በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሕይወት እንድቆይ የሚያደርግ ተስፋ አገኘሁ

በሕይወት እንድቆይ የሚያደርግ ተስፋ አገኘሁ

በሕይወት እንድቆይ የሚያደርግ ተስፋ አገኘሁ

ታትያና ቪሌስካ እንደተናገረችው

እናታችን በምንኖርበት አፓርታማ ላይ ተደብድባ ስትገደል ደስተኛ የነበረው ቤተሰባችን ተናጋ። ከአራት ወራት በኋላ አባቴ ራሱን ገደለ። ከዚያ በኋላ በሕይወት መኖር ጨርሶ አስጠላኝ። ታዲያ እስከ አሁን ድረስ በሕይወት ለመቆየትና ታሪኬን ለመናገር የበቃሁት እንዴት ነው? እስቲ ልንገራችሁ።

በምሥራቅ ዩክሬይን የምትገኘው ዶኔትስክ የብረታ ብረት ማቅለጫ ፋብሪካ የሚገኝባትና የከሰል ማዕድን የሚወጣባት ከተማ ነች። ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡት ነዋሪዎቿ የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሲሆኑ ታታሪዎችና ተግባቢ ናቸው። ከእነዚህ አንዳንዶቹ በኮከብ ቆጠራ ወይም በመናፍስት የሚያምኑ ሲሆን አብዛኞቹ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ አውደ ነገሥት ይገልጣሉ። ሌሎች ደግሞ አስማት ወይም በሩሲያኛ እንደሚጠራው ኮልዱንስ ያደርጋሉ። ከእነዚህ አንዳንዶቹ ለሕመማቸው ፈውስ ለማግኘት ወይም እንዲያው ለጨዋታ ብለው ሙታንን መጠየቅ ይፈልጋሉ።

አባቴ ጫማ ሠሪ ነበር። ምንም እንኳ በአምላክ መኖር እንደማያምን ቢናገርም በዚህች ምድር ላይ ያስቀመጠን አንድ አካል ይኖራል የሚል እምነት ነበረው። “እኛ በዚህች ምድር ላይ መጻተኞች ነን” ይል ነበር። እናቴ የትንሣኤ በዓል በመጣ ቁጥር ቤተ ክርስቲያን ትሄዳለች። “አምላክ በእርግጥ ካለ ቤተ ክርስቲያን የመሄድ ግዴታ አለብን” የሚል አመለካከት አላት። የተወለድኩት ግንቦት 1963 ነበር። ታላቅ እኅቴ ሉቦፍ እና ታናሽ ወንድሜ አሌክሳንድር ደስተኛ ለነበረው ቤተሰባችን ትልቅ ድርሻ አበርክተዋል።

“ጎጂ ጥንቆላ አይደለም”

ፕዮትር * የሚባል አንድ የሩቅ ዘመድ በከሰል ማዕድን ማውጫ ውስጥ ሲሠራ አደጋ ደርሶበት ጭንቅላቱ ስለተጎዳ ልዩ ክሊኒክ ውስጥ ሕክምና ማግኘት አስፈልጎት ነበር። የጤንነቱ ጉዳይ በጣም ስላሳሰበው ወደ ኮልዱን ሄዶ ምክር ጠየቀ። ጠንቋዩ ፕዩትርን ከመንፈሳዊ ዓለም ጋር አገናኘው። ባለቤቱም ሆነች ወላጆቼ ጥንቆላ የሚጠቅም ነገር እንዳልሆነ ቢነግሩትም እሱ ከእነርሱ የተሻለ እንደሚያውቅ ስለተሰማው አባባላቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። “የእኔ ጎጂ ጥንቆላ አይደለም። ሌላውን ለመጉዳት ተብሎ የሚደረግ ጥንቆላ አለ፤ የእኔ ግን ጎጂ አይደለም” በማለት ለማሳመን ሞከረ።

ፕዮትር ስለወደፊቱ ጊዜ ለማወቅና ሰዎችን ከጉዳት ለመጠበቅ የሚያስችል ኃይል እንዳለው ይናገር ነበር። ሆኖም ባለቤቱ ጥላው ሄደች።

ፕዮትር እኛ ጋር ለመቆየት ይመጣ የነበረ ሲሆን እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ለሳምንታት እኛ ጋ ይሰነብታል። በቤተሰባችን ላይ ያስከተለው ተጽዕኖ ቀላል አልነበረም። አባቴና እናቴ በሆነው ባልሆነው ይጨቃጨቁ ጀመር። ከጊዜ በኋላ ተለያዩ፤ ከዚያም ተፋቱ። ሁላችን ከእናታችን ጋር በሌላ አፓርታማ ውስጥ መኖር የጀመርን ሲሆን የእናታችን ሥጋ ዘመድ የሆነው ፕዮትር አንድኛውን እኛ ጋ ገባ።

ሉቦፍ አገባችና ከባለቤትዋ ጋር ወደ አፍሪካ ኡጋንዳ ሄደች። አሌክሳንድር ጥቅምት 1984 ለእረፍት ሲሄድ እኔ ደግሞ ለአንድ ሳምንት ወደ ጎርሎቭካ ሄድኩ። ከቤት ስወጣ ከእማማ ጋር በደንብም አልተሰነባበትንም ነበር። ምነው በደንብ በተሰናበትኳት ወይ ጭራሽ ትቻት ባልሄድኩ ኖሮ! እማማን ዳግም በሕይወት አላገኘኋትም።

“የምትወጂያት እናትሽ አርፋለች”

ከጎርሎቭካ ስመለስ አፓርታማው ተዘግቶና መግባት ክልክል እንደሆነ የሚገልጽ የፖሊስ ማስጠንቀቂያ በር ላይ ተንጠልጥሎ አገኘሁ። ከእግር እስከ ራሴ ወረረኝ። ወደ ጎረቤቶቻችን ሄድኩ። ኦልጋ በጣም ስለተረበሸች መናገር አልቻለችም። ባለቤትዋ ቭላድሚር “ታንያ፣ አንድ አሳዛኝ ነገር ተከስቷል። የምትወጂያት እናትሽ አርፋለች። የገደላት ፕዮትር ነው። ከዚያ በኋላ ወደ እኛ አፓርታማ መጥቶ ስልክ ደወለና እጁን ለፖሊስ ሰጠ” በማለት ቀስ ብሎ ነገረኝ።

የሰማሁት ዘግናኝ መርዶ እውነት መሆኑን ፖሊስ ካረጋገጠልኝ በኋላ የአፓርታማችንን ቁልፍ ሰጠኝ። ለፕዮትር ከፍተኛ ጥላቻ አደረብኝ። በጣም ከመናደዴ የተነሳ ስለ ጥንቆላ የሚናገሩ መጽሐፎቹን ጨምሮ አብዛኞቹን ዕቃዎቹን ሰብስቤ፣ በብርድ ልብስ ጠቀለልኩና በአቅራቢያችን ወደሚገኝ ሜዳ ወስጄ አቃጠልኳቸው።

አሌክሳንድር የሆነውን ሁሉ የሰማ ሲሆን እሱም እንደ እኔ ፕዮትርን በጣም ጠላው። ከዚያም አሌክሳንድር ለውትድርና ተመልምሎ ሄደ። አባቴ እኔ ጋ መጥቶ መኖር የጀመረ ሲሆን ሉቦፍ ከኡጋንዳ ተመልሳ ለጥቂት ጊዜያት አብራን ቆየች። ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች እየረበሹን እንዳሉ እንዲሰማን የሚያደርጉ ሁኔታዎች ነበሩ። በተጨማሪም አባቴ አስፈሪ ሕልም ይታየው ነበር። ለእናቴ ሞት ምክንያት እሱ እንደሆነ ስለሚሰማው “ባንለያይ ኖሮ አትሞትም ነበር” እያለ ይናገራል። ብዙም ሳይቆይ አባቴ በከባድ የመንፈስ ጭንቀት የተዋጠ ሲሆን እናቴ ከሞተች ከአራት ወር በኋላ ራሱን ገደለ።

አባታችንን ከቀበርን በኋላ አሌክሳንድር ወደ ውትድርናው ሲመለስ ሉቦፍም ወደ ኡጋንዳ ሄደች። ከቤታችን የ30 ደቂቃ መንገድ ርቆ በሚገኘው መኬይቭክ በሚባል ከተማ የሕንፃ ምህንድስና ኢንስቲትዩት ትምህርቴን ቀጥዬ ኑሮን እንደ አዲስ ለመጀመር ሞከርኩ። አንዳንድ ትዝታዎቼን ለማጥፋት ስል ቤቱን አሳደስኩትና አስጌጥኩት። ያም ሆኖ የአጋንንት ተጽዕኖ አሁንም አላቆመም ብዬ እንድጠረጥር የሚያደርግ ሁኔታ ነበር።

“አምላክ ሆይ፣ በእርግጥ ካለህ”

አሌክሳንድር የውትድርና አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ ቤት ተመለሰ። ሆኖም እኔና እሱ መጨቃጨቅ ጀመርን። ሚስት ስለ አገባ 170 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአዞፍ ባህር ዳርቻ ወዳለችው ሮስቶፍ የምትባል የሩሲያ ከተማ ሄጄ ጥቂት ወራት ቆየሁ። ከዚያም ሳይቃጠል የቀረ የፕዮትር ዕቃ ካለ ለማጥፋት ወሰንኩ።

እኔም ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ስላደረብኝ ራሴን ለመግደል አስብ ጀመር። “አምላክ በእርግጥ ካለ” የሚለው የእናቴ አነጋገር ብዙ ጊዜ በጆሮዬ ያቃጭል ነበር። አንድ ቀን ማታ ለመጀመሪያ ጊዜ ጸለይኩ። “አቤቱ አምላክ ሆይ፣ በእርግጥ ካለህ የሕይወትን ትርጉም አሳውቀኝ” በማለት ለመንኩት። ከሁለት ቀን በኋላ ወደ ኡጋንዳ ሄጄ እንድጠይቃት ሉቦፍ የላከችው ደብዳቤ ደረሰኝ። ስለዚህ ራሴን የመግደል ሐሳቤን ለሌላ ጊዜ አስተላለፍኩት።

ኡጋንዳ ያጋጠመኝ ያልጠበቅሁት ነገር

በምድር ላይ እንደ ዩክሬይንና ኡጋንዳ ፈጽሞ የማይመሳሰሉ አገሮች ያሉ አይመስለኝም። የተሳፈርኩበት አውሮፕላን መጋቢት 1989 ኢንቴቤ አረፈ። ከአውሮፕላን ስወርድ ልክ ምድጃ ውስጥ የገባሁ መሰለኝ። እንደዚያ ያለ ሙቀት አጋጥሞኝ አያውቅም! ከሶቭየት ህብረት ውጪ ስጓዝ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ ስለነበር እንዲህ ቢሰማኝ አያስደንቅም። ሕዝቡ የሚናገረው እንግ​ሊዝኛ ሲሆን እኔ ደግሞ ይህን ቋንቋ መናገር አልችልም።

በመኪና 45 ደቂቃ ወደሚፈጀው ወደ ካምፓላ ለመጓዝ ታክሲ ተሳፈርኩ። የመሬቱ አቀማመጥ እኔ ከምኖርበት አካባቢ ፍጹም የተለየ ከመሆኑ የተነሳ ሌላ ፕላኔት ላይ ያለሁ መሰለኝ! ሾፌሩ በጣም ጥሩ ሰው ነበር፤ እዚያ ከደረስን በኋላ ሉቦፍና ባለቤትዋ የሚኖሩበትን ቤት አሳየኝ። እንዴት ያለ ግልግል ነው!

ሉቦፍ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና ነበር። ስለነዚህ ሰዎች ምንም የማውቀው ነገር አልነበረኝም። ሉቦፍ ግን ልትነግረኝ ጓጉታ ነበር። እኔ ቤቱን እየተዘዋወርኩ ስመለከት እየተከተለች ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ራእይ የተማረችውንና የምታውቀውን ሁሉ አንድ በአንድ ነገረችኝ። እውነቱን ለመናገር በጣም ነበር የተበሳጨሁት!

አንድ ቀን ሉቦፍን የሚያስጠኑአት የይሖዋ ምሥክሮች ሊጠይቋት መጡ። አንዷ ማሪያኔ ትባላለች። በወቅቱ እንግሊዝኛ ስለማላውቅ በቀጥታ ልትሰብክልኝ አልሞከረችም። ሆኖም ሞቅ ካለው አቀራረብዋና ወዳጃዊ አስተያየቷ ቅንና ደስተኛ ሴት መሆንዋን ተገነዘብኩ። “እነሆ! ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” ከሚለው ቡክሌት ላይ ገነትን ለመግለጽ የገባ አንድ ሥዕል አሳየችኝ። “ይቺን ሴት ተመልከቺ” አለችኝ። “እሷ አንቺ ነሽ፤ ይችኛዋ ደግሞ እኔ ነኝ። ሁለታችንም በገነት ውስጥ ከእነዚህ ሰዎች ጋር አንድ ላይ እንኖራለን። አያስደስትም?”

ካምፓላ ያሉት ሌሎች ምሥክሮችም ሉቦፍንና ጆሴፍን ለመጠየቅ ተራ የገቡ ይመስል ነበር። በጣም ተግባቢዎች ስለነበሩ እኔን ለመማረክ ሆነ ብለው እንደዚያ እያደረጉ ነው ብዬ አስቤ ነበር። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በጌታ እራት ላይ ተገኘሁ። (ሉቃስ 22:​19) የተነገረው ነገር ባይገባኝም ሰዎቹ ባላቸው የወዳጅነት መንፈስ በእጅጉ ተማረክሁ።

‘ከዳር እስከ ዳር አንብቢው’

ማሪያኔ የሩሲያ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠችኝ። ከዚያ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ አልነበረኝም። “ከዳር እስከ ዳር አንብቢው። አንዳንዱ ነገር ባይገባሽም እንኳ ማንበብሽን አታቋርጪ!” ስትል አደራ አለችኝ።

ማሪያኔ በሰጠችኝ ስጦታ በጣም ስለተደሰትኩ ምክሯን ለመከተል ወሰንኩ። ‘ደግሞም የማላነበው ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁ ቢኖረኝ ምን ይሠራልኛል?’ ስል አሰብኩ።

ወደ ዩክሬይን ስመለስ መጽሐፍ ቅዱሴን ይዤ ተመለስኩ። ለሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ሞስኮ ሩሲያ ውስጥ ሥራ ጀመርኩና በሚኖረኝ ትርፍ ሰዓት መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመርኩ። ከዘጠኝ ወራት በኋላ ወደ ኡጋንዳ በተመለስኩ ጊዜ አጋምሼው ነበር። ካምፓላ ከደረስኩ በኋላ ማሪያኔ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ወደፊት ስለሚመጣው አስደሳች ተስፋ አሳየችኝ። ገነት! ትንሣኤ! እማማንና አባባን እንደገና ላያቸው ነው ማለት ነው! ዴኔትስክ ሳለሁ ላቀረብኩት ጸሎት መልስ እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ።​—⁠ሥራ 24:​15፤ ራእይ 21:​3-5

ስለ ክፉ መናፍስት የሚናገረውን ርዕስ ስናጠና ትንፋሼ ቁርጥ ቁርጥ ይል ነበር። ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ ስጠረጥረው የነበረውን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ አረጋገጠልኝ። ጥሩ ወይም ጎጂ ያልሆነ ጥንቆላ የሚባል ነገር የለም። ሁሉም አደገኛ ነው። ለዚህ ደግሞ በቤተሰባችን ላይ ከደረሰው የበለጠ ማስረጃ ማግኘት አላስፈለገኝም። የፕዮትርን ንብረት ሳቃጥል ሳላውቅ ትክክል የሆነውን ነገር አድርጌ ነበር። የጥንት ክርስቲያኖችም አምላክን ማገልገል በጀመሩ ጊዜ ለአስማት ይጠቀሙባቸው የነበሩትን ጽሑፎች በሙሉ አቃጥለው ነበር።​—⁠ዘዳግም 18:​9-12፤ ሥራ 19:​19

መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ በተረዳሁ መጠን እውነትን እንዳገኘሁ እርግጠኛ እየሆንኩ ሄድኩ። ሲጋራ ማጨስ አቆምኩ፤ ከዚያም ሕይወቴን ለይሖዋ መወሰኔን ለማሳየት ታኅሣሥ 1990 ተጠመቅኩ። ሉቦፍ ከሦስት ወር በፊት የተጠመቀች ሲሆን ጆሴፍ ደግሞ በ1993 ተጠመቀ።

ወደ ዶኔትስክ ተመለስኩ

በ1991 ወደ ዶኔትስክ ተመለስኩ። በዚያው ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች በዩክሬይን ሕጋዊ እውቅና አገኙ፤ ይህ ማለት ደግሞ በነፃነት መሰብሰብና በግልጽ መስበክ ያስችለናል ማለት ነው። የማይቸኩል ሰው ስናገኝ መንገድ ላይ እናወያየው ነበር። ብዙም ሳይቆይ በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች በበዙባት በዚያች አገር ብዙዎች ስለ አምላክ መንግሥት የማወቅ ጉጉት እንዳደረባቸው ተገነዘብን።

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እጥረት ነበረብን። ስለዚህ በዴኔትስክ ጎዳናዎች ላይ ጽሑፎችን ለማዋስ ቤተ መጻሕፍት አቋቁመን ነበር። በከተማው ዋነኛ አደባባይ ላይ መደርደሪያ አቁመን መጻሕፍትንና ቡክሌቶችን ዘረጋን። የወዳጅነት ስሜት ያላቸው መጠየቅ የሚወዱ ሰዎች ቆም ብለው ጥያቄዎችን ይጠይቁን ጀመር። ጽሑፍ መውሰድ የሚፈልጉ በትውስት ይወስዱ የነበረ ሲሆን የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ እንጋብዛቸዋለን።

በ1992 አቅኚ ማለትም የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆንኩ፤ እንዲሁም መስከረም 1993 በዜልተርስ ጀርመን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ትርጉም ቡድን ውስጥ እንድሠራ ጥሪ ቀረበልኝ። መስከረም 1998 በዩክሬይን ሌቪፍ በመገንባት ላይ የነበረው አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ወደ ዋርሶ ፖላንድ ተዛወርን።

በዩክሬይን የይሖዋ ሕዝቦች ያሳዩት ጭማሪ በጣም የሚያስደንቅ ነው። በ1991 በዴንስክ 110 ምሥክሮች የሚገኙበት አንድ ጉባኤ ብቻ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከ3, 000 በላይ ምሥክሮች የሚገኙባቸው 24 ጉባኤዎች አሉ! በ1997 ወደ ዶኔትስክ ያደረግኩት ጉዞ አስደሳችም አስጨናቂም ነበር።

“ፕዮትር ሲፈልግሽ ነበር”

ዶኔትስክ በቆየሁባቸው ጊዜያት ስለ ቤተሰባችን የምታውቅ ጁልያ የምትባል የይሖዋ ምሥክር “ፕዮትር ሲፈልግሽ ነበር። ሊያነጋግርሽ ይፈልጋል” ስትለኝ በጣም ደነገጥኩ።

የዚያን ዕለት ሳለቅስና ወደ ይሖዋ ስጸልይ አደርኩ። ፕዮትር የሚፈልገኝ ለምንድን ነው? በሠራው ወንጀል ምክንያት ለዓመታት ወኅኒ ቤት መቆየቱን አውቃለሁ። ባደረገው ነገር ምክንያት በጣም ስለጠላሁት ይሖዋ ወደፊት ስለሚያመጣው አዲስ ዓለም ሊማር አይገባውም ብዬ አሰብኩ። ለጥቂት ቀናት ስለሁኔታው ከጸለይኩ በኋላ ግን የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚገባው ማን መሆኑን መወሰን ያለብኝ እኔ እንዳልሆንኩ ተገነዘብኩ። ኢየሱስ ክርስቶስ አጠገቡ ተሰቅሎ ለነበረው ወንጀለኛ በገነት ውስጥ አብረው እንደሚኖሩ የገባው ቃል ትዝ አለኝ።​—⁠ሉቃስ 23:​42, 43

ይህን በአእምሮዬ በመያዝ ፕዮትርን ሄጄ ለማነጋገርና ስለ መሲሐዊው መንግሥት እንዲሁም አምላክ ስለሚያመጣው አዲስ የነገሮች ሥርዓት ልመሰክርለት ወሰንኩ። ጁልያ በሰጠችኝ አድራሻ መሠረት ከሁለት ወንድሞች ጋር ሆኜ ልፈልገው ሄድኩ። እዚያም ከእናቴ ሞት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፕዮትር ጋር ፊት ለፊት ተገናኘሁ።

ሁኔታው አስጨናቂ ነበር። የይሖዋ ምሥክር መሆኔንና መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ በግል የሚገጥሙንን አሳዛኝ መከራዎች ጨምሮ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሁላችንም ችግሮች ለምን እንደሚደርሱብን እንድገነዘብ እንደረዳኝ ገለጽኩለት። እንዲሁም እናታችንን ከዚያም አባታችንን በሞት ማጣት ምን ያክል እንደሚያሳዝን ነገርኩት።

ፕዮትር እማዬን እንዲገድል የነገረውን አንድ ድምፅ ሰምቶ እንደነበረና በዚያ ቀን የሆነውን ሁሉ አንድ በአንድ አስረዳኝ። እየነገረን ያለውን ዘግናኝ ታሪክ ሳዳምጥ ታድኖ እንደተያዘ እንስሳ በጣም ፈርቶ ስለነበረ ጥላቻና ኃዘኔታ ተደባለቀብኝ። ፕዮትር ተናግሮ ካበቃ በኋላ በጣም አስደናቂ ስለሆኑት ተስፋዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላሳየው ሞከርኩ። በኢየሱስ እንደሚያምን ነገረኝ።

ስለዚህ “መጽሐፍ ቅዱስ አለህ?” ስል ጠየቅኩት።

“እስከ አሁን የለኝም። ሆኖም አንድ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲመጣልኝ ጠይቄአለሁ” ሲል መለሰልኝ።

“አዲስ ላይሆንብህ ይችላል፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የእውነተኛው አምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።”​—⁠መዝሙር 83:​18 NW

ገና ይህን ስም ሲሰማ ቁጭ ብድግ አደረገው። “ይህንን ስም አትጥሪብኝ። ይህ ስም ሲጠራ ይረብሸኛል” አለኝ። ከዚያ በኋላ አምላክ ስለ ገባው አስደሳች ተስፋ ለመንገር ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ።

ወደቤት ስመለስ:- ይሖዋን ባላውቅ ኖሮ እኔም እንደ እናቴ በሰው እጅ ልገደል ወይ እንደ አባቴ ራሴን ላጠፋ አለበለዚያ እንደ ፕዮትር አሰቃቂ ድርጊቶችን ልፈጽም እችል ነበር እያልኩ አስብ ነበር። እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ለማወቅ በመቻሌ ከልብ አመስጋኝ ነኝ!

ያለፈውን ሳይሆን የወደፊቱን መመልከት

እነዚህ አስጨናቂ ተሞክሮዎች የስሜት ጠባሳ ጥለውብኝ አልፈዋል። አሁንም እንኳ አንዳንዴ ትዝ ሲሉኝ ስቃይና ጭንቀት ይፈጥሩብኛል። ሆኖም ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ማወቅ ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ ከስቃዬ ማገገም ጀምሬአለሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ባለፈ ነገር ላይ ሳይሆን ወደፊት በሚመጣው ላይ እንዳተኩር አስተምሮኛል። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ እንዴት ያለ ብሩህ ተስፋ ሰጥቷቸዋል!

ይህ ብሩህ ተስፋ ከያዘልን ነገሮች አንዱ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ሙታን ትንሣኤ ማግኘታቸው ነው። ወላጆቼ ዳግም ሕይወት ሲያገኙ ማየት ምንኛ አስደሳች ይሆንልኛል! “እኛ በዚህች ምድር ላይ መጻተኞች ነን” የሚለው የአባቴ አነጋገር በአንድ በኩል ሲታይ እውነት ነበር ማለት ይቻላል። እናቴ አምላክ አለ ወደሚለው አስተሳሰብ ማዘንበልዋ ምንም ስህተት አልነበረውም። እናትና አባቴ አምላክ በሚያመጣው አዲስ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ትንሣኤ አግኝተው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማስተማር የምጀምርበትን ጊዜ በጣም እናፍቃለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 ስሙ ተቀይሯል።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከእናቴ ሞት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእርሷ ገዳይ ጋር ፊት ለፊት ተገናኘን

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኡጋንዳ ውስጥ ያስጠኑኝ ሚስዮናውያን ማሪያኔ እና ሄንዝ ቨርትሆለትስ እቅፍ አድርገውኝ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካምፓላ በተጠመቅኩበት ጊዜ

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዋርሶ፣ ፖላንድ በዩክሬይን ቋንቋ በትርጉም ሥራ ሳገለግል