ ሕክምና ባለሙያዎች መካከል የውይይት መድረክ መክፈት ወሳኝ የሆነ ጠቀሜታ አለው።”

ይህ አስተያየት ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን (ጃማ) በኅዳር 11, 1998 እትሙ ላይ ያሰፈረው ነበር። ይኸው ርዕስ እንዲህ ሲል አትቷል:- “የአማራጭ ሕክምናዎች ቁጥር እየጨመረ በሄደ መጠን በተለይ ደግሞ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንደነዚህ ያሉትን ሕክምናዎች በሥራቸው ማስጠለል ሲጀምሩ የዚህ [የውይይት መድረክ] አስፈላጊነትም ይበልጥ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።”

መደበኛ የሚባሉትን ዓይነት ሕክምናዎች እየወሰዱም አማራጭ ሕክምናዎችን የሚጠቀሙ ታካሚዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ሄዷል። ይሁንና አንዳንዶች ለዶክተሮቻቸው ምን እያደረጉ እንዳሉ አይናገሩም። ከዚህ በመነሣት የሚያዝያ 2000 ተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ሄልዝ ኤንድ ኑትሪሽን ሌተር እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቧል:- “ስለምትወስዱት ሕክምና ዶክተራችሁን ከመደበቅ ይልቅ አብራችሁ እየተመካከራችሁ ብትወስዱ ትጠቀማላችሁ።” በማከልም “ዶክተሩ ወይም ዶክተሯ ተቀበሉትም አልተቀበሉት ሐሳባችሁን በማካፈላችሁ ትጠቀማላችሁ እንጂ አትጎዱም” ብሏል።

ይህ የተባለው አንዳንድ ዕፅዋት ከመደበኛው ሕክምና ጋር አብረው ሲወሰዱ የጤና ችግር ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ነው። ብዙ የጤና ባለሙያዎች አንዳንድ ታካሚዎች አማራጭ ሕክምናዎችን እንደሚመርጡ በመገንዘባቸው ለታካሚው ጥቅም ሲሉ ስለ ጤና ያላቸው የግል አመለካከት ከአማራጭ ሕክምና ባለሙያዎች ጋር ተጋግዘው ከመሥራት እንዳያግዳቸው ይጠነቀቃሉ።

አንባቢዎቻችን በብዙ አገሮች ያሉ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች እየተጠቀሙባቸው ያሉትን የአማራጭ ሕክምና ዓይነቶች በተመለከተ ግንዛቤ እንዲያገኙ ስንል ከዚህ ቀጥሎ ስለ ጥቂቶቹ መጠነኛ መግለጫ እንሰጣለን። ይሁን እንጂ እባክህ የንቁ! መጽሔት ከእነዚህ የሕክምና ዓይነቶች መካከልም ሆነ ከዚህ ውጭ ላለ ለየትኛውም ዓይነት ሕክምና ወግኖ እንደማይናገር አስታውስ።

ከዕፅዋት የሚዘጋጁ መድኃኒቶች

ከአማራጭ ሕክምና ዓይነቶች መካከል በጣም በሰፊው የተለመዱት እነዚህ መድኃኒቶች ሳይሆኑ አይቀሩም። ባለፉት ብዙ መቶ ዓመታት ዕፅዋት ለሕክምና ሲያገለግሉ የኖሩ ቢሆንም ሳይንቲስቶች በጥንቃቄ ያጠኗቸው የዕፅዋት ዝርያዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ እጅግ ጥቂት ብቻ ናቸው። በዕፅዋቱ ወይም በእነርሱ ተዋጽኦ ላይ ጥልቅ ምርምር ተደርጎ ስለ አስተማማኝነታቸውም ሆነ ስለ ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ መረጃ የተገኘባቸው ዕፅዋት ቁጥር ደግሞ ከዚህም ያነሰ ነው። ስለ እነዚህ ዕፅዋት የሚታወቀው አብዛኛው ነገር በታሪክ ዘመናት እነርሱን በመጠቀም ከተገኘው ተሞክሮ የመነጨ ብቻ ነው።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተደረጉት የተወሰኑ ሳይንሳዊ ምርምሮች ቀለል ያለ የመንፈስ ጭንቀት፣ ከዕድሜ ጋር የተዛመደ የመርሳት ችግር እና መጠነኛ የፕሮስቴት ዕጢ እብጠት የመሳሰሉትን ሁኔታዎች በማከም በኩል አንዳንድ ዕፅዋት ያላቸውን ጠቀሜታ አረጋግጠዋል። ጥናት ከተደረገባቸው ዕፅዋት አንዱ ብላክ ኮሆሽ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ብላክ ስኔክሩት፣ ባግቤን ወይም ራትልሩት በመባል ይታወቃል። የአሜሪካ ሕንዶች የዚህን ተክል ሥር በመቀቀል ከወር አበባና ከልጅ መውለድ ጋር ለሚዛመዱ ችግሮች ይጠቀሙበት ነበር። ሃርቫርድ ዉሜንስ ሄልዝ ዋች በሚያዝያ 2000 እትሙ ላይ እንዳለው ከሆነ በጀርመን ገበያ ላይ የዋለው የተወሰነ ደረጃ እንዲኖረው ሆኖ የተዘጋጀ የብላክ ኮሆሽ ተዋጽኦ “ከማረጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡትን የሕመም ስሜቶች ለማስታገስ” ውጤታማ ሊሆን ይችላል።

በአብዛኛው የእነዚህ ተፈጥሮአዊ መድኃኒቶች ተፈላጊነት እየጨመረ የመጣው የሚያስከትሉት ጉዳት በፋብሪካ ከሚመረቱት መድኃኒቶች ያነሰ ነው ከሚል እምነት ይመስላል። ይህ ባብዛኛው እውነት ቢሆንም አንዳንድ ዕፅዋት በተለይ ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር ተቀላቅለው ሲወሰዱ ጉዳት ያስከትላሉ። ለምሳሌ ያህል ለትንፋሽ መዘጋትና ለውፍረት ተፈጥሮአዊ መድኃኒት እንደሆነ የሚነገርለት አንድ በሰፊው የታወቀ ዕፅ የደም ግፊትና የልብ ምት እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል።

አንድ ታማሚ ያለበት የደም መፍሰስ ችግር እንዲባባስ የሚያደርጉ ዕፅዋትም አሉ። እነዚህ ዕፅዋት “ደም የሚያቀጥኑ” ናቸው ከሚባሉት የሕክምና መድኃኒቶች ጋር ከተወሰዱ ከባድ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ። እንደ ስኳር በሽታ ወይም ከፍተኛ የደም ግፊት ያለ ሥር የሰደደ በሽታ ያለባቸው ወይም ሌሎች መድኃኒቶችን የሚወስዱ ሰዎች ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ዕፅዋትን ሲወስዱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።​—⁠ከዚህ ርዕስ ጋር ተያይዞ የቀረበውን ሣጥን ተመልከት።

ሌላው የዕፅዋት መድኃኒቶችን በተመለከተ አሳሳቢ የሆነው ነገር በምርቶቹ ረገድ ወጥ የሆነ የጥራት ደረጃ እንዲኖራቸው ለማድረግ አለመቻሉ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከባድ መጠን ያላቸው ብረቶችና ሌሎችም የሚመርዙ ነገሮች የተገኙባቸው ምርቶች እንዳሉ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከዕፅዋት የሚሠሩ አንዳንድ ምርቶች በላያቸው ላይ ከተለጠፉት ቅመሞች መካከል የያዙት ጥቂቶቹን ብቻ ሆኖ ወይም ደግሞ ጭራሽ የትኛውንም ሳይዙ ተገኝተዋል። እነዚህ ምሳሌዎች የዕፅዋት ውጤት የሆኑትንም ሆነ ሌሎቹን ለሕክምና የሚያገለግሉ ነገሮች ስንገዛ ከታወቀ ወይም አስተማማኝ ከሆነ ምንጭ መሆን እንዳለበት የሚያስገነዝቡ ናቸው።

በምግብ ማሟያነት የሚወሰዱ መድኃኒቶች

እንደ ቪታሚንና ማዕድናት ያሉት በምግብ ማሟያነት የሚወሰዱ መድኃኒቶች እንደ ደም ማነስና ኦስቲኦፖሮሲስ ያሉትን አልፎ ተርፎም በልጆች ላይ የሚደርሱ የአካል ጉድለቶችን ጨምሮ በርካታ የጤና ችግሮችን በመከላከልና በማከም ረገድ ጠቃሚ እንደሆኑ ሲነገርላቸው ቆይቷል። መንግሥት ለዜጎቹ በሚያዝዘው የቪታሚንና የማዕድን መጠን በአንጻራዊ ሁኔታ ለችግር የማይዳርግና ጠቃሚ ነው ተብሎ ይታመናል።

በሌላ በኩል ለአንዳንድ የጤና ችግሮች ይረዳሉ በማለት ከፍተኛ መጠን መውሰድ ለጤና አደገኛ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ገንቢ ንጥረ ነገሮች ከሰውነት ጋር እንዳይዋሃዱ ወይም ሥራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ እንቅፋት ሊፈጥሩ እንዲሁም ሌሎች ከበድ ያሉ ጉዳቶችንም ሊያስከትሉ ይችላሉ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩ እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው ቪታሚን መውሰድን የሚደግፍ አጥጋቢ መረጃ ያለመገኘቱ በቸልታ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም።

ሆሚዮፓቲ

ሆሚዮፓቲ በጊዜው በሰፊው ጥቅም ላይ ውለው ከነበሩት ሕክምናዎች ሁሉ በሰውነት ላይ ጉዳት የማያደርስ ሕክምና እንዲሆን ታስቦ በ1700ዎቹ ዓመታት ብቅ ያለ የሕክምና ዓይነት ነው። ሆሚዮፓቲ “እሾህን በእሾህ” በሚል መርኅና እጅግ አነስተኛ መጠን ያለው መድኃኒት መስጠት በሚል ንድፈ ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ነው። የሆሚዮፓቲ መድኃኒቶች የሚዘጋጁት ፈዋሽ የሆነውን ቅመም በተደጋጋሚ በመበረዝ አንዳንድ ጊዜም የመጀመሪያው ንጥረ ነገር አንድ ሞሊኪውል እንኳ እስከማይገኝ ድረስ በመበረዝ ነው።

የሆነ ሆኖ የሆሚዮፓቲ ሕክምና ለበሽተኞች ከሚሰጠው ምንም ዓይነት ፈዋሽነት የሌለው የውሸት መድኃኒት ጋር ሲነጻጸር እንደ አስም፣ አለርጂ እንዲሁም የልጆች ተቅማጥ በሽታን የመሳሰሉትን ችግሮች በማከም በኩል የተወሰነ ውጤት አስገኝቷል። የሆሚዮፓቲ ውጤቶች በጣም የተበረዙ በመሆናቸው ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትሉ ይታሰባሉ። በጃማ የመጋቢት 4, 1998 እትም ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ይህ ነው ተብሎ በምርመራ ባልታወቀ ሥር የሰደደ በሽታ ለሚሰቃዩ ሰዎች ሆሚዮፓቲ በጣም ጠቃሚ የሕክምና አማራጭ ሊሆን ይችላል። ሆሚዮፓቲንም በተገቢው ቦታና ሁኔታ ከተጠቀምንበት ‘በኮሮጆአችን ውስጥ እንዳለ ሌላ አንድ መሣሪያ በመሆን’ ለዘመናዊው ሕክምና በማሟያነት ሊያገለግል ይችላል።” ሕይወትን ስጋት ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ድንገተኛ አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ግን ይበልጥ መደበኛ የሆኑትን የሕክምና ዓይነቶች መከታተሉ ጥበብ ይሆናል።

ካይረፕራክቲክ

የሰውነት ክፍሎችን በማሸትና በማንቀሳቀስ የሚከናወኑ በርካታ አማራጭ የሕክምና ዓይነቶች አሉ። ካይረፕራክቲክ በተለይ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሰፊው ከሚሠራባቸው የአማራጭ ሕክምና ዓይነቶች አንዱ ነው። ይህ ሕክምና የተዛነፉ የአከርካሪ አጥንቶችን በማስተካከል ሕመምን መፈወስ ይቻላል በሚል መሠረተ ሐሳብ ላይ የተመረኮዘ ነው። የካይረፕራክቲክ ባለሙያዎች የታካሚዎቻቸውን አከርካሪ ለማስተካከል በሰረሰር ላይ የሚያተኩሩት በዚህ ምክንያት ነው።

መደበኛው ሕክምና ሁልጊዜ የወገብ ሕመም አያስታግስም። በሌላ በኩል ግን የካይረፕራክቲክ ሕክምና የወሰዱ አንዳንድ ሰዎች ከፍተኛ እፎይታ እንዳገኙ ይናገራሉ። ካይረፕራክቲክ የሕመም ስሜት ከማስታገስ ውጭ ሌላ ፈውስ እንደማያስገኝ የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች አልተገኙም።

የካይረፕራክቲክ ሕክምና በሙያው በተካነ ሰው ከተሰጠ ሌላ ጉዳት የሚያስከትልበት አጋጣሚ አነስተኛ ነው። ይሁንና አንድ ሰው በአንገት አካባቢ የሚደረግ እሽት፣ ንቅነቃና ማጠማዘዝ ስትሮክ እና ሽባነትን የመሳሰሉትን ከባድ አደጋዎች ሊያስከትል እንደሚችል ማወቅ አለበት። እነዚህ ከባድ ችግሮች የሚከሰቱበትን አጋጣሚ ለመቀነስ አንዳንድ ባለሙያዎች ለግለሰቡ የሚሰጠው የሕክምና ዓይነት ሌላ ችግር የማያስከትልበት መሆኑን ለማረጋገጥ አስቀድሞ ጥሩ ምርመራ እንዲያደርግ ያበረታታሉ።

እሽት

እሽት (massage) ያለው ጥቅም በሁሉም ባሕሎች ውስጥ ለማለት ይቻላል ከታወቀ ቆይቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሳይቀር ተዘግቦለታል። (አስቴር 2:​12 NW ) ብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል (ቢ ኤም ጄ) በኅዳር 6, 1999 እትሙ ላይ እንዳሰፈረው “የማሸት ዘዴ በቻይናና በሕንድ ባሕላዊ ሕክምና ውስጥ የጎላ ስፍራ አለው። የአውሮፓውያን የአስተሻሸት ዘዴ የተወሰነ ስልት እንዲኖረው ያስቻለው በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ይኖር የነበረው ፓር ሄንሪክ ሊኝ ነው። ይህ የእርሱ የአስተሻሸት ስልት በአሁኑ ጊዜ ስዊዲሽ ማሳጅ ይባላል።”

ማሸት ጡንቻዎችን ለማፍታታት፣ የደም ዝውውርን ለማሻሻል እንዲሁም በህብረህዋሳችን ውስጥ የሚጠራቀመውን መርዝ ለማስወገድ እንደሚረዳ ይነገርለታል። ዛሬ ዶክተሮች የጀርባ ሕመም፣ የራስ ምታትና የምግብ መፈጨት ችግር ላለባቸው ሰዎች እሽት ያዝዛሉ። የእሽት ሕክምና የሚደረግላቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች ጥሩ ውጤት እንዳገኙበት ይናገራሉ። ዶክተር ሳንድራ ማክላነን እንደሚሉት “ሰማንያ በመቶ የሚሆነው ሕመም ከውጥረት ጋር የተያያዘ ሲሆን እሽት ደግሞ ውጥረትን ይቀንሳል።”

“አብዛኛዎቹ የአስተሻሸት ዘዴዎች ከፍተኛ ጉዳት የማስከተላቸው አጋጣሚ በጣም አነሽተኛ ነው” ሲል ቢ ኤም ጄ ሪፖርት አድርጓል። “ከእሽት ጋር የማይጣጣሙት ነገሮች ማንኛውም ሰው ሊገምታቸው የሚችሉ ናቸው። (ለምሳሌ ያህል የተቃጠለ አካልን ወይም ደም የቋጠረ የደም ሥር ያለበትን እግርና እጅ ማሸት ተገቢ አይሆንም) . . . የካንሰር ሕመም ያለባቸውን ሰዎች ማሸት የበሽታውን ስርጭት ያፋጥነዋል ለማለት የሚያስችል ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም።”

“እሽት መደበኛ ሕክምና እየሆነ በመጣ መጠን የባለሙያዎቹን ብቃት የማረጋገጡ ጉዳይ ተጠቃሚዎችን የሚያሳስብ ሆኗል። ይህም ተገቢ ነው” ሲሉ የአሜሪካን ማሳጅ ቴራፒስትስ አሶሲዬሽን የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኢ ዩስተን ለብረን ተናግረዋል። እንደ ቢ ኤም ጄ ምክር ከሆነ ያለ እውቀት የሚሠሩ ነገሮችን ለማስቀረት “ታካሚዎቹ ባለሙያው በተገቢው ተቆጣጣሪ አካል የተመዘገበ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።” ባለፈው ዓመት የወጣ አንድ ሪፖርት እንደጠቆመው የእሽት ባለሙያዎች በ28 የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ውስጥ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል።

አኩፓንቸር

አኩፓንቸር በዓለም ዙሪያ በጣም ታዋቂ እየሆነ የመጣ የሕክምና ዘዴ ነው። “አኩፓንቸር” የሚለው ቃል የተለያዩ ዓይነት ዘዴዎችን የሚያጠቃልል ቢሆንም ባብዛኛው በተወሰነ የሰውነት ክፍል ላይ ሹል መርፌዎችን በመሰካት በሰውነት ላይ የሕክምና ለውጥ ለማስገኘት የሚከናወን ነው። ባለፉት በርካታ አሥርተ ዓመታት ውስጥ የተከናወኑት ምርምሮች እንደጠቆሙት የአኩፓንቸር ሕክምና አንዳንድ ጊዜ የሕመም ስሜት ወይም የሰውነት ክፍሎችን መቆጣት ለማስታገስ የሚችሉት እንደ ኤንዶርፊንስ ያሉ የነርቭ ኬሚካሎች እንዲረጩ በማድረግ ሊሠራ ይችላል።

አንዳንድ የምርምር ውጤቶች አኩፓንቸር ብዙ ችግሮችን በማከም በኩል ውጤታማ ሊሆን እንደሚችልና ማደንዘዣዎችን ከመጠቀም የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ይጠቁማሉ። የዓለም የጤና ድርጅት አኩፓንቸር 104 ዓይነት ችግሮችን ለማከም ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችል እውቅና ሰጥቶአል። እንዲሁም ከዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የጤና ተቋሞች የተውጣጣ አንድ ኮሚቴ አኩፓንቸር ከቀዶ ሕክምና በኋላ የሚከሰተውን ሕመም፣ የጡንቻ ሕመም፣ በወር አበባ ምክንያት የሚከሰተውን ቁርጠት እንዲሁም በኬሞቴራፒ ምክንያትና በእርግዝና ወቅት የሚከሰተውን የማጥወልወልና የማስመለስ ችግር በማከም ረገድ ተቀባይነት እንዳለው የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ጠቅሷል።

በአኩፓንቸር ሕክምና ምክንያት የሚከሰቱ ከባድ ጉዳቶች እምብዛም ቢሆኑም አንዳንድ ሰዎች የቁስለት፣ የመደንዘዝ ወይም ሰውነትን የመውረር ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። በሚገባ የተቀቀሉ ወይም አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ የሚጣሉ መርፌዎችን መጠቀም የኢንፌክሽን አደጋዎችን ሊቀንስ ይችላል። ብዙ የአኩፓንቸር ሕክምና ሙያተኞች ትክክለኛውን ዓይነት ምርመራ ለማድረግ ወይም ሌሎች ይበልጥ የተሻሉ የሕክምና ዓይነቶችን ለመጠቆም የሚያስፈልገው ሙያዊ ችሎታ ይጎድላቸዋል። እንዲህ ያለውን የችሎታ ማነስ ቸል ማለት በተለይ ደግሞ የአኩፓንቸር ሕክምናው የተመረጠው ሥር የሰደዱ በሽታዎች ያስከተሉትን የሕመም ስሜት ለማስታገስ ከሆነ ጥበብ የጎደለው እርምጃ ይሆናል።

አማራጮቹ በርካታ ናቸው

በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ ቦታዎች አማራጭ ሕክምና ተብለው በሰፊው ከሚታወቁት በርካታ የሕክምና ዓይነቶች መካከል አንዳንዶቹን ለናሙና ያህል ለማቅረብ ተሞክሯል። ወደፊት ከእነዚህ መካከልም ሆነ እዚህ ላይ ካልተጠቀሱት ሌሎች የሕክምና ዓይነቶች መካከል የተወሰኑት ዛሬ አንዳንድ አገሮች እንዳደረጉት መደበኛ ሕክምና ተደርገው ተቀባይነት ያገኙ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ምናልባት ሊቀሩ እንዲያውም ሊወገዙ ይችሉ ይሆናል።

የሚያሳዝነው መጽሐፍ ቅዱስ ጭምር በትክክል እንደሚገልጸው ሕመምና ስቃይ ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር ተቆራኝተው ኖረዋል:- “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና።” (ሮሜ 8:​22) ሰዎች ከሚሰማቸው ሕመም እፎይታ ለማግኘት መጣራቸው የሚጠበቅ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ ይህንን እፎይታ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው? በሕክምና ረገድ ለምታደርገው ምርጫ ሊጠቅሙህ የሚችሉ አንዳንድ አስተያየቶችን እባክህ ቀጥሎ ተመልከት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከዕፅዋት የሚቀመሙ መድኃኒቶችን ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር መውሰድ የሚያስከትለው አደጋ ምንድን ነው?

ብዙውን ጊዜ በሐኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ አንዳንድ መድኃኒቶች አንድ ላይ እንዳይወስዱ ወይም ከመድኃኒቶቹ ጋር የአልኮል መጠጥ እንዳይወስዱ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። አንዳንድ ከዕፅዋት የሚቀመሙ መድኃኒቶችን በሐኪም ትእዛዝ ከሚሰጡ ሌሎች መድኃኒቶች ጋር ቀላቅሎ መውሰድ አደጋ አለው? ይህስ ልማድ ምን ያህል የተስፋፋ ነው?

ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን ላይ የወጣ አንድ ርዕስ “ከዕፅዋት የሚቀመሙ መድኃኒቶችን በሐኪም ትእዛዝ ከሚወሰዱ መድኃኒቶች ጋር አጣምሮ መውሰድን” የሚመለከት ዘገባ አውጥቷል። እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “ሐኪም ያዘዘላቸውን መድኃኒት እንደሚወስዱ ከተናገሩት 44 በመቶ የሚሆኑ አዋቂዎች መካከል ከአምስት አንዱ (18.4 በመቶው) ቢያንስ አንድ የዕፅዋት ውጤት የሆነ መድኃኒት ወይም ከፍተኛ መጠን ያለው ቫይታሚን አለዚያም ሁለቱንም በመድኃኒቱ ላይ ደርቦ እንደሚወስድ ተናግሯል።” እንዲህ ዓይነቱ ልማድ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ማወቁ ጥሩ ይሆናል።

አንዳንድ ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶችን የሚወስዱ ሰዎች ሰመመን መውሰድን የሚጠይቅ ሕክምና ሲደረግላቸው ሊያስቡበት የሚገባ ነገር አለ። የአሜሪካ አኒስቴዢዎሎጂስቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ጆን ኢልድ እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል:- “ጊንሰንግ እና ሴንት ጆንስ ዎርት የተባሉትን ጨምሮ አንዳንድ የተለመዱ ዕፅዋት የደም ግፊት በእጅጉ እንዲዋዥቅ እንደሚያደርጉ የሚገልጹ ሪፖርቶች አሉ። ይህ ማደንዘዣ በሚሰጥበት ጊዜ እጅግ አደገኛ ሊሆን ይችላል።”

እኒሁ ዶክተር ጨምረው እንዲህ ብለዋል:- “ጆንኮ ቢሎባ፣ ዝንጅብል እና ፊቨርፊውን የመሳሰሉት ደግሞ ደም እንዳይረጋ ሊያደርጉ የሚችሉ ሲሆን ይህም በሰረሰር ላይ ማደንዘዣ በሚሰጥበት ጊዜ ከባድ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። በሰረሰር አካባቢ ደም ከፈሰሰ ሽባነት ሊያስከትል ይችላል። ሴንት ጆንስ ዎርትም ቢሆን የማደንዘዝ ወይም እንቅልፍ የማስወሰድ ባሕርይ ያላቸውን የአንዳንድ መድኃኒቶች ኃይል ሊያጠናክር ይችላል።”

አንዳንድ የዕፅዋት ውጤቶችን ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር ቀላቅሎ መውሰድ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ማወቁ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ነው። በተለይ ነፍሰጡር የሆኑና የሚያጠቡ ሴቶች አንዳንድ የዕፅዋት ውጤቶችንና መድኃኒቶችን ቀላቅለው መውሰዳቸው በልጃቸው ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት ሊገነዘቡ ይገባል። በመሆኑም ታማሚዎች ምን ዓይነት ሕክምና እየወሰዱ እንዳለ (አማራጭ ሕክምናም ሆነ ሌላ ዓይነት) ለሐኪማቸው ማሳወቃቸው ተገቢ ይሆናል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አንዳንድ ዕፅዋት የጤና ችግሮችን በማከም በኩል ጠቃሚ ሆነው ተገኝተዋል

ብላክ ኮሆሽ

ሴንት ጆንስ ዎርት

[ምንጭ]

© Bill Johnson/Visuals Unlimited

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተሻለ ውጤት ለማግኘት ታካሚዎችና የጤና ባለሙያዎች መተባበር ይኖርባቸዋል