በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ኦክሲጅን የተራቡ ዓይኖች

በዓይን ብሌን ላይ የሚለጠፉ የፕላስቲክ ሌንሶችን የሚጠቀሙ አንዳንድ ሰዎች ዓይናቸውን ኦክሲጅን እየነፈጉት ሊሆን እንደሚችል ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል ዘግቧል። “ኮርኒያ [ብርሃን አሳላፊ የሆነው የዓይን ሽፋን] ከአየር ጋር ቀጥተኛ ንክኪ በመፍጠር ሊያገኘው የሚገባውን ኦክሲጅን በማያገኝበት ጊዜ ይህን ሁኔታ ለማካካስ የደም ሥሮች ማደግ ይጀምራሉ።” ይህም የዓይን መድከም አልፎ ተርፎም ዓይነ ስውርነት ሊያስከትል ይችላል። በቶሮንቶ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ሬይመንድ ስታይን “አስከፊው ሁኔታ የሚፈጠረው ሕመምተኛው ሌንሶቹን በጥንቃቄ ሳይዝ ሲቀርና ወደ ሐኪም ዘንድ ሄዶ ክትትል ሳያደርግ በሚቀርበት ጊዜ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ኦፕቶሜትሪስቶች ሕሙማን ለዓይናቸው ተስማሚ የሆነ የፕላስቲክ ሌንስ እንዲያገኙና የተሰጣቸውን ፕሮግራም ተከትለው ሌንሱን ማድረግና በጥንቃቄ መያዝ የሚችሉበትን መመሪያ ማግኘት እንዲችሉ የዓይን ሕክምና ባለሙያዎችን እንዲያማክሩ ያበረታታሉ።

የብራዚላውያን ወዳጅነት እየቀዘቀዘ ሄዷል

በአሁኑ ጊዜ ብራዚላውያን የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ ያደርጉት የነበረውን ያህል ጓደኝነት ሲመሠርቱ አይታይም ሲል ኡ ግሎቡ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። የአእምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑትና በሳኦ ፓውሎ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ማሪያ ኢቢጋይል ደ ሶዘ እንዳሉት ከሆነ በሥራው ዓለም ያለው ከፍተኛ ፉክክር፣ አንድን የአኗኗር ዘይቤ ይዞ ለመቀጠል የሚደረገው ትግልና የዕረፍት ጊዜ መቀነስ ለእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል። በሳኦ ፓውሎ የአድቬንቲስት የጤናማ ሕይወት ማዕከል ሜዲካል ዲሬክተር የሆኑት ሴዘ ቫስኮንሴሉስ ደ ሶዘ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “እውነተኛ ወዳጆች ለማግኘት ስሜታችንን ማካፈል፣ የልባችንን አውጥተን መናገርና ደስታችንንም ሆነ ሃዘናችንን ማጋራት፣ እንዲሁም ለመናገር የሚከብደንንም ሆነ የሚቀለንን ነገር ሁሉ መግለጽ ይኖርብናል። ይህ ጊዜና የጠበቀ ስሜታዊ ትስስር መፍጠር ይጠይቃል። አብዛኞቹ ሰዎች ስሜታቸውን ለሌሎች ማካፈል ቢፈልጉም ይፈራሉ። ራሳቸውን ለአደገኛ ሁኔታ ላለማጋለጥ ሲሉ የጠበቀ ወዳጅነት ከመመሥረት ይቆጠባሉ።”

ቁጣና ልብህ

ግሎብ ኤንድ ሜይል የተሰኘው ጋዜጣ ያወጣው ዘገባ “ቁጡ የሆኑ ሰዎች በልብ ድካም የመያዛቸው አጋጣሚ ቶሎ የመበሳጨት ባሕርይ ከሌላቸው ሰዎች በሦስት እጥፍ ገደማ [ይበልጣል]” ይላል። ለልብ ድካም የሚያጋልጥ ሁኔታን በተመለከተ ለስድስት ዓመት በተካሄደው ጥናት ላይ ወደ 13, 000 የሚጠጉ ሰዎች ተካፋይ ሆነዋል። መጀመሪያ ላይ ጥናቱ የሚካሄድባቸው ሰዎች ሁሉ ከልብ በሽታ ነፃ ነበሩ። ለእያንዳንዱ ሰው ተከታታይ ጥያቄዎች ከቀረቡ በኋላ የየሰዉ የቁጣ መጠን ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ በሚል በደረጃ ተከፈለ። በስድስቱ ዓመት ጊዜ ውስጥ 256ቱ ልብ ድካም ይዟቸዋል። መካከለኛ ደረጃ የተሰጣቸው ሰዎች ለልብ ችግሮች ሊጋለጡ የሚችሉበት አጋጣሚ 35 በመቶ ልቆ መገኘቱን ጥናቱ አመልክቷል። የጥናቱ ዋና አዘጋጅ የሆኑትና በሰሜን ካሮሊና ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ዶክተር ጃኒስ ዊልያምስ “ቁጣ በተለይ ጤናማ የሆነ የደም ግፊት ያላቸውን በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ለልብ ድካም ሊዳርግ ይችላል” ሲሉ ገልጸዋል። ስለዚህ ቁጡ የሆኑ ሰዎች ውጥረትን መቋቋም የሚቻልባቸውን ዘዴዎች ማጤን ይኖርባቸዋል።

የአጫሾች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል

“ሲጋራ ለአንድ መቶ ዘመን ያህል ያፈራቸው ወዳጆቹ ፊታቸውን እያዞሩበት መጥተዋል” ሲል ዎርልድዎች ኢሹ አለርት ዘግቧል። ከ1990 እስከ 1999 ባሉት ዓመታት የዓለም የሲጋራ ፍጆታ 11 በመቶ ቀንሷል። ይህ አዝማሚያ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ወደ ሁለት አሥርተ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የታየ ሲሆን በዚህች አገር በ1999 የነበረው የሲጋራ ፍጆታ በ1980 ከነበረው 42 በመቶ ቀንሷል። ዘገባው ፀረ ሲጋራ ዘመቻዎች መካሄዳቸው፣ ሰዉ ስለ ሲጋራ አደገኛነት ያለው ግንዛቤ እያደገ መምጣቱና የሲጋራ ዋጋ መናሩ ለፍጆታው መቀነስ ምክንያት እንደሆኑ ጠቅሷል። ከዚህም በተጨማሪ “እያንዳንዱ ሰው በነፍስ ወከፍ የሚያጨሰው ሲጋራ መጠን በፈረንሳይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ከነበረበት ከ1985 ወዲህ 19 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በቻይና ከ1990 ወዲህ 8 በመቶ እንዲሁም በጃፓን ከ1992 ወዲህ 4 በመቶ ቀንሷል” ይላል ዘገባው።

ብክለት የትንኝ ወረርሽኝ አስከተለ

የውኃ ብክለት ከፔሩ ትልልቅ ከተሞች አንዷ የሆነችውን አሬኪፓን አቋርጦ በሚፈሰው የቺሊ ወንዝ አቅራቢያ ተነካሽ ሦስት አፅቄዎች ለፈጠሩት ችግር የበኩሉን አስተዋጽኦ ሳያበረክት አልቀረም። በአቅራቢያው ባሉ ሠፈሮች የሚገኙት ነዋሪዎች የትናንሽ ተናካሽ ትንኞችን ወረራ ለመከላከል ሲሉ በአካባቢው ካሉት መደብሮች የፍሊት ዘር እስኪጠፋ ድረስ በርካታ የሦስት አፅቄ መከላከያ መድኃኒቶች ተጠቅመዋል። ወረርሽኙ ሊከሰት የቻለው በቺሊ ወንዝ ላይ በደረሰው የኬሚካል ብክለት ሳቢያ እንደሆነ ኤል ኮሜርስዮ የተሰኘው የሊማ ጋዜጣ ዘግቧል። መርዛም የሆኑ ንጥረ ነገሮች በወንዙ ውስጥ የሚገኙትንና “ለብዙ ዓመታት የእነዚህ ሦስት አፅቄዎች ተፈጥሯዊ የሥነ ሕይወት ሚዛን እንዲጠበቅ አድርገው” የነበሩትን በርካታ ጉርጦች ሳይጨርሷቸው እንዳልቀረ ጋዜጣው ጠቁሟል።

ኃይለኛ ወይን ጠጅ

የብሪታንያ ፖሊስና የአልኮል ቁጥጥር ቡድኖች በወይን ጠጅ ውስጥ ያለው የአልኮል መጠን መጨመሩ አልፎ አልፎ የሚጠጡ ሰዎችን ለስካር ሊዳርጋቸው እንደሚችል በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ። ከአሥር ዓመታት በፊት በአብዛኛው 13 ወይም 14 በመቶ የሚደርስ የአልኮል ይዘት የሚኖራቸው በልዩ ጠመቃ የሚዘጋጁ ወይም ከምግብ በኋላ የሚቀርቡ ወይን ጠጆች ብቻ ነበሩ። ዛሬ ዛሬ ግን ተራ የወይን ጠጆችም የአልኮል ይዘታቸው 14 በመቶ ይደርሳል። እነዚህ ወይን ጠጆች በአብዛኛው የሚገቡት በጣም የበሰለና ጣፋጭ የሆነ ወይን ለማፍራት የሚያስችል ሞቃታማ የአየር ጠባይ ያላቸው በመሆኑ ኃይለኛ ወይን ጠጅ ከሚያመርቱት እንደ አውስትራሊያ፣ ደቡብ አፍሪካና ቺሊ ካሉት አገሮች ነው። የለንደኑ ዘ ሰንዴይ ታይምስ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ ላይ አልኮል ኮንሰርን የተሰኘው የብሪታንያ ተቋም ረዳት ዲሬክተር የሆኑት ሜሪ-አን መኪበን የሰጡትን አስተያየት ጠቅሷል:- “በወይን ጠጆች ውስጥ ያለው የአልኮል መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ሲሆን ይህን ከፍተኛ የአልኮል መጠን ያላስተዋሉ ተጠቃሚዎች ግራ እየተጋቡ መጥተዋል።”

በንዴት የሚገነፍሉ የመንጃ ፈቃድ ተፈታኞች

“ወደ 500 በሚጠጉት የፈረንሳይ የመንጃ ፈቃድ ‘ፈታኞች’ ላይ የሚዥጎደጎደው የስድብ ውርጅብኝና የሚፈጸመው አካላዊ ጥቃት ከ1994 ወዲህ 150 በመቶ ጨምሯል” ሲል ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪብዩን የተሰኘው የፈረንሳይ ጋዜጣ ዘግቧል። ከተፈታኞቹ መካከል 20 ደቂቃ የሚወስደውን የመንጃ ፈቃድ ፈተና የሚያልፉት ከ60 በመቶ በታች ሲሆኑ ከፍተኛ ወጪ አውጥተው የአሽከርካሪነት ኮርስ ያልወሰዱ ተፈታኞች በሙሉ ማለት ይቻላል፣ ፈተናውን ይወድቃሉ። ወዳቂዎቹ ተፈታኞች በፈታኞቹ ላይ የሚገልጹት ቁጣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ፈታኞቹን በቡጢ ይመቷቸዋል እንዲሁም ፀጉራቸውን ይዘው ከመኪናው ውስጥ እየጎተቱ ያወጧቸዋል። እንዲያውም አንድ ሰው በኤድስ የተበከለ ደም ይዟል ያለውን መርፌ አውጥቶ ፈታኟን አሳድዷታል። በቅርቡ ፈተናውን ማለፍ የተሳነው አንድ የ23 ዓመት ሰው ፈታኙን በፕላስቲክ ጥይት መቶታል። እንዲህ ዓይነቶቹን የኃይል ድርጊቶች ማስወገድ ይቻል ዘንድ ተፈታኞቹ ማለፍ አለማለፋቸውን እዚያው በግንባር ከመናገር ይልቅ ውጤቱ በፖስታ እንዲደርሳቸው እንዲደረግ ፈታኞቹ ሐሳብ አቅርበዋል።

ፈጣን ፍርድ

በብራዚል ኤስፒሪቶ ሳንቶ ግዛት የሚገኙ ሦስት ዳኞች ፈጣን የፍትሕ እርምጃ ለመውሰድ እንዲረዳ ታስቦ የተዘጋጀውን የኮምፒዩተር ፕሮግራም በመሞከር ላይ ናቸው ሲል ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ዘግቧል። የኤሌክትሮኒክ ዳኛ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ፕሮግራም በላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች ሥራ ላይ ውሏል። ቀለል ያለ ድንገተኛ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ፖሊስ አንድ ዳኛና አንድ የፍርድ ቤት ጸሐፊ አደጋው ወደደረሰበት ቦታ ይጠራል። ፕሮግራሙ ሰብዓዊው ዳኛ ማስረጃውን አመዛዝኖ እዚያው አደጋው በተፈጸመበት ሥፍራ ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ይረዳው ዘንድ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ፕሮግራሙ “አሽከርካሪው ቀይ መብራት ጥሷል?” ወይም “አሽከርካሪው ሕጉ ከሚፈቅደው መጠን በላይ አልኮል ጠጥቷል?” እንደሚሉት ያሉ ተከታታይ ጥያቄዎች ለዳኛው በማቅረብ ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ ይረዳዋል። ከዚያ ውሳኔውንና ለውሳኔው መሠረት የሆነውን ደንብ በወረቀት አትሞ ያወጣል። ኒው ሳይንቲስት እንደሚለው ከሆነ ፕሮግራሙ “የገንዘብ ቅጣት ሊጥል፣ የጉዳት ካሳ እንዲከፈል ሊያደርግ አልፎ ተርፎም የእስር ቅጣት ሊበይን” ይችላል። የኮምፒዩተር ፕሮግራሙ ሰብዓዊ ዳኞች ይበልጥ ቀልጣፋ እንዲሆኑ በመርዳት በብራዚል ሕግ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ላይ ያለውን የሥራ ጫና እንደሚቀንስ ታምኖበታል።

ፈላጊ ያጡ እግር ኳስ ተጫዋቾች

“በፈረንሳይ ቡድኖች ውስጥ ታቅፈው እንዲጫወቱ ከአፍሪካ እየተመለመሉ ከሚወሰዱት ወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የፈረንሳይ ኅብረተሰብ አካል መሆን የሚችሉበት መንገድ [አጥተው] ሕገ ወጥ በሆነ ሥራ ይሠማራሉ” ይላል ማርያን የተሰኘው የፓሪስ የዜና መጽሔት። የፈረንሳይ መንግሥት “ምርጥ ወጣት ተጫዋቾች” ለመመልመል በየአገሩ የሚዞሩትን ይሉኝታ ቢስ ወኪሎች የሚያወግዝ ሪፖርት አውጥቷል። ከ13 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸውን ወደ 300 የሚጠጉ ልጆች ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የአፍሪካ ታዳጊ ወጣቶች እጅግ አጓጊ በሆነ የስፖርት መስክ ለመሠማራት በማለም ተታልለው ተወስደዋል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ከየትኛውም ክለብ ጋር ሕጋዊ ውል መፈራረም ባለመቻላቸው ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል። “የእግር ኳስ ተጫዋቾች ጠበቆች መዝገቦቻቸው ከስኬት ይልቅ ውድቀትን በሚያወሱ ታሪኮች የተሞሉ ናቸው” ሲል መጽሔቱ አስተያየቱን ሰጥቷል።

ኤድስ አፍሪካን እያመሳት ነው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኮፊ አናን ባለፈው ዓመት በአፍሪካ ኤድስ የገደላቸው ሰዎች ቁጥር በጦርነት ካለቁት ሰዎች ቁጥር እንደሚበልጥ ተናግረዋል። ይህም በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ፣ በሴራሊዮን፣ በአንጎላ፣ በኮንጎ ሪፑብሊክ፣ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ፣ በኤርትራና በሱዳን የተደረጉትን ጦርነቶች ይጨምራል። በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት 36 ሚልዮን የኤድስ ተጠቂዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ማለት ይቻላል፣ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ይገኛሉ። በኮትዲቭዋር በእያንዳንዱ የትምህርት ቀን የአንድ አስተማሪ ሕይወት በኤድስ ይቀጠፋል። በቦትስዋና ደግሞ የሰዎች አማካይ ዕድሜ ከ70 ዓመት ወደ 41 ዓመት አሽቆልቁሏል። ዚምባብዌ በ2005 ለጤና ከምትመድበው በጀት መካከል 60 በመቶ የሚሆነውን ለኤች አይ ቪ እና ለኤድስ ለማዋል እንደምትገደድ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ቢሆን በቂ አይሆንም። የተጠቂዎቹ ቁጥር ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰባቸው በማላዊና በዛምቢያ ኤድስ ተገቢው ትኩረት የተነፈገው ሲሆን በደቡብ አፍሪካ የኤድስ ህሙማን ወደ ጎን ገሸሽ ተደርገዋል ሲል ዘ ጋርዲያን የተሰኘው የለንደን ጋዜጣ ዘግቧል። “ማንኛችንም ብንሆን ይህ አሰቃቂ ሁኔታ በአፍሪካ የኑሮ ደረጃ፣ በኢኮኖሚ አቅሟ እንዲሁም በማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጥንካሬዋ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ገና ሙሉ በሙሉ መረዳት አልቻልንም” ሲሉ ሚስተር አናን ተናግረዋል።