በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፖላንድ ውስጥ በእምነት ላይ የደረሰ ፈተና

ፖላንድ ውስጥ በእምነት ላይ የደረሰ ፈተና

ፖላንድ ውስጥ በእምነት ላይ የደረሰ ፈተና

ያን ፈረንትስ እንደተናገረው

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፋፋም ገና ልጅ ነበርኩ። የይሖዋ ምሥክር የነበረው አጎቴ በደንብ ትዝ ይለኛል። ሁልጊዜ እቤት እየመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ያነብልን ነበር። ወላጆቼ ፍላጎት አልነበራቸውም፤ ሆኖም እኔ፣ ወንድሜ ዩዜፍ እና እህቴ ያኒና ደስ ይለን ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሁላችንም ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችንን ለማሳየት ተጠመቅን። ስጠመቅ ገና የ14 ዓመት ልጅ ነበርኩ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሕይወታችን ላይ ያሳደረውን በጎ ተጽዕኖ በመመልከት ወላጆቻችንም ማዳመጥ ጀመሩ። አባቴ መጽሐፍ ቅዱስ የጣዖት አምልኮን እንደሚያወግዝ ሲረዳ “የአምላክ ቃል እንደዚህ የሚል ከሆነ ቀሳውስቱ ደንቆሮዎች አድርገው አስቀርተውናል። የኔ ልጅ ሁሉንም ሥዕሎች ከግድግዳው ላይ አውርድና ወዲያ ጣላቸው!” አለኝ። ወላጆቼ ከሁለት ዓመት በኋላ ተጠመቁ። እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል።

ያሳለፍናቸው መከራዎች

ከጦርነቱ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ችግር ደርሶባቸዋል። ለምሳሌ ያህል የደህንነት ሠራተኞች ሎድዝ የሚገኘውን ቢሮ በድንገት ይፈትሹና እዚያ ሲሠሩ የተገኙትን ያስሩ ነበር። በምሥራቅ ፖላንድ የሚንቀሳቀሱት ብሔራዊ የጦር ኃይል በመባል የሚጠሩት የደፈጣ ተዋጊዎች በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ግፊት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የጭካኔ ድርጊቶች ይፈጽሙ ነበር። *

በተጨማሪም በዚህ ጊዜ የኮሚኒስት ባለሥልጣናት ትልልቅ ስብሰባዎችን እንድናደርግ ሰጥተውን የነበረውን ፈቃድ እንደገና የሰረዙብን ሲሆን በመካሄድ ላይ የነበሩትን ትልልቅ ስብሰባዎች ለማስተጓጎል ሳይቀር ሙከራ አድርገዋል። ሆኖም ተቃውሞው እየተባባሰ መምጣቱ የአምላክን መንግሥት ለመስበክ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ አጠናከረው። በ1949 በፖላንድ ከ14, 000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች እንደነበሩ ሪፖርት ተደርጓል።

ብዙም ሳይቆይ አቅኚ (የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚታወቁበት ስም ነው) ሆንኩ። የመጀመሪያ ምድቤ ከትውልድ ቦታዬ 500 ኪሎ ሜትር ይርቃል። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ወላጆቼ ከሚኖሩበት ብዙም በማይርቅ አካባቢ ይኸውም በሉብሊን ምሥራቃዊ ክልል በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ተሾምኩ።

እስራትና ስደት

የኮሚኒስት ባለሥልጣናት ሰኔ 1950 ይዘው አሰሩኝና ለዩናይትድ ስቴትስ ሰልለሃል በሚል ክስ ምድር ቤት በሚገኝ ቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ አሰሩኝ። ማታ ማታ ለምርመራ ወደ አንድ መርማሪ መኮንን እወሰዳለሁ። “የእናንተ ሃይማኖት ኑፋቄና የመንግሥታችን ጠላት ነው። ቢሯችሁ ለአሜሪካ የስለላ ድርጅት ይሠራል። ማስረጃ ማቅረብ እንችላለን! ወንድሞችህ በየክፍላተ ሃገሩ ተዘዋውረው ስለ ወታደራዊ ተቋሞችና ስለ ፋብሪካዎች መረጃ መሰብሰባቸውን አምነዋል” አለኝ።

እነዚህ ውንጀላዎች ፈጽሞ ሐሰት መሆናቸው የታወቀ ነው። የሆነ ሆኖ መኮንኑ “አሳፋሪ” ብሎ ከጠራው ድርጅት በገዛ ፈቃዴ መልቀቄን ለማሳየት እንድፈርም መከረኝ። እንድፈርም ለማድረግ በተደጋጋሚ ሞከረ። ሌላው ቀርቶ የማውቃቸውን የይሖዋ ምሥክሮች ስምና አድራሻ እንድሰጠው እንዲሁም ጽሑፎቻችን የሚሰራጩበትን ቦታ እንድጠቁመው ለማድረግ ሞከረ። ጥረቱ ሁሉ አልተሳካለትም።

ከዚያ በኋላ ፖሊሶች ራሴን እስክስት ድረስ በዱላ ደበደቡኝ። ከዚያም እንድነቃ ውኃ ከቸለሱብኝ በኋላ ምርመራው ቀጠለ። በሚቀጥለው ምሽት ውስጥ እግሬን ክፉኛ ገረፉኝ። እንድጸና ብርታቱን እንዲሰጠኝ ድምፄን ከፍ አድርጌ አምላክን ለመንኩት። ብርታት እንደሰጠኝ ተሰማኝ። ማታ ማታ የሚያደርጉብኝ ምርመራ ለአንድ ዓመት ያህል ቀጠለ።

ሚያዝያ 1951 ከእስር ተለቀቅኩ፤ ሆኖም ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ገና አልተፈቱም ነበር። ኃላፊነት ወዳለው ምሥክር ሄጄ አዲስ ምድብ እንዲሰጠኝ ጠየቅኩ። “እንደገና እያዛለሁ ብለህ አትፈራም?” ሲል ጠየቀኝ። “እንዲያውም እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ለመሥራት ከበፊቱ የበለጠ ቆርጫለሁ” ብዬ መለስኩለት። በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት መሥራቴን ቀጠልኩ፤ ከዚያም ጽሑፎቻችንን በፖላንድ የማተምና የማሰራጨቱን ሥራ እንዳደራጅ ተጋበዝኩ።

በወቅቱ መጠበቂያ ግንብ ለማባዛት ኋላቀር የማባዣ ማሽንና ስቴንስል እንጠቀም ነበር። ኅትመታችን ጥራት አልነበረውም፤ ወረቀት እንደልብ ስለማይገኝ በውድ ዋጋ እንገዛ ነበር። የማባዛቱን ሥራ የምናከናውነው በከብት መኖ መጋዘን፣ በምድር ቤትና እነዚህን በመሳሰሉ ሰዋራ ስፍራዎች ነበር። እንደዚያ ሲያደርጉ የተገኙ ሰዎች በእስራት ይቀጡ ነበር።

በተለይ ስንጠቀምበት የነበረውን አንዱን ጉድጓድ አስታውሰዋለሁ። ጉድጓዱ ከ10 ሜትር ጥልቀት በኋላ መጽሔቶችን ወደምናባዛበት አነስተኛ ክፍል የሚያደርስ መተላለፊያ ነበረው። ወደዚያ ለመድረስ በገመድ መውረድ ነበረብን። አንድ ቀን በገመድ በታሰረ ትልቅ የእንጨት ባልዲ ውስጥ ሆኜ ወደታች እየወረድኩ ሳለ ድንገት ገመዱ ተበጠሰ። ጉድጓዱ ውስጥ ወድቄ እግሬ ላይ ስብራት ደረሰብኝ። ሆስፒታል ተኝቼ ከተሻለኝ በኋላ ተመልሼ በማባዣ ማሽኑ ላይ መሥራት ቀጠልኩ።

በዚህ ጊዜ ዳኑታ ከምትባል አቅኚ ሆና በቅንዓት ከምታገለግል እህት ጋር ተዋወቅኩ። በ1956 ተጋባንና ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በማዕከላዊ ፖላንድ አገለገልን። በ1960 ሁለት ልጆች ያፈራን ሲሆን ዳኑታ ልጆቹን ለማሳደግ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድታቋርጥ ወሰንን። ብዙም ሳይቆይ እንደገና ተያዝኩና የአይጥ መንጋ ባለበት ክፍል ውስጥ ታሰርኩ። ከሰባት ወራት በኋላ የሁለት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ።

መታሰርና ከእስር መፈታት

በቢድጎሽ ወኅኒ ቤት ከ300 የሚበልጡ እስረኞች የነበሩ ሲሆን የመንግሥቱን መልእክት ልበ ቅን ለሆኑ ሰዎች ማካፈል እንድችል ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ፀጉር አስተካካይ ሆኜ መሥራት እንደምችል ለወኅኒ ቤቱ አዛዥ ሐሳብ አቀረብኩለት። የሚገርመው በሐሳቡ ተስማማ። ከዚያ ወዲያ የእስረኞችን ፀጉር መላጨት፣ ማስተካከልና ጥሩ ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች መመሥከር ጀመርኩ።

በፀጉር አስተካካይነት ከእኔ ጋር የሚሠራ አንድ እስረኛ ለውይይታችን ጥሩ ምላሽ ሰጠ። እንዲያውም ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማራቸውን ለሌሎች ሰዎች ማካፈል ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ የወኅኒ ቤቱ አዛዥ እሱ እንዳለው “በካይ ፕሮፓጋንዳ” ማሰራጨታችንን እንድናቆም አዘዘን። የሥራ ባልደረባዬ በአቋሙ ጸና። “ዱሮ እሰርቅ ነበር፤ አሁን ግን አቁሜያለሁ። በአንድ ወቅት የኒኮቲን ሱሰኛ ነበርኩ፤ አሁን ማጨስ አቁሜያለሁ። የሕይወት ትርጉሙ ስለገባኝ የይሖዋ ምሥክር መሆን እፈልጋለሁ” በማለት አስረዳው።

ከእስር ቤት ስፈታ “ዳቦ መጋገሪያ ቤት” ብለን የምንጠራውን ምስጢራዊ የኅትመት ሥራ እንድቆጣጠር ወደ ፖዝናን ተላክሁ። በ1950ዎቹ ማገባደጃ ላይ የኅትመት ሥራችን በእጅጉ ተሻሻለ። ለቴክኖሎጂያችን አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነውን በፎቶግራፍ ጥበብ አማካኝነት የገጾቹን ስፋት ማሳነስ የሚቻልበትን ዘዴ የተማርን ሲሆን በሮታፕሪንት የማተሚያ ማሽን ላይ መሥራት ለመድን። በ1960 መጻሕፍትን ማተምና መጠረዝም ጀምረን ነበር።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አንድ ጎረቤታችን ጠቆመብንና እንደገና ተያዝኩ። በ1962 ከተፈታሁ በኋላ ከሌሎች ጋር ሆኜ በሽቼትሲን እንዳገለግል ተመደብኩ። ሆኖም ለመሄድ ከመነሳታችን በፊት ምድባችን ኬልትሲ ስለሆነ ወደዚያ እንድንሄድ የሚገልጽ መልእክት ደረሰን። እኛ ይህ መመሪያ ከታማኝ ክርስቲያን ወንድሞች የመጣ መስሎን ነበር። ሆኖም እዚያ ስንደርስ ተያዝንና እንደገና አንድ ዓመት ከስድስት ወር ተፈረደብኝ። በውስጣችን የነበሩ አስመሳይ ክርስቲያኖች አሳልፈው ሰጡን። ከጊዜ በኋላ ይህንን ያደረጉት እነማን እንደሆኑ ተደርሶባቸው ከቦታቸው ተነስተዋል።

በመጨረሻ ከእስር ቤት ስፈታ በመላው ፖላንድ የሚደረገውን የኅትመት ሥራ በኃላፊነት የመከታተል መብት አገኘሁ። በ1974 ለአሥር ዓመታት ያህል የቆቅ ኑሮ ከኖርኩ በኋላ በኦፖል አድነው ያዙኝ። ወዲያው ዞብዝሂ ወደሚገኝ የወኅኒ ቤት ላኩኝ። የወኅኒ ቤቱ አዛዥ “ጵጵስናህ አክትሟል። ፕሮፓጋንዳ መንዛትህን የማታቆም ከሆነ ወኅኒ ትወርዳታለህ” አለኝ።

በወኅኒ ቤት መስበክ

የማከናውነው አገልግሎት እንዳላከተመ የተረጋገጠ ነው። እንዲያውም ሁለት እስረኞችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመርኩ። ከጊዜ በኋላ እድገት አድርገው እዚያው እስር ቤቱ ውስጥ ባለ አንድ ትልቅ የመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ አጠመቅኋቸው።

ሌሎች እስረኞችም ለስብከት ሥራችን በጎ ምላሽ ስለሰጡ ሚያዝያ 1977 የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር አንድ ላይ ተሰበሰብን። (ሉቃስ 22:​19) ከሁለት ወር በኋላ ሰኔ 1977 የተለቀቅኩ ሲሆን ከዚያ በኋላ አልታሰርኩም።

በዚህ ጊዜ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ለሥራችን የነበራቸው አመለካከት በመለሳለስ ላይ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባላት ጉብኝት ማድረጋቸው ለዚህ እንደረዳ ምንም ጥርጥር የለውም። ከእነዚህ መካከል ሦስቱ በ1977 በተለያዩ ከተማዎች ከበላይ ተመልካቾች፣ ከአቅኚዎችና ለረጅም ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑት ጋር ስብሰባ አድርገዋል። በቀጣዩ ዓመት ሁለቱ የሃይማኖት ጉዳይ ከሚመለከተው ቢሮ ጋር ውይይት አደረጉ። ይሁን እንጂ በሥራችን ላይ ተጥሎ የቆየው እገዳ ከ1989 በፊት አልተነሳም። በአሁኑ ጊዜ በፖላንድ ወደ 124, 000 የሚጠጉ ምሥክሮች ይገኛሉ።

ዳኑታ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጤና በማጣቷ አብራኝ መጓዝ አልቻለችም። ሆኖም እኔን የምታበረታታኝ ሲሆን ጉባኤዎችን በመጎብኘቱ ሥራ እንድቀጥል ትፈልጋለች። በእስር ቤት በቆየሁባቸው ጊዜያት ድጋፏ ስላልተለየኝ ዕድሜ ልኬን ሳመሰግናት እኖራለሁ።

ከ50 ዓመት በፊት ይሖዋ አምላክን ለማገልገል ያደረግኩት ውሳኔ በእርግጥም ትክክል ነበር። በሙሉ ልብ እሱን በማገልገል ታላቅ ደስታ አግኝቻለሁ። እኔና ባለቤቴ በኢሳይያስ 40:​29 ላይ የሚገኙት “ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፣ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል” የሚሉት ቃላት እውነት መሆናቸውን ተመልክተናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 የ1994 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ገጽ 213-22 ላይ ያለውን ተመልከት።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ጽሑፎችን ለማተም ሚሞግራፍ ማሽን እንጠቀም የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ሮታፕሪንት አገኘን

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

እኔና ባለቤቴ ዳኑታ