በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

አንዱን በሽታ ለማስወገድ ሌላ በሽታ መሸመት

“ከሠላሳ ዓመታት በፊት ከአምስት ግብፃውያን መካከል ሦስቱ ውኃ ውስጥ የሚኖሩ ቀንድ አውጣዎች በሚሸከሟቸው ጥገኛ ተውሳኮች ሳቢያ በሚከሰተው ቢልሃርዚያ የተሰኘ የሚያመነምን በሽታ ይጠቁ ነበር” ሲል ዚ ኢኮኖሚስት ገልጿል። ዘመናዊ መድኃኒቶችን በመጠቀም የተካሄዱት ፀረ ቢልሃርዚያ ዘመቻዎች አስጊውን ሁኔታ በእጅጉ ቀንሰውታል። ይሁን እንጂ መጀመሪያ ላይ ከተካሄዱት ዘመቻዎች አንዱ “በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቢልሃርዚያ ምትክ በግብፅ ምድር ዋነኛ የጤና ችግር የመሆን አዝማሚያ ላለው ሄፐታይተስ ሲ የተሰኘ ለሞት ሊዳርግ የሚችል ቫይረስ እንዲጋለጡ” ሳያደርግ አልቀረም። ለዚህ ምክንያት የሆነው ነገር ቢልሃርዚያን ለመዋጋት ጥቅም ላይ የዋሉት መርፌዎች “በተደጋጋሚ የተሠራባቸው መሆኑና በአብዛኛው ትክክለኛ በሆነ ጀርም አልባ የማድረግ ሂደት ውስጥ አለማለፋቸው ነው። . . . ሌላው ቀርቶ ሳይንቲስቶች ደም ወለድ የሆነውን ሄፐታይተስ ሲ ቫይረስ (ኤች ሲ ቪ) ለይተው ያወቁት በ1988 ነው” ይላል መጽሔቱ። የተካሄዱት ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ጊዜ ግብፅ “በዓለማችን ብዛት ያላቸው የሄፐታይተስ ሲ ተጠቂዎች የሚገኙባት አገር” ሆናለች። ወደ 11 ሚልዮን የሚጠጉ ግብፃውያን (ከ6 ግብፃውያን አንዱ ማለት ይቻላል) በሽታው ያለባቸው ሲሆን 70 በመቶ በሚሆኑት ላይ በሽታው ሥር ወደሰደደ የጉበት በሽታነት የሚለወጥ ከመሆኑም በላይ 5 በመቶዎቹን ለሞት ይዳርጋል። “ዶክተሮች ባላቸው መረጃ መሠረት በቫይረስ ሳቢያ የሚከሰት በሽታ በአንድ ጊዜ በዚህን ያህል መጠን የተሰራጨበት ሌላ አጋጣሚ እንደሌለ” የገለጸው ይህ መጽሔት “ትንሽ የሚያጽናናው ነገር ይህ መጠነ ሰፊ ዘመቻ ባይካሄድ ኖሮ ከዚህ ይበልጥ የብዙ ሰዎች ሕይወት በቢልሃርዚያ በሽታ ሊቀጠፍ ይችል የነበረ መሆኑ ነው” ሲል አክሎ ገልጿል።

ከልክ ያለፈ ንጽሕና?

በጀርመን ፍራይቡርግ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው ኢንቫይሮመንታል ሜዲስን ኤንድ ሆስፒታል ሃይጂን የተሰኘው ተቋም እንዳለው ከሆነ በቤት ውስጥ ለንጽሕና አገልግሎት በሚውሉ አንዳንድ የፋብሪካ ውጤቶች ውስጥ ያሉት ፀረ ባክቴሪያ ንጥረ ነገሮች ምንም ጠቀሜታ የሌላቸው አልፎ ተርፎም ጉዳት የሚያስከትሉ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል ቬስትፋሊሸ ናክሪክተን የተሰኘው የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል። “አንዳቸውም ቢሆኑ አስፈላጊ አይደሉም” ሲሉ የተቋሙ ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ፍራንትስ ዳሽነ ተናግረዋል። “እንዲያውም በተቃራኒው ተጠቃሚዎቹን ሊጎዱ ይችላሉ።” አንደኛ ነገር ከእንዲህ ዓይነቶቹ የፋብሪካ ውጤቶች አንዳንዶቹ በከፍተኛ ደረጃ አለርጂ የማስከተል ባሕርይ ያላቸውን ንጥረ ነገሮች የያዙ ናቸው። ዘገባው እንደሚለው መጥፎ ጠረን የያዙ ልብሶችን ለማንጻት እንዲሁ ማጠብ እንጂ ፀረ ባክቴሪያ ኬሚካሎችን መጠቀም አያስፈልግም። ዳሽነ “አካባቢያዊ ጉዳት የማያስከትሉ የንጽሕና መገልገያዎችን በመጠቀም በተለመደው መንገድ ንጽሕናን መጠበቁ በቂ ነው” ሲሉ ደምድመዋል።

ውጥረት የሚበዛባቸው ተማሪዎች

በትምህርት ዓመት መገባደጃ ላይ የሚኖረው የፈተና ጊዜ በብዙ ሕንዳውያን ልጆች ላይ ከባድ ውጥረት ያስከትላል ይላል ኤዥያን ኤጅ የተሰኘው የሙምባይ ጋዜጣ። ልክ የፈተና ጊዜ ሲደርስ ለማጥናት የሚደረገው ሩጫና ጥሩ ውጤት ለማምጣት የሚኖረው ጭንቀት አንዳንዶቹ ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ ይሆንባቸዋል። በተጨማሪም በፈተና ወቅት ወደ ሥነ አእምሮ ሐኪሞች የሚሄዱት ተማሪዎች ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል። አንዳንድ ወላጆች የልጆቻቸው የፈተና ውጤት ያማረ ሆኖ ለማየት ስለሚጓጉ ሁሉንም ዓይነት መዝናኛዎች ይከለክሏቸዋል። “ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድሩባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በተማሪዎቹ መካከል ፉክክር ይኖራል” ይላሉ የሥነ አእምሮ ሐኪም የሆኑት ቪ ኬ ሙንድራ። ብዙ ወላጆች “ልጃቸው ዘና እንዲል መርዳታቸው አእምሮውን እንደሚያድስለትና በተሻለ ሁኔታ እንዲያጠና ሊረዳው እንደሚችል አይገነዘቡም” ሲሉ አክለው ይገልጻሉ። ዶክተር ሀርሽ ሼቲ ፈተና “ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ [ክፍል] ባሉት ተማሪዎችም ላይ እንኳ ሳይቀር” ውጥረት እያሳደረ እንደመጣ ገልጸዋል።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚፈጸም ጋብቻ

በቅርቡ ብሔራዊ የቤተሰብ ጤና ድርጅት ያካሄደው ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ በሕንድ ትዳር ከሚመሠርቱት በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች መካከል 36 በመቶ የሚሆኑት ከ13 እስከ 16 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። በተጨማሪም ከ17 እስከ 19 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ልጃገረዶች መካከል 64 በመቶ የሚሆኑት ልጅ ወልደዋል አለዚያም ጸንሰዋል ሲል ኤዥያን ኤጅ የተሰኘው የሙምባይ ጋዜጣ ጥናቱን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። ከ20 እስከ 24 ባለው የዕድሜ ክልል ካሉት እናቶች ይልቅ ከ15 እስከ 19 ባለው የዕድሜ ክልል የሚገኙት እናቶች ከነፍሰ ጡርነት ጋር በተያያዙ ችግሮች ሊሞቱ የሚችሉበት አጋጣሚ በሁለት እጅ የሰፋ ነው ይላል ዘገባው። ከዚህም በላይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ15 እስከ 24 ባለው የዕድሜ ክልል በሚገኙት ወጣቶች መካከል በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉት ኢንፌክሽኖች በእጥፍ ጨምረዋል። ወጣቶቹ እውቀት የሚጎድላቸው መሆኑና ከጾታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ከእኩዮቻቸውና ከመገናኛ ብዙሃን የተሳሳተ መረጃ የሚያገኙ መሆኑ ለችግሩ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ጠበብት ይናገራሉ።