ካርቦን ሞኖክሳይድ—ድምፅ አልባው ገዳይ
ካርቦን ሞኖክሳይድ—ድምፅ አልባው ገዳይ
ብሪታንያ በሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ የተጻፈ
ብሪታንያ ውስጥ በየዓመቱ 50 የሚያክሉ ሰዎች የተበላሹ የቤት ውስጥ የማሞቂያ መሣሪያዎች በሚያወጡት ካርቦን ሞኖክሳይድ ምክንያት ተመርዘው ይሞታሉ። የለንደን አደጋ መከላከያ ማኅበር ሪፖርት እንዳደረገው “በአሁኑ ጊዜ በሥራ ቦታና በቤት ውስጥ ሰዎችን በመመረዝ ረገድ በአስቤስቶስ ምትክ ግንባር ቀደሙን ቦታ የያዘው ካርቦን ሞኖክሳይድ ነው።” ካርቦን ሞኖክሳይድ ምንድን ነው?
ካርቦን ሞኖክሳይድ ከሰል፣ ቅሪት ነዳጅ በተለይ ደግሞ ጋዝ በሚያቃጥል የመኪና ሞተር ወይም የማሞቂያ መሣሪያ ውስጥ እሳት ለመፍጠር የሚያስችሉት ነገሮች ሳይሟሉ ሲቀሩ የሚፈጠር ጋዝ ነው። ካርቦን ሞኖክሳይድ ምንም ዓይነት ቀለም፣ ሽታ ወይም ቃና የለውም። ታዲያ ገዳይ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
ቀይ የደም ሴሎች በጣም አስፈላጊ የሆነውን ኦክሲጅን ወደ ሰውነት ሕብረ ሕዋሶች ይወስዳሉ። ይሁን እንጂ ካርቦን ሞኖክሳይድን መርዛማ ያደረገው ነገር ቀይ የደም ሴሎች ከኦክስጅን ይልቅ ይህንን ጋዝ ለመውሰድ መምረጣቸው ነው። ሰውነት የኦክሲጅን እጥረት ሲያጋጥመው በካርቦን ሞኖክሳይድ ይመረዛል። ለረዥም ጊዜ በአነስተኛ መጠን ለሚረጭ የካርቦን ሞኖክሳይድ ጋዝ መጋለጥ በአንጎል ላይ ዘላቂ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። የሚታዩት ምልክቶች ራስ ምታት፣ ድብታ፣ ድካም፣ መጫጫን፣ ማቅለሽለሽና ራስን መሳት ሲሆኑ በጣም ከባሰ ደግሞ የልብ ምት መቀነስ፣ ስልምታ (coma) እና የመተንፈሻ አካላት መታወክን ይጨምራሉ። አንድ ሰው ድንገት በካርቦን ሞኖክሳይድ የመመረዝ አደጋ ቢያጋጥመው የኦክሲጅን እጥረቱ ወደ አንጎል ደርሶ ሞት ከማስከተሉ በፊት ወዲያው ኦክሲጅንና ለመተንፈስ የሚረዳውን እገዛ ማግኘቱ በጣም አስፈላጊ ነው።
ካርቦን ሞኖክሳይድ የሚያስከትላቸውን አደጋዎች ለማስቀረት ምን ማድረግ ይቻላል? ሁሉም መሣሪያዎቻችሁ በትክክል የተገጠሙና ዘወትር የባለሙያ ምርመራ የሚደረግላቸው መሆናቸውን አረጋግጡ። የእሳቱ ነበልባል ሰማያዊ በመሆን ፋንታ ቢጫ ከሆነ ይህ ያልተለመደ ዓይነት ነበልባል ምናልባት ካርቦን ሞኖክሳይድ እየወጣ መሆኑን የሚያሳይ ሊሆን ስለሚችል እንደ ማስጠንቀቂያ ምልክት አድርጋችሁ ተመልከቱት። በዛሬው ጊዜ በየአገሩ የተለያየ ዓይነት ያላቸው ካርቦን ሞኖክሳይድ መኖሩን የሚያስጠነቅቁ ደውሎች ማግኘት ይቻላል። ካርቦን ሞኖክሳይድ ሊያመነጩ የሚችሉ መሣሪያዎች ስትጠቀሙ ፈጽሞ ግዴለሾች አትሁኑ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያልተለመደ ዓይነት የእሳት ነበልባል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተለመደው የእሳት ነበልባል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ጊዜ በየአገሩ የተለያየ ዓይነት ያላቸው ካርቦን ሞኖክሳይድ መኖሩን የሚያስጠነቅቁ ደወሎች ማግኘት ይቻላል