በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሥቃይ ወደ ሰመመን

ከሥቃይ ወደ ሰመመን

ከሥቃይ ወደ ሰመመን

ከ1840ዎቹ ዓመታት በፊት በነበሩት ዘመናት ታካሚዎች ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል ሲገቡ ከመጨነቅም አልፈው እጅግ ይሸበሩ ነበር! ለምን? ምክንያቱም በጊዜው በቀዶ ሕክምና ወቅት የሚሰጥ ምንም ዓይነት ሰመመን አልነበረም። ዴኒስ ፍራደን “ዊ ሃቭ ኮንከርድ ፔይን” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ቀዶ ሐኪሞች ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል ሲገቡ በሁለት እጃቸው አንድ አንድ የውስኪ ጠርሙስ ይዘው መግባታቸው የተለመደ ነገር ነበር። የታካሚያቸውን ጩኸት መቋቋም ይችሉ ዘንድ አንድ ለራሳቸው አንድ ደግሞ ለታካሚያቸው ይዘው ይገቡ ነበር።”

ታካሚውን በመጠጥ ወይም በአደገኛ ዕፅ “ማስከር”!

ዶክተሮች፣ የጥርስ ሐኪሞችና ታካሚዎች ቀዶ ሕክምና የሚያስከትለውን ሥቃይ ለመቀነስ የማይሞክሩት ነገር አልነበረም። የቻይናና የሕንድ ዶክተሮች ማሪዋናና ሃሺሽ ይጠቀሙ ነበር። ኦፒየምና አልኮልም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በስፋት ጥቅም ላይ ውለው ነበር። “ሰመመን” (anesthesia) የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተጠቀመ የሚነገርለት ዳይስኮረዲዝ የተባለ አንድ ጥንታዊ የግሪክ ሐኪም ማንድሬክ የተባለው ዕፅና የወይን ድብልቆች ሰመመን የማስያዝ ኃይል እንዳላቸው ገልጿል። በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንድ ዶክተሮች ሂፕኖቲዝም በተባለው ዘዴ እስከመጠቀም ደርሰው ነበር።

ሆኖም የሚደርሰውን ሥቃይ ለማስቀረት የተደረጉት ጥረቶች ሁሉ አልሰመሩም። በመሆኑም ቀዶ ሐኪሞችና የጥርስ ሐኪሞች ሥራቸውን በተቻለ መጠን በፍጥነት ለማከናወን ይጥሩ ነበር፤ እንዲያውም እንደየፍጥነታቸው ደረጃ ይወጣላቸው ነበር። ይሁን እንጂ በጣም ፈጣን የሆኑትም እንኳ በታካሚው ላይ ከባድ ሥቃይ ማስከተላቸው አልቀረም። በመሆኑም ሰዎች በአብዛኛው ቀዶ ሕክምና ወይም ጥርስ ማስነቀል የሚያስከትለውን ሥቃይ ከመቀበል ይልቅ በተለያዩ የአካል ክፍሎች ላይ ከሚከሰቱት ዕበጦች አንስቶ እስከ ጥርስ መበስበስ ድረስ ያሉትን በሽታዎች ሁሉ ችሎ መኖር ይመርጡ ነበር።

ስዊት ቪትሪኦል እና ላፊንግ ጋዝ

በ1275 ሬይመንድ ሉለስ የተባለ አንድ ስፔይናዊ ሐኪም ኬሚካላዊ ሙከራ እያካሄደ ሳለ በኋላ ስዊት ቪትሪኦል በማለት የሰየመውን በቀላሉ የሚተንና የሚቀጣጠል ፈሳሽ ሠራ። በ16ኛው መቶ ዘመን በአብዛኛው ፓራሴልሰስ በሚል መጠሪያው የሚታወቀው ስዊዘርላንዳዊ ሐኪም ዶሮዎች ስዊት ቪትሪኦልን ወደ ውስጥ እንዲስቡ ባደረገ ጊዜ ዶሮዎቹን ከማስተኛቱም በላይ ምንም ዓይነት የሕመም ስሜት እንዳይሰማቸው ያደረገ መሆኑን አስተዋለ። ከእሱ በፊት እንደነበረው እንደ ሉለስ ሁሉ ፓራሴልሰስም በሰዎች ላይ አልሞከረውም። በ1730 ጀርመናዊው ኬሚስት ፍሮቤኒየስ በግሪክኛ “ሰማያዊ” የሚል ትርጓሜ ያለውን ኤተር የሚለውን የአሁኑን ስያሜ ሰጠው። ይሁን እንጂ ባለሙያዎች ኤተር ሰመመን የማስያዝ ኃይል እንዳለው ሙሉ በሙሉ የተገነዘቡት ከ112 ዓመታት በኋላ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በ1772 እንግሊዛዊው ሳይንቲስት ጆሴፍ ፕሪስትሊ ናይትረስ ኦክሳይድ የተሰኘውን ጋዝ አገኘ። መጀመሪያ ላይ ሰዎች ይህን ጋዝ በአነስተኛ መጠን እንኳ መሳብ ለሞት እንደሚዳርግ አድርገው ያስቡ ነበር። ይሁን እንጂ በ1799 ብሪታንያዊው ኬሚስትና የፈጠራ ሰው ሃምፍሪ ዴቪ በራሱ ላይ ሙከራ በማድረግ ጋዙ ምን እንደሚያስከትል ለማወቅ ወሰነ። ናይትረስ ኦክሳይዱ በሳቅ እንዲንከተከት ሲያደርገው እጅግ ተገረመ። በዚህም ሳቢያ ላፊንግ ጋዝ የሚል ቅጽል ስም አወጣለት። ዴቪ ናይትረስ ኦክሳይድ ስላለው ሰመመን የማስያዝ ባሕርይ የጻፈ ቢሆንም በዘመኑ ጉዳዩን ሥራዬ ብሎ የተከታተለው አልነበረም።

የኤተር እና የላፊንግ-ጋዝ ፓርቲዎች

ዴቪ ለጊዜው ሱሰኛ አድርጎት የነበረውን ላፊንግ ጋዝ እየሳበ ይፈጽመው የነበረው አስቂኝ ድርጊት በብዙዎች ዘንድ እየታወቀ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ በርካታ ሰዎች ራሳቸውን ለማዝናናት ሲሉ ይህን ጋዝ መሳብ ጀመሩ። እንዲያውም ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወሩ የተለያዩ ትርዒቶች የሚያቀርቡ ሰዎች በፕሮግራማቸው ላይ ከተመልካቾች መካከል ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ወደ መድረክ በመጥራት በየተራ ናይትረስ ኦክሳይድ እንዲስቡ ያደርጉ ነበር። በፈቃደኝነት ወደ መድረኩ የወጡት ሰዎች ጋዙን ሲስቡ የሚፈጽሙት ከቁጥጥር ውጪ የሆነ አስቂኝ ድርጊት ተመልካቾቹ ሆዳቸውን እስኪያማቸው ድረስ በሳቅ እንዲንከተከቱ ያደርጋቸዋል።

በዚሁ ወቅት ብዙዎች ኤተርንም ለመዝናኛነት መጠቀም ጀምረው ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ቀን ክሮፈርድ ደብሊው ሎንግ የተባለ አንድ ወጣት አሜሪካዊ ሐኪም ጓደኞቹ በኤተር ሰክረው ወዲያና ወዲህ እየተንገዳገዱ ሲላተሙ ምንም ዓይነት የሕመም ስሜት እንደማይሰማቸው አስተዋለ። ወዲያውኑ ለቀዶ ሕክምና ሊያገለግል እንደሚችል አሰበ። በእነዚህ “የኤተር ፓርቲዎች” ላይ የሚካፈል ጄምስ ቬነበል የተባለ አንድ ተማሪ ሁለት አነስተኛ ዕበጦችን ማስወጣት ይፈልግ ስለነበር ሙከራውን ለማካሄድ ጥሩ አጋጣሚ ነበር። ቬነበል ቀዶ ሕክምናው የሚያስከትለውን ሕመም በመፍራት ነገ ዛሬ ሲል ቆይቶ ነበር። በመሆኑም ሎንግ ኤተርን በመጠቀም ቀዶ ሕክምና እንዲያደርግ ሐሳብ አቀረበለት። ቬነበል በሐሳቡ በመስማማቱ መጋቢት 30, 1842 ላይ ምንም ዓይነት ሕመም ሳይሰማው ቀዶ ሕክምና አደረገ። ይሁን እንጂ ሎንግ እስከ 1849 ድረስ ይህን ግኝቱን አላሳወቀም ነበር።

የጥርስ ሐኪሞችም ሰመመን አገኙ

ታኅሣሥ 1844 ላይ ሆረስ ዌልስ የተባለ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ የጥርስ ሐኪም ጋርድነር ኮልተን የተባለ ሰው ናይትረስ ኦክሳይድን በመጠቀም ትርኢት ባሳየበት የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ተገኝቶ ነበር። ዌልስ ጋዙን ለመሳብ በፈቃደኝነት ራሱን ቢያቀርብም በዙሪያው እየተካሄደ ያለውን ነገር መከታተል በሚችልበት ሁኔታ ላይ ይገኝ ስለነበር በትርኢቱ ላይ የተካፈለ አንድ ሌላ ሰው እግሮቹን እስኪደሙ ድረስ ከአግዳሚ ወንበር ጋር ቢያላትማቸውም ምንም ዓይነት የሕመም ስሜት እንዳልተሰማው አስተዋለ። ያን ዕለት ማታ ዌልስ ናይትረስ ኦክሳይድን በጥርስ ሕክምና ላይ ለመጠቀም ወሰነ። መጀመሪያ ግን በራሱ ላይ ለመሞከር አሰበ። ኮልተን ጋዙን እንዲያቀርብለት ዝግጅት ካደረገ በኋላ የሥራ አጋሩ የሆነ ጆን ሪግስ የተባለ የጥርስ ሐኪም ከባድ ሕመም የፈጠረበትን መንጋጋውን እንዲነቅልለት አደረገ። ሕክምናው እንደታሰበው የተሳካ ነበር።

ዌልስ ይህን ግኝቱን በጓደኞቹ ፊት በሠርቶ ማሳያ መልክ በማቅረብ ይፋ ለማድረግ ወሰነ። ይሁን እንጂ በጣም ፈርቶ ስለነበር በቂ ጋዝ ሳይጠቀም ቀረ። በዚህም ሳቢያ ታካሚው ጥርሱ ሲነቀል በጣም ጮኸ። ሕክምናውን ሲመለከቱ የነበሩት ሰዎች ወዲያውኑ ዌልስን አፌዙበት። ሆኖም ታካሚውን መጠየቅ ይገባቸው ነበር። ምክንያቱም በኋላ ታካሚው ለዌልስ እንደገለጸው ጥርሱ ሲነቀል ቢጮኽም እንኳ ብዙም ሕመም አልተሰማውም ነበር።

መስከረም 30, 1846 ዊልያም ሞርተን የተባለ አንድ ሌላ አሜሪካዊ የጥርስ ሐኪም ሎንግ በ1842 የተጠቀመበትን የኤተር ውሁድ ለመውሰድ ፈቃደኛ የሆነን የአንድ ታካሚ ጥርስ ያላንዳች የሕመም ስሜት ለመንቀል ያደረገው ጥረት ስኬታማ ሆነ። ሞርተን የኤተር ውሁዱን ያዘጋጀው ቻርልስ ቶማስ ጃክሰን በተባለ የታወቀ ኬሚስት እገዛ ነበር። ሞርተን ከሎንግ በተለየ መልኩ ኤተር ያለውን ሰመመን የማስያዝ ባሕርይ ቀዶ ሕክምና በሚያደርግ አንድ ታካሚ ላይ በሠርቶ ማሳያ መልክ በይፋ ለማቅረብ ዝግጅት አደረገ። ጥቅምት 16, 1846 ላይ በቦስተን፣ ማሳቹሴትስ ሞርተን ለታካሚው ሰመመን ሰጠው። ከዚያም ዶክተር ዋረን የተባለ ቀዶ ሐኪም ከታካሚው መንገጭላ ሥር የበቀለን ዕባጭ በማውጣት ቀዶ ሕክምናውን በተሳካ ሁኔታ አከናወነ። ይህ ቀዶ ሕክምና ትልቅ እመርታ ነበር። ወዲያውኑ ወሬው ልክ እንደ ሰደድ እሳት በመላው ዩናይትድ ስቴትስና አውሮፓ ተሰራጨ።

ተጨማሪ ግኝቶች

በእነዚህ አስደሳች ግኝቶች ሳቢያ የመትነን ባሕርይ ያላቸውን የተለያዩ ንጥረ ነገሮች የመሞከሩ ሂደት ተጠናክሮ ቀጠለ። በ1831 ክሎሮፎርም የተገኘ ሲሆን በ1847 ስኬታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ዋለ። በአንዳንድ ቦታዎች ተመራጭ ሰመመን ሆኖ ማገልገል የጀመረው ወዲያውኑ ነበር። ብዙም ሳይቆይ በወሊድ ወቅት ክሎሮፎርምን ለሴቶች መስጠት የተጀመረ ሲሆን በ1853 ሚያዝያ ወር ላይ ለእንግሊዟ ንግሥት ቪክቶሪያም ጭምር ተሰጥቷል።

ሰውነትን ሙሉ በሙሉ ለማደንዘዝ የሚሰጠው ሰመመን የኋላ ታሪኩ በተወሰነ ደረጃ የጎደፈ መሆኑ ያሳዝናል። ሰመመን (ራሳቸውን የኬሚካል ውሁዶቹን ማለት አይደለም) እንዲገኝ በማድረጉ ከሁሉ ይበልጥ ሊወደስ የሚገባው ማን ነው? ሎንግ፣ ዌልስ፣ ሞርተን ወይስ ሞርተንን የረዳው ታዋቂው ኬሚስት ጃክሰን በሚለው ጉዳይ ላይ የጦፈ ክርክር ተነስቷል። በዚህ ጉዳይ ስምምነት ላይ መድረስ ያልተቻለ ቢሆንም ብዙዎች በረጋ መንፈስ መለስ ብለው ሲያስቡ አራቱም ሰዎች የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ያምናሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብዙውን ጊዜ ሪጅናል አኔስቲዥያ በመባል የሚታወቅ በተወሰነ የአካል ክፍል ላይ ብቻ ሰመመን የመስጠት ልማድ እየዳበረ መጣ። ሕሙማን አእምሯቸው ንቁ ሆኖ እንዳለ የተወሰነ የአካል ክፍላቸው ብቻ እንዲደነዝዝና ምንም ዓይነት ስሜት እንዳይሰማው የሚያደርጉ ሰመመኖች ጥቅም ላይ ዋሉ። በዛሬው ጊዜ የጥርስ ሐኪሞች በጥርስና በድድ ሕክምና ወቅት በአብዛኛው የሚጠቀሙት የተወሰነ የአካል ክፍልን ብቻ ለማደንዘዝ የሚያገለግሉ ሰመመኖችን ሲሆን ሌሎች ሐኪሞችም ቀላል ቀዶ ሕክምና ለማድረግና ቀላል የአካል ጉዳት ጥገና ለማካሄድ በእነዚህ ሰመመኖች ይጠቀማሉ። ሰመመን የሚሰጡ ባለሙያዎች ብዙውን ጊዜ ምጥ ለያዛቸው ሴቶችም እንዲህ ዓይነቶቹን ሰመመን የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮች ይሰጣሉ።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አኔስቲዚኦሎጂ ራሱን የቻለ የሕክምና ሙያ ዘርፍ እየሆነ መጣ። ዘመናዊዎቹ ሰመመን ሰጪ ባለሙያዎች ሕሙማንን ለቀዶ ሕክምና በማዘጋጀቱ ሥራ ይሳተፋሉ። በጣም የተራቀቀ መሣሪያ እንዲሁም ኦክስጅንን ጨምሮ የተለያዩ የኬሚካል ንጥረ ነገሮች ድብልቅ የሆኑና ሰመመን የሚያስይዙ ውስብስብ ንጥረ ነገሮችን ይጠቀማሉ። እንዲያውም ብዙ ታካሚዎች ዶክተራቸው ሰመመን የሚያስይዙ ጋዞች እንደሰጣቸው እንኳ አያውቁም። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ዶክተሩ እነዚህን ጋዞች የሚጠቀመው የመጀመሪያው ሰመመን በደም ሥራቸው ከተሰጣቸው በኋላ ነው። በተጨማሪም ሰመመን ሰጭው ባለሙያ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ የሕመም ስሜቱን በማስታገስ ረገድ የሚያከናውነው ሥራ ይኖራል።

ስለዚህ አንድ ቀን ቀዶ ሕክምና ማድረግ ቢያስፈልግህ በተቻለ መጠን ራስህን ለማረጋጋት ሞክር። እስቲ ሁለት መቶ ዘመን ያህል ወደ ኋላ መለስ በልና በአንድ ተራ የቀዶ ሕክምና አልጋ ላይ እንደተኛህ አድርገህ ለማሰብ ሞክር። በሩ ይከፈትና ቀዶ ሐኪምህ ሁለት የውስኪ ጠርሙሶች ይዞ ይገባል። በዛሬው ጊዜ አንድ ሰመመን ሰጭ ባለሙያ የሚጠቀምበት እጅግ የተራቀቀ መሣሪያ ግን ብዙም የሚያስፈራ አይደለም፤ አይመስልህም?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አኩፓንቸር የምሥራቃውያን የሕመም ማስታገሻ

አኩፓንቸር ሕመምን እንደሚያስታግስ የሚነገርለት ጥንታዊ የቻይናውያን ሕክምና ነው። ባለሙያዎቹ ብዙውን ጊዜ ሕክምና ከሚደረግለት የአካል ክፍል ራቅ ብለው በሚገኙ የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎች ላይ መርፌዎች ይሰካሉ። መርፌዎቹ አንዴ ከተሰኩ በኋላ ዝቅተኛ ቮልቴጅ ካለው የኤሌክትሪክ ዥረት (current) ጋር እንዲገናኙ ሊደረግ ይችላል። ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ “በቻይና በቀዶ ሕክምና ወቅት አኩፓንቸርን ሰውነትን ለማደንዘዝ ይጠቀሙበታል። ምዕራባውያን ጎብኚዎች ከባድ (እና ወትሮውንም ቢሆን ሥቃይ የሚያስከትል) ቀዶ ሕክምና የተወሰነ የአካል ክፍላቸው ብቻ በአኩፓንቸር እንዲደነዝዝ በተደረጉ ቻይናውያን ሕሙማን ላይ ሲካሄድ ተመልክተዋል” ሲል ይገልጻል።

የአኩፓንቸር ሕክምና መሰጠት ያለበት በቂ ችሎታ ባለውና የሕክምና ሥልጠና ባገኘ ሐኪም ብቻ ነው። ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና እንደሚለው ከሆነ “የአኩፓንቸር መርፌዎች ልብን ወይም ሳንባን ወግተው ከባድ አደጋዎች ያስከተሉባቸው ጊዜያት አሉ። በተጨማሪም ጀርም አልባ ያልተደረጉ መርፌዎች ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ ሄፓታይተስ፣ በተወሰነ የአካል ክፍል ላይ የሚፈጠር ኢንፌክሽንና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ።” እርግጥ ቀዶ ሕክምናዎች ራሳቸው ለአደጋ ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ሁሉ ማንኛውም ዓይነት ሰመመንም ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አኔስቲዚኦሎጂ ራሱን የቻለ የሕክምና ሙያ ዘርፍ ሆኗል

[ምንጭ]

Courtesy of Departments of Anesthesia and Bloodless Medicine and Surgery, Bridgeport Hospital - CT

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ገጽ 2 እና 23:- Reproduced from Medicine and the Artist (Ars Medica) by permission of the Philadelphia Museum of Art/Carl Zigrosser/ Dover Publications, Inc.