የፕሮስቴት ችግሮችን መቋቋም
የፕሮስቴት ችግሮችን መቋቋም
“ሀምሳ አራት ዓመት ሲሆነኝ ቶሎ ቶሎ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በየ30 ደቂቃው መሽናት ጀመርኩ። በዚህ የሕመም ምልክት ምክንያት ሐኪም አማከርኩና ፕሮስቴቴን ማስወጣት እንደሚያስፈልገኝ አወቅኩ።” በመላው ዓለም በሚገኙ የፕሮስቴት ክሊኒኮች ይህን የሚመስሉ ታሪኮች የተለመዱ ናቸው። አንድ ወንድ የፕሮስቴት ሕመም እንዳይደርስበት እንዴት መከላከል ይችላል? ሐኪም ማማከር የሚኖርበት መቼ ነው?
ፕሮስቴት የኮክ ፍሬ የመሰለ ቅርፅ ያለው ከፊኛ በስተግርጌ በሽንት ቱቦ ዙሪያ የሚገኝ እጢ ነው። (የወንድን የበጀድ አካባቢ የሚያሳየውን ሥዕላዊ መግለጫ ተመልከት።) የአንድ ጤነኛ የሆነ ዐዋቂ ወንድ ፕሮስቴት እጢ 20 ግራም ያህል ሲመዝን እጅግ ቢበዛ ከፊት ወደ ኋላ 4 ሳንቲ ሜትር ከላይ ወደ ታች 3 ሳንቲ ሜትር ከግራ ወደ ቀኝ 2 ሳንቲ ሜትር ይለካል። የፕሮስቴት ተግባር ከወንዴ የዘር ፈሳሽ 30 በመቶ የሚሆነውን ፈሳሽ ማመንጨት ነው። ይህ ሲትሪክ አሲድ፣ ካልስየምና ኢንዛይሞች የሚገኙበት ፈሳሽ የወንዴውን ዘር የመዋኘት ችሎታና ፅንስ የመፍጠር ችሎታ ሳያሻሽል አይቀርም። ከዚህም በላይ ከፕሮስቴት የሚመነጨው ፈሳሽ ውስጥ ዚንክ የተባለው ንጥረ ነገር ሲገኝ ይህም የመራቢያ አካላትን ከኢንፌክሽን እንደሚከላከል ሳይንቲስቶች ይገምታሉ።
ፕሮስቴት ሲታመም እንዴት ይታወቃል?
በወንዶች የበጀድ አካባቢ የሚሰሙ በርካታ የሕመም ስሜቶች ከፕሮስቴት እጢ ብግነት ወይም እብጠት ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ፕሮስታታይትስ ወይም የፕሮስቴት እጢ ብግነት ትኩሳት፣ በመሽናት ወቅት የሚሰማ ሕመምና የፊኛ አካባቢ ሕመም ሊያስከትል ይችላል። የፕሮስቴት እጢ በጣም በሚያብጥበት ጊዜ ሽንት እስከ መከልከል ይደርሳል። እጢው
የተቆጣው በባክቴሪያ ምክንያት በሚሆንበት ጊዜ ሕመሙ ባክቴሪያል ፕሮስታታይትስ ሲባል ችግሩ አጣዳፊ ወይም ለረጅም ጊዜ የቆየ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ በሽንት አባላካላት ላይ ከሚደርስ ኢንፌክሽን ጋር ይዛመዳል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ለፕሮስቴት ብግነት ምክንያት የሚሆነው ነገር ተለይቶ የማይታወቅ ሲሆን በዚህም ምክንያት በሽታው ነንባክቴሪያል ፕሮስታታይትስ ይባላል።የሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት፣ ሌሊት መሽናት፣ የሽንት የመፍሰስ ኃይል መቀነስና ከተሸናም በኋላ ፊኛ ባዶ እንዳልሆነ መሰማት የተለመዱ የፕሮስቴት ችግሮች መኖራቸውን የሚጠቁሙ ምልክቶች ናቸው። እነዚህ ምልክቶች ቢናይን ፕሮስታይትክ ሃይፐርፕላስያ (ቢ ፒ ኤች) ወይም የካንሰርነት ባሕርይ የሌለው የፕሮስቴት እብጠት መኖሩን ያመለክታሉ። ይህ ሕመም የሚያጠቃው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶችን ነው። በቢ ፒ ኤች የመያዝ አጋጣሚ እድሜ እየገፋ በሄደ መጠን እየጨመረ ይሄዳል። በሽታው 55 ዓመት ከሞላቸው ወንዶች መካከል 25 በመቶ በሚሆኑት ላይ 75 ዓመት ከሞላቸው ወንዶች መካከል ደግሞ 50 በመቶ በሚሆኑት ላይ ይገኛል።
በተጨማሪም ፕሮስቴት የካንሰርነት ባሕርይ ባለው እብጠት ሊጠቃ ይችላል። በአጠቃላይ የፕሮስቴት ችግር መኖሩን የሚጠቁሙ የሕመም ምልክቶች በማይኖሩበት ጊዜ እንኳን በየወቅቱ በሚደረግ መደበኛ ምርመራ የፕሮስቴት ካንሰር መኖሩን ማወቅ ይቻላል። ሕመሙ ሥር ሲሰድና ሲባባስ የሽንት መስመር መዘጋትና የፊኛ መወጠር ያስከትላል። ካንሰሩ ወደ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች ሲሰራጭም የወገብ ሕመም፣ የነርቭ መቃወስና በሊምፋቲክ ሲስተም መዘጋት ምክንያት የእግር እብጠት ሊደርስ ይችላል። በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 300, 000 ሰዎች በፕሮስቴት ካንሰር ሲያዙ 41, 000 የሚያክሉት በዚሁ በሽታ እንደሞቱ ተዘግቧል። ከ60 እስከ 69 ዓመት ከሆናቸው ወንዶች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑትና ከ80 እስከ 89 ዓመት ከሆናቸው መካከል 67 በመቶ የሚሆኑት በፕሮስቴት ካንሰር እንደሚያዙ ሳይንቲስቶች ያምናሉ።
በበሽታው የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ የሆኑት እነማን ናቸው?
ከ50 ዓመት እድሜ በኋላ በፕሮስቴት ካንሰር የመያዝ እድል በአፋጣኝ እንደሚያድግ በምርምር ተረጋግጧል። በዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ካንሰር የሚያዙት ጥቁሮች
ከነጮቹ በእጥፍ ይበልጣሉ። የበሽታው ስርጭት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተለያየ ሲሆን በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ አገሮች ከፍተኛ፣ በደቡብ አሜሪካ መካከለኛ፣ በእስያ ደግሞ ዝቅተኛ ነው። ይህም በፕሮስቴት ካንሰር እድገት ረገድ አካባቢያዊ ሁኔታዎች ወይም የአመጋገብ ልዩነት ትልቅ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ያመለክታል። አንድ ሰው የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ ወደሆነበት አገር ሲዛወር የእርሱም በበሽታው የመያዝ እድል ሊጨምር ይችላል።የፕሮስቴት ካንሰር ሕመምተኛ የሆኑ ዘመዶች ያሏቸው ወንዶች በበሽታው የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል። የአሜሪካ የካንሰር ማኅበር “በፕሮስቴት ካንሰር የተያዘ አባት ወይም ወንድም ያለው ሰው በበሽታው የመያዝ እድሉ በእጥፍ ይጨምራል” በማለት ያብራራል። እድሜ፣ ዘር፣ ብሔር፣ የቤተሰብ የጤና ሁኔታ፣ አመጋገብና አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ በበሽታው የመያዝን እድል ከፍ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች አንዳንዶቹ ናቸው። ቅባት የበዛበት ምግብ የሚያዘወትሩና
አካላዊ እንቅስቃሴ የማያደርጉ ሰዎች በፕሮስቴት ካንሰር የመያዛቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ነው።የፕሮስቴት በሽታዎችን መከላከል
ሳይንቲስቶች የፕሮስቴት ካንሰር ትክክለኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ገና በውል ያላወቁ ቢሆንም የዘር ውርሻና የሆርሞን ሁኔታዎች ድርሻ እንደሚኖራቸው ያምናሉ። ሁለቱን ሁኔታዎች ማለትም አመጋገብንና አካላዊ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የምንችል መሆኑ ጥሩ ነገር ነው። የአሜሪካ የካንሰር ማኅበር “ከእንስሳት የሚገኙ ከፍተኛ የቅባት መጠን ያላቸውን ምግቦች መቀነስና በአብዛኛው ከዕፅዋት የሚገኙ ምግቦች መመገብ” ጥሩ እንደሆነ ይመክራል። በተጨማሪም “በየቀኑ አምስት ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ ፍራፍሬና አትክልት መመገብ” እንዲሁም ዳቦ፣ ጥራጥሬ፣ ፓስታ፣ ሩዝ፣ ባቄላና ሌሎች የእህል ውጤቶችን ማዘውተር ጥሩ እንደሆነ ይገልጻል። ቲማቲም፣ ግሬፕ ፍሩትና ከርቡሽ ላይኮፒንስ በተባለው ንጥረ ነገር የበለጸጉ ሲሆኑ ይህ ንጥረ ነገር በዲ ኤን ኤ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል ባሕርይ ስላለው ከፕሮስቴት ካንሰር ሊከላከል ይችላል። በተጨማሪም አንዳንድ ጠበብት ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶችና ሚኒራሎች መውሰድ ሊጠቅም እንደሚችል ይናገራሉ።
የአሜሪካ ካንሰር ማኅበርም ሆነ የአሜሪካ ዩሮሎጂካል ማኅበር የፕሮስቴት ካንሰር መኖርና አለመኖሩን በሕክምና ምርመራ ማረጋገጥ ሕይወት አድን ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ። ካንሰር መኖሩ ገና ከጅምሩ ከታወቀ የሚሰጠው ሕክምና የተሳካ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ይሆናል። የአሜሪካ የካንሰር ማኅበር ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ወንዶች ወይም በበሽታው የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ከሆኑት የሚመደቡ ከሆኑ ደግሞ ከ45 ዓመት በላይ የሆናቸው ሁሉ ዓመታዊ ምርመራ ቢያደርጉ እንደሚበጃቸው ይመክራል። *
ምርመራው ፕሮስቴት-ስፔሲፊክ አንቲጅን የተባለውን የደም ምርመራ (ፒ ኤስ ኤ) የሚጨምር መሆን አለበት። ይህ አንቲጅን የፕሮስቴት ሕዋሳት የሚሠሩት ፕሮቲን ነው። የፕሮስቴት ሕመም በሚኖርበት ጊዜ የዚህ አንቲጅን መጠን ከፍተኛ ይሆናል። የአሜሪካ የካንሰር ማኅበር “የፒ ኤስ ኤ ምርመራህ ውጤት ከመደበኛው መጠን ከፍ ያለ ከሆነ በካንሰር የመያዝ እድልህ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነና ተጨማሪ ምርመራ ያስፈልግህ እንደሆነ ከሐኪምህ ጋር ተመካከር” ይላል። ይህ እጢ የሚገኘው በሽለላንጀት (rectum) አካባቢ በመሆኑ ዶክተሩ በፕሮስቴት እጢ ላይ ሊኖር የሚችለውን ጤናማ ያልሆነ ሁኔታ ዳብሶ (የዲ አር ኢ ምርመራ በማካሄድ) ሊያውቅ ይችላል። (በገጽ 18 ላይ የሚገኘውን የወንዱን የበጀድ ክፍል የሚያሳየውን ሥዕል ተመልከት።) “የፒ ኤስ ኤ ወይም የዲ አር ኢ ምርመራ ችግር መኖሩን በሚጠቁምበት ጊዜ” እና ዶክተሩ በፕሮስቴት እጢው ላይ የባዮፕሲ ምርመራ እንዲደረግ ማዘዝ ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ሲያስፈልገው የሽለላንጀት አካባቢ አልትራ ሳውንድ ምርመራ (ቲ አር ዩ ኤስ) በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ይህ ምርመራ 20 ደቂቃ ያህል ይወስዳል።
ዓመታዊው የዩሮሎጂ ምርመራ የፕሮስቴት ካንሰር መኖርና አለመኖሩን ለማጣራት ከማስቻሉም በላይ ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ቢ ፒ ኤች መኖር አለመኖሩን ገና ከጅምሩ ስለሚያሳውቅ ይበልጥ ቀለል ባለ ሕክምና በሽታውን ለመቆጣጠር ያስችላል። (“የቢ ፒ ኤች ሕክምና” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በንጹሕ ሥነ ምግባር መመላለስም አንድን ሰው ፕሮስታታይትስ ሊያስከትሉ ከሚችሉ የአባለዘር በሽታዎች ሊጠብቀው ይችላል።
ለፕሮስቴት እጢህ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግህ አስፈላጊ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ሰው ከተደረገለት ቀዶ ሕክምና ሙሉ በሙሉ አገግሟል። በእርሱ አስተያየት “ሁሉም ወንዶች” ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ባይኖራቸው እንኳን “በየዓመቱ የሕክምና ምርመራ ማድረግ ይኖርባቸዋል።”
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.13 በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ከሆነ “የቢናይን ፕሮስቴቲክ ሃይፐርፕላስያ (ቢ ፒ ኤች) ምልክቶች” የሚለውን ሣጥን እንድትመለከት እናበረታታሃለን።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የቢናይን ፕሮስታቲክ ሃይፐርፕላስያ (ቢ ፒ ኤች) ምልክቶች
መመሪያ:- ከታች ያሉትን ጥያቄዎች ተስማሚውን ቁጥር በማክበብ መልስ።
ከ1-6 ድረስ ላሉት ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ:-
0—ፈጽሞ የለም
1—ከአምስቱ ከአንድ ጊዜ በታች
2—ከግማሽ ጊዜ በታች
3—ለግማሽ ጊዜ
4—ከግማሽ ጊዜ በላይ
5—ሁልጊዜ ማለት ይቻላል
1. ባለፈው ወር ሸንተህ ከጨረስህ በኋላ ፊኛህ ሙሉ በሙሉ ባዶ እንዳልሆነ የተሰማህ ስንት ጊዜ ነው? 0 1 2 3 4 5
2. ባለፈው ወር ከሁለት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ድጋሚ ለመሽናት የተገደድከው ስንት ጊዜ ነው? 0 1 2 3 4 5
3. ባለፈው ወር በምትሸናበት ጊዜ ሽንትህ ቁርጥ ቁርጥ እያለ ያስቸገረህ ስንት ጊዜ ነው? 0 1 2 3 4 5
4. ባለፈው ወር ሽንትህን ቋጥረህ ለመቆየት የተቸገርክባቸው ጊዜያት ምን ያህል ይሆናሉ? 0 1 2 3 4 5
5. ባለፈው ወር የሽንትህ አወራረድ ደካማ የሆነው ስንት ጊዜ ነው? 0 1 2 3 4 5
6. ባለፈው ወር አምጠህ የሸናኸው ስንት ጊዜ ነው? 0 1 2 3 4 5
7. ባለፈው ወር ከተኛህበት አንስቶ ጧት እስከተነሣህበት ጊዜ ሽንት ለመሽናት የተነሣኸው በአማካይ ስንት ጊዜ ነው? (ስንት ጊዜ እንደተነሳህ የሚጠቁመውን ቁጥር አክብብ።) 0 1 2 3 4 5
የተከበቡት ቁጥሮች ድምር የቢ ፒ ኤች ምልክቶችህ ጠቅላላ ውጤት ይሆናል። አነስተኛ:- 0-7፣ መካከለኛ:- 8-19፣ ከባድ:- 20-35
[ምንጭ]
(ከአሜሪካ ዩሮሎጂካል ማኅበር የተወሰደ)
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የቢ ፒ ኤች ሕክምና
▪ መድኃኒቶች:- እንደ በሽተኛው የሕመም ምልክቶች የተለያዩ መድኃኒቶች ሊወሰዱ ይችላሉ። ተስማሚውን መድኃኒት ሊያዝልህ የሚችለው ሐኪምህ ብቻ ነው።
▪ ክትትል ማድረግ:- በሽተኛው ምንም ዓይነት መድኃኒት መውሰድ ሳያስፈልገው በተወሰኑ ጊዜያት ምርመራ ያደርጋል።
▪ ቀዶ ሕክምና:-
(ሀ) ትራንስዩሬትራል ሪሴክሽን ኦቭ ዘ ፕሮስቴት (ቲ ዩ አር ፒ ) የተሰኘው ቀዶ ሕክምና ሲካሄድ ቀዶ ሐኪሙ በሽንት ቧንቧው በኩል የኤሌክትሪክ ቀለበት ያለበት መሣሪያ (ሬሴክቶስኮፕ) ያስገባና በሽተኛውን ህብረሕዋስ እየቆረጠ ደም ሥሮቹን ይዘጋል። የውጪውን ቆዳ መቅደድ አያስፈልግም። ቀዶ ሕክምናው 90 ደቂቃ ያህል ይፈጃል። ትራንስዩሬትራል ቀዶ ሕክምና የሚያደርሰው ቁስል ቆዳ በመቅደድ ከሚሰጠው ሕክምና በጣም ያነሰ ነው።
(ለ) ትራንስዩሬትራል ኢንሲዥን ኦቭ ፕሮስቴት (ቲ ዩ አይ ፒ ) ከቲ ዩ አር ፒ ጋር ተመሳሳይ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ አሠራር የፊኛውን አንገትና ራሱን የፕሮስቴት እጢውን ከውስጥ በኩል ትንሽ በመቁረጥ የሽንት ቱቦው እንዲሰፋ ይደረጋል።
(ሐ) ቆዳ በመክፈት ሕክምና የሚሰጠው ፕሮስቴቱ በጣም በማበጡ ምክንያት ትራንስዩሬትራል ቀዶ ሕክምና ማድረግ በማይቻልበት ጊዜ የሚደረግ ነው። የውጩን ቆዳ መክፈት ግዴታ ይሆናል።
(መ) የሌዘር ቀዶ ሕክምና የሌዘር ጨረሮችን በመጠቀም ያበጡትን የፕሮስቴት ህብረሕዋሶች በማትነን የሚሰጥ ቀዶ ሕክምና ነው።
የሚሰጠውን የሕክምና ዓይነት የሚወስነው በሽተኛው ነው። ያውም ሕክምና ለመውሰድ ፈቃደኛ ከሆነ ነው። በቅርቡ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ የወጣ ዘገባ እንዳመለከተው በሽታው በተለይ በእድሜ በገፉ ወንዶች “ጤንነት ላይ ዘላቂ ጉዳት የማያደርስና እድገቱ አዝጋሚ ሆኖ እያለ ለበሽታው የሚሰጠው ሕክምና ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል” አንዳንድ ጠበብት የፕሮስቴት ካንሰር መኖርና አለመኖሩን ለማጣራት የሚካሄደው ምርመራ አስፈላጊነቱ እምብዛም አይታያቸውም።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከቀዶ ሕክምናው በፊት ዶክተሩን ልትጠይቅ የምትችላቸው ጥያቄዎች
1. ይሻላል የምትለው የትኛውን የሕክምና ዓይነት ነው?
2. ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልገኝ ለምንድን ነው?
3. ከቀዶ ሕክምና ሌላ አማራጭ አለ?
4. ቀዶ ሕክምና ማድረጉ ምን ጥቅም ይኖረዋል?
5. ቀዶ ሕክምና ማድረጉ ምን አደጋ ሊኖረው ይችላል? (እንደ ደም መፍሰስ ወይም ስንፈተ ወሲብ ያሉ ችግሮች)
6. ቀዶ ሕክምና ባላደርግስ?
7. ሌላ ሐሳብ ከየት ላገኝ እችላለሁ?
8. እንዲህ ዓይነቱን ቀዶ ሕክምና ያለ ደም በማከናወን ረገድ ምን ተሞክሮ አለህ?
9. ቀዶ ሕክምናው የሚደረገው የት ነው? የሆስፒታሉ ሐኪሞችና ነርሶች በሽተኛው ደም በመውሰድ ረገድ ያለውን መብት ያከብራሉ?
10. ምን ዓይነት ሰመመን መውሰድ ያስፈልገኛል? ሰመመን ሰጪው ደም ሳይሰጥ በሚደረግ ቀዶ ሕክምና ልምድ አለው?
11. ለመዳን ምን ያህል ጊዜ ይወስድብኛል?
12. ቀዶ ሕክምናው ምን ያህል ያስከፍለኛል?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የወንድን የበጀድ አካባቢ የሚያሳይ ሥዕላዊ መግለጫ
ፊኛ
ፕሮስቴት
ሽለላንጀት
የሽንት ቱቦ
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለጤና ተስማሚ የሆነ አመጋገብና ልከኛ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በፕሮስቴት ካንሰር የመያዝን ዕድል ሊቀንስ ይችላል