በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ሁለተኛ ሐኪም ማማከር አስፈላጊ ነውን?

“ከሕክምና ጋር በተያያዘ ብዙዎቻችን ሁለተኛ ሐኪም ማማከር አግባብነት የጎደለው ድርጊት ሆኖ ይሰማናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ታካሚዎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ ሊያደርጋቸው ይችላል” ሲል በሜክሲኮ ሲቲ እየታተመ የሚወጣው ዘ ኒውስ ገልጿል። ታካሚዎች ሁለተኛ ሐኪም ቢያማክሩ ዶክተራቸው ቅር እንደሚሰኝ ይሰማቸዋል። ሆኖም “ታካሚዎች ሁለተኛ ሐኪም ቢያማክሩ አብዛኞቹ ዶክተሮች ቅር እንደማይሰኙ” ጋዜጣው ገልጿል። “ዶክተርህ በዚህ ቅር የሚሰኝ ከሆነ ችግር እንዳለ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።” በዛሬው ጊዜ ሐኪሞችም ሆኑ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ታካሚዎች ሁለተኛ ሐኪም ቢያማክሩ የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ በር ሊከፍትላቸው እንደሚችል ያምናሉ። በጆርጂያ የሚገኘው ክሊኒካዊ ኦንኮሎጂ ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ማይክል አንድሩዝ ታካሚዎቻቸው ብዙውን ጊዜ እሳቸው ባቀረቡላቸው ሐሳብ ላይ ይበልጥ እንዲተማመኑ የሚያደርግ ምክር ይዘው ስለሚመለሱ ሁለተኛ ሐኪም እንዲያማክሩ እንደሚያበረታቷቸው ተናግረዋል። የአንድ የሕዝብ ጤና እንክብካቤ ቡድን ዲሬክተር “ታካሚዎች ለአደጋ የተጋለጠው የእነሱ አካል መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም” ብለዋል።

በሕፃናት ላይ የሚፈጸም በደል በሕንድ

በሕንድ በየአሥር ደቂቃው አንድ ሕፃን በዝሙት አዳሪነት እንዲሠማራ ይደረጋል ሲል ዘ ኒው ኢንዲያን ኤክስፕሬስ ዘግቧል። ይህ ማለት በየዓመቱ 50, 000 የሚሆኑ ሕንዳውያን ሕፃናት በወሲብ ንግድ ለመሠማራት ይገደዳሉ ማለት ነው። በኬራላ ግዛት በልጆች ላይ የሚፈጸመውን ወሲባዊ በደል አስመልክቶ በተካሄደው ሴሚናር ላይ ሌላ አስደንጋጭ ግኝት ሪፖርት ተደርጓል። አንዳንድ ዶክተሮች “ብቃቱ ስለሌላቸውም ሆነ በጉዳዩ እጃቸውን ጣልቃ ላለማስገባት ሲሉ ተገድደው የተደፈሩ ሰዎችን ጉዳይ ለመመርመር ፈቃደኛ እንዳልሆኑ” ጋዜጣው ዘግቧል። ወላጆችም ሳይቀሩ ለችግሩ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደረጉባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ታውቋል። የማኅበራዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ የሆኑት ስሪሌካ “ወላጆች በማኅበረሰቡ ዘንድ መጥፎ ስም ላለማትረፍና ማኅበራዊ ተቀባይነትን ላለማጣት ሲሉ በልጆቻቸው ላይ የተፈጸመውን [የማስነወር] ድርጊት ሪፖርት ሳያደርጉ ይቀራሉ” ብለዋል።

‘ጥበብ ከዕድሜ ጋር ይመጣል’

የሰዎች ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ አንዳንድ የአንጎል ክፍሎች አዳዲስ ሕዋሳት እንደሚያመነጩ ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል ሲል የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል። ቀደም ሲል ሰዎች ለአካለ መጠን ከደረሱ በኋላ የአንጎል ሕዋሳት አይራቡም ተብሎ ይታመን ነበር። “ሕዋሳቱ እንዲራቡ ለማነቃቃት የሚያስችለው ቁልፉ ነገር አእምሮን ማሠራት ነው” ይላል ዘ ታይምስ። በቅርቡ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ በሆነ ሰዎች ላይ የተካሄደ ጥናት እንዳመለከተው ትምህርት መቅሰምና ከሌሎች ሰዎች ጋር የተለያዩ ግንኙነቶች ማድረግ አዳዲስ የአንጎል ሕዋሳትና የመገናኛ መስመሮች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። ተመራማሪዎቹ ከሌሎች ሰዎች ጋር ግንኙነት ማድረግ “ጤናን፣ ዕድሜንና ኑሮን” እንደሚያሻሽል አረጋግጠዋል። ኒውሮሳይንቲስት የሆኑት ሱዛን ግሪንፊልድ “ብዙ ልምድ ባካበትህ መጠን በአንጎልህ ሕዋሳት መካከል ያሉት መገናኛ መስመሮች እየጨመሩ ይሄዳሉ። በመሆኑም ሰዎች ዕድሜያቸው እየገፋ በሄደ መጠን ይበልጥ ጥበበኛ ይሆናሉ” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

የሰሜን ባሕር መንገድ

የአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን ቅመማ ቅመም ነጋዴ ሮበርት ቶርን በአንድ ወቅት በአርክቲክ በኩል ከአውሮፓ ወደ ሩቅ ምሥራቅ የሚወስድ የባሕር መንገድ የማግኘት ሕልም ነበረው። በዛሬው ጊዜ የምድር ሙቀት መጠን በመጨመሩ ሳቢያ የቶርን ሕልም እውን ሆኗል ይላል የለንደኑ ዘ ታይምስ። በአሁኑ ጊዜ በሩስያና በምሥራቅ ሳይቤሪያ የባሕር ዳርቻዎች የሚገኙት የውኃ አካላት በበጋ ወራት ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል፣ ከበረዶ የጠሩ ስለሚሆኑ ዕቃ ጫኝ መርከቦች ከሰሜን ባሕር ተነስተው በአርክቲክ ክልል በመዞር በቤሪንግ የባሕር ወሽመጥ በኩል ወደ ፓስፊክ መጓዝ ይችላሉ። ይህ የጉዞ መስመር በበረዶ በሚሸፈንበት ጊዜ ከአውሮፓ የሚነሱ መርከቦች ወደ ሩቅ ምሥራቅ ለመጓዝ ስዊዝ ቦይን መጠቀም፣ በደቡባዊ አፍሪካ ጫፍ በኩል ዞሮ መጓዝ አለዚያም ደግሞ በፓናማ ቦይ በኩል ማቋረጥ ይኖርባቸዋል። በሰሜን ባሕር መንገድ በኩል መጓዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ከጀርመን፣ ሀምቡርግ እስከ ጃፓን፣ ዮኮሃማ ድረስ ያለውን ርቀት በግማሽ በመቀነስ ከ13, 000 ኪሎ ሜትር በታች በሆነ ርቀት እንዲወሰን ያደርገዋል።

ከደም ምርመራ ጋር የተያያዙ ችግሮች

“በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት አገሮች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከሰዎች በሚለገስ ደም ላይ የተሟላ ምርመራ ስለማያደርጉ ኤድስና ሌሎች በሽታዎች የሚዛመቱበት አጋጣሚ ይበልጥ እየሰፋ ሄዷል” ይላል አሶስዬትድ ፕሬስ ያወጣው ዘገባ። ከዓለም የጤና ድርጅት በተገኘ መረጃ ላይ የተመሠረተው ይህ ዘገባ “የኤድስ ቫይረስ ካለባቸው ሰዎች መካከል ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆኑት በቫይረሱ ሊያዙ የቻሉት በደም ሥራቸው በተሰጣቸው ደም አማካኝነት ነው” ሲል አክሎ ይገልጻል። ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ የሚተላለፈው ኤድስ ብቻ አይደለም። በየዓመቱ ከ8 እስከ 16 ሚልዮን የሚደርሱ የሄፐታይተስ ቢ ኢንፌክሽኖችና ከ2 እስከ 4 ሚልዮን የሚደርሱ የሄፐታይተስ ሲ ኢንፌክሽኖች የሚከሰቱት በደም ሥር በሚሰጥ ደምና ንጽሕናቸው ባልተጠበቁ መርፌዎች ሳቢያ ነው። በደም ላይ በቂ ምርመራ እንዳይካሄድ እንቅፋት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ምርመራው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ ነው። በአንድ ዩኒት ደም ውስጥ እነዚህ በካይ ነገሮች መኖር አለመኖራቸውን ለመመርመር ከ40 እስከ 50 የአሜሪካ ዶላር ይጠይቃል። ከዚህም ሌላ እንዲህ ዓይነቶቹ ምርመራዎች “በተለይ በቂ ሥልጠና ባላገኙ ሠራተኞች ወይም ተገቢውን መሥፈርት ባላሟላ መሣሪያ የሚካሄዱ ከሆነ ሁልጊዜ አስተማማኝ ሆነው ሊገኙ አይችሉም” ሲል ዘገባው ይገልጻል።

ለአደጋ የሚያጋልጡ ጓደኞች

ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን ላይ የወጣው አንድ ጥናት እንደሚለው ከሆነ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አሽከርካሪዎች በሚያሽከረክሩት መኪና ውስጥ ተሳፋሪዎች በሚኖሩበት ጊዜ ለሞት ሊዳርግ ለሚችል አደጋ የሚጋለጡበት አጋጣሚ የሰፋ ይሆናል። በሜሪላንድ ዩ ኤስ ኤ በጆንዝ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ተመራማሪዎች አንድ የ16 ዓመት አሽከርካሪ በአደጋ ሳቢያ ሕይወቱን ሊያጣ የሚችልበት አጋጣሚ መኪናው ውስጥ አንድ ተሳፋሪ በሚኖርበት ጊዜ 39 በመቶ፣ ሁለት ተሳፋሪዎች በሚኖሩበት ጊዜ 86 በመቶ እንዲሁም ሦስትና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ተሳፋሪዎች በሚኖሩበት ጊዜ 282 በመቶ እንደሚጨምር ለማረጋገጥ ችለዋል። ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ሆነው በጥናቱ ላይ የተጠቀሱት ነገሮች “እኩዮች የሆኑ ጓደኞች መኪናው ውስጥ በመኖራቸው ሳቢያ የሚፈጸሙ . . . አደገኛ የሆኑ ድርጊቶች” ናቸው። እነዚህ ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ድርጊቶች በከፍተኛ ፍጥነት ማሽከርከርን፣ ሌላ ተሽከርካሪን በጣም ተጠግቶ መንዳትን፣ የትራፊክ መብራት ጥሶ መሄድን፣ አደገኛ ዕፆች ወስዶ ወይም አልኮል ጠጥቶ መንዳትንና እርስ በርስ የሚላፉ ተሳፋሪዎች በሚያደርጉት ነገር መሳብን ይጨምራሉ።

በቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ መመገብ ለጤና ጠቃሚ ነው

ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ጤና እንዲኖራቸው መርዳት ከሚችሉባቸው ከሁሉ የተሻሉ መንገዶች አንዱ አብረዋቸው እንዲመገቡ ማድረግ ነው ይላል ግሎብ ኤንድ ሜይል የተሰኘው ጋዜጣ። የሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ማቲዉ ጊልማን እንዳሉት ከሆነ “በቤተሰብ ደረጃ የሚበሉ ምግቦች ልጆችና በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ለብቻቸው ከሚመገቧቸው ምግቦች ይበልጥ ገንቢ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዙ ናቸው።” ከቤተሰቦቻቸው ጋር አንድ ላይ የሚመገቡ ልጆች የቀረቡላቸውን ፍራፍሬዎችና አትክልቶች እንዲሁም ለሰውነታቸው አስፈላጊ የሆኑትን ቫይታሚኖችና ማእድናት የመመገባቸው አጋጣሚ ይበልጥ ሰፊ ከመሆኑም በላይ የስኳርና የስብ ፍጆታቸው ይቀንሳል። ከዚህም በተጨማሪ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ መመገብ ቤተሰቡ ስለ ጥሩ አመጋገብ እንዲወያይ በር እንደሚከፍትና ልጆች ከቤታቸው ውጪ በሚመገቡበትም ጊዜ ሊከተሉት የሚችሉት የተሻለ የአመጋገብ ልማድ እንዲያዳብሩ እንደሚረዳ ተመራማሪዎቹ አረጋግጠዋል። ከ9 እስከ 14 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 16, 000 ገደማ የሚሆኑ ልጆች ላይ ከሚካሄደው ቀጣይነት ያለው የምርምር ፕሮጄክት የተገኘው አዲስ ጥናት እንዳመለከተው “መማር በሚችሉበት ዕድሜ ላይ ካሉ አምስት ልጆች መካከል በአብዛኞቹ ቀናት እራታቸውን ከወላጆቻቸው ጋር የሚበሉት ሁለቱ ብቻ ሲሆኑ ከአምስቱ አንዱ ጨርሶ ከወላጆቹ ጋር አይመገብም” ሲል ግሎብ ገልጿል።

ምርጥ ሸማኔዎች

“የሸረሪት ድር በምድር ላይ ካሉት በጣም ጠንካራ ቁሶች አንዱ ነው” ይላል ኒው ሳይንቲስት የተሰኘው መጽሔት። እያንዳንዱ ድር ከመበጠሱ በፊት የርዝማኔውን አራት እጥፍ ያህል ሊወጠር የሚችል ሲሆን በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ የአንድ እርሳስ ያህል ውፍረት ያለው ድር በበረራ ላይ ያለን አንድ ትልቅ አውሮፕላን ሊያስቆም ይችላል እስከ መባል ደርሷል። ተመራማሪዎች የሸረሪትን የሽመና ምስጢር ለማወቅና በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ለምሳሌ ያህል በዛሬው ጊዜ ጥይት የማይበሳቸው ሰደርያዎች ለመሥራት የሚመረጠው ቁስ “ወደ መፍላት ደረጃ እስኪቃረብ ድረስ እንዲሞቅ የተደረገ ውፍር ሰልፈሪክ አሲድ” በመጠቀም የሚሠራው ኬቭላር የተሰኘው ሰው ሠራሽ ቁስ ነው ሲል መጽሔቱ ይገልጻል። ይሁን እንጂ ኬቭላር በሚመረትበት ጊዜ የሚፈጠሩት ተጓዳኝ ውጤቶች መርዛማ ከመሆናቸውም በላይ በቀላሉ ሊወገዱ የሚችሉ ዓይነት አይደሉም። በአንጻሩ ሸረሪቶች ድር የሚሠሩት “ፕሮቲንና ተራ ውኃ” በመጠቀም ሲሆን “ይህን ለመሥራት የሚጠቀሙት የአሲድና የአልካሊን እንዲሁም የሙቀት መጠን በሰው አፍ ውስጥ ካለው ጋር የሚመጣጠን ነው።” በተጨማሪም በዚህ የውኃና የፕሮቲን ድብልቅ የሚሠራው ድር በዝናብ ታጥቦ ሊወሰድ የማይችል ነው። በመሆኑም ኒው ሳይንቲስት “ለብዙ ዓመታት ጥናት ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም የሸረሪት ድር አሁንም ድረስ እንቆቅልሽ ነው” ሲል ገልጿል።

ብክለት በቤት ውስጥ

“በደጃፍህ ከሚገኝ የአትክልት ሥፍራ ይልቅ ቤትህ ሊበከል የሚችልበት አጋጣሚ አሥር እጅ የሰፋ ነው” ይላል የለንደኑ ዘ ታይምስ። የሕንፃ ምርምር ተቋም በ174 የብሪታንያ ቤቶች ላይ ያካሄደው ጥናት በቤት ውስጥ ቺፑድና ሌሎች ሰው ሠራሽ ንጥረ ነገሮች ካሉባቸው ዕቃዎች የሚወጣው የፎርማልዴሃይድ ተን መጠን በውጪ ካለው ጋር ሲነጻጸር አሥር እጅ በልጦ መገኘቱን አመልክቷል። ምርመራ ከተካሄደባቸው ቤቶች መካከል አሥራ ሁለቱ የዓለም የጤና ድርጅት የአየር ጥራት ደረጃን አስመልክቶ ያወጣውን መሥፈርት አያሟሉም። ሰው ሠራሽ ንጥረ ነገሮችን የያዙ የቤት ውስጥ ዕቃዎች፣ ከፕላስቲክ የተሠሩ ወለሎች፣ የሕንፃና የማስጌጫ ቁሶች፣ ለጽዳት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች ወይም የማሞቂያና የማብሰያ መሣሪያዎች ካርቦን ሞኖኦክሳይድ፣ ናይትሮጅን ዳይኦክሳይድ፣ የቤንዚን ተን ወይም በቀላሉ የሚተኑ ካርቦናማ ውህዶች ሊፈጥሩ ይችላሉ። በካንሰር መንስኤነቱ የሚታወቀው የቤንዚን ተን ለጽዳት በሚያገለግሉ የሚነፉ ንጥረ ነገሮች ውስጥና በትምባሆ ጢስ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በቤት ውስጥ የሚኖረውን አየር ከሚበክሉ ነገሮች መካከል የሚደመር ነው። ሄልዝ ዊች? የተሰኘው መጽሔት አዘጋጅ የሆኑት ሻርሎት ጋን ብዙዎቹ ሰዎች ካላቸው ጊዜ ውስጥ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆነውን የሚያሳልፉት በቤት ውስጥ ነው። “የምንጠቀምባቸውን የኬሚካል ውጤቶች መጠን መቀነስ፣ ጥቂት መስኮቶችን መክፈትና የጋዝ መገልገያዎች በደንብ መዘጋታቸውን ማረጋገጥ” በቤት ውስጥ የሚኖረውን አየር የጥራት ደረጃ ለማሻሻል እንደሚረዳ ተናግረዋል።