በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳይንስ የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝ ይችላልን?

ሳይንስ የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝ ይችላልን?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ሳይንስ የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝ ይችላልን?

ከዓመታት በፊት እንዲህ ያለውን ጥያቄ ማንሣት እንደ ፌዝ የሚቆጠር ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን አንዳንድ ሰዎች ይህንን ጉዳይ በቁም ነገር ማጤን ጀምረዋል። ሳይንቲስቶች በሰዎችም ላይ ሊሠሩ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ አንዳንድ ዘዴዎችን በመጠቀም የዝንቦችንና የአንዳንድ ነፍሳትን ሕይወት በእጥፍ ማራዘም ችለዋል።

በምርምር እንደተረጋገጠው መደበኛው የሰው ልጅ ሕዋስ በተወሰነ ቁጥር ብቻ የመባዛት አቅም ያለው ሟች አካል ነው። እዚህ ቁጥር ላይ ከደረሱ በኋላ ሕዋሳቱ መከፈላቸውን ያቆማሉ። ይህ ሂደት ሰዎች የሚያረጁበትንና የሚሞቱበትን ጊዜ ከሚቆጣጠር ተፈጥሮአዊ ሰዓት ጋር ተመሳስሏል። ዛሬ ሳይንቲስቶች ይህንን ሰዓት ለማስተካከል እየጣሩ ነው።

አንድ በሰፊው የሚታመንበት ንድፈ ሐሳብ የማርጀት ምሥጢሩ ያለው ቴሎሚር ተብሎ በሚጠራው የዲ ኤን ኤ ክር ጫፍ ላይ መሆኑን ይገልጻል። ቴሎሚር የጫማ ማሰሪያው እንዳይተረተር ከሚከላከለው በጫማ ማሰሪያ ጫፍ ላይ ካለው ፕላስቲክ ጋር ተመሳስሏል። ሳይንቲስቶቹ እያንዳንዱ ሕዋስ በተከፈለ ቁጥር ቴሎሚሩ እንደሚቃጠል ፊውዝ እያጠረ እንደሚሄድ አስተውለዋል። የኋላ ኋላ እያጠረ ሄዶ ሕዋሳቱ መከፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። ይሁን እንጂ ቴሎሚሩ ራሱ እንዳያጥር የሚከላከሉ ኤንዛይሞች አሉ። በመሆኑም በዚህ ንድፈ ሐሳብ መሠረት ይህ ሁኔታ ሕዋሳቱ ያለ ገደብ መባዛታቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ የሚቻልበትን አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል። በዚህ ሥራ የተካፈሉ የአንድ ኩባንያ ባለ ሥልጣን “ይህ የሰው ልጅ ያለመሞትን ባሕርይ መላበስ ይችላል ብለን ያሰብንበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት ሁሉ ሳይንቲስቶች አይደሉም።

ሞት እንዴት መጣ?

እርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑ ሰዎች የሰው ልጅ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ ሲያምኑ ብዙ ሺህ ዓመታት ተቆጥረዋል። ትምክህታቸውን የጣሉት ግን በሰብዓዊ ሳይንቲስቶች ላይ ሳይሆን ሕያው ነገሮችን ሁሉ በፈጠረው ታላቁ ሳይንቲስት በይሖዋ አምላክ ላይ ነው።​—⁠መዝሙር 104:​24, 25

የሰው ልጅ እንዲሞት የፈጣሪ ዓላማ እንዳልነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት በመልኩ ፈጥሮ በገነት ውስጥ አኖራቸው። ፍጹማን ስለነበሩ የአእምሮም ሆነ የአካል እንከን አልነበረባቸውም። በዚህ መልኩ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ነበራቸው። አምላክ ለእነርሱ ያሰበላቸው ነገር ይህ ነበር። ልጆችን እንዲወልዱና ቀስ በቀስም ገነትን እያሰፉ ምድርን እንዲሸፍኑ ትእዛዝ ሰጣቸው።​—⁠ዘፍጥረት 1:​27, 28፤ 2:​8, 9, 15

በዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ላይ እንደተገለጸው አዳም በሞት እንደሚያስቀጣው እያወቀ ሆን ብሎ በአምላክ ላይ ዓመፀ። አልፎ ተርፎም ያለመታዘዝን ጎዳና በመከተሉ ገና ባልተወለዱት ዘሮቹ ላይ ሳይቀር ኃጢአትንና ሞትን አመጣ። ሐዋርያው ጳውሎስ ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” (ሮሜ 5:​12) በሌላ አባባል አዳም ኃጢአት ስለ ሠራ አካላዊ ፍጽምናውን አጥቷል። ቀስ በቀስ እያረጀ ሄደና በመጨረሻ ሞተ። የእርሱም ልጆች ይህን የእርሱን እንከን ወርሰዋል።

በመሆኑም ሰዎች መሞት የጀመሩት አዳም በሠራው ዓመፅና ከዚህ የተነሣ አምላክ ባስተላለፈው ፍርድ ምክንያት ነው። የሰው ልጆች ይህንን ፍርድ መቀልበስ አይችሉም። ሳይንስ በሕክምናው መስክ ብዙ መሻሻሎችን ቢያደርግም ከዛሬ 3, 500 ዓመታት በፊት በሙሴ አማካኝነት የተመዘገቡት በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቃላት ዛሬም እውነት ናቸው:- “የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፣ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፣ እኛም እንገሠጻለንና።”​—⁠መዝሙር 90:​10

ይሖዋ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ያደረገው ዝግጅት

የሚያስደስተው ግን ለዘላለም የመኖር ተስፋ አለ! አሁን ባለንበት ጊዜ ሰው ሁሉ መሞቱ የማይቀር ቢሆንም ይህ ሁኔታ እስከ ዘላለሙ እንዲቀጥል የይሖዋ ዓላማ አይደለም። አዳምና ሔዋን መሞት ይገባቸው የነበረ ቢሆንም አምላክ ገና ካልተወለዱት ልጆቻቸው መካከል እርሱ ላሳየው ፍቅራዊ ጥበቃ አድናቆት የሚያሳዩ ብዙ ሰዎች እንደሚኖሩ አውቆ ነበር። እንደነዚህ ያሉት ግለሰቦች በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን ዝግጅት አድርጎላቸዋል። መዝሙራዊው “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 37:​29) ይሁን እንጂ ይህ የሚሆነው እንዴት ነው?

እዚህ ውጤት ላይ የሚደረሰው የሰው ልጅ የዲ ኤን ኤን ምሥጢር ስለሚፈታ አይደለም። ይልቁንም የዘላለም ሕይወት ይሖዋ እምነት እንዳላቸው ለሚያሳዩ ሰዎች የሚሰጠው ስጦታ ነው። የአዳምና ሔዋን ልጆች መቤዠት እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘብ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድ አዘጋጅቷል። ኢየሱስ ይህንን ዝግጅት አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”​—⁠ዮሐንስ 3:​16

ልክ እንደ አዳም ሁሉ ኢየሱስም ፍጹም ሰው ነበር። ከአዳም በተለየ መልኩ ግን ኢየሱስ ለአምላክ ፍጹም ታዛዥ ሆኗል። በመሆኑም ኢየሱስ የአዳምን ኃጢአት ለመክፈል ፍጹም ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ችሏል። የፍትሕን ሚዛን በሚያስጠብቀው በዚህ የፍቅር እርምጃ የአዳም ልጆች ከሞት ኩነኔ ነፃ ሊወጡ ይችላሉ። ከዚህም የተነሣ በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ሰዎች ሁሉ የአምላክን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ያገኛሉ።​—⁠ሮሜ 5:​18, 19፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:​5, 6

ሰዎች አለፍጽምናን አሸንፈው የዘላለም ሕይወት ማምጣት የሚችሉ ቢሆን ኖሮ ቤዛ መክፈልም አያስፈልግም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ጥበብ ያለበት ምክር ይሰጣል:- “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ። ነፍሱ ትወጣለች ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል። የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውም በአምላኩ በእግዚአብሔር የሆነ ሰው ምስጉን ነው፤ እርሱም ሰማይንና ምድርን ባሕርንም፣ በእነርሱ ያለውንም ሁሉ የፈጠረ፤ እውነትን ለዘላለም የሚጠብቅ።”​—⁠መዝሙር 146:​3-6

የዘላለም ሕይወት የሚገኘው በሳይንሳዊ ምርምር ሳይሆን ከይሖዋ ነው። አምላክ ለማድረግ ያሰበውን ነገር ሁሉ ማድረግ ይችላል፤ ደግሞም ያደርገዋል። “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም።”​—⁠ሉቃስ 1:​37

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Charles Orrico/SuperStock, Inc.