ትዳራችሁን መታደግ ትችላላችሁ!
ትዳራችሁን መታደግ ትችላላችሁ!
መጽሐፍ ቅዱስ ባሎችንም ሆነ ሚስቶችን ሊጠቅሙ በሚችሉ ተግባራዊ ምክሮች የተሞላ ነው። ይህ ደግሞ ሊያስደንቀን አይገባም። ምክንያቱም የጋብቻ መሥራች መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ ያስጻፈው አምላክ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ትዳርን ሥሎ የሚያቀርብበት መንገድ ከእውነታው ያልራቀ ነው። ባልና ሚስቶች “መከራ” ወይም ኒው ኢንግሊሽ ባይብል እንደሚለው “ሥቃይና ሐዘን” እንደሚያጋጥማቸው ሳይሸሽግ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ይሁን እንጂ ጋብቻ ደስታ እንዲያውም የስሜት እርካታ ሊያስገኝ እንደሚችልና ማስገኘትም እንዳለበት ይናገራል። (ምሳሌ 5:18, 19) እነዚህ ሁለት ሐሳቦች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አይደሉም። አንድ ባልና ሚስት ከባድ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም የጠበቀና ፍቅር የሰፈነበት ዝምድና ሊመሠርቱ እንደሚችሉ የሚያመለክቱ ናቸው።
በእናንተ ትዳር ውስጥ እንዲህ ያለው ዝምድና ተጓድሏል? በአንድ ወቅት በመካከላችሁ የነበረው ቅርርብና ደስታ በሐዘንና ምሬት ተውጦአል? ትዳራችሁ ፍቅር ከራቀው በርካታ ዓመታት ያለፉ ቢሆን እንኳ ያጣችሁትን መልሳችሁ ማግኘት ትችላላችሁ። እርግጥ፣ ከእውነታው የራቀና ሊሆን የማይችል ነገር መመኘት የለባችሁም። ፍጹም ያልሆኑ ወንድና ሴት ፍጹም የሆነ ትዳር ሊመሠርቱ አይችሉም። ቢሆንም አፍራሽ የሆኑ አዝማሚያዎችን ለመቀልበስ ልትወስዷቸው የምትችሏቸው እርምጃዎች አሉ።
ከዚህ ቀጥሎ የሰፈረውን ሐሳብ በምታነቡበት ጊዜ በተለይ የራሳችሁን ትዳር የሚመለከቱትን ነጥቦች ለይታችሁ ለማውጣት ሞክሩ። በትዳር ጓደኛችሁ ጉድለቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ልትሠሩባቸው የምትችሏቸውን አንዳንድ ሐሳቦች በመምረጥ ቅዱስ ጽሑፋዊውን ምክር በሥራ አውሉ። ትዳራችሁ ከገመታችሁት የበለጠ ተስፋ እንዳለው ትገነዘቡ ይሆናል።
ለትዳር ጓደኛችሁ ያላችሁ ስሜትና ስለገባችሁት ቃል ኪዳን ያላችሁ አመለካከት ግንባር ቀደም ቦታ ስለሚኖረው በመጀመሪያ ሊኖራችሁ ስለሚገባው ዝንባሌ እንነጋገር።
ስለ ቃል ኪዳናችሁ ያላችሁ አመለካከት
በትዳራችሁ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ጥረት ለማድረግ አርቆ አሳቢ መሆን አስፈላጊ ነው። አምላክ ጋብቻን የመሠረተው ሁለት ሰብዓዊ ፍጥረታትን ሊለያዩ በማይችሉበት ሁኔታ ለማጣመር አስቦ ነው። (ዘፍጥረት 2:24፤ ማቴዎስ 19:4, 5) ስለዚህ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ያላችሁ ዝምድና በፈለጋችሁ ጊዜ ትታችሁት እንደምትሄዱት ሥራ ወይም የኪራይ ውላችሁን በመሰረዝ ብቻ ጓዛችሁን ጠቅልላችሁ እንደምትለቁት ቤት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ስታገቡ የመጣው ቢመጣ ከትዳር ጓደኛዬ ጋር ተቆራኝቼ እኖራለሁ ብላችሁ ቃል ገብታችኋል። ኢየሱስ ክርስቶስ 2, 000 ከሚያክሉ ዓመታት በፊት “እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” በማለት ያረጋገጠው ይህን ጥብቅ ቃል ኪዳን ነው።—ማቴዎስ 19:6
አንዳንዶች ‘አሁንም አብረን እየኖርን ነው። ታዲያ ይህ ቃል ኪዳናችንን የምናከብር መሆናችንን አያረጋግጥምን?’ ይሉ ይሆናል። ምናልባት ያረጋግጥ ይሆናል። ይሁን እንጂ በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች መግቢያ ላይ እንደተገለጸው አብረው የሚኖሩ አንዳንድ ባልና ሚስቶች ፍቅር በጠፋበት ትዳር ውስጥ ስለተጠመዱ ወደፊትም ሆነ ወደኋላ ሊያንቀሳቅስ በማይችል ነውጠኛ ባሕር ላይ እንዳሉ ያህል ናቸው። የእናንተ ግብ ትዳራችሁ ተቻችላችሁ የምትኖሩበት ብቻ ሳይሆን ደስታ የምታገኙበትም እንዲሆን ማድረግ መሆን ይገባዋል። ቃል ኪዳን አክባሪነታችሁ ለጋብቻ ዝግጅት ብቻ ሳይሆን ልትወዱትና ልትንከባከቡት ለማላችሁለት ግለሰብ በምታሳዩት ታማኝነት መንጸባረቅ ይኖርበታል።—ኤፌሶን 5:33
ለትዳር ጓደኛችሁ የምትናገሩት ነገር ለቃል ኪዳናችሁ ያላችሁ አክብሮት ምን ያህል የጠለቀ መሆኑን ሊያሳይ ይችላል። ለምሳሌ አንዳንድ ሚስቶች ወይም ባሎች በመካከላቸው የተነሳው ጭቅጭቅ በሚጋጋልበት ጊዜ ሳይታወቃቸው “ጥዬህ እሄዳለሁ!” ወይም “ሌላ የሚወደኝ ሰው እፈልጋለሁ!” ይላሉ። እንደነዚህ ያሉት አነጋገሮች ከልብ ያልተነገሩ ቢሆኑም ምንጊዜም በሩ ክፍት እንደሆነና ተናጋሪው ባሰኘው ጊዜ ለመሄድ ዝግጁ መሆኑን በመጠቆም ቃል ኪዳኑን ሊያላሉት ይችላሉ።
ፍቅር በትዳራችሁ ውስጥ ዳግመኛ እንዲሰፍን እንደዚህ ያለውን ማስፈራሪያ ከንግግራችሁ አስወግዱ። አንድ ቀን መልቀቃችሁ እንደማይቀር የምታውቁትን ቤት ታስጌጣላችሁ? ታዲያ እንዴት የትዳር ጓደኛችሁ ሊፈርስ ለሚችል ትዳር እንድትለፋ ወይም እንዲለፋ ትጠብቃላችሁ? መፍትሔ ለማስገኘት ልባዊ ጥረት ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።
አንዲት ሴት ከባልዋ ጋር ብጥብጥ የነገሠበት ጊዜ ካሳለፈች በኋላ ያደረገችው ይህንን ነበር። “በእሱ ላይ ምንም ያህል ጥላቻ ቢያድርብኝ እንኳ ልፈታው አስቤ አላውቅም። ምንም ዓይነት ጉድለት ቢፈጠር በሆነ መንገድ እንጠግነው ነበር። አሁን ውጣ ውረድ ከበዛበት የሁለት ዓመት ጉዞ በኋላ በደስታ መኖር ጀምረናል ብዬ በሐቀኝነት ለመናገር እችላለሁ” ብላለች።
አዎን፣ ቃል ኪዳን ማክበር ማለት ተቻችሎ መኖር ሳይሆን ለጋራ ግብ አብሮ በቅንጅት መሥራት ማለት ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ባለው ወቅት ላይ ጋብቻችሁ ከመፍረስ የዳነው የገባችሁበትን ግዴታ በማክበራችሁ ብቻ እንደሆነ ሊሰማችሁ ይችላል። እንዲህ ከተሰማችሁ ተስፋ አትቁረጡ። የነበራችሁን ፍቅር መመለስ ትችላላችሁ። እንዴት?
የትዳር ጓደኛችሁን ማክበር
መጽሐፍ ቅዱስ “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር . . . ይሁን” ይላል። (ዕብራውያን 13:4፤ ሮሜ 12:10) እዚህ ላይ “ክቡር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌሎች ቦታዎች ላይ “ውድ፣” “ብርቅ፣” “ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው” ተብሎ ተተርጉሟል። ለአንድ ነገር ከፍተኛ ግምት ወይም ዋጋ ስንሰጥ ለዚያ ነገር የሚያስፈልገውን እንክብካቤ ለማድረግ ማንኛውንም ጥረት እናደርጋለን። አንድ በጣም ውድ የሆነ አዲስ መኪና ያለው ሰው ለመኪናው ምን ያህል ጥንቃቄ እንደሚያደርግ አስተውላችሁ ይሆናል። ውድ ዋጋ ያወጣበትን መኪና ሁልጊዜ ይወለውለዋል፣ አስፈላጊውንም ጥገና ያደርግለታል። ትንሽ ጭረት ቢያይበት እንኳን ከመጠን በላይ ይበሳጫል! ሌሎች ደግሞ ለጤንነታቸው ይህንን የመሰለ ጥንቃቄ ሲያደርጉ ይታያሉ። ለምን? ለጤንነታቸው ከፍተኛ ዋጋ ስለሚሰጡ ሊጠብቁት ይፈልጋሉ።
ለትዳራችሁም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ጥንቃቄና ጥበቃ 1 ቆሮንቶስ 13:7) “ከመጀመሪያውም ቢሆን በመካከላችን እውነተኛ ፍቅር አልነበረም” ወይም “የምናደርገውን አናውቅም ነበር” ወይም “ገና ሳንበስል ነበር የተጋባነው” ብላችሁ ትዳራችሁን ማደስ የምትችሉበትን አጋጣሚ በመዝጋት አስቀድማችሁ እጃችሁን ከመስጠት ይልቅ ሁኔታው ይሻሻላል የሚል ተስፋ ይዛችሁ ለመሻሻል የሚያስችሏችሁን እርምጃዎች በመውሰድ ውጤቱን ለምን በትዕግሥት አትጠብቁም? አንዲት የጋብቻ አማካሪ “ሊያነጋግሩኝ የሚመጡት ብዙዎቹ ሰዎች ‘ከዚህ በላይ መቋቋም አልችልም!’ ይሉኛል። ዝምድናቸውን በፈርጅ በፈርጁ ከፋፍለው መሻሻል የሚያስፈልገው የትኛው ጎን እንደሆነ ከመመርመር ይልቅ በጋራ የሚካፈሏቸውን እሴቶች፣ በጥንቃቄ ያካበቱትን የጋራ ታሪክና ሊኖራቸው የሚችለውን የወደፊት ተስፋ ጨምሮ መላ ትዳራቸውን በችኮላ አሽቀንጥረው ይጥላሉ” ብለዋል።
አድርጉ። መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “ሁሉን ተስፋ ያደርጋል” ይላል። (ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በጋራ ያሳለፋችሁት ታሪክ ምን ይመስላል? ምንም ያህል ችግር ቢያጋጥማችሁ ትዝ የሚላችሁ አስደሳች ጊዜ፣ ያገኛችሁት ጥሩ ውጤት ወይም በጋራ የተወጣችሁት ችግር ሳይኖር አይቀርም። እነዚህን መለስ ብላችሁ አስቡና ዝምድናችሁን ለማሻሻል ልባዊ ጥረት በማድረግ ትዳራችሁንና የትዳር ጓደኛችሁን እንደምታከብሩ አሳዩ። ይሖዋ የትዳር ጓደኞች አንዳቸው ሌላውን እንዴት እንደሚይዙ በትኩረት እንደሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። ለምሳሌ በነቢዩ ሚልክያስ ዘመን ይሖዋ በሰበብ አስባቡ ሚስቶቻቸውን እየፈቱ ያታልሏቸው የነበሩትን እስራኤላውያን ባሎች ወቅሷል። (ሚልክያስ 2:13-16) ክርስቲያኖች ትዳራቸው ለይሖዋ አምላክ ክብር የሚያመጣ እንዲሆን ይፈልጋሉ።
ግጭት—ምን ያህል ከባድ ነው?
በጋብቻ ውስጥ ለፍቅር መጥፋት ዋነኛው ምክንያት ባልና ሚስቱ በመካከላቸው የሚፈጠረውን ግጭት መፍታት አለመቻላቸው ይመስላል። ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት የሆኑ ሰዎች ስለሌሉ በሁሉም ጋብቻዎች አልፎ አልፎ አለመግባባት መፈጠሩ አይቀርም። ይሁን እንጂ ሁልጊዜ የሚጋጩ ባለትዳሮች ከዓመታት በኋላ ፍቅራቸው እንደቀዘቀዘ ይገነዘቡ ይሆናል። እንዲያውም ‘ከመጀመሪያውም የምንጣጣም አልነበርንም። ሁልጊዜ እንደተጣላን ነው’ ብለው እስከ መደምደም ሊደርሱ ይችላሉ።
ይሁን እንጂ ግጭት መኖሩ ለአንድ ትዳር ግብዓተ መሬት መሆን የለበትም። ጥያቄው ግጭቱ መያዝ ያለበት እንዴት ነው? የሚለው ነው። በተሳካ ትዳር ውስጥ ባልና ሚስቱ አንድ ዶክተር እንዳሉት “አብረው የሚኖሩ ጠላቶች” ሳይሆኑ ስለ ችግሮቻቸው መነጋገር ይችላሉ።
“አንደበት ያለው ኃይል”
እናንተም ሆናችሁ የትዳር ጓደኛችሁ ስለ ችግሮቻችሁ እንዴት መናገር እንዳለባችሁ ታውቃላችሁ? ሁለታችሁም ችግሮቻችሁን አውጥታችሁ ለመናገር ፈቃደኞች መሆን አለባችሁ። ይህ በእውነትም ለመማር ብርቱ ጥረት የሚያስፈልገው ችሎታ ነው። ለምን? አንደኛ ነገር፣ ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችን አልፎ አልፎ ‘በቃል እንሰናከላለን።’ (ያዕቆብ 3:2) ከዚህ አልፎ ደግሞ አንዳንዶች ያደጉት ግልፍተኛ የሆነ ወላጅ ባለበት ቤት ውስጥ ነው። ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምረው በቁጣ መገንፈል ወይም መሳደብ መጥፎ ነገር እንዳልሆነ ተምረው ያድጋሉ። እንዲህ ባለው ሁኔታ ሥር ያደገ ልጅ “ቁጡ ሰው” ወይም “ወፈፍተኛ” ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 29:22) በተመሳሳይ እንዲህ ባለው ቤት ያደገች ሴት ‘ጨቅጫቃና ነዝናዛ’ መሆኗ አይቀርም። (ምሳሌ 21:19፣ የ1980 ትርጉም ) ሥር የሰደዱ አስተሳሰቦችንና የአነጋገር ልማዶችን ነቅሎ ለማውጣት ቀላል አይሆንም። *
ስለዚህ ግጭቶችን በአግባቡ ለመፍታት አዳዲስ የሐሳብና የስሜት አገላለጾችን መማር ያስፈልጋል። ይህ እንደ ቀላል የሚታይ ነገር አይደለም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው” ይላል። (ምሳሌ 18:21) አዎን፣ የትዳር ጓደኛችሁን የምታነጋግሩበት መንገድ ከቁም ነገር የሚገባ መስሎ ባይታይም ዝምድናችሁን ሊያድሰውም ሆነ ሊያፈርሰው ይችላል። “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ። የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው” ይላል ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ።—ምሳሌ 12:18
በዚህ ረገድ ዋናው በደለኛ የትዳር ጓደኛችሁ እንደሆነ ቢሰማችሁም አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ስለምትናገሩት ነገር አስቡ። የምትናገሯቸው ቃላት የሚያቆስሉ ናቸው ወይስ የሚፈውሱ? ቁጣ የሚያነሳሱ ናቸው ወይስ የሚያበርዱ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች” ይላል። በአንጻሩ ደግሞ “የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች።” (ምሳሌ 15:1) ሻካራ ቃላት በዝግታ ቢነገሩም እንኳን ሁኔታውን ማጋጋላቸው አይቀርም።
እርግጥ የተረበሻችሁበት ነገር ካለ ስሜታችሁን የመግለጽ መብት አላችሁ። (ዘፍጥረት 21:9-12) ይህን ለማድረግ ግን የሽሙጥ፣ የስድብ ወይም የሚያዋርዱ ቃላት መጠቀም አስፈላጊ አይደለም። በራሳችሁ ላይ የጸና ገደብ አብጁ። “አልወድሽም” ወይም “አንቺን ያገባሁበት ቀን የተረገመ ይሁን” እንደሚሉት ያሉትን ቃላት በትዳር ጓደኛችሁ ላይ ፈጽሞ ላለመሰንዘር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። በተጨማሪም ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ በቀጥታ ትዳርን አስመልክቶ ባይሆንም እንኳ ‘በቃል መዋጋትና በረባ ባልረባው መጨቃጨቅ’ ሲል ከገለጸው ነገር መራቅ ጥበብ ነው። * (1 ጢሞቴዎስ 6:4, 5 NW ) የትዳር ጓደኛችሁ እንደነዚህ ባሉት ዘዴዎች የሚጠቀም ከሆነ እናንተ አጸፋውን መመለስ አያስፈልጋችሁም። ሰላምን ለመከታተል የበኩላችሁን አድርጉ።—ሮሜ 12:17, 18፤ ፊልጵስዩስ 2:14
ጭቅጭቁ ተካርሮ ስሜት በሚጋጋልበት ጊዜ አነጋገርን መቆጣጠር ቀላል እንደማይሆን አይካድም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ “አንደበትም እሳት ነው” ብሏል። “አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም። የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው።” (ያዕቆብ 3:6, ) ታዲያ ቁጣ እየተካረረ ሲሄድ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? የትዳር ጓደኛችሁን በግጭቱ ላይ ፍም በሚጨምር ሳይሆን ግጭቱን በሚያበርድ መንገድ ማነጋገር የምትችሉት እንዴት ነው? 8
የከረሩ ግጭቶችን ማብረድ
አንዳንዶች የትዳር ጓደኛቸው ባደረገው ነገር ላይ ሳይሆን በራሳቸው ስሜት ላይ ሲያተኩሩ ቁጣቸውን ለማብረድና ለመሠረታዊ ችግራቸው መፍትሔ ለማግኘት እንደቀለላቸው ተገንዝበዋል። ለምሳሌ “አስከፍተሽኛል” ወይም “እንዲህ ማለት አይገባሽም” ከማለት ይልቅ “የተናገርሽው ነገር አስከፍቶኛል” ማለቱ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል። እርግጥ የተሰማችሁን ስሜት በምትገልጹበት ጊዜ የድምፃችሁ ቃና ምሬት ወይም ንቀት የተቀላቀለበት መሆን የለበትም። ዓላማችሁ የተፈጠረው ችግር ላይ እንዲተኮር ማድረግ እንጂ ግለሰቡን በቀጥታ ማጥቃት መሆን የለበትም።—ዘፍጥረት 27:46–28:1
በተጨማሪም ምንጊዜም ቢሆን ‘ዝም ለማለትም ሆነ ለመናገር ጊዜ እንዳለው’ አስታውሱ። (መክብብ 3:7) ሁለት ሰዎች አንድ ላይ የሚናገሩ ከሆነ አንዳቸውም ስለማያዳምጡ ምንም የሚገኝ ውጤት አይኖርም። ስለዚህ አዳማጮች የምትሆኑበት ተራ ሲደርስ ‘ለመስማት የፈጠናችሁ ለመናገር ደግሞ የዘገያችሁ ሁኑ።’ ‘ለቁጣ የዘገያችሁ’ መሆናችሁም የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። (ያዕቆብ 1:19) የትዳር ጓደኛችሁ የሚናገረውን እያንዳንዱን ሻካራ ንግግር ቃል በቃል አትውሰዱ። ‘ለቁጣ ችኩል አትሁኑ።’ (መክብብ 7:9) ከዚህ ይልቅ ከትዳር ጓደኛችሁ ንግግር በስተጀርባ ያለውን ስሜት ለመረዳት ሞክሩ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቁጣ ያዘገየዋል፣ ለበደለኛውም ይቅር ይል ዘንድ ክብር ይሆንለታል” ይላል። (ምሳሌ 19:11) አንድ ባል ወይም ሚስት አስተዋይ መሆናቸው ከግጭቱ በስተጀርባ ያለውን ሁኔታ ለመመልከት ይረዳቸዋል።
ለምሳሌ አንዲት ሚስት ባልዋ ከእርሷ ጋር በቂ ጊዜ እንደማያሳልፍ አማርራ ስትናገር ስለ ሰዓትና ደቂቃ ብቻ መናገሯ አይደለም። በይበልጥ ስለ ስሜቷ እንደማያስብ ወይም ደንታ ቢስ እንደሆነ መናገሯ ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይ አንድ ባል ሚስቱ የሆነ ያልሆነውን እንደምትገዛ አማርሮ ሲናገር የሚናገረው ስለ ብርና ስለ ሣንቲም ብቻ ላይሆን ይችላል። በይበልጥ በውሳኔው ላይ የእርሱ ሐሳብ አለመጠየቁ እንዳስከፋው መግለጹ ሊሆን ይችላል። አስተዋይ የሆነ ባል ወይም አስተዋይ የሆነች ሚስት የጉዳዩን ውጪያዊ ገጽታ ብቻ ሳይሆን ወደ ችግሩ እምብርት ጠልቀው ይመለከታሉ።—ምሳሌ 16:23
እንዲህ ማድረግ የመናገሩን ያህል ይቀላል? እንደማይቀል የታወቀ ነው! አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም ደግነት የጎደላቸው ቃላት ይሰነዘራሉ፣ የስሜት መጋጋልም ይኖራል። እንዲህ ያለው ሁኔታ መጀመሩን ስትመለከቱ የምሳሌ 17:14ን ምክር መከተል ሊያስፈልጋችሁ ይችላል:- “ጠብ ሳይበረታ አንተ ክርክርን ተው።” ስሜታችሁ በረድ እስኪል ንግግሩን አቁሞ ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ምንም ስህተት የለበትም። ከቁጥጥር ውጭ ሳትሆኑ በእርጋታ መነጋገር ካልቻላችሁ አንድ የጎለመሰ ወዳጃችሁ አብሯችሁ እንዲቀመጥና ችግራችሁን ለመፍታት እንዲረዳችሁ መጠየቅ ጥሩ ሊሆን ይችላል። *
ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት መያዝ
ትዳራችሁ ስትጠናኑ በነበረበት ወቅት አልማችሁት የነበረውን ዓይነት ሳይሆን ቢቀር ተስፋ አትቁረጡ። አንድ የጠበብት ቡድን “ትዳር ለአብዛኞቹ ሰዎች ፍጻሜ የሌለው ደስታ ብቻ የሚገኝበት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ አስደሳች በሌሎች ጊዜያት ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል” ብሏል።
አዎን፣ ትዳር በፍቅር ልብ ወለድ ታሪኮች የሚገለጸው ዓይነት አይሁን እንጂ ሐዘን ብቻ የሚያስከትል መሆን የለበትም። ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተቻችላችሁ ለመኖር የምትገደዱበት ጊዜ ቢኖርም በመካከላችሁ የተፈጠረውን አለመግባባት ገሸሽ አድርጋችሁ አንድ ላይ በመሆናችሁ ብቻ የምትደሰቱበት፣ የምትጫወቱበትና እንደ ወዳጆች የምትነጋገሩበት ጊዜም ይኖራል። (ኤፌሶን 4:2፤ ቆላስይስ 3:13) የቀዘቀዘውን ፍቅራችሁን ለማቀጣጠል የምትችሉበት አጋጣሚ እንዲህ ያለው ጊዜ ሊሆን ይችላል።
ፍጹማን ያልሆኑ ሁለት ሰዎች ፍጹም የሆነ ትዳር ሊመሠርቱ እንደማይችሉ አስታውሱ። ቢሆንም መጠነኛ የሆነ ደስታ ማግኘት ይችላሉ። በእርግጥም ችግሮች መኖራቸው ባይቀርም በእናንተና በትዳር ጓደኛችሁ መካከል ያለው ዝምድና የከፍተኛ እርካታ ምንጭ ሊሆንላችሁ ይችላል። አንድ ነገር እርግጠኛ ሁኑ:- እናንተና የትዳር ጓደኛችሁ የጋራ ጥረት ካደረጋችሁ፣ እንደ አስፈላጊነቱ ለመለወጥ ፈቃደኛ ከሆናችሁና አንዳችሁ የሌላውን ጥቅም ከፈለጋችሁ ትዳራችሁን ለመታደግ እንደምትችሉ ለማመን በቂ ምክንያት ይኖራችኋል።—1 ቆሮንቶስ 10:24
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.22 የወላጆች ተጽዕኖ በትዳር ጓደኛ ላይ ሻካራ ቃል ለመናገር ሰበብ አይሆንም። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ዝንባሌ ሥር ሊሰድና ለመንቀል አስቸጋሪ ሊሆን የሚችልበትን ምክንያት ለመረዳት ያስችላል።
^ አን.25 “በረባ ባልረባው መጨቃጨቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛው ቃል “እርስ በርስ መናቆር” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።
^ አን.31 የይሖዋ ምሥክሮች የጉባኤ ሽማግሌዎችን እርዳታ ሊጠይቁ ይችላሉ። የጉባኤ ሽማግሌዎች በባለትዳሮች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባታቸው አግባብ ባይሆንም ችግር የገጠማቸውን ባለትዳሮች ሊረዱ ይችላሉ።—ያዕቆብ 5:14, 15
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የምትናገሯቸው ቃላት የሚያቆስሉ ናቸው ወይስ የሚፈውሱ?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ኳሱን ቀስ ብላችሁ ወርውሩ
መጽሐፍ ቅዱስ “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደተቀመመ፣ በጸጋ ይሁን” ይላል። (ቆላስይስ 4:6) ይህ በትዳር ውስጥም በጣም የሚሠራ ምክር ነው! በምሳሌ ለማስረዳት የተወረወረ ኳስ የመቅለብ ጨዋታ እየተጫወታችሁ ነው እንበል። ኳሱን የምትወረውሩት ቀስ አድርጋችሁ በቀላሉ ሊቀለብ በሚችል መንገድ ነው። ጓደኛችሁን እንዲጎዳ አድርጋችሁ በኃይል አትወረውሩትም። ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በምትነጋገሩበት ጊዜም ይህንኑ ሥርዓት ተከተሉ። መራራና ሻካራ ቃላትን መወርወር ጉዳት ከማስከተል ሌላ ፋይዳ አይኖረውም። ከዚህ ይልቅ የትዳር ጓደኛችሁ ልታስተላልፉ የፈለጋችሁትን ነጥብ መጨበጥ በሚችልበት መንገድ በዝግታና በለሰለሰ አንደበት ተናገሩ።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ትዝ ይበላችሁ!
ቀደም ባሉት ዘመናት የተለዋወጣችኋቸውን ደብዳቤዎች ወይም ካርዶች አንብቡ። ፎቶግራፎቻችሁን ተመልከቱ። ‘ወደ ትዳር ጓደኛዬ የሳበኝ ነገር ምን ነበር? በጣም አደንቅ የነበረው የትኞቹን ባሕርያት ነው? በምን ዓይነት እንቅስቃሴዎች እንካፈል ነበር? ያስቁን የነበሩት ነገሮች ምንድን ናቸው?’ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። ከዚያ በኋላ እንዲህ ዓይነቶቹን ትዝታዎቻችሁን እያነሳችሁ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተነጋገሩ። “እንዲህ የሆነበት ጊዜ ትዝ ይልሃል/ሻል?” በማለት የሚጀምር ጭውውት በአንድ ወቅት ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር የነበራችሁን የጋራ ስሜት ሊቀሰቅስ ይችላል።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የትዳር ጓደኛ ብትለውጡም ችግራችሁ አይለወጥም
ፍቅር በጠፋበት ትዳር ውስጥ ተጠምደው እንደተያዙ የሚሰማቸው አንዳንድ ባለትዳሮች ከአዲስ የትዳር ጓደኛ ጋር አዲስ ሙከራ ለማድረግ ይፈተናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ምንዝርን ያወግዛል። እንዲህ ያለውን ኃጢአት የሚሠራ “አእምሮ የጎደለው [“ሞኝ፣” ኒው ኢንግሊሽ ባይብል]” እንደሆነና ‘ነፍሱንም እንደሚያጠፋ’ ይናገራል። (ምሳሌ 6:32) በመጨረሻም ምንዝር የፈጸመው ሰው ንስሐ ካልገባ የአምላክን ሞገስ ያጣል። ይህ ደግሞ ከማንኛውም ዓይነት ውድቀት የከፋ ይሆንበታል።—ዕብራውያን 13:4
ምንዝር መፈጸም ሞኝነት እንደሆነ በሌሎች መንገዶችም ማየት ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ አዲስ የትዳር ጓደኛ ያፈራ ሰው የመጀመሪያ ትዳሩን ያፈረሱበትን ችግሮች አሁንም እንደገና መጋፈጡ አይቀርም። ዶክተር ዳያን ሜድቬድ ሌላ ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ ያነሳሉ:- “አዲሷ ተጓዳኝህ ስላንተ ያወቀችው የመጀመሪያው ነገር የትዳር ጓደኛህን ለመክዳት ፈቃደኛ የሆንክ ሰው መሆንህን ነው። ቃል የገባህለትን ግለሰብ እንደምትከዳ ታውቃለች። በተጨማሪም ሰበብ ለመፍጠር አንደኛ እንደሆንክ፣ ከገባኸው ቃል በቀላሉ ልትወሰድ እንደምትችል፣ ስሜታዊ ደስታ ወይም የግል ፍላጎት በቀላሉ የምትያዝበት ወጥመድ እንደሆነ ታውቃለች። . . . ሁለተኛዋስ የትዳር ጓደኛህ እንደገና በሌላ ሴት እንደማትወሰድ እንዴት እርግጠኛ ልትሆን ትችላለች?”
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች የሚገኝ ጥበብ
• ምሳሌ 10:19:- “በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም፤ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው።”
በምትናደዱበት ጊዜ ያላሰባችሁትን ነገር ልትናገሩና በኋላ ልትቆጩ ትችላላችሁ።
• ምሳሌ 15:18:- “ቁጡ ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ ትዕግሥተኛ ሰው ግን ጸጥ ያሰኘዋል።”
አጥንት የሚሰብር ነገር መናገር የትዳር ጓደኛችሁ ስህተቱን አምኖ እንዳይቀበል ሊያደርግ የሚችል ሲሆን በትዕግሥት ማዳመጥ ግን ሁለታችሁም መፍትሔ ለማግኘት ጥረት እንድታደርጉ ይረዳል።
• ምሳሌ 17:27:- “ጥቂት ቃልን የሚናገር አዋቂ ነው፣ መንፈሱም ቀዝቃዛ የሆነ አስተዋይ ነው።”
ቁጣችሁ እየተጋጋለ እንደሄደ ከተሰማችሁ ወደ ከረረ ጠብ ከመድረሳችሁ በፊት ዝም ብትሉ ጥሩ ይሆናል።
• ምሳሌ 29:11:- “ሰነፍ ሰው ቍጣውን ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል።”
ራስን መግዛት በጣም አስፈላጊ ነው። በቁጣ ገንፍሎ መጥፎ ቃላት መሰንዘር የትዳር ጓደኛችሁን ከማራቅ ሌላ ምንም ፋይዳ አይኖረውም።