በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስደናቂ የነፍስ አድን ተግባር

አስደናቂ የነፍስ አድን ተግባር

አስደናቂ የነፍስ አድን ተግባር

ቤኒን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

“የይሖዋ ምሥክሮች ባያድኗቸው ኖሮ እነዚያ ሦስት ሰዎች አልቆላቸው ነበር!” ይህ ወሬ ረቡዕ ሚያዝያ 19, 2000 በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በቤኒን በካላቫይ ከተማ ተናፍሶ ነበር። ሦስቱ ሰዎች እነማን ናቸው? የይሖዋ ምሥክሮች ሊያድኗቸው የቻሉትስ እንዴት ነው?

ከማለዳው 12:​30 ገደማ ፊሊፕ ኢሌግብ እና ሮዤ ኩኑግብ ቤኒን ከሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር ተያይዞ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ በሚያደርጉበት ቦታ አንዳንድ ሥራዎችን ለማከናወን በዝግጅት ላይ ነበሩ። ያን ዕለት ምሽት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ዓመታዊውን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ለማክበር በዚያ ይሰበሰባሉ። * በድንገት ጆሮ የሚያደነቁር አንድ ድምፅ የማለዳውን ፀጥታ አደፈረሰው። ፊሊፕ እና ሮዤ በዋናው ጎዳና ላይ አደጋ እንደተከሰተ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደባቸውም።

ከጥቂት ሰኮንዶች በኋላ አንድ ሰው “አብረውኝ የሚሠሩ ሦስት ሰዎች ሲሚንቶው ተጭኗቸዋል!” ሲል ጩኸቱን አቀለጠው። ፊሊፕ እና ሮዤ ወደ ጎዳናው ሮጡ። እዚያ ሲደርሱ 20 ቶን የሚመዝን አንድ የጭነት መኪና በጎኑ ተጋድሟል። በጣም ብዙ ከረጢት ሲሚንቶ ከመኪናው ላይ ተንዷል።

በትልቅ ስብሰባ ቦታ ላይ ሠራተኛ የሆነው ዦዙኤ ዲዶላንቪ አደጋው ስፍራ ቀድሞ ደርሶ ኖሮ በጋቢናውና በሲሚንቶው መካከል የተጣበቀን አንድ ሰው ለማውጣት ይታገላል። ከጋቢናው እንደምንም የወጣው ሾፌር በድንጋጤ ያለበት ጠፍቶታል። ሆኖም እንደ ምንም ብሎ “ሲሚንቶ የተናደባቸው ሌሎች ሁለት ሰዎች አሉ!” ብሎ ጮኸ። በዚያ ሲያልፉ የደረሰውን አደጋ የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች ሲሚንቶ የያዙትን ከረጢቶች ማንሳት ቢጀምሩም ሲሚንቶው እንደ እሳት ስለሚፋጅ መቀጠል አልቻሉም። ሲሚንቶው ከሚመረትበት ፋብሪካ ምድጃ ገና እንደወጣ ነበር!

ነፍስ የማዳን ተግባር

ፊሊፕ፣ ሮዤ እና ዦዙኤ የተቆለለውን ሲሚንቶ አንድ በአንድ ማንሳት ጀመሩ። እንደ እሳት የሚፋጀውና እያንዳንዱ ከረጢት 50 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ሲሚንቶ እጃቸውን አንገበገበው። ሁኔታውን ያባባሰው ደግሞ ከፈነዱት ከረጢቶች የሚፈሰው ሲሚንቶ በጣም ከመፋጀቱ የተነሳ ጣቶቻቸው ውኃ እንዲቋጥሩ ከማድረጉም በላይ እየቦነነ መተንፈስ የሚያስቸግር መሆኑ ነው። ዦዙኤ ከአደጋው በኋላ “እጆቼ በተለይ ደግሞ ጣቶቼ ተንገብግበው ነበር። ሆኖም በሲሚንቶ ከረጢቶቹ የተቀበረው ማንም ይሁን ማን የመዳን ዕድል ይኖረዋል ብዬ አስብ ነበር” ሲል ተናግሯል።

ሦስቱ ሰዎች 40 የሚያክሉ ከረጢቶችን ካነሱ በኋላ የጅባ ምንጣፍ አዩ። በጣም የሚገርመው ሁለቱ ሰዎች ከጅባው ሥር ነበሩ። ሁለቱም በሕይወት ተገኙ! አደጋው ሲከሰት ሰዎቹ በሲሚንቶ ከረጢቶቹ ላይ ጅባ አንጥፈው ተኝተው ነበር። ከመኪናው ላይ ሲገለበጡ ጅባው እነሱ ላይ ስላረፈ ከሲሚንቶው ትኩሳት መዳን ቻሉ።

አደጋው በተከሰተ ጊዜና ከአደጋው በኋላ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ነበር። ፊሊፕ፣ ሮዤ እና ዦዙኤ እንደዚህ ባለ ሁኔታ ሥር የነበረውን ሁለት ቶን ቁልል ሲሚንቶ በፍጥነት በማንሳታቸው ያልተደነቀ አልነበረም። እንዲሁም እነዚህ ሦስት ሰዎች በዓይን እንኳን የማያውቋቸውን ሰዎች ለመርዳት ይህን ያህል በመድከማቸው ተደንቀዋል። በሳላቫይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው እነርሱ ስላከናወኑት የጀግንነት ተግባር ሳይሰማ አልቀረም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ኢየሱስ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ቅዱስ በዓል በየዓመቱ ያከብራሉ።​—⁠ ሉቃስ 22:​19

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮዤ ከአደጋው በኋላ ጅባውን እንደያዘ