በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆችን በዱር ማሳደግ

ልጆችን በዱር ማሳደግ

ልጆችን በዱር ማሳደግ

ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ፍንትው ብላ በወጣችው የማለዳ ፀሐይ በሣር በተሸፈኑት የአፍሪካ አውላላ ሜዳዎች ላይ አንድ ግልገል ተወለደ። እናቱ የረጠበውንና የሚያብረቀርቀውን ጨቅላዋን በሚብረከረኩ እግሮቹ እንዲቆም ወደ ታች ዝቅ ብላ በዝግታ ታነሳዋለች። ሌሎች እናቶችና እህቶቹ ወዲያውኑ ቀረብ ብለው አትኩረው ይመለከቱታል፣ ይነካኩታል፣ ያሸቱታል። ከ90 ሴንቲ ሜትር የማይበልጠውና 120 ኪሎ ግራም ብቻ የሚመዝነው የዝሆን ግልገል በሌሎቹ የመንጋው አባላት ዘንድ ልዩ ስሜት ይፈጥራል።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኘው የአሜሪካ ምድር ከጣት ቤዛ ብዙም የማትበልጥ አነስተኛ የወፍ ጎጆ በአንድ የዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ተንጠልጥላ ትታያለች። በዚህች የወፍ ጎጆ ውስጥ ከበራሪ ሦስት አፅቄዎች የማይበልጡ ጥንድ ቢ ሃሚንግበርዶች ሁለት ትናንሽ ጫጩቶችን ያሳድጋሉ። በሚያስደንቅ ፍጥነት የሚበርሩት እነዚህ በኅብረ ቀለም ያሸበረቁ ወፎች ትናንሾቹ ጫጩቶቻቸው ወዳሉበት የሚቀርቡ ትላልቅ እንስሶችን አልፎ ተርፎም ሰዎችን ከማባረር ወደኋላ የማይሉ ደፋር ወላጆች ናቸው።

ጨቅላ እንስሶች ሁላችንንም ይማርኩናል። ሕፃናትም እንኳ ቡችሎችን ሲመለከቱ በግርምት ይፈዝዛሉ። በድመት ግልገል ቡረቃ፣ የእናቷ ፀጉር ላይ ልጥፍ ብላ በምትታይ ማራኪ የሆነች ትንሽ ዝንጀሮ ወይም ጎጆዋ ውስጥ ሆና ትኩር ብላ በምትመለከት የጉጉት ጫጩት ትኩረቱ የማይሳብ ማን አለ?

ጨቅላ እንስሳት ሁሉ እንደ ሰብዓዊ ሕፃናት ሙሉ በሙሉ የወላጆቻቸው ጥገኞች እንደሆኑ አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። አንዳንዶቹ ትናንሽ እግሮቻቸው መሬት እንደነኩ ብዙም ሳይቆዩ ወዲያና ወዲህ መሮጥ ይጀምራሉ። ሌሎቹ ደግሞ ከተወለዱ በኋላ ዞር ብሎ የሚያያቸው ስለማይኖር ራሳቸውን ከአደጋ ጠብቀውና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ለመኖር ይገደዳሉ። ይሁን እንጂ የብዙዎቹ ጨቅላ እንስሳትና ሦስት አፅቄዎች ሕይወት በወላጆቻቸው አሳዳጊነት፣ ጥበቃ፣ ቀላቢነት፣ ማሠልጠኛና እንክብካቤ ላይ የተመካ ነው። ይህ ደግሞ በወላጆቹና በልጆቹ መካከል በሚኖረው የጠበቀ ዝምድና ላይ የተመሠረተ ነው።

እንክብካቤ ያደርጋሉ ተብለው የማይጠበቁ

አብዛኞቹ ሦስት አፅቄዎች፣ ዓሦች፣ እንቁራሪት አስተኔዎች (amphibians) እና ገበሎ አስተኔዎች (reptiles) የልጆቻቸው ደህንነት እምብዛም አያሳስባቸውም። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ በዚህ ረገድ በጣም ለየት ያሉ ናቸው። ለልጆቻቸው እንክብካቤ ያደርጋሉ ተብለው ከማይጠበቁት እንስሶች አንዱ አስፈሪው የናይል አዞ ነው። ይህ ደመ ቀዝቃዛ ገበሎ አስተኔ የሚያደርገው ወላጃዊ እንክብካቤ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። እንቁላሎቹ ሞቃት በሆነ አሸዋ ውስጥ ከተጣሉ በኋላ ወላጆቹ ከአካባቢው ሳይርቁ የወደፊት ዝርያቸውን ከአደጋ ይጠብቃሉ። ትንንሽ አዞዎች የሚፈለፈሉበት ጊዜ ሲደርስ እናትየው እንቁላሎቹን እንድትቀፈቅፍ ምልክት ለመስጠት ድምፅ ማሰማት ይጀምራሉ። ከዚያ በኋላ እናትየው የተፈለፈሉትን ትናንሽ አዞዎች ኃይለኛ በሆኑት መንጋጭላዎቿ ቀስ ብላ ወደ ውኃው ዳር ትወስድና አሸዋውን ከላያቸው ላይ ታጥብላቸዋለች። አባትየውም የተፈለፈሉትን አዞዎች ወደ ውኃው ወስዶ የማጠብ ልማድ አለው። ጨቅላዎቹ አዞዎች ልክ እንደ ዳክዬ ጫጩቶች ለተወሰኑ ቀናት ውኃው ውስጥ እናታቸውን በቅርብ እየተከተሉ ይቆያሉ። ይህም አስፈሪ በሆነው ኃይሏ ተከልለው ከማንኛውም ጥቃት እንዲጠበቁ ይረዳቸዋል።

የሚያስገርመው ነገር አንዳንድ ዓሦችም ከአንድ ጥሩ ወላጅ የሚጠበቀውን ዓይነት እንክብካቤ ያደርጋሉ። ጨው አልባ በሆነ ውኃ ውስጥ የሚኖሩት ቲላፒያ በመባል የሚጠሩት አብዛኞቹ ዓሦች እንቁላሎቻቸውን ከጣሉ በኋላ ከአደጋ ለመጠበቅ ሲሉ በአፋቸው ይይዟቸዋል። እንቁላሎቹ ከተፈለፈሉ በኋላ ትንንሾቹ ዓሦች ከወላጆቻቸው ሳይርቁ እንደ ልባቸው ይዋኛሉ። አደጋ በሚያንዣብብበት ጊዜ እናትየዋ ዓሣ አፏን በሃይል ትከፍትና ልጆቿ ተስፈንጥረው ገብተው እንዲደበቁ ታደርጋለች። አደጋው ሲያልፍ ጨቅላዎቹ ዓሦች እንደገና ወጥተው የተለመደ እንቅስቃሴያቸውን ይቀጥላሉ።

በተጨማሪም ጉንዳኖች፣ ንቦችና ምስጦች ለልጆቻቸው የሚያደርጉት እንክብካቤና ጥበቃ በጣም የሚያስገርም ነው። ማኅበራዊ ሦስት አፅቄዎች በመባል የሚታወቁት እነዚህ ነፍሳት የየራሳቸውን መንደር መሥርተው የሚኖሩ ከመሆኑም በላይ ለእንቁላሎቻቸው መጠለያ ይሠራሉ፣ እንዲሁም ለልጆቻቸው ቀለብ ያቀርባሉ። የማር ንብ በዚህ ረገድ በምሳሌነት የምትጠቀስ ናት። በሺህ የሚቆጠሩ ‘ትጉህ ሠራተኛ ንቦች’ ተባብረው በመሥራት በቀፏቸው ውስጥ የሚገኙትን ጨቅላ ንቦች ይንከባከባሉ። በተፈጥሮ ያገኙትን ጥበብ በመጠቀም ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበትን ቦታ ይገነባሉ፣ ይጠግናሉ፣ ያጸዳሉ፣ አልፎ ተርፎም የሙቀቱንና የእርጥበቱን መጠን ይቆጣጠራሉ።

ወላጅ ወፎች

አብዛኞቹ ወፎች ጥሩ ወላጆች ናቸው። ጎጆአቸውን የሚሠሩበትን ቦታ ለመምረጥ፣ ጎጆአቸውን ለመሥራትና ጫጩቶቻቸውን ለማሳደግ ከፍተኛ ጊዜና ጉልበት ያውላሉ። አፍሪካን ሆርንቢል የተባለ አንድ ታማኝ ወፍ 120 ቀናት በሚቆየው የመራቢያ ወቅት ከ1, 600 ጊዜ በላይ ወደ ጎጆው በመመላለስ ወደ 24, 000 የሚጠጉ የፍራፍሬ ቁርጥራጮች ሲያመጣ ተስተውሏል!

ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር የሚታወቀው አልባትሮስ የተሰኘው ወፍም እንክብካቤ በማድረግ ረገድ እምነት የሚጣልበት ነው። አባትየው ወፍ ምግብ ፍለጋ ቃል በቃል በሺህዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች በሚጓዝበት ጊዜ ታማኝ ጥንዱ ጎጆዋ ውስጥ ሆና በትዕግሥት መምጫውን ትጠባበቃለች።

በረሃማ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ አንዳንድ ወፎች የጫጩቶቻቸውን ጥም ለማርካት አንድ ጥሩ ዘዴ ይጠቀማሉ። ውኃ ወደተጠራቀመበት ጉድጓድ ሄደው ደረታቸው ላይ የሚገኙትን ላባዎች በውኃ ካራሱ በኋላ ወደ ጎጆአቸው በመመለስ ጫጩቶቻቸው በውኃ ከራሱት ላባዎቻቸው ላይ እንዲጠጡ ያደርጋሉ።

አንዳንድ የወፍ ዝርያዎች በርካታ ጫጩቶችን የመመገቡ ሥራ ከአቅማቸው በላይ በሚሆንበት ጊዜ ሌሎች ወፎች ጫጩቶቻቸውን “በሞግዚትነት” እንዲያሳድጉላቸው ያደርጋሉ። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ የሚያበረክቱት የተሟላ የዕድገት ደረጃ ላይ የደረሱ የወላጆቹ ልጆች ሲሆኑ ጫጩቶቹን በመመገብና በመጠበቅ ረገድ የበኩላቸውን ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው።

ወላጃዊ ጥበቃ

ጫጩት ወፎችን መጠበቅም ራሱን የቻለ የሙሉ ጊዜ ሥራ ነው። ጫጩት የፈለፈሉ ወፎች ከባድ ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ በአብዛኛው ክንፎቻቸውን ዘርግተው ጎጆአቸውን በመሸፈን ጫጩቶቻቸው እንዳይቀዘቅዛቸውና እንዳይበሰብሱ ይከላከላሉ። ስታርሊንግ የተባሉት ወፎች የጎጆአቸውን ንጽሕና በመጠበቅ ረገድ የተዋጣላቸው ናቸው። እነዚህ ብልህ ወፎች ጎጆአቸውን ከቅማልና ከቁንጫ ለመጠበቅ አንዳንድ መርዛማ የሆኑ ዕፅዋትን እየቀነጠሱ በጎጆአቸው ውስጥና ዙሪያ ያከማቻሉ። ይህም ጎጂዎቹን ሦስት አፅቄዎች የሚገድል ወይም የሚያርቅ ተባይ ማጥፊያ ሆኖ ያገለግላቸዋል።

ጫጩት የፈለፈለች ዉድኮክ የተባለች ወፍ ጫጩቷን ለመታደግ የምትጠቀምበት ብልሃት እጅግ የሚያስደንቅ ነው። አደጋ በሚያጠላበት ጊዜ ጫጩቷን በእግሮቿና በሰውነቷ መካከል አጥብቃ ይዛ ክንፎቿን በመዘርጋት ውድ ንብረቷን ከአደጋ ነፃ ወደሆነ ክልል ይዛት ትበራለች። አንዳንድ ደፋር ወፎች ጉዳት የደረሰባቸው መስለው በመታየት ለአደን የተሰማራ እንስሳ ወደ ጫጩቶቻቸው እንዳይቀርብ ትኩረቱን ይሰርቁታል። እናቲቱ ጉዳት የደረሰባት በማስመሰል መሬት ላይ በመንደፋደፍ አዳኙን አታልላ ከጎጆዋ እንዲርቅ ካደረገችው በኋላ በርራ ትሄዳለች። ጎጆአቸውን መሬት ላይ የሚሠሩ ወፎች አዳኝ እንስሳትን ከአካባቢው ለማራቅ የተለየ ድምፅ ሊያሰሙ ይችላሉ። በሰሜን አሜሪካ የምትገኘውና መሬት ውስጥ በቆፈረችው ጉድጓድ የምትኖረው ጉጉት አዳኝ እንስሳ ጉድጓዷን በሚያገኝበት ጊዜ የእባብ ዓይነት ድምፅ ታሰማለች። ጥንት በአካባቢው የሰፈሩ ሰዎች ጫጩት ጉጉቶች ከራሳቸው ጉድጓድ ርቀው ድምፅ በሚያሰሙ እባቦች ጉድጓድ ውስጥ ይቀመጡ እንደነበረ በእርግጠኝነት ተናግረዋል!

አጥቢ እናቶች

ከስፍነ-እንስሳ (animal kingdom) መካከል ወላጃዊ እንክብካቤ በማድረግ ረገድ አጥቢ እንስሳትን የሚያክል የለም። የዝሆን እናቶች ለልጆቻቸው ልዩ ፍቅር ያላቸው ሲሆን በመካከላቸው የሚኖረው የጠበቀ ዝምድና እስከ 50 ዓመት ድረስ ሊዘልቅ ይችላል። ግልገሉ የእናቱ ጥገኛ ነው። እናትየው ግዙፉን ሰውነቷን በመጠቀም ከፀሐይ ሐሩር ትከልለዋለች፣ በደንብ ታጠባዋለች፣ እንዲሁም በአፏ ከያዘችው ተክል ላይ በትንሹ ኩምቢው ቀጥፎ እንዲበላ ትፈቅድለታለች። ሰውነቱ ላይ ውኃ እየረጨችና በኩምቢዋ እየፈተገች አዘውትራ ታጥበዋለች። አንድን የዝሆን ግልገል ማሳደግ የመላው ቤተሰብ ኃላፊነት በመሆኑ እንስት የሆኑ ሌሎች የመንጋው አባላት በመንጋው ውስጥ ያሉትን ግልገሎች በመመገብ፣ በማሠልጠንና በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።

ሌላዋ ግዙፍ አጥቢ እንስሳ ጉማሬ ስትሆን ልጅዋን ውኃ ውስጥ ልትወልድ ትችላለች። ግልገሎቹ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ ጠልቀው መጥባት የሚችሉ ሲሆን አየር ለመሳብ ብቅ ይሉና እንደገና ውኃው ውስጥ ጠልቀው መጥባታቸውን ይቀጥላሉ። እናትየው ግልገሏን ማንም እንዲነካባት አትፈቅድም።

ዝንጀሮዎችም ለልጆቻቸው ጥሩ እንክብካቤ ያደርጋሉ። እናትየዋ ከወለደች በኋላ ልጅዋን ለመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሰዓታት ቢያንስ በአንድ እጅዋ አንገቷ ሥር ወይም ትከሻዋ አካባቢ በደንብ አጥብቃ ትይዘዋለች። በመጀመሪያው ሳምንት ጨቅላው ዝንጀሮ አብዛኛውን ጊዜውን በደመ ነፍስ እናቱ ፀጉር ላይ ተጣብቆ ያሳልፋል። እናቲቱ ሌሎች እንስት ዝንጀሮዎች ልጅዋን እንዲይዙ ልትፈቅድ ትችላለች። ዝንጀሮዎቹ ከመንጋቸው ጋር የተቀላቀለውን ትንሹን ደስ የሚል ዝንጀሮ ይደባብሱታል፣ ፀጉሩን ያበጥሩለታል፣ እቅፍ አድርገው ይይዙታል፣ እንዲሁም ያጫውቱታል።

በእርግጥም ብዙዎቹ ፍጥረታት “እጅግ ጠቢባን” ከመሆናቸውም በላይ ለልጆቻቸው በሚያደርጉት እንክብካቤ ረገድ በጣም የሚያስደንቅ ተሰጥኦ አላቸው። (ምሳሌ 30:​24-28) አንድን አስፈላጊ የሆነ ነገር የመረዳት ወይም አንድን ሁኔታ በማጥናት ብልሃት በተሞላበት መንገድ ምላሽ የመስጠት ችሎታቸው እንዲሁ በአንዳች አጋጣሚ የተገኘ ነገር ሊሆን አይችልም። የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ማለትም የሁሉ ነገሮች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ያወጣው የረቀቀ ንድፍ ውጤት ነው።​—⁠መዝሙር 104:​24

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጉጉት ጫጩቶች

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቲላፒያ የተሰኙት ዓሦች እንቁላሎቻቸውን ከጣሉ በኋላ በአፋቸው ይይዟቸዋል

[ምንጭ]

Courtesy LSU Agricultural Center

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አዞዎች ግልገሎቻቸውን ያጓጉዛሉ

[ምንጭ]

© Adam Britton, http://crocodilian.com

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አልባትሮስ እና ጫጩቷ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሆርንቢል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስታርሊንግ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዉድኮክ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

እናት ጉማሬ ግልገሏን ማንም እንዲነካባት አትፈቅድም

[ምንጭ]

© Joe McDonald

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እናት ዝንጀሮዎች የልጆቻቸውን ፀጉር ያበጥራሉ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጦጣዎች

[ምንጭ]

© Joe McDonald