በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያህል የቀጠንኩት ለምንድን ነው?

ይህን ያህል የቀጠንኩት ለምንድን ነው?

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .

ይህን ያህል የቀጠንኩት ለምንድን ነው?

ጀስቲን ቀጠን ያለና የተሟላ ጤንነት ያለው ወጣት ቢሆንም በቁመናው ፈጽሞ ደስተኛ አይደለም። “የተወሰነ ክብደት ለመጨመር እየጣርኩ ነው” ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል። ያሁኑ አመጋገቡ በቀን አምስት ጊዜ ሲሆን ይህም እስከ 4, 000 ካሎሪ ይደርሳል። ይሁን እንጂ የሚፈልገው በጡንቻ የዳበረ አካል እንዲኖረው ነው። ስለዚህም እንዲህ በማለት አክሎ ተናግሯል:- “እኔና አንድ የቅርብ ጓደኛዬ በጠዋት ተነስተን የሥራ ሰዓት ከመድረሱ በፊት ክብደት ለማንሳት ወደ ስፖርት አዳራሽ የምንሄድባቸው ቀናት አሉ።”

ቫኔሳም ቀጭን ከሚባሉት አንዷ ናት። ሆኖም በክብደቷ በኩል ምንም ቅር አይላትም። “ትንሽ ልጅ ሳለሁ ልጆች ይቀልዱብኝና ቀጮ እያሉ ይጠሩኝ ነበር” በማለት ታስታውሳለች። “ይሁን እንጂ አሁን ስለቅጥነቴ መጨነቅ ትቻለሁ። ተፈጥሮዬን በጸጋ ተቀብዬዋለሁ።”

‘ተፈጥሯችሁን በጸጋ ተቀበሉ።’ ይህ ጥሩ ምክር ይመስላል። ይሁን እንጂ በተግባር ለማዋል ይከብድህ ይሆናል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ወጣት እንደመሆንህ መጠን ‘በአፍላ ጉርምስና’ ላይ ትሆን ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 7:​36 NW ) በተለይ ፈጣን አካላዊ ለውጥ የሚታይበት ይህ ወቅት በጣም አስቸጋሪ ነው። በጉርምስና ወቅት የሰውነትህ ክፍሎች በተለያየ መጠን ያድጉ ይሆናል፤ እጅህ፣ እግርህና የፊት ገጽታህ ፈጽሞ የማይመጣጠን ሊመስል ይችላል። * ይህም እንድታፍርና እንደማትስብ ሆኖ እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል። ይሁን እንጂ ሁሉም ወጣቶች በተመሳሳይ ፍጥነት እድገት እንደማያደርጉ እሙን ነው። ስለዚህ አንዳንድ የእድሜ እኩዮቻችሁ ጡንቻማ አካል ወይም ሴቶቹ አንስታይ የሰውነት ቅርጽ ሲያዳብሩ እናንተ ግን በአንጻራዊ ሁኔታ ቀጭን መስላችሁ ትታዩ ይሆናል።

ከአሁን ቀደም በጣም ወፍራም እንደሆኑ ስለሚሰማቸው ወጣቶች ብዙ ቢባልም በጣም ቀጭን እንደሆኑ የሚሰማቸው ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ችላ ይባላሉ። ይህ በተለይ ቅጥነት የውበት ምልክት ተደርጎ በማይታይባቸው በተወሰኑ ጎሳዎችና በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የሚታይ ሊሆን ይችላል። እንደዚህ ባሉት ቦታዎች አንዲት ቀጭን ልጅ “ከሲታ” በመሆኗ ብቻ ኃይለኛ ነቀፋ ሊደርስባት ይችላል።

ስለ ወንዶችስ ምን ለማለት ይቻላል? እንደ ተመራማሪዋ ሱዛን ቦርዶ አባባል “ከ1980ዎቹ ቀደም ብሎ ባሉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ሰዎች ስለራሳቸው ቁመና ያላቸውን አስተያየት በተመለከተ የተካሄዱት ጥናቶች እንደጠቆሙት “ሴቶች በመስተዋት ሲመለከቱ የሚታያቸው ጉድለታቸው ብቻ ነው።” ወንዶችስ? ቦርዶ እንዲህ በማለት ይቀጥላሉ:- “ወንዶች ራሳቸውን በመስተዋት ሲመለከቱ የሚታያቸው ምንም የማያስከፋ አሊያም ከጠበቁት የተሻለ ቁመና ነው።” ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሁኔታው እየተለወጠ መጥቷል። ቦርዶ የፊት ቀዶ ህክምና ከሚደረግላቸው ታካሚዎች መካከል ሩብ የሚሆኑት ወንዶች መሆናቸውን ካስተዋሉ በኋላ ወጣት ወንዶች ስለ አካል ብቃታቸው ይበልጥ መጨነቅ ለመጀመራቸው ምክንያቱ በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎቹም ምዕራባውያን አገሮች በሚሠሩት የካናቴራና የውስጥ ሱሪ ማስታወቂያዎች ላይ ያሉት ወንዶች “ፍጹም” ተክለ ሰውነት እንደሆነ ጠቅሰዋል። ይህ በአሥራዎቹ ዕድሜ በሚገኙት ወንዶች ላይ ተጽእኖ እንዳሳደረ የታወቀ ነው። የወንድ ሞዴሎችን የመሰለ ጡንቻማ የሰውነት ቅርጽ ከሌላቸው ብቁ እንዳልሆኑ ሊሰማቸው ይችላል።

ስለዚህ ቀጭን ከሆናችሁ ‘ችግሬ ምን ይሆን?’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ደስ የሚለው ግን ይህ በአብዛኛው ከችግር ጋር የተያያዘ አለመሆኑ ነው።

ቀጭን የሆናችሁበት ምክንያት

ቀጭን መሆን ለብዙ ወጣቶች በጣም የተለመደ ነገር ነው። ብዙውን ጊዜ ይህ ሁኔታ ጉርምስናንና ኮረዳነትን ተከትሎ የሚመጣው የእድገት እመርታና በሰውነት ውስጥ የሚካሄደው ፈጣን ገንባፍራሽ ቅንባሮ (metabolism) የሚያሳድረው ተጽእኖ ውጤት ነው። አብዛኛውን ጊዜ እያደጋችሁ ስትሄዱ ሰውነታችሁ የሚያደርገው ገንባፍራሽ ቅንባሮ እየቀነሰ ይሄዳል። ይሁን እንጂ ጤናማ አመጋገብ ኖሯችሁም በጣም ቀጭን ከሆናችሁ የስኳር በሽታን የመሳሰሉ የሰውነት ክብደት የሚቀንሱ የጤና ችግሮች ሊኖርባችሁ ስለሚችል ሐኪም ማማከሩ የተሻለ ሊሆን ይችላል።

ስቴቨን ሌቭንክሮን የተባሉ ታዋቂ የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ባለሞያ ለንቁ! መጽሔት የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥተዋል:- “አኖሬክሲያ አለባት ተብላ ወደ እኔ የተላከች አንዲት በጣም ከሲታ ልጅ አስታውሳለሁ። በእርግጥም ደግሞ የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ችግር ያለባት ትመስል ነበር። ሆኖም ወዲያውኑ ችግሯ የሆድ እቃ እንጂ ሥነ ልቦናዊ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። የቤተሰቡ ሐኪም ክሮንዝ የነበረባትን ከባድ የአንጀት ችግር አላወቀላትም። እንዲህ ያለው ስህተት በዚህች ልጅ ላይ ሞት ሊያስከትል ይችል ነበር።” የስኳር በሽታ ወይም ሌላ ማንኛውም ዓይነት ክብደት የሚቀንስ በሽታ ካለባችሁ ሐኪማችሁ የሚሰጣችሁን ምክር በጥንቃቄ መከተላችሁ ጥበብ ነው።

እርግጥ፣ አንዳንድ ጊዜ ቅጥነት የስሜት ውጥረት ምልክት ሊሆን ይችላል። ዶክተር ሌቭንክሮን አናቶሚ ኦቭ አኖሬክሲያ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በርከት ያሉ “ኢንሱሊን በየጊዜው መውሰድ ያለባቸው የስኳር ሕመምተኞች አሁንም አሁንም ምግብ አምጣ ከሚለው አንስቶ እስከ ቡሊሚያና አኖሬክሲያ ድረስ የተለያዩ የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ችግሮች አሉባቸው” የሚለውን የአንዳንድ ተመራማሪዎች እምነት አስፍረዋል። አንድ ብቁ ሐኪም ይህን የመሰለ የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ችግር መኖር አለመኖሩን ሊወስን ይችላል። *

ተግባራዊ ሐሳቦች

ሐኪም አማክራችሁ ከቅጥነት በስተቀር ሌላ የጤና ችግር እንደሌለባችሁ ተረዳችሁ እንበል። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? መጽሐፍ ቅዱስ በኢዮብ 8:​11 ላይ “በውኑ ደንገል ረግረግ በሌለበት መሬት ይበቅላልን? ወይስ ቄጠማ ውኃ በሌለበት ቦታ ይለመልማልን?” በማለት ይናገራል። አንድ ተክል ተስማሚ የአየር ጠባይና ምግብ ሲያገኝ በጥሩ ሁኔታ እንደሚያድግ ሁሉ እናንተም ጤነኞች ሆናችሁ ወደ ሙሉ ሰውነት ለማደግ የተመጣጠነ ምግብ ያስፈልጋችኋል። ፍላጎታችሁ ክብደት መጨመርም ሆነ መቀነስ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው።

ይሁን እንጂ ቶሎ ክብደት እጨምራለሁ ብላችሁ በማሰብ ብዙ ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች ከመመገብ ተቆጠቡ። የሥነ ምግብ ባለሙያ የሆኑት ሱዛን ክላይነር ሰውነታቸውን በተለይም ጡንቻዎቻቸውን ቅርጽ ለማስያዝና ለማወፈር ሲሉ የሰውነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች የሚወስዱትን ምግብ አስመልክተው ጥናት ሲያካሂዱ እንዲህ ያሉት ሰዎች በቀን እስከ 6,000 ካሎሪ የሚደርስ ምግብ እንደሚወስዱ ተገንዝበዋል! ሆኖም እንደ ክላይነር አባባል ከሆነ “አሳሳቢ የሆነው የዚህ ጥናት ውጤት እነዚህ ሰዎች በየዕለቱ በአማካይ ከ200 ግራም የሚበልጥ ቅባት መመገባቸው ነው። ይህም በ250 ግራም ቅቤ ውስጥ ከሚገኘው ቅባት ጋር የሚመጣጠን ነው! ይህ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙዎቹን ለበሽታ ሊዳርግ የሚችል መጠን ነው። ለረዥም ጊዜ ይህን የሚያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ቅባት የመመገብ ልማድ የልብ በሽታ ያስከትላል።”

የዩናይትድ ስቴትስ እርሻ መምሪያ (ዩ ኤስ ዲ ኤ) እንዳለው ከሆነ የአንድ የተመጣጠነ ምግብ መሠረት እንደ ዳቦ፣ ጥራጥሬ፣ ሩዝና ፓስታ በመሳሰሉት ኃይል ሰጪ ምግቦች የተገነባ ነው። ሁለተኛውን ደረጃ የያዙት ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬዎች ናቸው። ዩ ኤስ ዲ ኤ መጠነኛ የሥጋና የወተት ተዋጽኦዎች ብቻ እንዲወሰዱ ሐሳብ ያቀርባል።

በየዕለቱ ምን ምን ነገሮችን እንደምትመገቡና የተመገባችሁት ምግብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ማስታወሻ መያዝ ትችሉ ይሆናል። ለአንድ ሳምንት ያህል በኪሳችሁ ውስጥ ማስታወሻ ያዙና የበላችሁትን እያንዳንዱን የምግብ ዓይነትና መቼ እንደበላችሁ መዝግቡ። በተለይ ሁልጊዜ ጥድፊያ ላይ ከሆናችሁ እንበላለን ብላችሁ የምታስቡትን ያህል እንደማትበሉ ስትገነዘቡ ትገረሙ ይሆናል። በአሥራዎቹ እድሜ ውስጥ የምትገኙና እንደልባችሁ የምትሯሯጡ ወጣቶች እንደመሆናችሁ መጠን በቀን ውስጥ በቀላሉ 3, 000 ወይም ከዚያም በላይ ካሎሪ ልታቃጥሉ ትችላላችሁ! በተጨማሪም ሳንድዊች እና ፒትዛ የመሳሰሉ ፈጣን ምግቦችን በብዛት ስለምትመገቡና በቂ መጠን ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬዎች ስለማትመገቡ አመጋገባችሁ የሚገባውን ያህል የተመጣጠነ እንዳልሆነ ትገነዘቡ ይሆናል።

ውድ የሆኑ ተጨማሪ ምግቦችን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? አስፈላጊ ላይሆኑ ይችላሉ። ብዙ ባለሙያዎች ሰውነታችሁ የሚያስፈልጉትን ንጥረ ነገሮች በሙሉ ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦች በመመገብ ማግኘት እንደምትችሉ ያምናሉ። ከምንም በላይ ግን ኃይል ሰጪ መድኃኒት የመሳሰሉትን ጊዜያዊ ጥቅም ብቻ የሚያስገኙ ነገሮች አትጠቀሙ። ኃይል ሰጪ መድኃኒቶችን አላግባብ የመጠቀም ልማድ በአሥራዎቹ እድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ችግር ብቻ አለመሆኑ የሚያሳዝን ነው። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “አንዳንድ ተመራማሪዎች በተወሰነ መጠን የአኖሬክሲያ ተቃራኒ ነው የሚሉትና እየተስፋፋ የመጣው የልጃገረዶች [የኃይል ሰጪ መድኃኒቶች] ተጠቃሚነት በወጣት ወንዶች ዘንድ ከ1980ዎቹ አንስቶ ከነበረው ልማድ ጋር የሚተካከል ሆኗል” በማለት ዘግቧል። በዮናይትድ ስቴትስ 175, 000 የሚያህል በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በአሥራዎቹ እድሜ የሚገኙ ሴቶች ኃይል ሰጪ መድኃኒቶችን እንደሚወስዱ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። እነዚህ መድኃኒቶች የማይፈለጉ የፊት ላይ ፀጉሮችን፣ የወር አበባ መዛባትን እንዲሁም በሴቶች ላይ የጡት ካንሰርን፣ በወንዶች ላይ ፕሮስቴት ካንሰርን፣ እንዲሁም በወንዶችና በሴቶች ላይ የደም ቅዳዎች ጥበትንና የጉበት ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች አሳዛኝ የሆኑ ውጤቶች ያስከትላሉ። ኃይል ሰጪ መድኃኒቶች ያለ ሐኪም ትእዛዝና ቁጥጥር ፈጽሞ ሊወሰዱ አይገባም።

ልከኛና ምክንያታዊ መሆን

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከአምላካችን ጋር ልካችንን አውቀን እንድንሄድ’ ይነግረናል። (ሚክያስ 6:​8 NW ) ልከኝነት ያለብንን የአቅም ገደብ መገንዘብን ይጨምራል። ልከኝነት ቁመናችሁን በተመለከተ እውነታውን እንድትቀበሉ ይረዳችኋል። ማራኪ መስሎ ለመታየት መፈለግ ምንም ስህተት የለበትም። ይሁን እንጂ ከመጠን በላይ ስለቁመናችሁ መጨነቅ ምናልባት የፋሽን አውጪዎችንና የሸቀጣ ሸቀጥ አምራቾችን ካልሆነ በቀር ማንንም አይጠቅምም። የትኛውም ወንድ ትክክለኛው ጂን እስከሌለው ድረስ ጥሩ አመጋገብ ስላለው ወይም ጥሩ ልምምድ ስላደረገ ብቻ ታዋቂ የሚያደርገውን የሰውነት ቅርጽ ማዳበር እንደማይችል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለሙያዎች ይስማማሉ። ሴት ከሆንሽ ደግሞ ምንም ያህል ብትበይ ሰውነትሽ ላይወፍር ይችላል።

ደስ የሚለው ግን ለልብሶቻችሁ ትንሽ ትኩረት መስጠታችሁ ብቻ እንደ አካላዊ ጉድለት አድርጋችሁ የምታዩትን ነገር ለመሸፈን ብዙ ሊረዳችሁ ይችላል። እነዚህን ጉድለቶቻችሁን የሚያጎሉ ልብሶች አትልበሱ። ጠቆር ያለ ቀለም ያላቸው ልብሶች ቀጭን ሰዎች ይበልጥ ቀጭን መስለው እንዲታዩ ስለሚያደርጉ ነጣ ያሉ ልብሶች መልበስ ጥሩ እንደሆነ አንዳንዶች ሐሳብ ይሰጣሉ።

በተጨማሪም ከቁመናችሁ ይበልጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር ስብዕናችሁ እንደሆነ አስታውሱ። በሌሎች ፊት ማራኪ ሆናችሁ እንድትታዩ በማድረግ ረገድ ከፈረጠመ ጡንቻ ወይም ለተወሰነ አለባበስ ከሚሆን የሰውነት ቅርጽ ይልቅ የሚያስደስት ፈገግታና የደግነት ባሕርይ ብዙ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ጓደኞቻችሁ በሰውነት ቅርጻችሁ ያለማቋረጥ የሚያንቋሽሹዋችሁ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ “የተሰወረ የልብ ሰው” ብሎ ለሚጠራው ውስጣዊ ማንነታችሁ ከፍተኛ ግምት የሚሰጡ ጓደኞች ለማግኘት ጣሩ። (1 ጴጥሮስ 3:​4) ደግሞም ‘ሰው ፊትን እግዚአብሔር ግን ልብን’ እንደሚያይ ፈጽሞ አትርሱ።​—⁠1 ሳሙኤል 16:​7

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . አካላዊ እድገቴ ጤናማ ነውን?” በሚል ርዕስ በመስከረም 22, 1993 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ላይ የወጣውን ተመልከት።

^ አን.12ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . ስለ ውፍረት ይህን ያህል የምጨነቀው ለምንድን ነው?” የሚለውን የሐምሌ 1999 ንቁ! እና “ስለ ውፍረት የሚሰማኝን ጭንቀት እንዴት ማሸነፍ እችላለሁ?” የሚለውን የነሐሴ 1999 ንቁ! መጽሔት ተመልከት።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ወጣቶች ቀጭን በመሆናቸው ራሳቸውን ይወቅሳሉ