በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቻይናውያን መድኃኒት ቤት ሲጎበኝ

የቻይናውያን መድኃኒት ቤት ሲጎበኝ

የቻይናውያን መድኃኒት ቤት ሲጎበኝ

ክዎክ ኪት ከታመመ ጥቂት ቀናት ያለፉ በመሆኑ ሐኪም ዘንድ ለመሄድ ይወስናል። ቻይናዊ እንደመሆኑ መጠን ወደ ቻይና የባሕል ሐኪም መሄድ ይመርጣል። የቤተሰባቸው ወዳጅ የሆነ አንድ ሰው በአቅራቢያቸው ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶች (herb) መሸጫ ሱቅ ያለው አንድ የባሕል ሐኪም ያውቃል። ሐኪሙ ሕመሙን ሊፈውስለት የሚችል የዕፅ ሻይ ሊቀምምለት እንደሚችል ለክዎክ ኪት ይነግረዋል።

በአብዛኞቹ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች እንደሚታየው ሁሉ በቻይናም ሰዎች የሚታከሙበት ሁኔታ በምዕራባውያን አገሮች ያሉ ሰዎች ከሚታከሙበት ሁኔታ ይለያል። በምዕራቡ ዓለም አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው ወደ ሐኪም ለመሄድ ሲፈልግ ቀጠሮ ይይዛል፣ ወደ ሐኪሙ ቢሮ ይሄዳል፣ ምርመራ ያደርጋል፣ እንዲሁም መድኃኒት ይታዘዝለታል። ከዚያም ታካሚው የታዘዘለትን መድኃኒት ለማግኘት ወደ መድኃኒት ቤት መሄድ ይኖርበታል። ወደ አንድ የቻይና ሐኪም ዘንድ ቀርቦ ሕክምና ማግኘት ግን በጣም ቀላል ነው። የዕፅዋት መድኃኒቶች ቀማሚና የቻይናውያን የባሕል ሕክምና ባለሙያ የሆነ ሰው ሙሉ ቀን ወደሚሠራበት የዕፅ መሸጫ ሱቅ ትሄዳለህ። በዚያው በሄድክበት ሰዓት ሊመረምርህ፣ በሽታህን ለይቶ ሊያውቅ፣ የሚያዝልህን ከዕፅዋት የተቀመመ መድኃኒት ለክቶ ሊሰጥህና አወሳሰዱን ሊነግርህ ይችላል! *

ዕፅዋት እንደ መድኃኒት?

አብዛኞቹ ምዕራባውያን እንደ ኪኒን፣ እንክብልና መርፌ ካሉ ነገሮች ጋር የተላመዱ ቢሆንም እንዲህ ዓይነቶቹ መድኃኒቶች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታዩ አዲሶች ናቸው። ለብዙ ሺህ ዓመታት ሰዎች ተፈጥሯዊ በሆኑ ነገሮች ፈውስ ለማግኘት ሲጥሩ ኖረዋል። ለምሳሌ ያህል በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ዕብራውያን ሐኪሞች እንደ ዘይትና ወይን ጠጅ ባሉ መድኃኒቶች ይጠቀሙ ነበር። (ኢሳይያስ 1:​6፤ ኤርምያስ 46:​11፤ ሉቃስ 10:​34) ብጉንጅን ለማከም በደረቀ በለስ የተዘጋጀ የቁስል መድኃኒት ይጠቀሙ የነበረ ይመስላል።​—⁠2 ነገሥት 20:​7

እንዲያውም እያንዳንዱ ብሔር ወይም ሕዝብ ማለት ይቻላል፣ በሆነ ወቅት ላይ የተለያዩ ሕመሞችንና በሽታዎችን ለማከም ዕፅዋትንና ከተለያዩ ነገሮች የተቀመሙ ንጥረ ነገሮችን ተጠቅሟል። በአሁኑ ጊዜ ምግብ ለማጣፈጥ የምንጠቀምባቸው በርካታ ቅመሞች እንኳ በአንድ ወቅት ለሕክምና አገልግሎት ውለዋል። እንዲህ ሲባል ግን እነዚህ ልማዶች ሁልጊዜ የታሰበውን ያህል ስኬት ያስገኙ ነበር ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ዓይነቶቹ ልማዶች ብዙውን ጊዜ ከአጉል እምነትና ከድንቁርና ጋር የተያያዙ ነበሩ። ያም ሆኖ ግን ለብዙ ሺህ ዓመታት ይህን መንገድ በመጠቀም ሕሙማንን ለማከም ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ሌላው ቀርቶ በዛሬው ጊዜ በሰፊው ጥቅም ላይ ከዋሉት መድኃኒቶች መካከል አንዳንዶቹ ከዕፅዋት የተገኙ ናቸው።

የቻይናውያን ሕክምና ንድፈ ሐሳብና አጠቃቀም

በሽታን ከዕፅዋት በተቀመሙ መድኃኒቶች ማከም በቻይና ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የያዘ ልማድ ነው። ሁዋንግ ዲ የተባለው ቢጫው ንጉሠ ነገሥት በቻይና ውስጥ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች አሁንም ድረስ የሚጠቀሙበትን ኔይ ጂንግ የተሰኘውን የውስጥ ደዌ ሕክምና መመሪያ እንዳጠናቀረ አፈ ታሪክ ይናገራል። * የተጻፈበት ዘመን አከራካሪ የሆነው ይህ መመሪያ አንድ የምዕራባውያን የሕክምና መጽሐፍ ሊያካትታቸው የሚችላቸውን በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች የያዘ ነው። ምርመራ የሚካሄድበትን መንገድ፣ የበሽታ ምልክቶችን፣ መንስኤ የሚሆኑትን ነገሮች፣ ሕክምና የሚሰጥበትንና በሽታን መከላከል የሚቻልበትን መንገድ ብቻ ሳይሆን ስነ ብልትንና አካላዊ አሠራርን በተመለከተም ማብራሪያ ይሰጣል።

የዪን-ያንግ መሠረተ ትምህርት በአብዛኞቹ የደቡብ ምሥራቅ እስያ የጥበብ ሥራዎች ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ሁሉ በቻይና ሕክምና ጽንሰ ሐሳብና አጠቃቀም ላይም ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል። በዚህ ረገድ ዪን ቅዝቃዜን፣ ያንግ ደግሞ ሙቀትን የሚያመለክት ሲሆን ተጻራሪ የሆኑ ሌሎች በርካታ ነገሮችንም ያመለክታሉ። * ከዚህም በተጨማሪ በሽታን ለይቶ ለማወቅና ሕክምና ለመስጠት ሜሪዲያን የሚባሉ በአኩፓንቸር ሕክምና ወቅት መርፌዎች የሚሰኩባቸው በሰውነት ላይ ያሉ መሥመሮች ግምት ውስጥ ይገባሉ። በበሽተኛው ላይ የተከሰተውን የዪን-ያንግ መዛባት ለማስተካከል ቀዝቃዛ አለዚያም ሞቃት ተደርገው የሚታሰቡ ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶችና ምግቦች ይታዘዙለታል።

ለምሳሌ ያህል ትኩሳት ያለው ታካሚ ከፍተኛ ሙቀት እንዳለው ስለሚቆጠር ሊያቀዘቅዙ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶች ይታዘዙለታል። በዛሬው ጊዜ የዪን-ያንግ መሠረተ ትምህርት በቀጥታ የማይጠቀስ ቢሆንም እንኳ አንድን በሽተኛ ማከም የሚቻልበትን መንገድ ለማወቅ አሁንም ድረስ ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት ይሠራበታል። ይሁን እንጂ አንድ የቻይና የባሕል ሕክምና ባለሙያ በሽታን ለይቶ የሚያውቀው እንዴት ነው? ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ዕፅዋት የሚሸጡበት መደብርስ ምን ይመስላል? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ክዎክ ኪት ወዳጁ ወደ ጠቆመው መደብር ሲሄድ ለምን አብረነው አንጓዝም?

የዕፅዋት ውጤቶች የሚገኙበት ለየት ያለ መደብር

በጣም የሚገርም ነው! ዛሬ ክዎክ ኪት ሐኪሙ ዘንድ ለመቅረብ ትንሽ ወረፋ መጠበቅ ሊኖርበት ነው። የፍሉ ወይም የጉንፋን ወረርሽኝ በመኖሩ ይመስላል፣ ሁለት ታካሚዎች ቀድመውት ደርሰዋል። እስከዚያው መደብሩን እየቃኘን እንቆይ።

ልክ እንደገባን መጀመሪያ ትኩረታችንን የሚስቡት ነገሮች መግቢያው ላይ ክፍት በሆኑ በርሜሎች ውስጥ ተከምረው የሚታዩት ደረቅ ሸቀጣ ሸቀጦች ማለትም እንጉዳይ፣ ስካሎፕ (ሼልፊሽ)፣ አባሎኒ (የባሕር እንስሳ)፣ በለስ፣ ለውዝና ሌሎች የሚበሉ ነገሮች ናቸው። እርግጥ ነው፣ በዚህ መደብር ውስጥ ለምግብነት የሚያገለግሉ ነገሮች ይገኛሉ። ሆኖም ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በመድኃኒትነት ሊታዘዙ ይችላሉ።

ከእነዚህ ነገሮች ባሻገር ዓይናችንን ወርወር ስናደርግ ደግሞ ጠባብ በሆነው መደብር ግራና ቀኝ የቆሙ ባለ መስተዋት ባንኮኒዎች እንመለከታለን። በእነዚህ ባንኮኒዎች ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ እንደልብ የማይገኙ ወይም ለየት ያሉ ዕፅዋት፣ ማዕድናትና የደረቁ የእንስሳት ክፍሎች ይገኛሉ። ቀረብ ብለን ስናይ የአጋዘን ቀንድ፣ ሉል፣ የደረቁ እንሽላሊቶችና ሲ ሆርስ ተብለው የሚጠሩ ትናንሽ ዓሦች እንዲሁም ሌሎች እንግዳ የሆኑ ነገሮች እንመለከታለን። እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የአውራሪስ ቀንድ፣ የድብ የሐሞት ከረጢትና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች የእንስሳት አካል ክፍሎች በእንዲህ ዓይነቶቹ ባንኮኒዎች ውስጥ ይገኙ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን እገዳ ተጥሎባቸዋል።

በመደብሩ ሌላ ጎን ደግሞ እንደ ጉንፋንና ሆድ ቁርጠት ላሉ የተለመዱ ዓይነት በሽታዎች መድኃኒት የሚሆኑ የዕፅዋት ድብልቆችን የያዙ ፓኬቶች እንዲሁም ከዕፅዋት የተቀመሙ የቻይና መድኃኒቶችን የያዙ ብልቃጦች ተቀምጠው እንመለከታለን። ረዳት ሠራተኛውን ወይም ሻጩን ምን እንዳመመህ ከነገርከው በብልቃጥ የተዘጋጀ መድኃኒት ይሰጥሃል አለዚያም የዕፅዋት ድብልቆች የያዘ ፓኬት ይሰጥህና እቤትህ እንዴት አዘጋጅተህ ልትወስደው እንደምትችል ይነግርሃል።

ከሻጩ በስተጀርባ በአንድ ወገን ብዙ ዓይነት የደረቁ ሥራሥሮች፣ ቅጠሎችና ቀምበጦች የያዙ ትልልቅ ጠርሙሶች የተቀመጡባቸው መደርደሪያዎች ይገኛሉ። እነዚህ ዕፅዋት ደንበኞቹ ጠንቅቀው የሚያውቋቸውና ራሳቸው ገዝተው ለመድኃኒትነት አለዚያም ለምግብነት ሊጠቀሙባቸው የሚችሏቸው ናቸው። በሌላ ወገን ደግሞ በርካታ ያረጁ መሳቢያዎች ያሉት እስከ ጣሪያ የሚደርስ ቁም ሳጥን ይገኛል። እንዲህ ዓይነቱ የዕፅዋት ውጤቶች ማስቀመጫ ቁም ሳጥን መቶና ከዚያ በላይ የሚሆኑ መሳቢያዎች ሊኖሩት ስለሚችል ባይትዚግዌ ወይም “መቶ ልጆች ያሉት ቁም ሳጥን” በመባል ሲጠራ ቆይቷል። እነዚህ መሳቢያዎች ብዙ ጊዜ የሚታዘዙትን ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶች ወዲያው ለማግኘት የሚረዱ ሲሆን በተደጋጋሚ የሚታዘዙት መድኃኒቶች በቀላሉ ሊገኙ በሚችሉባቸው ቦታዎች እንዲቀመጡ ይደረጋል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ መሳቢያዎች ምን ምን መድኃኒቶች እንደያዙ ለመለየት የሚያስችል ምልክት ሲደረግባቸው አይታይም። ልምድ ያካበቱት ረዳት ሠራተኞች እያንዳንዱ መድኃኒት የት እንደሚገኝ ጠንቅቀው ያውቃሉ።

ረዳት ሠራተኛው መድኃኒት ለታዘዘላት ሴት ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶችን ቅልጥፍና በተሞላበት ሁኔታ እንዴት እየመዘነ እንደሚሰጥ ልብ በል። ብዙም ጥንካሬ የሌለው ቢሆንም እንኳ ትክክለኛ የሆነውን የእስያ ሚዛን ይጠቀማል። ሚዛኑ በአንደኛው ጫፍ ላይ በሦስት ክሮች የተንጠለጠለ ክብ ትሪ በሌላኛው ጫፍ ደግሞ ሊለዋወጥ የሚችል የክብደት መለኪያ የያዘ ዘንግ አለው። ከዕፅዋት የሚቀመሙ አንዳንድ መድኃኒቶች ከመጠን በላይ ከተወሰዱ ለሞት ሊዳርጉ እንደሚችሉ ስለሚያውቅ በሚመዝንበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል። እንዲህ ሲባል ግን ሁሉን ነገር እየመዘነ ይሰጣል ማለት አይደለም። በተለያዩ መሳቢያዎች ውስጥ ከሚገኙ ከዕፅ የተቀመሙ የተለያዩ መድኃኒቶች ግማሽ እፍኝ ያህል እየቆነጠረ በአንድ የመጠቅለያ ወረቀት ላይ ሲያስቀምጥ እንመለከተዋለን። አዎን፣ ጥሩ ታዝበሃል፣ የታዘዘው መድኃኒት ሲኬዳ ከተሰኘው ሦስት አፅቄ ቅርፊት የተቀመመን ንጥረ ነገር ይጨምራል። ድብልቁን ጠቅልሎ ለሴትየዋ ሲሰጣት እንዴት እንደምታዘጋጀው ይነግራታል።

ከዕፅዋት የሚቀመሙ መድኃኒቶች የሚዘጋጁበትና የሚወሰዱበት መንገድ የተለያየ ነው። አንዳንዶቹ በዱቄት መልክ ይዘጋጃሉ። ሕመምተኛው መድኃኒቱን በሞቀ ውኃ ውስጥ ካሟሟው በኋላ ይጠጣዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ የተላቆጡ ናቸው። ከማር ጋር አለዚያም ከአንዳንድ የአልኮል መጠጦች ጋር ይወሰዳሉ። ይሁን እንጂ ሴትየዋ የተነገራት በአብዛኛው የሚሠራበትን ዲኮክሽን የተባለውን ዘዴ እንድትጠቀም ነው። ድብልቁን በሸክላ ድስት ውስጥ ለአንድ ሰዓት ያህል ታፈላዋለች ማለት ነው። ከዚያም በየጥቂት ሰዓቱ የተወሰነ መጠን ትጠጣለች። ሴትየዋ የታዘዘላትን መድኃኒት እንደገና ማግኘት ከፈለገች ወደ መደብሩ ተመልሳ መውሰድ ትችላለች።

አሁን ክዎክ ኪት ሐኪሙ ዘንድ የሚቀርብበት ተራ ደረሰ። ሐኪሙ የደም ግፊቱን አይለካም፣ የልብ ምቱንም አያዳምጥም። የበሽታውን ምልክቶች ግን ይጠይቀዋል። ጥሩ እንቅልፍ ይተኛል? የምግብ አለመፈጨት ችግር አለበት? የምግብ ፍላጎቱ፣ አንጀቱ፣ የሰውነቱ የሙቀት መጠንና የቆዳው ሁኔታና ቀለም እንዴት ነው? ሐኪሙ ዓይኑንና የምላሱን የተለያዩ ክፍሎች ቀለም በደንብ ይመለከታል። ከዚያም ሁለቱንም ክንዶቹን የተለያዩ ቦታዎች ላይ ጠበቅና ላላ እያደረገ በመያዝ የልብ ትርታውን ያዳምጣል። ይህ አሠራር የተለያዩ አባላካላትና የሰውነት ክፍሎች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይጠቁማል የሚል እምነት አለ። እንዲያውም ሐኪሙ የሸተተውን ለየት ያለ ጠረን ሁሉ ግምት ውስጥ ያስገባል! በሽታው ምን ሆኖ ተገኘ? መጠበቅ እንደሚቻለው ክዎክ ኪት ፍሉ ይዞታል። ዕረፍት ማድረግ እንዲሁም ብዙ ፈሳሽ መውሰድና የታዘዘለትን መድኃኒት እያፈላ መጠጣት ይኖርበታል። የታዘዘለት ከዕፅዋት የተቀመመ ሻይ የሚመርር ቢሆንም እንኳ ያሽለዋል። ሐኪሙ የትኞቹን ምግቦች ማስወገድ እንዳለበት የሚነግረው ከመሆኑም በላይ ክዎክ ኪት መድኃኒቱን ከወሰደ በኋላ አፉ ላይ ጥሩ ጣዕም እንዲኖረው ሊያደርግ የሚችል ተቀምሞ የተዘጋጀ ፕሪም በደግነት መንፈስ ተገፋፍቶ ያዝዝለታል።

ክዎክ ኪት የታዘዘለትን በፓኬት የተዘጋጀ ከዕፅዋት የተቀመመ መድኃኒት ይዞ ይሄዳል። ሐኪሙ ጋር ቀርቦ ምርመራ ለማድረግና የታዘዘለትን መድኃኒት ለመግዛት ያወጣው ወጪ ከ20 ዶላር ያነሰ ነው። ጥሩ ዋጋ ነው። መድኃኒቱ ተዓምራዊ ፈውስ ባያስገኝለትም እንኳ ክዎክ ኪት በጥቂት ቀናት ውስጥ ይሻለዋል። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ብዙ መውሰድ ቶሎ ያሽላል በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ የሚሠሩትን ስህተት ከመፈጸም መታቀብ አለበት። ከዕፅዋት የተቀመሙ አንዳንድ መድኃኒቶችን ከልክ በላይ በመውሰዳቸው ከባድ ችግሮች ስለገጠሟቸው ሰዎች መስማት ያልተለመደ ነገር አይደለም።

በአንዳንድ አገሮች ከዕፅዋት በሚቀመሙ መድኃኒቶችም ሆነ በቻይና ባሕላዊ ሕክምና ባለሙያዎች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችሉ መስፈርቶች እምብዛም የሉም። ይህም ከዕፅዋት የሚቀመሙ መድኃኒቶችን አስመስሎ ለመሥራትና አልፎ ተርፎም አደገኛ የዕፅዋት ድብልቆችን ፈዋሽ መድኃኒቶች አስመስሎ ለመሸጥ በር ከፍቷል። በመሆኑም ብዙዎቹ የእስያ ሕሙማን ወደ ባሕላዊ የቻይና ሐኪም የሚሄዱት ዘመዶቻቸውና የቅርብ ወዳጆቻቸው በሚሰጧቸው ጥቆማ ላይ ተመርኩዘው ነው።

እርግጥ ነው፣ ከዕፅዋት በሚቀመሙ መድኃኒቶችም ይሁን በምዕራባውያን መድኃኒቶች የሚሰጥ ማንኛውም ሕክምና ለሁሉም በሽታዎች ፈውስ ሊያስገኝ አይችልም። ያም ሆነ ይህ፣ የቻይናውያን መድኃኒት ቤትም ሆነ የባሕላዊ ሕክምና ባለሙያው በእስያ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ይቀጥላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ንቁ! የትኛውንም የሕክምና ዓይነት በመጥቀስ ይኼኛው የሕክምና ዓይነት ለጤና ችግሮች የተሻለ ነው የሚል ሐሳብ አያቀርብም። ክርስቲያኖች የሚከታተሉት የትኛውም ዓይነት ሕክምና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።

^ አን.8 ከዦ ሥርወ መንግሥት በፊት ገዥ ሆኖ ያስተዳድር እንደነበረ በአፈ ታሪክ የሚነገርለት ቢጫው ንጉሠ ነገሥት ከ2697 እስከ 2595 ከዘአበ እንደገዛ ይገመታል። ይሁን እንጂ ብዙ ምሁራን ከ1100 እስከ 250 ከዘአበ እንደቆየ የሚገመተው የዦ ሥርወ መንግሥት እስካከተመበት ጊዜ ድረስ ኔይ ጂንግ በጽሑፍ እንዳልሠፈረ ያምናሉ።

^ አን.9 “ዪን” የተሰኘው የቻይና ፊደል ቃል በቃል ሲተረጎም “ከለላ” ወይም “ጥላ” ማለት ሲሆን ጨለማን፣ ቅዝቃዜንና ሴትነትን ያመለክታል። “ያንግ” ደግሞ በአንጻሩ ብሩህና ሞቃት የሆኑ ነገሮችን እንዲሁም ወንድነትን ያመለክታል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶች በሚሸጡበት መደብር ውስጥ የደረቁ ዓሦችን (ሲ ሆርስ) ጨምሮ እንግዳ የሆኑ ነገሮች ሊገኙ ይችላሉ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የደረቁ ሥራሥሮች፣ ቅጠሎችና ቀንበጦች በጥንቃቄ ይመዘናሉ