በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቫይኪንጎች—ድል አድራጊዎችና ቅኝ ገዢዎች

ቫይኪንጎች—ድል አድራጊዎችና ቅኝ ገዢዎች

ቫይኪንጎች—ድል አድራጊዎችና ቅኝ ገዢዎች

ጊዜው 793 እዘአ ሰኔ ወር ላይ ነው። ከእንግሊዝ የኖርዝአምበርላንድ የባሕር ዳርቻ ርቃ በምትገኘውና ሆሊ ተብላም በምትጠራው ሊንደስፋርን የተሰኘች አነስተኛ ደሴት የሚኖሩት መነኮሳት እርጋታ በተሞላበት ሁኔታ ዕለታዊ ተግባራቸውን በማከናወን ላይ ናቸው። አነስተኛ ከፍታ ያላቸው ለዓይን የሚማርኩ መርከቦች በከፍተኛ ፍጥነት በማዕበሉ ላይ እየቀዘፉ ወደ ደሴቲቱ በመቃረብ ላይ መሆናቸውን አላወቁም ነበር። መርከቦቹ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ተጠግተው ቆሙ። ሰይፍና መጥረቢያ የያዙ በጺም የተሸፈነ አስፈሪ ፊት ያላቸው ሰዎች ከመርከቦቹ ላይ እየዘለሉ በመውረድ ገዳሙን ወረሩ። በፍርሃት በተሸበሩት መነኮሳት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ከፍተኛ እልቂት አደረሱ። ወራሪዎቹ በገዳሙ ውስጥ የነበሩትን ወርቅ፣ ብር፣ ዕንቁና ሌሎች ውድ ሀብቶች ከዘረፉ በኋላ ዳግመኛ ወደ ሰሜን ባሕር በማቅናት ተሰወሩ።

ዘራፊዎቹ ቫይኪንጎች ሲሆኑ በድንገት የሚፈጽሙት ወረራ የብዙዎችን አውሮፓውያን ትኩረት ከመሳቡም በላይ በቫይኪንጎች ታሪክ ውስጥ ታላቅ ምዕራፍ ከፍቷል። ብዙም ሳይቆይ ቫይኪንጎች በሕዝቡ ላይ ታላቅ ሽብር በመፍጠራቸው “ጌታ ሆይ፣ ከኖርዝሜን ቁጣ ሰውረን” የሚለው ጸሎት በመላው የእንግሊዝ ምድር ያስተጋባ ጀመር። *

ለመሆኑ ቫይኪንጎች እነማን ናቸው? በታሪክ ገጾች ላይ ድንገት ብቅ ብለው ለሦስት መቶ ዘመናት ገንነው ከቆዩ በኋላ እልም ብለው የጠፉ ያህል የሆኑት ለምንድን ነው?

ገበሬዎችና ዘራፊዎች

ቫይኪንጎች ከቫይኪንግ ዘመን 2, 000 ዓመት ገደማ አስቀድሞ ከሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ወደ ስካንዲኔቪያ ማለትም ወደ ዴንማርክ፣ ኖርዌይና ስዊድን መፍለስ የጀመሩት የጀርመን ሕዝቦች ዝርያዎች ናቸው። ለወረራ የሚሰማሩትን ጨምሮ ቫይኪንጎች እንደ ቅድመ አያቶቻቸው በግብርና የሚተዳደሩ ነበሩ። በጣም ቀዝቃዛ በሆኑት የስካንዲኔቪያ ክልሎች የሚኖሩት ደግሞ በአብዛኛው በአደን፣ ዓሣ በማጥመድ እንዲሁም የዓሣ ነባሪ ውጤቶችን በመሸጥ ይተዳደሩ ነበር። የቫይኪንግ ነጋዴዎች በትልልቅ ማኅበረሰቦች ታቅፈው ይኖሩ የነበረ ሲሆን ጠንካራ በሆኑ ጀልባዎቻቸው የአውሮፓ የንግድ መርከቦች በሚጓዙባቸው መስመሮች ይንቀሳቀሱ ነበር። ታዲያ እነዚህ ምንም ክፋት የማያውቁ የሚመስሉ ሰዎች በአንድ ትውልድ ውስጥ በድንገት ብቅ ብለው እንዲህ ሊገንኑ የቻሉት እንዴት ነው?

አንዱ ምክንያት የሕዝብ ቁጥር መብዛት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ብዙ ታሪክ ጸሐፊዎች ይህ አባባል ሊሠራ የሚችለው የተወሰነ የእርሻ መሬት በነበራት የምዕራብ ኖርዌይ ክልል ብቻ ነው ይላሉ። ዚ ኦክስፎርድ ኢሉስትሬትድ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ቫይኪንግስ “ከመጀመሪያዎቹ የቫይኪንግ ትውልዶች መካከል አብዛኞቹ ይፈልጉ የነበረው መሬት ሳይሆን ሀብት ነበር” ሲል ይገልጻል። ይህ አባባል በተለይ ሥልጣናቸውን ጠብቀው ለማቆየት ሲሉ ከፍተኛ ገቢ ይፈልጉ በነበሩት ነገሥታትና የነገድ አለቆች ላይ ይሠራል። ሌሎች ቫይኪንጎች ደግሞ ስካንዲኔቪያን ለቅቀው የወጡት በቤተሰብ መካከል የሚከሰተውን ቂም በቀልና የእርስ በርስ ጦርነትን በመሸሽ ሊሆን ይችላል።

ሌላው ምክንያት ደግሞ ባለጸጋ የሆኑ የቫይኪንግ ወንዶች ብዙውን ጊዜ ከአንድ በላይ ሚስት የማግባት ልማድ የነበራቸው መሆኑ ሊሆን ይችላል። በዚህም ሳቢያ ብዙ ልጆች ይወልዳሉ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ የቤተሰቡን ውርስ የሚያገኘው የበኩር ልጁ ብቻ በመሆኑ ሌሎቹ ልጆች ራሳቸው ጥረው ግረው ለመኖር ይገደዳሉ። ዘ በርዝ ኦቭ ዩሮፕ የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ ውርስ የተነፈጉ ወንዶች ልጆች “በአገር ቤት በሚገኝ ድልም ሆነ በባሕር ላይ በሚፈጸም ዝርፊያ የሚተዳደር በርካታ አባላት ያቀፈ አደገኛ ተዋጊ ቡድን መሠረቱ።”

ቫይኪንጎች ድንገተኛ ወረራ በመፈጸም ወዲያውኑ ከአካባቢው ለመሰወር የሚያስችሏቸው ረጃጅም መርከቦች ነበሯቸው። ታሪክ ጸሐፊዎች እነዚህን ረጃጅም መርከቦች በመካከለኛው ዘመን መጀመሪያ ላይ ከተፈበረኩ ምርጥ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተርታ በማሰለፍ ለመርከቦቹ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። በቀላሉ የመንሳፈፍ ባሕርይ ያላቸውና በተወጠረ ሸራ ወይም በመቅዘፊያዎች የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ማራኪ ቅርፅ ያላቸው መርከቦች ቫይኪንጎች በሚንቀሳቀሱበት ባሕር፣ ሐይቅና ወንዝ ሁሉ ላይ የበላይነት እንዲቀዳጁ አስችለዋቸዋል።

የቫይኪንጎች መስፋፋት

አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚሉት የቫይኪንግ ዘመን የጠባው በሊንደስፋርን ወረራ ከማካሄዳቸው ጥቂት ቀደም ብሎ በስምንተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ነው። ያም ሆነ ይህ ቫይኪንጎች በሊንደስፋርን ላይ ያካሄዱት ወረራ የሕዝብ ትኩረት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። አቅጣጫቸውን ከእንግሊዝ ወደ አየርላንድ በመቀየር ውድ በሆኑ ሀብቶች የተሞሉ ገዳማትን በድጋሚ ዒላማ አደረጉ። ቫይኪንጎች ረጃጅም መርከቦቻቸውን በምርኮና በባሮች ሞልተው የክረምቱን ወቅት ለማሳለፍ ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ። ይሁን እንጂ በ840 እዘአ ይህን ልማዳቸውን በመተው የክረምቱን ወቅት ዝርፊያ ባካሄዱባቸው አካባቢዎች አሳለፉ። እንዲያውም የአየርላንዷ ከተማ ደብሊን የቫይኪንጎች ከተማ ሆና ነበር። ከዚህም ሌላ በ850 እዘአ የክረምቱን ወራት በእንግሊዝ ምድርም ተቀምጠው ማሳለፍ የጀመሩ ሲሆን በቴምዝ ወንዝ ጫፍ ላይ የምትገኘው የታኔት ደሴት የመጀመሪያ ሰፈራቸው ሆነች።

ብዙም ሳይቆይ የዴንማርክና የኖርዌይ ቫይኪንጎች እንደ ቀድሞው ዘራፊዎች ሆነው ሳይሆን በደንብ የተደራጁ ተዋጊዎች ሆነው በረጃጅም የጦር መርከቦች ተጭነው ወደ ብሪታንያ ደሴቶች ደረሱ። ከእነዚህ መርከቦች አንዳንዶቹ እስከ 30 ሜትር የሚደርስ ርዝመት ሊኖራቸው ይችል የነበረ ሲሆን እስከ 100 ተዋጊዎች ሊጭኑ ይችላሉ። በቀጣዮቹ ዓመታት ቫይኪንጎች የእንግሊዝን ሰሜን ምሥራቅ ክልል በቁጥጥራቸው ሥር ያዋሉ ሲሆን በዚህ አካባቢ የዴንማርክ ባሕልና ሕግ እየገነነ በመሄዱ ቦታው ዴንሎው የሚል ስያሜ ለማግኘት በቅቷል። ይሁን እንጂ በደቡብ እንግሊዝ በዌሲክስ ግዛት የሳክሰን ንጉሥ የሆነው አልፍሬድና በእግሩ የተተኩት ነገሥታት ቫይኪንጎችን መመከት ችለው ነበር። ሆኖም በ1016 በአሺንግተን ከባድ ውጊያ ከተካሄደና በዚያው ዓመት መገባደጃ ላይ የዌሲክሱ ንጉሥ ኤድመንድ ከሞተ በኋላ ክርስቲያን ነኝ ይል የነበረው የቫይኪንግ መሪ ካንዩት ብቸኛው የእንግሊዝ ንጉሥ ሆነ።

አውሮፓን አካልሎ ወደ ሌሎች ድንበሮች መሻገር

በ799 እዘአ የዴንማርክ ቫይኪንጎች በወቅቱ ፍሪዣ በመባል የሚታወቀውን ከዴንማርክ አንስቶ እስከ ኔዘርላንድ ድረስ የተዘረጋውን የአውሮፓ የባሕር ጠረፍ ክልል መውረር ጀመሩ። ከዚያም ወረራቸውን በመቀጠል እንደ ለዎር እና ሴን ባሉት ወንዞች ላይ በመቅዘፍ በአውሮፓ እምብርት እስከሚገኙት ከተሞችና መንደሮች ድረስ በመዝለቅ ዘረፉ። በ845 እዘአ ቫይኪንጎች ፓሪስን ሳይቀር በዘበዙ። ቻርልስ ዘ ቦልድ በመባል የሚታወቀው የፍራንኮች ንጉሥ ከተማይቱን ለቅቀው እንዲወጡ 3, 000 ኪሎ ግራም የሚመዝን ብር ከፍሏቸዋል። እንደዚያም ሆኖ ግን በኋላ ተመልሰው በመምጣት ከፓሪስም አልፈው ትረዋን፣ ቬርዳንን እና ቱልን ወረሩ።

ከዚህም በተጨማሪ ቫይኪንጎች ወደ ስፔይንና ፖርቱጋል በማቅናት በታሪክ የሚታወቀውን የመጀመሪያውን ወረራ በ844 እዘአ አካሄዱ። የተለያዩ ትንንሽ ከተሞችን ከመበዝበዛቸውም በላይ ሴቪልን ለተወሰነ ጊዜ በቁጥጥራቸው ሥር አውለው ነበር። “ይሁን እንጂ” ይላል ካልቸራል አትላስ ኦቭ ዘ ቫይኪንግ ዎርልድ፣ “የአረብ መከላከያ ሠራዊት በኃይል ስለመከታቸው ቫይኪንጎች ሠራዊታቸው ተደምስሶ ማለት ይቻላል፣ ወዲያውኑ ለማፈግፈግ ተገደዱ።” ሆኖም በ859 እዘአ በ62 የጦር መርከቦች ተጭነው ተመልሰው መጡ። የስፔይንን የተወሰኑ ክፍሎች ካወደሙ በኋላ ሰሜን አፍሪካን ወረሩ። መርከቦቻቸው በምርኮ ቢሞሉም እንኳ ወደ ኢጣሊያ በማቅናት ፒዛንና ሊናን (ቀደም ሲል ሉና በመባል የምትታወቀውን) በዘበዙ።

ቫይኪንጎች ከስዊድን ተነስተው በስተ ምሥራቅ በኩል ቦልቲክን በማቋረጥ በምሥራቅ አውሮፓ ወደሚገኙት አንዳንድ ታላላቅ የውኃ ላይ የጉዞ መስመሮች ማለትም ቮልቾፍ፣ ሎቫት፣ ኒፐር እና ቮልጋ በመባል ወደሚታወቁት ወንዞች አቀኑ። በመጨረሻም ወደ ጥቁር ባሕርና በሀብት ወደ በለጸጉት የባይዛንታይን ግዛት መሬቶች ደረሱ። እንዲያውም አንዳንድ የቫይኪንግ ነጋዴዎች በቮልጋ ወንዝና በካስፒያን ባሕር በኩል ወደ ባግዳድ መጓዝ ችለዋል። ውሎ አድሮም የስዊድን የጎሳ አለቆች በኒፐርና በቮልጋ አካባቢ የሚገኙት የስላቭ ሰፋፊ መሬቶች ገዥዎች ሆነዋል። ወራሪዎቹ ሩስ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ሲሆን አንዳንዶች “የሩስ አገር” የሚል ትርጉም ያለው “ሩስያ” የሚለው ቃል የመጣው ከዚህ እንደሆነ ያምናሉ።

ወደ አይስላንድ፣ ግሪንላንድ እና ኒውፋውንድላንድ ማቅናት

የኖርዌይ ቫይኪንጎች ትኩረታቸውን ራቅ ብለው ወደሚገኙት በርካታ ደሴቶች አዙረው ነበር። ለምሳሌ ያህል በስምንተኛው መቶ ዘመን የኦርክኒን እና የሼትላንድን ደሴቶች ተቆጣጥረው የነበረ ሲሆን በዘጠነኛው መቶ ዘመን ደግሞ የፌሮንና የሄብረዲስን ደሴቶች እንዲሁም ምሥራቅ አየርላንድን ተቆጣጠሩ። እንዲያውም ቫይኪንጎች አይስላንድን በቅኝ ግዛት ይዘው ነበር። በዚያም የአልቲንግን ፓርላሜንት አቋቁመዋል። አሁንም ድረስ የአይስላንድ የአስተዳደር አካል የሆነው አልቲንግ በምዕራቡ ዓለም ካሉት የፓርላማ ሸንጎዎች ሁሉ በጥንታዊነቱ ግንባር ቀደሙን ስፍራ የያዘ ነው።

ቀዩ ኤሪክ የተባለው ቫይኪንግ በ985 እዘአ በግሪንላንድ ቅኝ ግዛት አቋቋመ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በዚያው ዓመት ብያድኒ ሄርዮልፍሰን የተባለ ሌላ ኖርስማን ከወላጆቹ ጋር ለመገናኘት ከአይስላንድ ወደ ግሪንላንድ መጓዝ ጀመረ። ሆኖም አቅጣጫውን ስቶ ግሪንላንድን አልፎ ሄደ። “ብያድኒ ሰሜን አሜሪካን ያየ የመጀመሪያው ኖርስማን ሳይሆን አይቀርም” ይላል ካልቸራል አትላስ ኦቭ ዘ ቫይኪንግ ዎርልድ።

የብያድኒን ሪፖርት መሠረት በማድረግ ከ1000 እዘአ በኋላ ሳይሆን አይቀርም፣ የቀዩ ኤሪክ ልጅ የሆነው ሌፍ ኤሪክሰን በስተ ምዕራብ ከግሪንላንድ ወደ ባፍን ደሴትና ወደ ላብረዶር የባሕር ዳርቻ ተጓዘ። ከዚያም በሥፍራው ከሚያድገው የዱር ወይን ወይም እንጆሪ በመነሳት ቪንላንድ የሚል ስያሜ ወደሰጠው ወደ ባሕር ገባ ያለ ርእሰ ምድር አቀና። * ሌፍ ወደ ግሪንላንድ የተመለሰው የክረምቱን ወቅት በዚያው ካሳለፈ በኋላ ነበር። በቀጣዩ ዓመት የሌፍ ወንድም ቱርቫል የተወሰኑ ሰዎች አስከትሎ ወደ ቪንላንድ የተጓዘ ቢሆንም ከአገሬው ተወላጆች ጋር በተፈጠረ ግጭት ተገደለ። ይሁን እንጂ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከ60 እስከ 160 የሚሆኑ ቫይኪንጎች በቪንላንድ የሠፈሩ ቢሆንም ከአገሬው ተወላጆች ጋር በነበረው የማያባራ ግጭት ሳቢያ ከሦስት ዓመት ገደማ ቆይታ በኋላ ዳግም ላይመለሱ አካባቢውን ለቅቀው ሄዱ። የእንግሊዝ ቅጥረኛ ሆኖ ይሠራ የነበረ ጆን ካቦት የተባለ ኢጣሊያዊ አገር አሳሽ ሰሜን አሜሪካ ለእንግሊዝ እንደምትገባ የተናገረው ወደ 500 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ነው።

የቫይኪንግ ዘመን ፍጻሜ

ቫይኪንጎች በዘመናቸው ፍጻሜ ላይ የስካንዲኔቪያ ሥርወ መንግሥቶች የሚያስተዳድሯቸው በርከት ያሉ አዳዲስ ፖለቲካዊ ግዛቶች አቋቁመዋል። ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ ብዙዎቹ ቫይኪንጎች በሄዱባቸው አካባቢዎች ካሉት ባሕሎች ጋር በመዋሃድ በሃይማኖት ጭምር ካገሬው ጋር እስከ መመሳሰል የደረሱ በመሆኑ ባዕድ እንደሆኑ ለረጅም ጊዜ አልዘለቁም። ለምሳሌ ያህል ኖርማንዲ (“የኖርዝሜን ምድር” ወይም ኖርማንስ ማለት ነው) የተባለውን በፈረንሳይ የባሕር ዳርቻ የሚገኘውን ክልል በከፊል የተቆጣጠረው ሮሎ የተባለው የቫይኪንግ የነገድ አለቃ እምነቱን ለውጦ ካቶሊክ ሆኗል። የኖርማንዲው መስፍን ዊልያም ከዝርያዎቹ አንዱ ነው። የኖርማንን ዝርያዎችና የእንግሊዝን ቫይኪንጎች እርስ በርስ ካፋለመው በ1066 በሄስቲንግዝ ከተካሄደው ውጊያ በኋላ ድል የተቀዳጀው መስፍኑ ዊልያም የእንግሊዝ ንጉሥ ሆኖ ዘውድ ደፋ።

ዊልያም እንግሊዝ ለየትኛውም የስካንዲኔቪያውያን ተጽዕኖ እንዳትንበረከክ ቀዳዳውን ሁሉ በመድፈን አፋጣኝ እርምጃ ከመውሰዱም በላይ በመካከለኛው ዘመን የነበረውን የፈረንሳይ የአስተዳደር ሥርዓት፣ የመሬት ባለቤትነት መብትና ኢኮኖሚያዊ አሠራር በማስፈን አገሪቱን ወደ ፊውዳል ዘመን አሸጋገረ። በመሆኑም “የቫይኪንግ ዘመን ያከተመበትን ዓመት ለይተን እናስቀምጥ ከተባለ” ይላል ዘ ቫይኪንግስ የተሰኘው በኤልዘ ሮስዳል የተዘጋጀው መጽሐፍ፣ “ከ1066 ሌላ የትኛውንም ዘመን ልንጠቅስ አንችልም።” ከዚህም በተጨማሪ በ11ኛው መቶ ዘመን በስካንዲኔቪያ የነበሩት የመጀመሪያዎቹ የቫይኪንግ ንጉሣዊ መንግሥታት ወደ ነፃ ብሔራዊ መንግሥታት ተለወጡ።

ሦስት መቶ ዘመናት ያስቆጠረው የቫይኪንግ ታሪክ በተለያዩ እንቅስቃሴዎችና ክንውኖች የተሞላ ነው። ቫይኪንጎች ሰይፍ እየመዘዙና መጥረቢያ እያነሱ ሕዝብ የሚጨርሱ ኋላ ቀር ወራሪዎች ብቻ አልነበሩም። በርቀት የሚገኙ አገሮችን በቅኝ ግዛትነት በመያዝና አልፎ ተርፎም በየሄዱበት ቦታ ከሚገጥማቸው ባሕል ጋር በመዋሃድ ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር መላመድ የሚችሉ መሆናቸውንም አሳይተዋል። በአገራቸው በግብርና ሥራ እየተዳደሩ ይኖሩ የነበረ ሲሆን በባዕድ አገሮች ደግሞ መንበረ ዙፋን ላይ ተቀምጠው አስተዳድረዋል። አዎን፣ ቫይኪንጎች በመርከበኝነትና በጦረኝነት ብቻ ሳይሆን በግብርናና በፖለቲካም የተዋጣላቸው መሆናቸውን አስመስክረዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ቫይኪንጎች ከስካንዲኔቪያ ውጪ ባሉት አገሮች ብዙውን ጊዜ አረማውያን፣ ዴንማርካውያን፣ ኖርዝሜን ወይም ኖርስሜን በሚሉት መጠሪያዎች ይታወቃሉ። አብዛኞቹ ዘመናዊ ታሪክ ጸሐፊዎች በቫይኪንግ ዘመን የነበሩትን ሁሉንም ስካንዲኔቪያውያን “ቫይኪንግ” በሚለው ቃል የሚጠሯቸው በመሆኑ እኛም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ይህንኑ መጠሪያ መጠቀም መርጠናል። “ቫይኪንግ” የሚለው ስያሜ ከየት እንደመጣ አይታወቅም።

^ አን.20 በኒውፋውንድላንድ ሰሜናዊ ጫፍ በሚገኘው በላንሶሜዶዝ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ በዚህ ሥፍራ የተገኘውን አርኪኦሎጂያዊ መረጃ መሠረት በማድረግ በሣር የተሸፈኑ የኖርስ ሕንፃዎች በድጋሚ ተገንብተዋል። ይህ መረጃ ቫይኪንጎች ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት በዚህ አካባቢ እንደነበሩ የሚጠቁም ቢሆንም ይህ መንደር በስፋት የሚነገርለት የቪንላንድ ምድር አካል መሆኑ አጠራጣሪ ነው።​—⁠የሐምሌ 8, 1999 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ተመልከት።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የቫይኪንግ ሃይማኖት

ቫይኪንጎች ኦዲን፣ ቶር፣ ፍሬይ፣ ፍሬያ እና ሄል የሚባሉትን ጨምሮ በአፈ ታሪክ የሚነገሩትን በርካታ አማልክት ያመልኩ ነበር። የጥበብና የጦርነት አምላክ የሆነው ኦዲን የሁሉም የበላይ ነው። ፍሪጋ ሚስቱ ነች። ቶር የጭራቆች ገዳይና የነፋሳትና የዝናብ ገዥ ነው። ፍሬይ ምግባረ ብልሹ የሆነ የሰላምና የመራባት አምላክ ነው። እህቱ ፍሬያ የፍቅርና የመራባት የሴት አምላክ ናት። ሄል ደግሞ የታችኛው ዓለም የሴት አምላክ ነች።

የኖርስ አፈ ታሪክ በእንግሊዝኛና በአንዳንድ ሌሎች ቋንቋዎች በሳምንት ውስጥ ላሉት አንዳንድ ቀናት ስያሜዎች መሠረት ሆኖ አገልግሏል። ቲዩስዴይ (ማክሰኞ) የሚለው ስያሜ የኦዲን (ዎደን በመባልም ይታወቃል) ልጅ ከሆነው ከቲር የተወሰደ ነው። ዌንስዴይ (ረቡዕ) የዎደን ቀን፣ ተርስዴይ (ሐሙስ) የቶር ቀን፣ ፍራይዴይ (ዓርብ) ደግሞ የፍሪጋ ቀን ማለት ነው።

እንደ አምላኪዎቻቸው ሁሉ የቫይኪንግ አማልክትም ሀብት ያካበቱት በስርቆት፣ በመገዳደርና በማታለል እንደሆነ ይነገራል። ኦዲን በውጊያ ጀብዱ ፈጽመው የሞቱ ሰዎች አስጋርድ (የአማልክት መኖሪያ) በመባል በሚታወቀው ሰማያዊ ዓለም በታላቁ ቫልሃላ አዳራሽ ቦታ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል። በዚያም እንደ ልባቸው እየበሉና እየጠጡ እንዲሁም እየተፋለሙ መኖር ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ የቫይኪንግ መኳንንት ሲቀበሩ ጀልባ ወይም በጀልባ ቅርጽ የተደረደሩ ድንጋዮች አብረዋቸው እንዲቀበሩ ይደረግ ነበር። ምግብ፣ የጦር መሣሪያዎች፣ ጌጣ ጌጦች፣ የታረዱ እንስሳት፣ ምናልባትም ደግሞ የተሠዋ ባሪያ ከአስከሬኑ ጋር አብረው ይቀበራሉ። አንዲት ንግሥት በምትሞትበት ጊዜ ደግሞ ገረዷ አብራ ልትቀበር ትችላለች።

ብዙውን ጊዜ ከቫይኪንጎች ጋር በተያያዘ የሚጠቀሰው ባለ ቀንድ የራስ ቁር ከቫይኪንጎች ዘመን 1, 000 ዓመታት አስቀድሞ ይሠራበት የነበረ ሲሆን ይደረግ የነበረው አንዳንድ ሥነ ሥርዓቶች ይካሄዱ በነበረበት ወቅት ብቻ ይመስላል። የቫይኪንግ ተዋጊዎች የራስ ቁር ማድረግ ከፈለጉ ያደርጉ የነበረው ከብረት ወይም ከቆዳ የተሠሩ ሾጣጣ ቅርፅ ያላቸው ተራ የራስ ቁሮችን ነበር።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የቫይኪንግ መስፋፋት

ኖርዌይ

አይስላንድ

ግሪንላንድ

ባፊን ደሴት

ላብረዶር

ኒውፋውንድላንድ

ዴንማርክ

እንግሊዝ

አየርላንድ

ኔዘርላንድ

ፈረንሳይ

ፖርቱጋል

ስፔይን

አፍሪካ

ኢጣሊያ

ስዊድን

ሩስያ

ካስፒያን ባሕር

ባግዳድ

ዩክሬይን

ጥቁር ባሕር

ኢስታንቡል

[ምንጭ]

Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቫይኪንጎችን ረጅም መርከብ በማስመሰል የተሠራ

[ምንጭ]

ገጽ 2 እና 22:- Antonion Otto Rabasca, Courtesy of Gunnar Eggertson

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የቫይኪንግ የጦር መሣሪያዎች

የቫይኪንግ የራስ ቁር

[ምንጭ]

የጦር መሣሪያዎችና የራስ ቁር:- Artifacts on display at the Museum of National Antiquities, Stockholm, Sweden

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሌፍ ኤሪክሰን