መፍትሔውን ለማግኘት የሚደረገው ያላቋረጠ ጥረት
መፍትሔውን ለማግኘት የሚደረገው ያላቋረጠ ጥረት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ ለልጆችና በልጆች ላይ እየደረሱ ላሉት ችግሮች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል። በ1946 መጨረሻ ላይ በጦርነት በፈራረሱ አካባቢዎች ይኖሩ ለነበሩ ሕፃናት አስፈላጊውን እንክብካቤ ለመስጠት የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ የሕፃናት መርጃ ድርጅትን (ዩኒሴፍ) በጊዜያዊነት አቋቋመ።
በ1953 ይህ ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የተቋቋመው ድርጅት ቋሚ ድርጅት ሆነ። ይህ ድርጅት በአሁኑ ጊዜ የሚጠራው የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ተብሎ ቢሆንም ዩኒሴፍ የተባለውን የመጀመሪያውን ምህጻረ ቃል እንደያዘ ቀጥሏል። ዩኒሴፍ ከግማሽ መቶ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ በመላው ዓለም ለሚኖሩ ሕፃናት ምግብ፣ ልብስና ሕክምና ሲያቀርብና አጠቃላይ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ሲጥር ቆይቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መብቶችን መግለጫ በ1959 በማጽደቁ በሕፃናት ላይ የሚደርሱት ችግሮች የበለጠ ትኩረት አገኙ። (ገጽ 5 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ይህ ሰነድ በሕፃናት ላይ ለሚደርሱት ችግሮች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ ለማድረግና በዚህም አማካኝነት ከሕዝብ በሚገኘው የገንዘብና ሌላ ዓይነት እርዳታ ችግሮቹን ለመፍታት ይረዳል ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር።
ይሁን እንጂ የኮልየር የ1980 ዓመት መጽሐፍ እንደሚለው “ከሃያ ዓመት በኋላ እንኳን እነዚህ ‘መብቶች፣’ በተለይም ከሥነ ምግብ፣ ከጤናና ከቁሳዊ ደህንነት ጋር ተዛማጅነት ያላቸው መብቶች 1.5 ቢልዮን ከሚያክሉት የዓለም ሕፃናት ለአብዛኞቹ ሊሟሉ አልቻሉም።” ስለዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናትን ችግሮች መፍታት አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብና ራሱ ባወጣው መግለጫ የተቀበላቸውን ግቦች በመንተራስ 1979ን ዓለም አቀፍ የሕፃናት ዓመት ሲል ሰይሟል። መንግሥታዊ፣ ሕዝባዊ፣ ሃይማኖታዊና ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች መፍትሔ ለማፈላለግ በሚደረገው ጥረት ለመካፈል አልዘገዩም።
“ከንቱ ዘበት” ሆኖ የሚቀር ነውን?
የዩኒሴፍ ሪፖርት እንደሚያመለክተው በታዳጊ አገሮች የሚኖሩ ሕፃናት በዚሁ ዓለም አቀፍ የሕፃናት ዓመት አስከፊ ሁኔታ የገጠማቸው መሆኑ በጣም ያሳዝናል። በዓመቱ መጨረሻ ላይ እንደታየው 200 ሚልዮን የሚያክሉት በቂ ምግብ አላገኙም። አምስት ዓመት
ሳይሞላቸው ከሞቱት 15 ሚልዮን የሚያክሉ ሕፃናት መካከል ደግሞ ግማሽ የሚሆኑት የሞቱት በቂና የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው ነው። በዚሁ ዓመት በእነዚህ አገሮች በእያንዳንዱ ደቂቃ ከሚወለዱት 100 ሕፃናት መካከል 15ቱ አንደኛ ዓመታቸውን ሳይጨርሱ ይሞቱ ነበር። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመጨረስ የሚችሉት ከ40 በመቶ ያነሱ ነበሩ። በኢንዲያን ኤክስፕረስ ላይ የወጣ አንድ ርዕሰ አንቀጽ ዩኒሴፍ ያወጣውን ሪፖርት አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት ይህ የሕፃናት ዓመት “ከንቱ ዘበት” ሆኖ ቀርቷል በማለት አማሯል።ይህ ጥረት እንደማይሳካ አስቀድመው ያወቁ ግለሰቦች ነበሩ። ለምሳሌ ፋብሪሲዮ ዴንቲቼ ገና በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ሌስፕሬሶ በተባለው መጽሔት ላይ “ይህን ችግር ለማስወገድ የሕፃናት ዓመት ከመሰየም የበለጠ ነገር ያስፈልጋል” ሲሉ ጽፈው ነበር። “ዛሬ ለምንኖረው ሁኔታ የዳረገን የአኗኗር ስልታችን በመሆኑ መለወጥ ያለበትም ይኸው አኗኗራችን ነው” ሲል መጽሔቱ አስተያየቱን ሰጥቷል።
በሕፃናት ላይ ለሚደርሱት ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በመቀጠል በመስከረም ወር 1990 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት የዓለም መሪዎች ጉባኤ ተደረገ። በታሪክ ዘመናት ከተደረጉት ታላላቅ የመሪዎች ጉባኤዎች አንዱ ነበር። ከ70 የሚበልጡ የመንግሥታት መሪዎች ተገኝተዋል። ስብሰባው የተደረገው ኅዳር 20 ቀን 1989 ጸድቆ መስከረም 2 ቀን 1990 ሥራ ላይ የዋለውን የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን አፈጻጸም ለመከታተል ነበር። ይህ ስምምነት በወሩ መጨረሻ ላይ በ39 አገሮች ተቀባይነት አግኝቷል።
“ኮንቬንሽኑ ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን ተቀባይነት ያገኘ የሰብዓዊ መብቶች ውል ለመሆን በመቻሉ የሕፃናት መብቶች እንዲከበሩ ዓለም አቀፍ የሆነ ከፍተኛ ግፊት አሳድሯል” በማለት ዩኒሴፍ ተናግሯል። በእርግጥም ኮንቬንሽኑ እስከ ኅዳር 1999 ድረስ በ191 አገሮች ተቀባይነት አግኝቷል። ዩኒሴፍ ስለተገኘው ውጤት በኩራት ሲናገር “የሕፃናትን መብቶች በመጠበቅና በማክበር ረገድ የሕፃናት ኮንቬንሽን ከጸደቀ ወዲህ ባሉት አሥር ዓመታት የተገኘው ውጤት በማንኛውም የታሪክ ዘመን በእንዲህ ያለ ጊዜ ውስጥ ከተገኘው ውጤት ይልቃል” ብሏል።
ይህን የመሰለ ውጤት ሊገኝ ይቻል እንጂ የጀርመን ፕሬዚዳንት ዮሐንስ ራው “በዚህ ባለንበት ዘመንም እንኳ ሳይቀር ሕፃናት መብት እንዳላቸው ማሳሰቢያ ሊሰጠን ማስፈለጉ በጣም የሚያሳዝን ነው” ለማለት ተገድደዋል። አዎን፣ አሁንም ሕፃናት ከባድ ችግር እንዳለባቸው ማሳሰብ አስፈላጊ ሆኗል። ዩኒሴፍ በኅዳር 1999 “ገና ብዙ የሚሠራ ሥራ” መኖሩን አምኖ በመቀበል የሚከተለውን ማብራሪያ
ሰጥቷል:- “በመላው ዓለም 12 ሚልዮን የሚያክሉ አምስት ዓመት ያልሞላቸው ሕፃናት በአብዛኛው በቀላሉ ሊወገዱ በሚችሉ ምክንያቶች በየዓመቱ እንደሚሞቱ ይገመታል። በታዳጊ አገሮች የሚኖሩ 130 ሚልዮን ሕፃናት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት የማግኘት እድል የላቸውም . . . የችግሩ መጠን ቢለያይም እንኳ 160 ሚልዮን የሚያክሉ ሕፃናት በቂ ምግብ የማግኘት ችግር አለባቸው። . . . ፈላጊ ያጡ በርካታ ሕፃናት በየሕፃናት ማሳደጊያውና በሌሎች ተቋሞች በቂ ትምህርትና ሕክምና ተነፍጓቸው ይማቅቃሉ። እነዚህ ሕፃናት አብዛኛውን ጊዜ አካላዊ በደል ይፈጸምባቸዋል። ወደ 250 ሚልዮን የሚጠጉ ሕፃናት ከአቅማቸው በላይ የሆነ ሥራ ይሠራሉ።” በተጨማሪም 600 ሚልዮን የሚያክሉ ሕፃናት በከባድ ድህነት እንደሚማቅቁና 13 ሚልዮን የሚያክሉ ደግሞ በ2000 ዓመት መጨረሻ ላይ ቢያንስ አንድ ወላጃቸውን በኤድስ እንደሚነጠቁ ተጠቅሷል።የፖለቲካ መሪዎች ለእነዚህ ችግሮች አጥጋቢ መፍትሔ ማግኘት የተሳናቸው ይመስላል። ይሁንና በልጆች ላይ የሚደርሱት ችግሮች በታዳጊ አገሮች ብቻ የተወሰኑ አይደሉም። በምዕራባውያን አገሮች የሚኖሩ ብዙ ልጆችም ሊያገኙት ያልቻሉት መሠረታዊ የሆነ ነገር አለ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በዚህ ባለንበት ዘመንም እንኳ ሳይቀር ሕፃናት መብት እንዳላቸው ማሳሰቢያ ሊሰጠን ማስፈለጉ በጣም የሚያሳዝን ነው”
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መብቶች ድንጋጌ:-
● ስምና ዜግነት የማግኘት መብት።
● የመወደድ፣ የመፈቀር፣ ስሜታቸውን ሊረዱ የሚችሉ ሰዎችን ድጋፍ የማግኘት እንዲሁም ቁሳዊ ዋስትና የማግኘት መብት።
● በቂ ምግብ፣ መጠለያና የሕክምና አገልግሎት የማግኘት መብት።
● የአካል ጉዳተኛ ከሆነ በአካላዊ፣ በአእምሮአዊም ሆነ በማኅበራዊ ሁኔታዎች ረገድ ልዩ እንክብካቤ የማግኘት መብት።
● በማንኛውም ሁኔታ ጥበቃና እርዳታ የማግኘት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መካከል የመሆን መብት።
● ከማንኛውም ግዴለሽነት የተሞላበት አያያዝ፣ ጭካኔና ብዝበዛ ጥበቃ የማግኘት መብት።
● የተሟላ የመጫወቻና የመዝናኛ አጋጣሚ የማግኘትና ግላዊ ችሎታዎቹን ለማዳበርና ጠቃሚ የሆነ የኅብረተሰቡ አባል ለመሆን የሚያስችለውን መደበኛ ትምህርት በነፃና በእኩልነት የማግኘት መብት።
● ነፃነቱና ሰብዓዊ ክብሩ በተጠበቀበት ሁኔታ ችሎታዎቹን በተሟላ ሁኔታ የማዳበር መብት።
● በሰዎች መካከል መግባባት፣ መቻቻል፣ ሰላም፣ ወዳጅነትና ወንድማማችነት በሰፈነበት ሁኔታ የማደግ መብት።
● በዘሩ፣ በቀለሙ፣ በፆታው፣ በሃይማኖቱ፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አስተሳሰቡ፣ በብሔሩ ወይም በማኅበራዊ ደረጃው፣ በንብረቱ፣ በልደቱ ወይም በማንኛውም ሌላ ደረጃ ምክንያት አድልዎ ሳይደረግበት በእነዚህ መብቶች ተጠቃሚ የመሆን መብት።
[ምንጭ]
Summary based on Everyman’s United Nations
[በገጽ 3 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
UN PHOTO 148038/Jean Pierre Laffont
UN photo
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ገጽ 4 እና 5 ላይ ያሉት ፎቶዎች Giacomo Pirozzi/Panos Pictures