በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወቱን እንዲያተርፍ ረዳው

ሕይወቱን እንዲያተርፍ ረዳው

ሕይወቱን እንዲያተርፍ ረዳው

የታኅሣሥ 22, 1999 የ“ንቁ!” (እንግሊዝኛ) እትም “አፈና​—⁠በዓለም ዙሪያ ስጋት ያሳደረው ለምንድን ነው?” የሚል የሽፋን ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። ዊልያም ሉዊስ ቴሬል ይህ የ“ንቁ!” እትም ሕይወቱን ለማትረፍ እንደረዳው ተናግሯል።

መጋቢት 10, 2000 ዓርብ ጠዋት አራት ሰዓት ገደማ ላይ ጆሴፍ ሲ ፓልሺንስኪ ጁንየር የተባለ ሰው ቴሬልን በጠመንጃ አፈሙዝ ከቤቱ አግቶ ወሰደው። ቴሬል ጭንቀት ላይ ወድቆ በነበረበት ወቅት በዚያ ንቁ! መጽሔት ላይ የወጡት ሐሳቦች በአእምሮው ይመላለሱ እንደነበረ ተናግሯል። ንቁ! መጽሔቱ አንድ ሰው በሚታገትበት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለበት ባለሙያዎች የሰጡትን ቀጥሎ ያለውን ምክር ይዟል:-

“ተባባሪ ሁን፤ የግትርነት ጠባይ አታሳይ። አጋቾቻቸውን ፊት ለፊት የሚቃወሙ ታጋቾች አብዛኛውን ጊዜ ጭካኔ ለተሞላበት ድርጊት የተጋለጡ ሲሆን ለመገደል ወይም ለብቻቸው ተወስደው ለመቀጣት የሚኖራቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ነው።

“አትረበሽ። ታፍነው ከሚወሰዱ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በሕይወት እንደሚተርፉ አስታውስ።”

“የሚቻል ከሆነ ጭውውት ጀምር እንዲሁም የሚያግባቡ ሐሳቦችን ለመለዋወጥ ሞክር። አፋኞቹ በአንተነትህ ካዩህ አንተን ለመጉዳት ወይም ለመግደል አይነሳሱም።

“የሚያስፈልጉህን ነገሮች [ለአፋኞቹ] ትሕትና በተሞላበት መንገድ አሳውቃቸው።”

“የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ለታጋቹ ጥበቃ ያስገኝለታል። ክሪሚናል ቢሄቪየር የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- ‘ታጋቹና አጋቹ ይበልጥ በተግባቡ መጠን አንዱ ለሌላው ያለው አሳቢነት ይጨምራል። ይህ ሁኔታ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አጋቹ ታጋቹን የመጉዳት አዝማሚያ ላይኖረው እንደሚችል ይጠቁማል።’ ”

የይሖዋ ምሥክር የሆነው የ53 ዓመቱ ዊልያም ቴሬል ለ14 ሰዓታት ያህል ታግቶ በቆየበት ወቅት ይህን ምክር ለመከተል የቻለውን ሁሉ አድርጓል። ከእነዚህ 14 ሰዓታት ውስጥ አብዛኛውን ያሳለፈው የጠመንጃ አፈሙዝ ተደግኖበት ነበር። ቴሬል ችግር ውስጥ የወደቀው ፓልሺንስኪ ሰርቆ የሚያሽከረክረው መኪና ኢንተርስቴት ሀይዌይ 95 በሚባለው ጎዳና ላይ እንዳለ ነዳጅ በመጨረሱ በአቅራቢያው ወዳለው ገጠራማ አካባቢ ሄዶ የቴሬልን ቤት ባንኳኳ ጊዜ ነበር።

ቴሬል መንገደኛው ያጋጠመውን ችግር ከሰማ በኋላ ሰውዬውን የመርዳት ፍላጎት አደረበት። ፓልሺንስኪ የሚጠጣ ውኃ እንዲሰጠውና ወደ ባልቲሞር፣ ሜሪላንድ፣ ዩ ኤስ ኤ እንዲያደርሰው ጠየቀ። ቴሬል ቨርጂኒያ ውስጥ ወደምትገኘው ፍሬደሪክስበርግ የተባለች ከተማ ድረስ የሚሸኘው ሰው እንደሚፈልግለትና የቀረውን መንገድ በአውቶቡስ ሊሄድ እንደሚችል ነገረው። ቴሬል ለመንገደኛው የሚጠጣ ውኃ ይዞ ሲመለስ መሣሪያ ደገነበት። ፓልሺንስኪ መሄድ ወደሚፈልግበት ቦታ እንዲያደርሰው ቴሬልን አዘዘው።

ምክሩን በሥራ ማዋል

ቴሬል በኢንተርስቴት 95 ጎዳና ላይ በሚያሽከረክርበት ወቅት የፍጥነት ገደቡን እንዲጠብቅና ወደ እነሱ ትኩረት ሊስብ በሚችል ሁኔታ እንዳይነዳ ፓልሺንስኪ የሰጠውን መመሪያ አከበረ። ቴሬል በግል ለእሱ አሳቢነት በማሳየትና ሁለቱ ለመገናኘት ስላበቃቸው ሁኔታ በማንሳት የ31 ዓመቱን ፓልሺንስኪን በተረጋጋ መንፈስ ያነጋግረው ጀመር። ፓልሺንስኪ ከእሱ ጋር ያላትን ጓደኝነት ያቋረጠችውን ትሬሲ የተባለች ፍቅረኛውን ለማግኘት ከሦስት ቀን በፊት ያለችበት ድረስ ሄዶ እንደነበር ነገረው። እዚያም ትሬሲን ይዞ እንዳይሄድ ለማስጣል የሞከሩትን ሁለት ጓደኞቿንና አንድ ጎረቤቷን በጥይት መትቶ ገደላቸው። ከዚያም ትሬሲ አምልጣ ሄደች።

በሚቀጥለው ቀን ምሽት ፓልሺንስኪ በጠመንጃ አስፈራርቶ መኪና ለመውሰድ ባደረገው ሙከራ አንድ የሁለት ዓመት ልጅ በተባራሪ ጥይት ተመትቶ መንገጭላው ወለቀ። በተጨማሪም ጄኒፈር ሊን ሜክዶነል ታሽከረክረው የነበረ መኪና በጥይት ተመትቷል። የሚያሳዝነው ጄኒፈር በጥይት ተመትታ የሞተች ሲሆን ሌላው ጥይት ደግሞ በመኪናው ውስጥ ለአንድ ዓመት ልጃቸው የተገጠመውን ባዶ ወንበር በስቶት ነበር። ጄኒፈርና ባለቤቷ ቶማስ ወደ ይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ እያመሩ የነበረ ሲሆን በዚያን ዕለት ምሽት በሚደረገው ስብሰባ ላይ ሁለቱም ክፍል ያቀርቡ ነበር። የጄኒፈር እናት ሤራ ፍራንሲስ እንዲህ ብለዋል:- “ሕፃኑን ወደ መንግሥት አዳራሽ ሳይወስዱት የቀሩት ያን ቀን ብቻ ነበር። [ወስደውት ቢሆን ኖሮ] ሁለቱንም አጥተን ነበር ማለት ነው።”

ቴሬል ቀስ በቀስ አጋቹን የሞቀ ውይይት ውስጥ እያስገባው ሲሄድ ፓልሺንስኪ ማንንም የመጉዳት ዓላማ እንዳልነበረው ከዚህ ይልቅ ለትሬሲ እውነተኛ ፍቅር እንዳለውና ከእሷ ጋር መሆን እንደሚፈልግም ነገረው። ቴሬል እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ያለፈው እንደማይመለስ ከዚህ ይልቅ የወደፊት ሕይወቱን ማስተካከል እንደሚችል ነገርኩት፤ እጁን እንዲሰጥም አበረታታሁት። እስር ቤት እየሄድኩ እንደምጠይቀውና መጽሐፍ ቅዱስ ላስጠናው እንደምችል ነገርኩት።” በኋላ መረዳት እንደተቻለው ፓልሺንስኪ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀበት ከ1987 አንስቶ ከአሥር ወራት በስተቀር መላ ሕይወቱን ያሳለፈው በእስር ቤትና በአእምሮ ሕክምና ተቋማት አሊያም በአመክሮ ነበር።

ቴሬል ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኖ ለረጅም ጊዜ ያገለገለ እንደመሆኑ መጠን ያካበተውን ተሞክሮ በመጠቀም ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የሕይወት ታሪኮችን እየጠቀሰ መንፈሱ የተረበሸውን ወጣት ማግባባቱን ቀጠለ። ለምሳሌ ያህል በዳዊት ሠራዊት ውስጥ በወታደርነት በሚያገለግለው በኦርዮ ሚስት ልቡ ስለተሰረቀውና ጥሩ ሰው ስለነበረው የእስራኤሉ ንጉሥ ዳዊት ነገረው። ዳዊት ሴትዮዋ ከእሱ ማርገዝዋን ሲያውቅ ኦርዮ ጦር ሜዳ ላይ እንዲገደል ሁኔታዎችን አቀነባበረ። ዳዊት የሠራው ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ጥበብ በተሞላበት መንገድ ሲነገረው ከልቡ ንስሐ በመግባቱ የአምላክን ሞገስ መልሶ ሊያገኝ ችሏል።​—⁠2 ሳሙኤል 11:​2–12:​14

ቴሬል በሽሽት ላይ ካለው ሰው ጋር ጥሩ መግባባት በመፍጠር ጆቢ በሚለው ቅጽል ስሙ ይጠራው ጀመር። አንድ የገበያ አዳራሽ አጠገብ መኪናውን ካቆሙ በኋላ ፓልሺንስኪ እሱን ለማስያዝ ከሞከረ ተጨማሪ ሰዎችን እንደሚገድል በማስጠንቀቅ ቴሬልን ምግብና አንድ አነስተኛ ቴሌቪዥን እንዲገዛ ላከው። ቴሬል በሽሽት ላይ ያለው ሰው ስሜቱ አለመረጋጋቱን በመገንዘብ ፍላጎቱን አከበረለት። በመጨረሻ ፓልሺንስኪ ስለፈጸመው ወንጀል በቴሌቪዥን የተሰራጨውን የ5 ሰዓት ዜና ከተከታተለ በኋላ ቴሬልን ተሰናብቶ ከባልቲሞር ወጣ ብሎ ወደሚገኘው የከተማው ክፍል በመግባት ተሰወረ።

ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ፓልሺንስኪ ሰዎችን አግቶ የያዘበት ቤት ተከበበ። በሽሽት ላይ ያለው ሰው ቴሬልን ጠቅሶ ስለነበር ቴሬል በድርድሩ እንዲካፈል ተጠራ። የሚያሳዝነው ድርድሩ ሳይሳካ በመቅረቱ መጋቢት 22 ላይ ፖሊሶች ወደ መኖሪያ ቤቱ በኃይል ገብተው ፓልሺንስኪን በጥይት ገደሉት። ሌላ የተጎዳ ሰው አልነበረም።

ከዚህ በኋላ ቴሬል ሕይወቱን ለማትረፍ እንደረዳው የተናገረለትን የንቁ! እትም 600 ቅጂዎች ወሰደ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ቅጂዎችን ለሰዎች አበርክቷል። ቴሬል ንቁ! ላይ የሚወጡትን ጠቃሚ ትምህርቶች የማንበብ ልማድ በማዳበሩ ያገኘውን ጥቅም ያደንቃል። እርስዎም መጽሔቱን በማንበብ እንደሚጠቀሙ እናምናለን።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዊልያም ቴሬል