በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከመቶ ዓመት በፊት የመጀመሪያው

ከመቶ ዓመት በፊት የመጀመሪያው

ከመቶ ዓመት በፊት የመጀመሪያው

የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር ሕጋዊ የመተዳደሪያ ደንብ ታኅሣሥ 15, 1884 በዩ ኤስ ኤ፣ ፔንስልቬኒያ በመንግሥት ደረጃ እውቅና አገኘ። * በፔንስልቬኒያ የማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት ተቋቋመ። ከጊዜ በኋላ ሚያዝያ 23, 1900 በለንደን፣ እንግሊዝ ለመጀመሪያው ቅርንጫፍ ቢሮ መሥሪያ የሚሆን ቦታ ተገኘ። ቦታው እዚህ ላይ እንደሚታየው በምሥራቅ ለንደን በ131 ጂፕሲ ሌን፣ ፎረስት ጌት አካባቢ ይገኝ ነበር።

ከመቶ ዓመት በፊት የመጀመሪያው ቅርንጫፍ ቢሮ ሲቋቋም እንግሊዝ ውስጥ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው የሚጠሩ በድምሩ 138 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ከሁለት ዓመት በኋላ በ1902 በጀርመን ሁለተኛ ቅርንጫፍ ቢሮ የተከፈተ ሲሆን በ1904 ደግሞ ተጨማሪ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በአውስትራሊያና በስዊዘርላንድ ተቋቋሙ።

አንደኛው የዓለም ጦርነት ባበቃበት ዓመት በ1918 በዓለም ዙሪያ በስብከቱ ሥራ በመካፈል ላይ የነበሩ 3, 868 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሪፖርት ያደርጉ ነበር። በቀጣዩ ዓመት አምስተኛው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ በካናዳ ተቋቋመ። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በፍጥነት እየተዳረሰ ሲሄድ በበርካታ አገሮች ውስጥ አዳዲስ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የተከፈቱ ሲሆን በ1921 ብቻ እንኳ ስድስት ቢሮዎች ተቋቋሙ።

በ1931 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስም መጠቀም ሲጀምሩ በዓለም ዙሪያ 40 ቅርንጫፍ ቢሮዎች ነበሩ። (ኢሳይያስ 43:​10-12) በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ቁጥሩ ወደ 49 አደገ! በ1938 ከፍተኛ ቁጥራቸው 59, 047 የደረሰ በ52 አገሮች ውስጥ የሚሰብኩ ምሥክሮች ነበሩ። ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት በበርካታ አገሮች ውስጥ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ከባድ ተቃውሞ መቃጣት ጀምሮ ነበር።

ፖለቲካዊ የበላይነትና አምባገነንነት ከአገር ወደ አገር እየተስፋፋ ሲሄድና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መስከረም 1939 ሲፈነዳ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች በበርካታ አገሮች ውስጥ ተዘጉ። በ1942 ሥራ ያላቆሙት 25 ቅርንጫፍ ቢሮዎች ብቻ ነበሩ። የሚያስገርመው ግን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ አውዳሚ በነበረው በዚያ ጦርነት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ሥራቸውን የቀጠሉ ከመሆናቸውም በላይ በዘመናዊ ታሪካቸው ከፍተኛ እድገት ከታየባቸው ጊዜያት አንዱ ይህ ወቅት ነበር።

ሌላው ቀርቶ በ1945 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃና አብዛኞቹ የዓለማችን ከተሞች ፈራርሰው በነበረበት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች በድጋሚ የተከፈቱ ከመሆኑም በላይ አዳዲሶችም ተመሥር​ተዋል። በ1946 በዓለም ዙሪያ 57 ቅርንጫፍ ቢሮዎች ነበሩ። የምሥክሮቹ ቁጥርስ ምን ያህል ነበር? ከፍተኛ ቁጥራቸው 176, 456 ደርሶ ነበር! ይህ በ1938 ከነበረው ሦስት እጥፍ ገደማ ነው!

የመጀመሪያዎቹ ቅርንጫፍ ቢሮዎች እየሰፉ የሄዱበት መንገድ

በ1911 በእንግሊዝ ለንደን የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጀመሪያው ቅርንጫፍ ቢሮ ተጨማሪ ቢሮዎችና የመኖሪያ ቦታ ወዳለው ወደ 34 ክሬቨን ቴሬስ ተዛወረ። ከዚያም ሚያዝያ 26, 1959 በለንደን ሚል ሂል አዲስ የተገነቡ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች ለአምላክ ተወሰኑ። ከጊዜ በኋላ ተጨማሪ መኖሪያ ቤቶች የተሠሩ ሲሆን በመጨረሻም (በ1993) በዚያው አካባቢ በ18, 500 ካሬ ሜትር ላይ ማተሚያና የአስተዳደር ቢሮ ሕንፃዎች ለአምላክ ተወስነዋል። በዚህ ቦታ በየዓመቱ ከ90 ሚልዮን በላይ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! ቅጂዎች በ23 ቋንቋዎች ይታተማሉ።

በሁለተኛው የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ላይ የታየው መስፋፋት ይበልጥ አስገራሚ ነው። በ1923 የጀርመን ቅርንጫፍ ቢሮ ወደ ማግድበርግ ተዛወረ። እዚያ ማኅበሩ በራሱ የማተሚያ መሣሪያ ያተመው የመጀመሪያው መጠበቂያ ግንብ የሐምሌ 15, 1923 ነበር። በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ አጠገቡ ያለው መሬት ተገዝቶ ተጨማሪ ሕንፃዎች የተገነቡ ሲሆን የመጠረዣ መሣሪያና ተጨማሪ ማተሚያዎች ተገዝተዋል። በ1933 ናዚዎች ቅርንጫፍ ቢሮውን ወረሱ፤ ምሥክሮቹም ታገዱ እንዲሁም ሁለት ሺህ የሚያህሉት ወደ ማጎሪያ ካምፖች ተላኩ።

በ1945 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃ በወቅቱ የምሥራቅ ጀርመን ክፍል በሆነው በማግድበርግ የነበረው ንብረት የተመለሰ ሲሆን ቅርንጫፍ ቢሮውም በድጋሚ ተከፈተ። ይሁን እንጂ ነሐሴ 30, 1950 የኮሙኒስት ፖሊሶች ሕንፃዎቹን ወርረው ሠራተኞቹን ያሰሩ ከመሆናቸውም በላይ በምሥራቅ ጀርመን የምሥክሮቹ ሥራ ታገደ። በዚህ መሃል በ1947 በምዕራብ ጀርመን፣ በቪስባደን መሬት ተገዝቶ ነበር። በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት እያደገ የመጣውን የጽሑፍ ፍላጎት ለማሟላት ሲባል በዚያ የተገነቡትን የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች በተደጋጋሚ ማስፋት አስፈልጓል።

በቪስባደን ተጨማሪ ሕንፃዎች ለመሥራት የሚያስችል ቦታ በመጥፋቱ በ1979 በዜልተርስ አቅራቢያ 30 ሄክታር መሬት ተገዛ። ወደ አምስት ዓመት ከሚጠጋ የግንባታ ሥራ በኋላ ሚያዝያ 21, 1984 አንድ ሰፊ ቅርንጫፍ ቢሮ ለአምላክ ተወሰነ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ቅርንጫፍ ቢሮው ከአንድ ሺህ በላይ ሠራተኞች መያዝ እንዲችል ተጨማሪ ሕንፃዎች ተሠርተዋል። በየወሩ ከ30 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ከ16 ሚልዮን በላይ መጽሔቶች በዜልተርስ በሚገኙት ግዙፍ ዘመናዊ የማተሚያ መሣሪያዎች ይታተማሉ። እንዲሁም በቅርቡ በአንድ ዓመት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሶችን ጨምሮ ከ18 ሚልዮን በላይ መጻሕፍት በመጠረዣ ክፍሉ ተዘጋጅተዋል።

ኅትመት የሚካሄድባቸው ሌሎች ትልልቅ ቅርንጫፍ ቢሮዎች

በ1927 በጃፓን ኮቤ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅርንጫፍ ቢሮ ተከፈተ። ይሁን እንጂ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ምሥክሮቹ የደረሰባቸው ከባድ ስደት እንቅስቃሴያቸውን ገታው። ሆኖም ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ቅርንጫፍ ቢሮው በቶኪዮ እንደገና ተከፈተ። በዚህ ቦታ ተጨማሪ ሕንፃ ለመሥራት የሚያስችል መሬት በመጥፋቱ በኑማዙ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ተሠርቶ በ1973 ለአምላክ ተወሰነ። እነዚህ ሕንፃዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በመጥበባቸው ምክንያት በኤቢና ሰፋ ያሉ አዳዲስ ሕንፃዎች ተገንብተው በ1982 ለአምላክ ተወሰኑ። በዚህ ቦታ ለ900 ሠራተኞች መኖሪያ የሚሆኑ ሕንፃዎች ግንባታ በቅርቡ ተጠናቅቋል። በ1999 በጃፓንኛ ብቻ በሚልዮኖች ከሚቆጠሩ መጻሕፍት በተጨማሪ ከ94 ሚልዮን በላይ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! ቅጂዎች ታትመዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በተለያዩ አገሮች ውስጥ በሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ተጨማሪ ሕንፃዎች ተገንብተዋል። በ1929 ሜክሲኮ ውስጥ በሜክሲኮ ሲቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ተቋቋመ። ከዚያም የምሥክሮቹ ቁጥር 60, 000 ሲደርስ ከከተማው ውጭ ሰፋ ያለ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ተገነባ። በ1974 ሕንፃው ለአምላክ የተወሰነ ሲሆን በ1985 እና በ1989 ተጨማሪ ሕንፃዎች ተገንብተዋል። በቅርቡ ይጠናቀቃሉ ተብለው የሚጠበቁ አንድ ትልቅ የማተሚያ ሕንፃና ተጨማሪ መኖሪያ ቤቶች አሉ። በመሆኑም በቅርቡ የሜክሲኮ ቅርንጫፍ ቢሮ 1, 200 ሠራተኞች ማስተናገድ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። አሁንም ቢሆን ቅርንጫፍ ቢሮው ከ500, 000 በላይ ለሚሆኑ ምሥክሮችና ለሌሎች በሜክሲኮ ለሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሁም በአቅራቢያው ባሉ አገሮች ለሚኖሩ ሕዝቦች መጽሔቶችና መጻሕፍት እያዘጋጀ በማቅረብ ላይ ይገኛል።

በ1923 በብራዚል ሪዮ ዲ ጄኔሮ ቅርንጫፍ ቢሮ የተከፈተ ሲሆን በኋላም ግሩም የሆኑ አዳዲስ የመኖሪያ ሕንፃዎች ተሠርተዋል። ሆኖም ሳኦ ፓውሎ የብራዚል የንግድና የትራንስፖርት ማዕከል በመሆንዋ በ1968 በዚህች ከተማ አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ ተገነባ። በ1970ዎቹ አጋማሽ በብራዚል ወደ 100, 000 ገደማ የሚጠጉ ምሥክሮች ነበሩ። ይሁን እንጂ በሳኦ ፓውሎ ተጨማሪ ሕንፃዎች ለመሥራት የሚያስችል ቦታ ስላልነበረ ከከተማው ወደ 150 ኪሎ ሜትር ገደማ ወጣ ብሎ በሚገኘው በሴዛርዩ ላንዠ 115 ሄክታር መሬት ተገዛ። መጋቢት 21, 1981 በአዲሱ ቦታ የተገነቡት የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች ለአምላክ ተወሰኑ። በዚህ ቦታ ተጨማሪ ሕንፃዎች በመሠራታቸው ቅርንጫፍ ቢሮው ወደ 1, 200 ገደማ ሰዎች ማስተናገድ ይችላል። በብራዚል ለአብዛኛው የደቡብ አሜሪካና ለሌሎች የዓለም ክፍሎች መጽሔቶችና መጻሕፍት ይታተማሉ።

ኅትመት የሚካሄድበት ሌላ ትልቅ ቅርንጫፍ ቢሮ በ1990ዎቹ መጀመሪያ በኮሎምቢያ፣ ቦጎታ አቅራቢያ ተሠርቷል። እዚህ በመላው ሰሜናዊ ምዕራብ የደቡብ አሜሪካ ክፍል የሚሠራጩ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ይታተማሉ።

በየዓመቱ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ መጽሔቶችን የሚያትሙ ሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች በአርጀንቲና፣ በአውስትራሊያ፣ በካናዳ፣ በፊንላንድ፣ በኢጣሊያ፣ በኮርያ፣ በናይጄርያ፣ በፊሊፒንስ፣ በደቡብ አፍሪካና በስፔይን ይገኛሉ። በተጨማሪም በኢጣሊያ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ መጽሐፍ ቅዱሶችን ጨምሮ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ መጻሕፍትን በየዓመቱ በበርካታ ቋንቋዎች ያትማል። እርግጥ ከ40 ሚልዮን መጻሕፍትና ከአንድ ቢልዮን መጽሔቶች በላይ የሚሆነው አብዛኛው ዓመታዊ ኅትመት የሚካሄደው በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት እንዲሁም በኒው ዮርክ ሰሜናዊ ግዛት በሚገኘው ማተሚያ ነው።

በእርግጥም የዛሬ መቶ ዓመት አንድ ብሎ የጀመረው የቅርንጫፍ ቢሮዎች ቁጥር ዛሬ 109 መድረሱ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። እነዚህ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በ234 አገሮች ውስጥ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች ፍላጎት ለማሟላት በመሥራት ላይ የሚገኙ ሲሆን በእነዚህ ቢሮዎች ውስጥ ወደ 13, 000 የሚጠጉ በፈቃደኝነት የሚያገለግሉ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች አሉ! በእርግጥም እነዚህ ሠራተኞች የሚያከናውኑት ሥራ በማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኙት ወደ 5, 500 የሚጠጉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ከሚያከናውኑት ሥራ ጋር ተዳምሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ይህ የመንግሥት ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል’ ሲል የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።​—⁠ማቴዎስ 24:​14

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 በወቅቱ የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ትራክት ማኅበር ተብሎ ይጠራ ነበር።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቶም ሀርት እንግሊዝ ውስጥ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንደነበረ ይታመናል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ34 ክሬቨን ቴሬስ የነበረው የለንደን ቅርንጫፍ ቢሮ (ፎቶው ላይ በስተቀኝ በኩል)

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ በለንደን ሥራው የሚካሄድባቸው ሕንፃዎች