በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆች የሚወደዱ እና የሚፈለጉ መሆናቸው እንዲሰማቸው ማድረግ ይገባል

ልጆች የሚወደዱ እና የሚፈለጉ መሆናቸው እንዲሰማቸው ማድረግ ይገባል

ልጆች የሚወደዱ እና የሚፈለጉ መሆናቸው እንዲሰማቸው ማድረግ ይገባል

“ልጅ ትንሽ ፍቅር ብትሰጠው የእጥፍ እጥፍ አድርጎ ይመልስልሃል።” ይህን የጻፉት የ19ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ ደራሲና ሃያሲ የነበሩት ጆን ረስኪን ናቸው። አብዛኞቹ ወላጆች በአጸፋው ከሚገኘው ፍቅርም የበለጠ በልጆቹ ላይ ለሚያስከትለው በጎ ተጽዕኖ ሲባል ልጆችን መውደድ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስገኝ ይስማማሉ።

ለምሳሌ ላቭ ኤንድ ኢትስ ፕሌስ ኢን ኔቸር (ፍቅርና ፍቅር በተፈጥሮ ውስጥ ያለው ቦታ) የተባለው መጽሐፍ ልጆች ፍቅር ካላገኙ “ይበልጥ ለሞት ይጋለጣሉ” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። ዕውቁ የብሪታንያ ተወላጅ አንትሮፖሎጂስት አሽሊ ሞንታጉ “ፍቅር ሳያገኝ ያደገ ልጅ ፍቅር አግኝቶ ካደገው ልጅ በባዮኬሚካላዊ፣ በፊዚዮሎጂያዊና በሳይኮሎጂያዊ ጥንቅሩ የተለየ ነው። ፍቅር ያላገኘው ልጅ በአስተዳደጉ ሳይቀር ይለያል” እስከ ማለት ደርሰዋል።

ቶሮንቶ ስታር ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ የደረሰን አንድ ጥናት በመጥቀስ ዘግቧል። “ብዙ ጊዜ ሳይታቀፉ፣ ሳይደባበሱና ሳይተሻሹ ያደጉ ልጆች . . . ከመደበኛው ከፍ ያለ የውጥረት ሆርሞን ይገኝባቸዋል” ብሏል። በእርግጥም በሕፃንነት ወቅት አካላዊ እንክብካቤ ሳያገኙ መቅረት “በመማርና በማስታወስ ችሎታ ላይ ዘላቂ የሆነ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።”

እነዚህ ግኝቶች ወላጆች ከልጆቻቸው አጠገብ መሆናቸው አስፈላጊ መሆኑን ያጎላሉ። እንዲህ ካልሆነ እንዴት በወላጅና በልጅ መካከል ጠንካራ ትስስር ሊፈጠር ይችላል? ይሁን እንጂ በበለጸጉ የዓለም ክፍሎች ሳይቀር በአሁኑ ጊዜ የሚታየው አዝማሚያ ልጅን ከወላጁ አግልሎ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ብቻ ማቅረብ መሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል። ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ይላካሉ፣ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት ይላካሉ፣ ወደ ሥራ ይላካሉ፣ ወደ ዕረፍት ማሳለፊያ ካምፖች ይላካሉ፣ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸው ገንዘብ ተሰጥቷቸው ወደ መዝናኛ ሥፍራዎች እንዲሄዱ ይደረጋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጉያ ተነጥለው በጥላቻ በሚመለከቷቸው ትላልቅ ሰዎች ሲከበቡ ውስጥ ውስጡን የተተዉ፣ የማይፈለጉና የማይወደዱ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። በበርሊን ከተማ ወደ 3, 000 የሚጠጉ ሕፃናት ጎዳና ተዳዳሪ ሊሆኑ የቻሉበት አንዱ ምክንያት ብዙዎቹ ልጆች እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ስለሚሰማቸው ሊሆን ይችላል። “እኔን የሚፈልግ ማንም ሰው የለም” ሲል የተናገረው ሚካ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆነናል። በተመሳሳይም አንድ የዘጠኝ ዓመት ጀርመናዊ ልጅ “በውሻችን እቀናለሁ” ሲል አማሯል።

በሕፃናት ላይ የሚፈጸም በደል ዓይነቱ የተለያየ ነው

የሕፃናት ችላ መባል መጽሐፍ ቅዱስ “የተፈጥሮ ፍቅር [NW ]” የሚለው ባሕርይ እየጠፋ መምጣቱን የሚያሳይ የበደል ዓይነት ነው። (ሮሜ 1:​31፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​3) ይበልጥ መጥፎ ወደሆኑ የበደል ዓይነቶችም ሊመራ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ዓለም አቀፍ የሕፃናት ዓመት ተብሎ ከተሰየመው ከ1979 ወዲህ በሕፃናት ላይ ለሚፈጸመው አካላዊ ግፍና ወሲባዊ በደል የበለጠ ትኩረት ተሰጥቷል። እርግጥ ትክክለኛውን አሕዛዊ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ መጠኑ ከአገር ወደ አገር ይለያያል። ይሁን እንጂ ወሲባዊ በደል የሚፈጸምባቸው ሕፃናት ወደ አዋቂነት እድሜ የሚሸጋገሩት በቀላሉ የማይሽር ቁስል ይዘው ነው።

በሕፃናት ላይ የሚፈጸመው በደል ዓይነቱ ምንም ይሁን ምን የሚያስተላልፍላቸው መልእክት የማይወደዱና የማይፈለጉ መሆናቸውን ነው። ችግሩ እየጨመረ ሄዷል። ዲ ቬልት የተባለው የጀርመን ጋዜጣ እንደሚለው “ማኅበራዊ ስንኩልነት ይዘው የሚያድጉ ልጆች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል።” በመቀጠል “ሕፃናት ከወላጆቻቸው እቅፍ የሚያገኙትን ሙቀት አጥተዋል። [የሐምቡርግ የሕፃናት አመራር ማዕከል ዲሬክተር የሆኑት ገርት ሮማይክ] እንደሚሉት በሕፃናትና በወላጆች መካከል ያለው ስሜታዊ ትስስር በጣም ደካማ ወይም ከመጀመሪያም ፈጽሞ የሌለ እየሆነ መጥቷል። እንደነዚህ ያሉት ሕፃናት ፈጽመው የተጣሉ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ከስጋት ነፃ የሆነ ሕይወት የማግኘት ፍላጎታቸው ሳይሟላ ይቀራል።”

ተፈላጊ የመሆንና የመወደድ መብታቸውን የተነፈጉ ሕፃናት የሚሰማቸውን ምሬትና ብስጭት ችላ ባሏቸው ላይ ወይም በጠቅላላው ማኅበረሰብ ላይ ይወጣሉ። አንድ የካናዳ ግብረ ኃይል ከአሥር ዓመታት በፊት ባቀረበው ሪፖርት አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ “መላው ማኅበረሰብ ጨርሶ እንደማያስብለት የሚሰማው አንድ ሙሉ ትውልድ ይታጣል” ብሏል።

ፍቅርና ተፈላጊነት ሳያገኙ ያደጉ ወጣቶች ከችግሮቻቸው ያመለጡ መስሏቸው ከቤታቸው ይወጡና በወንጀል፣ በዕፅ ሱሰኝነትና በሥነ ምግባር ብልግና በተዘፈቁ ከተሞች ከባድ ለሆኑ ችግሮች ይጋለጣሉ። እንዲያውም ከ20 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ፖሊስ በሰጠው ግምታዊ አኃዝ መሠረት በአንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከተማ ብቻ ከ20, 000 የሚበልጡ ከወላጆቻቸው የኮበለሉ 16 ዓመት ያልሞላቸው ልጆች ይገኙ እንደነበር ታውቋል። እነዚህ ልጆች ለእንዲህ ዓይነት ሕይወት ሊዳረጉ የቻሉት “በቤተሰብ መፈራረስና አብዛኛውን ጊዜ የአልኮል ወይም የአደገኛ ዕፅ ሱሰኞች በሆኑ ወላጆች በሚፈጸም የጭካኔ ድርጊት ሳቢያ” እንደሆነ ተገልጿል። ነፍሳቸውን ለማቆየት ሲሉ ወደ ጎዳና ይወጡና ዝሙት አዳሪዎች ይሆናሉ። ሰብዓዊ ክብራቸውን ተገፍፈው በአሳዳሪዎቻቸው እየተደበደቡ ይኖራሉ። የሚደርስባቸውን ቅጣት ስለሚፈሩ ከዚህ ኑሮአቸው ለማምለጥ ፈጽሞ አይሞክሩም።” ይህን የመሰለውን አሳዛኝ ሁኔታ ለመለወጥ ልባዊ ጥረት ቢደረግም አሁንም ለመወገድ አለመቻሉ በእጅጉ ያሳዝናል።

ከላይ በተገለጸው ሁኔታ ሥር ያደጉ ልጆች ትልቅ ሰው ሲሆኑ ሚዛናዊ ያልሆኑና አብዛኛውን ጊዜ የራሳቸውን ልጆች በአግባብ ለማሳደግ የማይችሉ ይሆናሉ። ራሳቸው የማይፈለጉና የማይወደዱ ሆነው ስላደጉ እነሱኑ የመሰሉ ፍቅርና ተፈላጊነት የተነፈጋቸው ልጆች ያፈራሉ። አንድ ጀርመናዊ የፖለቲካ ሰው “ፍቅር ያላገኙ ሕፃናት በጥላቻ የተሞሉ አዋቂዎች ይሆናሉ” በማለት ሁኔታውን ገልጸዋል።

በእርግጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ ወላጆች ልጆቻቸው የሚወደዱና የሚፈለጉ መሆናቸውን እንዲያውቁ የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ላይ ናቸው። ይህንንም በቃል ከመናገር አልፈው ማንኛውም ሕፃን ሊያገኝ የሚገባውን የቅርብ ትኩረትና ፍቅር ለልጆቻቸው በመስጠት በተግባር በማሳየት ላይ ናቸው። ቢሆንም ችግሮች፣ አዎን፣ ከግለሰብ ወላጆች አቅም በላይ የሆኑ ችግሮች አልቀሩም። ለምሳሌ፣ በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች የዘረጓቸው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓቶች ሕፃናት በቂ የሆነ የጤና እንክብካቤ፣ ተስማሚ ትምህርትና በቂ ምግብ እንዲያገኙ ማድረግም ሆነ ከሕፃናት ጉልበት ብዝበዛና አስከፊ ከሆነ የኑሮ ሁኔታ እንዲጠበቁ ማድረግ አልቻሉም። አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ስግብግብ፣ ምግባረ ብልሹና ራስ ወዳድ የሆኑ እንዲሁም አሳቢነት የጎደላቸው ትላልቅ ሰዎች የሚፈጽሙት ድርጊት ችግሩን ያባብሰዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኮፊ አናን እንደሚከተለው ብለው በመጻፍ አንዳንዶቹን ዋነኛ የሆኑ የሕፃናት ችግሮች ጠቅሰዋል:- “በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ በሚያደርግ አስከፊ ድህነት ሥር ይኖራሉ። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት ግጭትና የኢኮኖሚ ቀውስ ባስከተለባቸው መከራ ይማቅቃሉ። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በጦርነቶች ምክንያት አካላቸውን ሲያጡ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ወላጆቻቸውን የሚያጡ ወይም ሕይወታቸው የሚያልፍ ሕፃናትም እጅግ ብዙ ናቸው።”

ይሁን እንጂ ተስፋው ሙሉ በሙሉ የጨለመ አይደለም። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅትንና (ዩኒሴፍ) የዓለም ጤና ድርጅትን የመሰሉ በተባበሩት መንግሥታት ሥር የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች የሕፃናትን ኑሮ ለማሻሻል ብዙ ደክመዋል። አናን እንዲህ ብለዋል:- “ጤናማ ሆነው የሚወለዱ፣ ክትባት የሚያገኙ፣ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ እንዲሁም የመማር፣ የመጫወትና የልጅነት ኑሮ የመኖር ነፃነት ያገኙ ሕፃናት ቁጥር ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ይቻላል ተብሎ ይታሰብ ከነበረው በእጅጉ ጨምሯል።” ቢሆንም “ባገኘነው ውጤት ተኩራርተን የምንቀመጥበት ጊዜ አይደለም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው

አንዳንድ ሕፃናት ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል። በ1960ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ዓለም ከደርዘን በላይ በሚሆኑ አገሮች በሺህዎች የሚቆጠሩ ታሊዶማይድ ሕፃናት የሚባሉ የአካል ጉዳተኞች የሆኑ ሕፃናት መወለዳቸውን የሚገልጽ አስደንጋጭ ዜና ሰማ። ታሊዶማይድ የተባለው እንቅልፍ አስወሳጅ መድኃኒት በነፍሰ ጡር ሴቶች ሲወሰድ በሚወለዱት ሕፃናት ላይ ያልተጠበቀ ጠንቅ በማስከተሉ እጅና እግሮቻቸው የሰለሉና እንዲያውም ጨርሶ እጅና እግር የሌላቸው ሕፃናት ተወለዱ። የብዙዎቹ ሕፃናት እጆችና እግሮች ከዓሣ ክንፍ ያልበለጡ ነበሩ።

ከአራት አሥርተ ዓመታት በኋላ ደግሞ በአብዛኛው ልጆችን ለአካል ጉዳተኛነት እየዳረጉ ያሉት ፈንጂዎች ናቸው። * አንዳንዶች እንደሚገምቱት ከሆነ በዓለም ዙሪያ ከ60 ሚልዮን እስከ 110 ሚልዮን የሚደርሱ ፈንጂዎች ተቀብረው ይገኛሉ። በርካታ ሕፃናትን ጨምሮ 26, 000 የሚያክሉ ሰዎች በየዓመቱ ይሞታሉ ወይም የአካል ጉዳተኞች ይሆናሉ። ጆዲ ዊልያምስ ፈንጂዎች እንዲታገዱ ለማድረግ ባካሄዱት ዘመቻ ምክንያት የሰላም የኖቤል ተሸላሚ ከሆኑበት ከ1997 ወዲህ ለዚህ ችግር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል። ቢሆንም ዛሬም የተቀበሩ ፈንጂዎች አልተወገዱም። አንድ የጀርመን ፖለቲከኛ ፈንጂዎችን ከምድር ገጽ ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ ሲናገሩ “በተከፈተ ቧንቧ ሥር በሚገኝ ገንዳ ውስጥ እየተጠራቀመ ያለን ውኃ በሻይ ማንኪያ ጨልፎ ለመጨረስ የመሞከር ያህል ነው” ብለዋል።

ሌሎቹ ልዩ ትኩረት ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ደግሞ ወላጆቻቸውን ያጡ ናቸው። የሰዎች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ዓላማው ልጆች የእናታቸውንም ሆነ የአባታቸውን ፍቅራዊ እንክብካቤ አግኝተው እንዲያድጉ ነበር። አንድ ሕፃን እንዲህ ያለ ሚዛኑን የጠበቀ የወላጆች ድጋፍ ያስፈልገዋል።

የሕፃናት ማሳደጊያና የጉዲፈቻ ድርጅቶች ሁለቱንም ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ችግሮች ለማቃለል ይጥራሉ። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ትኩረት ሳያገኙ የሚቀሩት አሳዳጊ ማግኘት የሚያስፈልጋቸውና እጅግ አንገብጋቢ ችግር ያለባቸው ሕፃናት መሆናቸው በእጅጉ ያሳዝናል። ታማሚዎች የሆኑ፣ የመማርና የመረዳት ችግር ያለባቸው፣ የአካል ጉዳተኞች ወይም ወላጆቻቸው የባዕድ አገር ሰዎች የሆኑ ሕፃናት አሳዳጊ ሳያገኙ ይቀራሉ።

ግለሰቦች ቋሚ የሆነ የገንዘብ መዋጮ በመስጠት በድሀ አገሮች የሚኖሩ ሕፃናትን “እንዲያሳድጉ” የሚያበረታቱ ድርጅቶች ተቋቁመዋል። በዚህ መልክ የተሰበሰበው ገንዘብ ሕፃናትን ለማስተማር ወይም ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ ይውላል። ከተፈለገ ዝምድናውን ለማጠንከር ፎቶግራፎችንና ደብዳቤዎችን መለዋወጥ ይቻላል። ይህ ዓይነቱ ዝግጅት ጠቃሚ ቢሆንም የተሟላ ነው ለማለት አይቻልም።

ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችን ለመርዳት ለተደረገው ጥረት ምሳሌ የሚሆነን በ1999 ሃምሳኛ ዓመቱን ያከበረ አንድ ድርጅት አለ።

የኤስ ኦ ኤስ የሕፃናት መንደር

በ1949 ኼርማን ገማይነ በኦስትሪያ አገር በኢምስት ከተማ የኤስ ኦ ኤስ የሕፃናት መንደር ብለው የጠሩትን ድርጅት መሠረቱ። ይህ ድርጅታቸው ከዚህ አነስተኛ ጅምር ተነስቶ 131 በሚያክሉ የአፍሪካ፣ የእስያ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች የሚገኙ 1, 500 የሚያክሉ መንደሮችንና ሌሎች ተመሳሳይ ተቋሞችን የሚያቅፍ ሆኗል።

ገማይነ ሥራቸውን የመሠረቱት እናት፣ ወንድሞችና እህቶች፣ ቤትና መንደር በሚሉ አራት መሠረታዊ መርሆዎች ላይ ነበር። አንዲት “እናት” አምስት ወይም ስድስት ወይም ከዚያ ሊበልጡ የሚችሉ ልጆች ለሚገኙበት “ቤተሰብ” መሠረት ትሆናለች። አብራቸው በመኖር ከእውነተኛ እናት የሚጠበቀውን ፍቅርና ትኩረት ለማሳየት ትጥራለች። ሕፃናቱ አድገው “ከቤት” እስኪወጡ ድረስ ከዚያው “ቤተሰብ” እና ከዚያችው “እናት” ጋር አብረው ይኖራሉ። በአንድ “ቤተሰብ” ውስጥ የተለያየ ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት እንዲኖሩ ይደረጋል። ታላላቅም ሆነ ታናናሽ “ወንድሞች” እና “እህቶች” ስለሚኖሩአቸው ሕፃናቱ እርስ በእርስ መረዳዳት ይማራሉ። ይህም ራሳቸውን ብቻ የሚወዱ እንዳይሆኑ ይረዳቸዋል። ሕፃናቱ በተቻለ መጠን ገና በትንሽነታቸው በ“ቤተሰብ” እንዲታቀፉ ጥረት ይደረጋል። በሥጋ የሚዛመዱ ወንድማማቾችና እህትማማቾች ሁልጊዜ በአንድ “ቤተሰብ” እንዲኖሩ ይደረጋል።

በአንድ መንደር ውስጥ እያንዳንዳቸው በየራሳቸው ቤት የሚኖሩ 15 የሚያክሉ “ቤተሰቦች” ይኖራሉ። ሁሉም ሕፃናት “እናታቸውን” በቤት ውስጥ ሥራ እንዲረዱ ማሰልጠኛ ይሰጣቸዋል። አባት ባይኖርም አባታዊ ምክርና አስፈላጊውን ተግሣጽ የሚሰጥ ወንድ እንዲኖር ዝግጅት ይደረጋል። ሕፃናቱ በመንደሩ በሚገኝ ትምህርት ቤት ይማራሉ። እያንዳንዱ “ቤተሰብ” ወጪዎቹን የሚሸፍንበት የተወሰነ ገንዘብ ይሰጠዋል። ምግብና ልብስ ከዚያው ከመንደሩ ይገዛል። ዓላማው ሕፃናቱ ከመደበኛው የቤተሰብ ኑሮ እንዲሁም ከቤተሰብ ችግሮችና ደስታዎች ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግና በተቻለ መጠን የተለመደውን ዓይነት ኑሮ እንዲኖሩ ለማስቻል ነው። ይህም ሲያድጉ የራሳቸውን ቤተሰብ መሥርተው እንዲያስተዳድሩ ይረዳቸዋል።

ፍጹም የሆነው መፍትሔ ገና አልተገኘም

የጉዲፈቻና የሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅቶች፣ ኤስ ኦ ኤስ የሕፃናት መንደሮች፣ ዩኒሴፍና ተመሳሳይ ድርጅቶች ችግረኛ ሕፃናትን ለመርዳት የሚያደርጉት ጥረት የሚመሰገን ነው። ይሁን እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ አንዳንድ ሰዎች በተለያዩ ችግሮች እየተንገላቱ ሕይወታቸውን ለመግፋት የሚገደዱ መሆኑን መካድ አይችሉም። ምንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ ሽባ ሆኖ ለተወለደ ሕፃን እጅና እግር ሊተክሉ፣ የአእምሮ ጉዳተኛ የሆነን ሕፃን አእምሮ ሊያንቀሳቅሱ፣ አንድን ሕፃን ተለያይተው ወይም ተፋተው ከነበሩ ወላጆቹ ጋር እንደገና አብሮ እንዲኖር ሊያደርጉ ወይም የሞተበትን ወላጅ ሊመልሱለት አይችሉም።

የሰው ልጆች ምንም ያህል ቢጥሩ ለሕፃናት ችግሮች ፍጹም የሆነ መፍትሔ ማስገኘት አይችሉም። ይሁን እንጂ እነዚህ ችግሮች መፍትሔ ማግኘታቸው አይቀርም! አዎን፣ ምናልባትም አንተ ከምታስበው ይበልጥ በቀረበ ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ያገኛሉ። ግን እንዴት?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17የተቀበሩ ፈንጂዎች​— መፍትሔ ይገኝላቸው ይሆን?” በሚል ጭብጥ ሥር በግንቦት 2000 እትማችን ላይ የወጡትን ተከታታይ ርዕሶች ተመልከት።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አንድ ሕፃን የአባቱም ሆነ የእናቱ ፍቅርና ትኩረት ያስፈልገዋል