በስሜት ማዕበል መናጥ
በስሜት ማዕበል መናጥ
አንድ አረጋዊ “ለሞት የሚያደርስ በሽታ እንደያዘኝ ከተነገረኝ በኋላ የተሰማኝን ፍርሃት ወደ ጎን ገሸሽ ለማድረግ ሞከርኩ። ሆኖም ወደፊት ስለሚገጥመኝ ሁኔታ ያደረብኝ ስጋት በብርቱ አደከመኝ” በማለት ያስታውሳሉ። የእኚህ አረጋዊ ቃል አንድ ሕመም አካላዊ ጉዳት ካደረሰ በኋላ በዚሁ ብቻ ሳይወሰን የስሜት መቃወስም እንደሚያስከትል ያሳያል። ቢሆንም እንደነዚህ ያሉትን የስሜትና የአካል ቀውሶች በተሳካ ሁኔታ ተቋቁመው የሚኖሩ ሰዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ሥር የሰደዱ ሕመሞችን ለመቋቋም የሚያስችሉ መንገዶች እንዳሉ ያረጋግጡልሃል። ምን ለማድረግ እንደምትችል ከማብራራታችን በፊት ግን አስቀድመን በመጀመሪያ እንዴት ያሉ ስሜቶች ሊሰሙህ እንደሚችሉ እንመልከት።
አለማመን፣ አለመቀበል፣ በትካዜ መዋጥ
አንተ የሚሰማህ ስሜት ሌሎች ከሚሰማቸው የተለየ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም የጤና ሊቃውንትና ሕመምተኛ የሆኑ ግለሰቦች የጤና እክል የገጠማቸው ሰዎች የሚደርሱባቸው ተመሳሳይ የስሜት ችግሮች እንዳሉ ይናገራሉ። የመጀመሪያው ድንጋጤና ለማመን የመቸገር ስሜት ካለፈ በኋላ ሁኔታውን ለመቀበል እምቢተኛ የመሆን ስሜት ይከተላል። ‘እውነት ሊሆን አይችልም፣’ ‘አንድ ስህተት መኖር አለበት፣’ ‘ምናልባት የምርመራውን ውጤት አሳስተው ይሆናል’ የሚል ሐሳብ ይመጣል። አንዲት ሴት ካንሰር እንዳለባት ስታውቅ የተሰማትን ስትናገር “ብርድ ልብስህ ውስጥ ሽፍንፍን ብለህ ከተደበቅህ በኋላ ስትገለጥ ሁሉ ነገር አልፎ የሚቆይህ ይመስልሃል” ብላለች።
ይሁን እንጂ እውነታውን መቀበል ስትጀምር ለመቀበል ፈቃደኛ ያለመሆን ስሜት እየጠፋ ይሄድና እንደ ጥቁር ደመና የሚጋርድ ሐዘን በቦታው ይተካል። ‘ከእንግዲህ ምን ያህል እኖራለሁ?’ ‘ቀሪ ሕይወቴን በከባድ ሕመም ላሳልፍ ነው?’ የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ይመላለሱብሃል። ሕመሙ ከመታወቁ በፊት ወደነበረው ጊዜ ለመመለስ ትመኛለህ። ግን አይሆንልህም። ወዲያው ኃይለኛና አስጨናቂ በሆኑ ሌሎች ስሜቶች መናጥ ልትጀምር ትችላለህ። ከእነኚህ ሌሎች ስሜቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
ሥጋት፣ የመረበሽ ስሜት፣ ፍርሃት
ከባድ ሕመም ሕይወትህ በስጋትና በመረበሽ ስሜት እንዲዋጥ ያደርጋል። ፓርኪንሰንስ ዲዝዝ የተባለ የሚያንቀጠቅጥ በሽታ የያዘው አንድ ሰው “ስለ ወደፊቱ ሁኔታዬ ለማወቅ አለመቻሌ አንዳንድ ጊዜ ሕይወቴን ተስፋ አስቆራጭ ያደርግብኛል። እያንዳንዱ ቀን የሚያመጣውን አዲስ ነገር እጠብቃለሁ” ብሏል። በተጨማሪም በሽታህ ፍርሃት ሊያሳድርብህ ይችላል። ሳታውቀው በድንገት የመጣብህ ከሆነ ቅስም የሚሰብር ፍርሃት ሊያድርብህ ይችላል። ለረዥም ጊዜ ሳይታወቅልህ ቆይቶ በቅርቡ በምርመራ የተረጋገጠ ሕመም ከሆነ ግን ወዲያውኑ የፍርሃት ስሜት ላይሰማህ ይችላል። እንዲያውም መጀመሪያ ላይ አሁን ሰዎች በእርግጥ ታማሚ መሆንህንና ስታስመስል የኖርክ አለመሆንህን እንደሚያውቁልህ ስለሚሰማህ የእፎይታ ስሜት ሊሰማህ ይችላል። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ይህ የእፎይታ ስሜት የበሽታህ ምንነት በሚያስከትልብህ ፍርሃት ሊተካ ይችላል።
በተጨማሪም ሕይወትህን ለመቆጣጠር የማትችል መሆንህ ያስጨንቅሃል። በተለይ በተወሰነ ደረጃ ራሴን ችዬ መኖር አለብኝ የሚል አቋም ያለህ ሰው ከሆንክ የሌሎችን እርዳታ ፈላጊ መሆንህ በጣም ያስፈራሃል። መላ ሕይወትህ በበሽታህ ቁጥጥር ሥር መዋሉና እያንዳንዱ እንቅስቃሴህ በሕመምህ የተገደበ መሆኑ ያስጨንቅሃል።
ቁጣ፣ ኀፍረት፣ ብቸኝነት
ጊዜ እየገፋ በሄደ መጠን ሕይወትህን መቆጣጠር እንደሚሳንህ መገንዘብህ የቁጣ ስሜት ይቀሰቅስብሃል። ‘ለምን በኔ ላይ ደረሰ? ይህ ሁሉ የደረሰብኝ ምን በድዬ ነው?’ እያልክ ራስህን ትጠይቃለህ። ይህ በጤንነትህ ላይ የደረሰው አደጋ አግባብ እንዳልሆነና ትርጉም የለሽ እንደሆነ ይሰማሃል። በተጨማሪም በኀፍረትና ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ልትዋጥ ትችላለህ። አንድ ሽባ የሆነ ሰው “ይህ ሁሉ የደረሰብኝ አጉል የሆነ ድርጊት ስፈጽም በገጠመኝ አደጋ ምክንያት መሆኑን ሳስበው ያሳፍረኛል” ብሏል።
በተጨማሪም የብቸኝነት ስሜት መረቡን ሊጥልብህ ይችላል። በአካል ገለልተኛ መሆንህ ከማኅበራዊ ኑሮም በቀላሉ እንድትገለል ያደርግሃል። ሕመምህ ከቤት እንዳትወጣ አድርጎህ ከሆነ ከቀድሞ ጓደኞችህ ጋር መገናኘት አትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ ከሰዎች ለመገናኘት የምትፈልገው አሁን ነው። መጀመሪያ ሰሞን ሲያጨናንቁህ የነበሩት ጠያቂዎችና ስልክ ደዋዮች ቀስ በቀስ እየራቁ ይሄዳሉ።
ወዳጆች እየራቁ መሄዳቸው የሚያሳዝን ነገር በመሆኑ አንተም በአጸፋው ራስህን ማግለል ትጀምር ይሆናል። እርግጥ፣ እንደ ቀድሞው ከሰዎች ጋር ለመቀላቀል የተወሰነ ጊዜ ሊያስፈልግህ ይችላል። ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት ላይ ራስህን በይበልጥ እያገለልክ ከሄድህ ያጋጠመህ ማኅበራዊ ብቸኝነት (ሰዎች አንተን ማግለላቸው) ስሜታዊ ብቸኝነት (ራስህን ማግለል) ያስከትልብሃል። በሁለቱም ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ የብቸኝነት ስሜት ይታገልሃል። * እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የዛሬውን ቀን አድር ይሆን ብለህ ታስባለህ።
ከሌሎች መማር
ይሁን እንጂ ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ አድርገህ አታስብ። የጤና እክል የገጠመህ በቅርብ ጊዜ ከሆነ በመጠኑም ቢሆን ሕይወትህን እንድትቆጣጠር የሚረዱህ ተግባራዊ እርምጃዎች አሉ።
ተከታታይ ርዕሶች የያዘው ይህ ጽሑፍ ሥር የሰደደውን የጤንነት ችግርህን ሙሉ በሙሉ ሊፈታ እንደማይችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ የቀረበው መረጃ ራስህን ከገጠመህ ሁኔታ ጋር እንድታስታርቅና ችግርህን እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል። ካንሰር የያዛት አንዲት ሴት ያሳለፈችውን የስሜት ውጣ ውረድ እንደሚከተለው በማለት ጠቅለል አድርጋ ገልጻዋለች:- “ሁኔታውን ለመቀበል ተቸግሬ ከቆየሁ በኋላ ከፍተኛ የቁጣ ስሜት አደረብኝ፤ ከዚያም እርዳታ ለማግኘት መጣር ጀመርኩ።” አንተም ከአንተ በፊት እንዲህ ዓይነት ውጣ ውረድ የገጠማቸው ሰዎች ያሳለፉትን በመመርመር እንዴት እርዳታ ልታገኝ እንደምትችል ከተሞክሯቸው ተማር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.12 እርግጥ እነዚህ የተለያዩ ስሜቶች በብዙ ሰዎች ላይ የሚደርሱበት መጠንም ሆነ ቅደም ተከተል የተለያየ ነው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘ለምን በኔ ላይ ደረሰ? ይህ ሁሉ የደረሰብኝ ምን በድዬ ነው?’ እያልክ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል