በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዋክብት በሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይገባልን?

ከዋክብት በሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይገባልን?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ከዋክብት በሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይገባልን?

“በከዋክብት አማካኝነት የወደፊት ዕጣ ፋንታቸውን ለማወቅ የሚጥሩ ወጣቶችና ዐዋቂዎች ስፍር ቁጥር የላቸውም።”​—⁠ሊቀ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል።

አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ከ4 አሜሪካውያን አንዱ ውሳኔ በሚያደርግበት ጊዜ በኮከብ ቆጠራ ይጠቀማል። በኮከብ ቆጠራ ምልክቶች የሚጠቀሙት በዚህ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ሰዎች ብቻ አይደሉም። በዓለም ዙሪያ ማለት ይቻላል፣ ሰዎች ገንዘብ ነክ ከሆኑ ጉዳዮች፣ ከጉዞ ዕቅዶች፣ ከሥራ ለውጥ፣ ከሠርግ ቀንና ከወታደራዊ ስልት ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን ለማድረግ በኮከብ ቆጠራ ይጠቀማሉ። በኮከብ ቆጠራ አማካኝነት የትዳር ጓደኛሞች ሊሆኑ የሚችሉ ጥንዶችን መለየት አልፎ ተርፎም አቻ ሊሆኑ የማይችሉ ጥንዶችን ማወቅ እንደሚቻል ተደርጎ ይታመናል። ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ኮከብ ቆጠራ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ትኩረት ማርኮ ይገኛል። ይሁን እንጂ ይህ ልማድ የመነጨው ከየት ነው?

ታሪካዊ አመጣጡ

የተለያዩ የኮከብ ቆጠራ ልማዶች ሥረ መሠረታቸው በታሪክ እስከሚታወቁት እስከ ጥንቶቹ ሥልጣኔዎች ድረስ ብዙ ዘመናት ወደ ኋላ ይመልሰናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንኳ ሳይቀር “ፀሐይን ለሚዞሩ ሌሎች ዓለማትና ለከዋክብት” ሲል ይጠቅሳል። (2 ነገሥት 23:​5 የ1980 ትርጉም ) በጥንት ዘመን ሂንዱዎች እንዲሁም ቻይናውያን፣ ግብፃውያን፣ ግሪኮችና ሌሎች ሕዝቦች በኮከብ ቆጠራ ይጠቀሙ እንደነበር በግልጽ መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ የኮከብ ቆጠራ ምልክቶችን የሚጠቅሱ እጅግ ጥንታዊ የሚባሉ መረጃዎች ይገኙ የነበረው በጥንቷ ባቢሎን ነው።

ባቢሎናውያን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ሲሉ ኮከብ ቆጠራን ፈለሰፉ። የሰማይ አካላትን እንቅስቃሴ በመመልከት ዝርዝር ጉዳዮችን የያዙ ቻርቶችና ሰንጠረዦች ተዘጋጁ። በእነዚህ ሰንጠረዦች በመጠቀም የሰው ልጆችን ጉዳዮችና ምድራዊ ክስተቶችን የሚመለከቱ ትንቢቶች ይነገሩ ጀመር። ብዙውን ጊዜም የኮከብ ቆጣሪዎች አስተያየት ሳይጠየቅ ፖለቲካዊ ወይም ወታደራዊ ውሳኔዎች አይተላለፉም ነበር። በመሆኑም ልዩ ጥበብና ተአምራዊ ኃይል አለኝ የሚል አንድ የካህናት ክፍል ታላቅ ተጽእኖ ማሳደር ጀመረ። እንዲያውም በባቢሎን የሚገኙ ታላላቅ ቤተ መቅደሶች በሙሉ የሰማይ አካላትን እንቅስቃሴ ለመከታተል የሚያስችሉ መዋቅሮችን ያቀፉ ነበሩ።

በዘመናችን የኮከብ ቆጠራ ምልክቶች በብዙ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ቀጥለዋል። በኮከብ ቆጠራ ትንበያ አናምንም የሚሉ ሰዎች እንኳ አንዳንድ ጊዜ እንዲሁ ለመዝናናት በሚል ወይም የማወቅ ጉጉት አድሮባቸው የኮከብ ቆጠራ ቻርቶችን ለመመልከት ሊነሳሱ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ ኮከብ ቆጣሪዎች የተናገሯቸው አንዳንድ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ይህ ማለት ግን በኮከብ ቆጠራ መጠቀም ጠቃሚ ነው ማለት ነውን? የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች በኮከብ ቆጠራ መጠቀምን በተመለከተ የነበራቸው አመለካከት ምንድን ነው?

ስውር የሆኑ አደጋዎች

ከባቢሎናውያን በተለየ መልኩ ታማኝ አይሁዶች በኮከብ ቆጠራ አይጠቀሙም ነበር። ለዚህም በቂ ምክንያት ነበራቸው። አምላክ በማያሻማ ሁኔታ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋቸዋል:- “ምዋርተኛም፣ ሞራ ገላጭም፣ አስማተኛም፣ መተተኛም፣ በድግምት የሚጠነቁልም፣ መናፍስትንም የሚጠራ፣ ጠንቋይም፣ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው።” *​—⁠ዘዳግም 18:​10-12፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

የአምላክ አገልጋዮች ኮከብ ቆጠራን የሚጻረር ጽኑ አቋም ወስደዋል። ለምሳሌ ያህል ታማኙ ንጉሥ ኢዮስያስ “ለበኣልና ለፀሐይ ለጨረቃና ለከዋክብት . . . ያጥኑ የነበሩትንም” አስወግዷል። ኢዮስያስ የወሰደው እርምጃ “በእግዚአብሔርም ፊት ቅን” እንደነበረ የተነገረ ከመሆኑም በላይ ይህን እርምጃ በመውሰዱ አምላክ ባርኮታል። (2 ነገሥት 22:​2፤ 23:​5) ይሁን እንጂ፣ አንዳንዶች ‘ቢያንስ ቢያንስ ኮከብ ቆጣሪዎች የተናገሯቸው አንዳንዶቹ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙ የለ እንዴ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል።

በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ” ስለነበረች አንዲት ልጃገረድ እናነባለን። ጌቶችዋ ልጅቷ በነበራት ችሎታ በመጠቀም ብዙ ትርፍ ያገኙ በመሆኑ ትናገረው ከነበረው ትንቢት መካከል አንዳንዱ ፍጻሜውን ያገኝ የነበረ ይመስላል። ይሁን እንጂ ይህች ልጅ ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች በመተንበይ ረገድ ከነበራት ችሎታ በስተጀርባ የነበረው ነገር ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት [“ርኩስ መንፈስ ያደረባት፣” የ1980 ትርጉም ]” እንደነበረች ይገልጻል።​—⁠ሥራ 16:​16

መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምም በሞላው በክፉው” ማለትም በሰይጣን ዲያብሎስ እንደተያዘ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:​19) ሰይጣንና አጋንንቱ አንዳንድ ትንበያዎች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ የተለያዩ ሁኔታዎች በፈለጉት አቅጣጫ በመምራት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ትኩረት መሳብ ችለዋል።

ኮከብ ቆጠራ ዲያብሎስ ሰዎችን በመቆጣጠርና በሰዎች ላይ ተጽእኖ በማሳደር ዓላማውን እንዲፈጽሙ ለማድረግ ከሚጠቀምባቸው ‘መሸንገያዎች’ አንዱ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ኮከብ ቆጠራን ጨምሮ የሰይጣንን አታላይ ዘዴዎች ‘እንዲቃወሙ’ አጥብቆ ማሳሰቡ ምንም አያስደንቅም። (ኤፌሶን 6:​11) እንዲህ ሲባል ግን የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ መመሪያ የምናገኝበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም ማለት ነውን?

መጽሐፍ ቅዱስ​—⁠አስተማማኝ መመሪያ

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውሳኔ ለማድረግ አስተማማኝ መመሪያ ሆኖ አግኝተውታል። መዝሙራዊው ዳዊት እንደገለጸው “የእግዚአብሔር ትእዛዝ የታመነ ነው፤ ማስተዋል ለጎደላቸው ጥበብን ይሰጣል።” (መዝሙር 19:​7 የ1980 ትርጉም፤ 119:​105) እንዲህ ሲባል ግን መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው በእያንዳንዱ ሁኔታ ሥር ሊያደርገው የሚገባውን ነገር አንድ በአንድ ይዘረዝራል ማለት አይደለም። ሆኖም የአምላክ ቃል የማስተዋል ችሎታችንን ለማሰልጠን ሊረዱን የሚችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዟል። ይህ ደግሞ መልካሙንና ክፉውን እንድንለይ የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል።​—⁠ዕብራውያን 5:​14

ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሌላው ቀርቶ እንዲሁ ለመዝናናት ብለው ወይም ደግሞ የማወቅ ጉጉት አድሮባቸው እንኳ የኮከብ ቆጠራ ቻርቶችንና ሰንጠረዦችን አለመጠቀማቸው አግባብነት ያለው ነው። ከዚህ ይልቅ የጥበብ እርምጃ በመውሰድ የአምላክ ቃል ስውር ከሆኑት አጋንንታዊ ተጽእኖዎች ጭምር እንዲርቁ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ይከተላሉ። ከኮከብ ቆጠራ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ከፈቀድክ የአምላክን በረከት ለዘላለም ማግኘት ትችላለህ።​—⁠መዝሙር 37:​29, 38

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 ምዋርት ስውር በሆኑ ኃይሎች አማካኝነት መረጃ ማግኘትን በተለይ ደግሞ ወደፊት ስለሚሆኑት ነገሮች ማወቅን የሚጨምር ነው።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምሥራቃውያን ኮከብ ቆጠራ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምዕራባውያን ኮከብ ቆጠራ