በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እሳት! መጠቀም ያለብህ የትኛውን እሳት ማጥፊያ ነው?

እሳት! መጠቀም ያለብህ የትኛውን እሳት ማጥፊያ ነው?

እሳት! መጠቀም ያለብህ የትኛውን እሳት ማጥፊያ ነው?

ብዙውን ጊዜ ግድግዳ ላይ ተሰቅለው የምናያቸውን ትናንሽ ድምፅ አልባ ዘብ ጠባቂዎች ብዙም ትኩረት ሳንሰጣቸው እናልፋለን! ይሁን እንጂ አንድ ቀን ቢሯችንን ወይም ፋብሪካችንን አልፎ ተርፎም ቤታችንን ከእሳት ይታደጉልን ይሆናል። በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ ልናንቀሳቅሳቸው የምንችላቸው እሳት ማጥፊያዎች በምድጃ ላይ እንዳለ በእሳት የተያያዘን መጥበሻ ወይም በቤት ማሞቂያ የተቀጣጠለን መጋረጃ የመሰሉ ቀለል ያሉ የእሳት አደጋዎች ተባብሰው ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው በፊት ለመከላከል ሊረዱ ይችላሉ። ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጡ የጦር መሣሪያዎች ጨካኙ ጠላት ኃይሉን ከማጠናከሩ በፊት ወዲያውኑ ለማጥፋት ታልመው የተሠሩ ናቸው።

ይህ ጠላት መልኩ ብዙ ነው። የእንጨት እሳት፣ የዘይትና የጋዝ እሳት ወይም የኤሌክትሪክ እሳት ሊነሳ ይችላል። በመሆኑም እነዚህ አነስተኛ የእሳት ማጥፊያዎችም ዓይነታቸው የተለያየ ነው። ጠላትህንም ሆነ መሣሪያዎችህን በሚገባ ማወቅ እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። ይህ በሙያው እንደ ሠለጠነ የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኛ የጠለቀ እውቀት ማካበት የሚጠይቅ ባይሆንም እንኳ ጥቂት መሠረታዊ ደንቦችን ማወቅ ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል የሚከተለው ዓይነት ሁኔታ ቢገጥምህ ምን ታደርጋለህ?

አንድ ዳቦ ጋጋሪ ዳቦ ለመጋገር ዘይት በደንብ የተደረገባቸው 20 አዳዲስ መጋገሪያ ሳህኖች ምድጃ ውስጥ ከትቶ እያሞቀ ነው። ይሁን እንጂ ሙቀት መቆጣጠሪያው ተበላሽቶ ስለነበር የሙቀት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ዘይቱ መጨስ ጀመረ። ጋጋሪው ወዲያውኑ ጓንት አጥልቆ ምድጃውን በመክፈት ሳህኖቹ የተደረደሩበትን ብረት ስቦ አወጣው። ሆኖም ይህን በሚያደርግበት ጊዜ እየጨሰ ያለው ዘይት አየር እንደ ልብ በማግኘቱ እሳቱ በአንድ ጊዜ ተንቦገቦገ! ቃጠሎው ተባብሶ ነበልባሉ ወደ ጣሪያ ደረሰ። ራሱን ከጉዳት መጠበቅ የቻለው ዳቦ ጋጋሪ እየተጣደፈ ወጥቶ በሰኮንዶች ውስጥ የካርቦን ዳይኦክሳይድ እሳት ማጥፊያ ይዞ በመመለስ ወዲያውኑ እሳቱን አጠፋው። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ተጨማሪ ጢስ ተፈጠረና ዘይቱ እንደገና ተቀጣጠለ። ይህ ዑደት አራት ጊዜ ተደጋገመ! ዳቦ ጋጋሪው እሳት ማጥፊያው እንዳያልቅ ስለሰጋ በአቅራቢያው የነበረውን እሳት ማጥፊያ ብርድ ልብስ ዕቃው ላይ ጣለው። ብርድ ልብሱ እሳቱን ከናካቴው ሲያጠፋለት ልቡ ተንፈስ አለ።

አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ሊባባስ የሚችልን እሳት ለማጥፋት በተቻለ መጠን የተሻለ መሣሪያ መጠቀም እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ዳቦ ጋጋሪው የሚጨስ ነገር በሚኖርበት ጊዜ በአብዛኛው መከሰቱ የማይቀረውን በኬሚካላዊ አፀግብሮት ሳቢያ የሚፈጠር እሳት በተመለከተ አንዳንድ ግንዛቤ ቢኖረው ኖሮ ምድጃውን በማጥፋትና በሮቹን በመዝጋት ምድጃው በራሱ እንዲቀዘቅዝ ማድረግ ይችል ነበር። ወይም ደግሞ መጀመሪያ የእሳት ማጥፊያ ብርድ ልብሱን ተጠቅሞ ከዚያ በኋላ ካስፈለገ የካርቦን ዳይኦክሳይዱን የእሳት ማጥፊያ መጠቀም ይችል ነበር። በዚያም ሆነ በዚህ ይህ ገጠመኝ ስለ እሳት ባሕርይና እሳትን በተሻለ ሁኔታ ማጥፋት ስለሚቻልበት መንገድ መሠረታዊ የሆነ ግንዛቤ ማግኘት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ያሳያል።

እሳት የሚፈጥረው “ትሪያንግል”

የእሳት ትሪያንግል በመባል የሚታወቀውና ለቃጠሎ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥረው ግልጽና የማያሻማ ቀመር የሚከተለው ነው:- ነዳጅ ሲደመር ኦክሲጅን ሲደመር ሙቀት ይሆናል እሳት። ከዚህ ላይ አንዱን ብትቀንስ እሳቱን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ዳግመኛ እንዳይነሳም ማድረግ ትችላለህ። ይህ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ እስቲ እንመልከት።

ነዳጅ:- ልክ እንደ እኛ እሳትም ምግብ ካላገኘ ይሞታል። የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች በደን ውስጥ እሳት በሚነሳበት ጊዜ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በመጠቀም እሳቱ የሚመጣበትን ዋና መስመር እንደ ዛፍ ካሉ ነገሮች በማጽዳት እሳቱን ያጠፉታል። በወጥ ቤት ውስጥ ደግሞ ነዳጁን ማስወገድ ማለት ጋዙን መዝጋት ብቻ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በሌሎች ሁኔታዎች ነዳጁን በቀላሉ እንዲቋረጥ ማድረግ አይቻል ይሆናል።

ኦክሲጅን:- እሳት መንደድ ይችል ዘንድ አሁንም ልክ እንደ እኛ መተንፈስ አለበት። አንድ አካፋ ሙሉ ቆሻሻ ወይም የእሳት ማጥፊያ ብርድ ልብስ እሳት ላይ ብትጥል እሳቱን ታፍነዋለህ። በነገራችን ላይ እሳቱን ለማፈን የኦክሲጅኑ መጠን የግድ ወደ ዜሮ መውረድ አያስፈልገውም። የኦክሲጅኑን መጠን በአየር ውስጥ ካለው 21 በመቶ መጠን ወደ 15 በመቶ አካባቢ ብታወርደው አንዳንድ ጠጣር የሆኑ ነገሮችን ጨምሮ በቀላሉ የሚያያዙ ፈሳሾችን የመሰሉ ብዙ ንጥረ ነገሮች መንደዳቸውን እንዲያቆሙ ልታደርግ ትችላለህ።

ሙቀት:- የቤት ማሞቂያ መሣሪያ፣ ምድጃ፣ ከልክ ያለፈ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያልፍባቸው ሽቦዎች፣ የእሳት ፍንጣሪ ወይም ፍም፣ መብረቅ፣ በመበስበስ ላይ ያሉ ተክሎች፣ በቀላሉ የመትነን ባሕርይ ያላቸው ኬሚካሎች ወይም ሌሎች በርካታ ነገሮች እሳት ሊፈጥር የሚችል ሙቀት ሊያመነጩ ይችላሉ። ጭስ ሲወጣ ከተመለከትክ በተለይ ደግሞ ጭሱ የሚወጣው በማሞቂያ ላይ ካለ ስብ ወይም ከምግብ ማብሰያ ዘይቶች ከሆነ ብዙም ሳይቆይ እሳት ሊቀጣጠል እንደሚችል መዘንጋት የለብህም።

ለእያንዳንዱ ዓይነት አነስተኛ እሳት ታልመው የተሠሩ

ብዙዎቹ መኖሪያ ቤቶች እሳት ማጥፊያዎች ባይኖሯቸውም እንኳ ፋብሪካዎች፣ ቢሮዎችና ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሕንፃዎች በአብዛኛው እነዚህን መሣሪያዎች አሟልቶ የመገኘት ሕጋዊ ግዴታ አለባቸው። ዋና ዋናዎቹ የእሳት ማጥፊያ ዓይነቶች ውኃ፣ እርጥብ ኬሚካሎች፣ አረፋ፣ ደረቅ ፓውደርና ካርቦን ዳይኦክሳይድ ናቸው። የሃሎን ጋዝ የእሳት ማጥፊያዎች በምድር ከባቢ አየር ውስጥ በሚገኘው የኦዞን ንብር ላይ ጉዳት ያደርሳሉ በሚል እንዲወገዱ ተደርጓል። ተጠቃሚዎች አደጋ በሚፈጠርበት ወቅት ትክክለኛውን እሳት ማጥፊያ መጠቀም እንዲችሉ ለመርዳት ሲባል አብዛኞቹ እሳት ማጥፊያዎች መቼ ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባና እንደማይገባ የሚጠቁሙ ስዕሎች ወይም የቀለም ኮዶች እንዲኖሯቸው ይደረጋል። በተጨማሪም አብዛኞቹ የተለያዩ የእሳት ዓይነቶችን ለይተው የሚያመለክቱ እንደ ኤ፣ ቢ ወይም ሲ ያሉ ፊደላት አሏቸው። የእሳት ማጥፊያውን እጀታ ስንጫን የታመቀው ጋዝ ንጥረ ነገሩን በቱቦው ጫፍ በከፍተኛ ፍጥነት ተፈትልኮ እንዲወጣ ይገፋዋል። እሳት ማጥፊያዎች በውስጣቸው የታመቀ ጋዝ ስለሚገኝ በየጊዜው መፈተሽ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም እሳት ማጥፊያዎች ምንጊዜም መውጪያዎች አካባቢ በቀላሉ ሊደረስባቸው በሚችሉ ቦታዎች መቀመጥ አለባቸው። እስቲ አሁን እያንዳንዱን የእሳት ማጥፊያ ዓይነት በአጭሩ እንመልከት።

የደረቅ ፓውደር እሳት ማጥፊያዎች ኬሚካላዊ በሆነ መንገድ ቃጠሎን የሚገቱ ሲሆን ሁለገብ እሳት መከላከያ ተብለው ሊጠሩ የሚችሉ ዓይነት ናቸው። ደረቅ ፓውደር የኤ መደብና የቢ መደብ እሳቶችን ብቻ ሳይሆን የሲ መደብ (የኤሌክትሪክ ዕቃዎች) እሳትንም በመዋጋት ረገድ ውጤታማ ነው። ይህ ሁለገብ እሳት ማጥፊያ ለቤትህ ጥበቃ ግሩም አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል እሙን ነው። ደረቅ ፓውደር ቤትን ሊያቆሽሽ ቢችልም እሳት ከሚያስከትለው ጥፋት አንጻር ሲታይ ግምት ውስጥ የሚገባ ላይሆን ይችላል።

የታመቀ ውኃ የያዙ እሳት ማጥፊያዎች በወረቀት፣ በእንጨት፣ በፕላስቲክ፣ በቆሻሻ ወይም በጨርቆች ላይ የሚነሱ እሳቶችን ለማጥፋት ተስማሚ ናቸው። እነዚህ በአብዛኛው መደብ ኤ የእሳት ዓይነቶች በመባል ይታወቃሉ። ውኃ ሙቀትን በከፍተኛ ደረጃ የመምጠጥ ባሕርይ ያለው በመሆኑ እሳትን በማጥፋት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። በቂ መጠን ያለው ውኃ ሙቀትን የሚያስወግድበት ፍጥነት እሳት ሙቀትን መልሶ ለመፍጠር ከሚወስደው ጊዜ የላቀ በመሆኑ እሳቱ ይከስማል። ይሁን እንጂ በቀላሉ የመንደድ ባሕርይ ባላቸው ፈሳሽ ነገሮች ላይ ውኃ አትጠቀም። ውኃ ከተጠቀምክ እሳቱን በከፍተኛ ፍጥነት ታዛምተዋለህ! በተጨማሪም ውኃ ኤሌክትሪክ የሚያስተላልፍ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊኖርባቸው በሚችሉ ሽቦዎች ላይ ውኃም ሆነ ከውኃ ጋር የተደባለቁ ፈሳሾችን የያዙ እሳት ማጥፊያዎች መጠቀም የለብህም።

የእርጥብ ኬሚካል እሳት ማጥፊያዎች ከውኃ ጋር የተቀላቀለ የታመቀ አልካሊ ጨው የያዙ ሲሆኑ በነዳጅ ዘይት ውጤቶች ላይ የሚነሳን እሳት የማጥፋት ብቃት ባይኖራቸውም እንኳ በተለይ በስብና በምግብ ማብሰያ ዘይቶች ለሚነሳ እሳት ፍቱን መድኃኒቶች ናቸው። የመደብ ኤ እሳትን በማጥፋት ረገድም ውጤታማ ናቸው።

የአረፋ የእሳት ማጥፊያዎች የመደብ ኤ እሳትን ብቻ ሳይሆን በይበልጥ መደብ ቢ በመባል የሚታወቀውን በቀላሉ የመንደድ ባሕርይ ባላቸው ፈሳሾች (እንደ ማሽን ላሉ ነገሮች የሚያገለግሉ የኢንዱስትሪ ቅባቶች፣ ነዳጅ፣ ቀለም) ላይ የሚነሳውን እሳት በማጥፋት ረገድ የተዋጣላቸው ናቸው። ሁለት ዓይነት የአረፋ የእሳት ማጥፊያዎች ስላሉ ለአንተ ይበልጥ ተስማሚ የሚሆነው የትኛው እንደሆነ አጣርተህ ለማወቅ ሞክር። አረፋው እየተቃጠለ ባለ ፈሳሽ ላይ ሲነፋ ምንም ነገር በማያሳልፍ ስስ ሽፋን ፈሳሹን በመሸፈን በቀላሉ የመትነን ባሕርይ ያላቸው ተኖች እንዳይንቀሳቀሱና ምንም ኦክሲጅን እንዳያገኙ ያደርጋል። ስለዚህ አረፋው ፈሳሹ ውስጥ ዘልቆ ከመግባት ይልቅ በቀላሉ ላዩ ላይ እንዲፈስ በዝግታ መርጨት ያስፈልጋል። ኤሌክትሪክ አጠገብ አረፋ እንዳትረጭ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል።

የካርቦን ዳይኦክሳይድ እሳት ማጥፊያዎች በጋዝ ሳቢያ ከሚፈጠር እሳት በስተቀር ለሁሉም ዓይነት እሳት ያገለግላሉ ለማለት ይቻላል። እነዚህ እሳት ማጥፊያዎች ካርቦን ዳይኦክሳይድ ኦክሲጅንን ያስወግዳል በሚለው መርህ መሠረት ጥቅም ላይ የዋሉ ናቸው። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንዳየነው የሚቀጣጠለው ንጥረ ነገር ሙቀቱን ጠብቆ መቆየት ከቻለ ዳግመኛ ሊነድድ ይችላል። ካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ እንደመሆኑ መጠን አየር በበዛበት ክፍት ቦታ ላይ ውጤታማነቱ ይቀንሳል። ይሁን እንጂ ምንም የማያቆሽሽ መሆኑ በረቀቁ ማሽኖችና የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች ላይ የሚነሳን እሳት ለማጥፋት ተመራጭ ያደርገዋል። ይሁን እንጂ ካርቦን ዳይኦክሳይድ በተፋፈገ ክፍል ውስጥ ትንፋሽ አሳጥቶ ራስን ሊያስት ወይም ሊገድል ስለሚችል በእንዲህ ዓይነት ክፍል ውስጥ ከተጠቀምክበት እሳቱ እንደጠፋ ክፍሉን ለቅቀህ መውጣትና በሩን በኋላህ መዝጋት ይኖርብሃል።

እሳት ማጥፊያ ብርድ ልብስ * በቀላሉ ልንጠቀምበት የምንችል የእሳት መከላከያ ሲሆን በወጥ ቤት ምድጃ አናት ላይ ወይም በአንድ ምንጣፍ የተወሰነ ቦታ ላይ ብቻ የሚነሳን እሳት የመሰለ አነስተኛና ብዙም ያልተስፋፋን እሳት ለማጥፋት ተስማሚ ነው። ብርድ ልብሱን በግድግዳ ላይ ከሚሠቀለው ንጹሕና አነስተኛ ማስቀመጫው ውስጥ አውጥተህ ራስህን ከነበልባሉ ለመከላከል ፊት ለፊትህ ከዘረጋኸው በኋላ እሳቱ ላይ ጣለው። ሙቀቱን የሚያመነጨውን መሣሪያ ገና አልዘጋኸው ከሆነ በተቻለ መጠን በፍጥነት ዝጋው።

በተጨማሪም ልብስህ በእሳት ከተያያዘ የእሳት ማጥፊያ ብርድ ልብሶች ሕይወትህን ሊታደጉት ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በሚገጥምህ ጊዜ የሚከተለውን እጅግ ጠቃሚ የሆነ መመሪያ አስታውስ:- “ባለህበት ቁም፣ መሬት ላይ ተኛ፣ ከዚያ ተንከባለል።” እሳቱን ከማራገብ ሌላ የምትፈይደው ነገር ስለማይኖር ፈጽሞ መሮጥ የለብህም። በምትንከባለልበት ጊዜ እሳት ማጥፊያ ብርድ ልብሱን ሰውነትህ ላይ መጠቅለል ከቻልክ ወይም ሌላ ሰው ከጠቀለለልህ እሳቱን በተሻለ ፍጥነት ልታጠፋው ትችላለህ።

ከእሳት ማጥፊያዎች የተሻለ ነገር

እርግጥ፣ ከእሳት ለመጠበቅ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ቀድሞውኑ እሳት እንዳይነሳ መከላከል ነው። ስለዚህ የማስተዋል ችሎታህን በሚገባ መጠቀም ይኖርብሃል። ክብሪቶችንና እሳት መለኮሻዎችን ልጆች በማይደርሱበት ቦታ አስቀምጥ። በቀላሉ በእሳት ሊያያዙ የሚችሉ ነገሮችን በሙሉ ከምድጃው አካባቢ ማራቅ ይኖርብሃል። ምግብ በምታበስልበት ጊዜ በእሳት ሊያያዙ የሚችሉ ሰፊና ረጅም እጅጌ ያላቸውን ልብሶች አትልበስ። ጭስ በሚፈጠርበት ጊዜ ድምፅ የሚሰጡ መሣሪያዎችን ቤትህ ውስጥ አስገጥም።

ከዚህ ቀጥሎ አንዳንድ ተጨማሪ ሐሳቦች ቀርበዋል። በኤሌክትሪክ ሽቦዎች ወይም በኤሌክትሪክ መስመር ማስረዘሚያዎች ውስጥ የሚያልፈው የኤሌክትሪክ ኃይል ከልክ አልፎ ሽቦዎቹን እንዳያቀልጥ ጥንቃቄ አድርግ። ስብ የሆኑ ነገሮችን ወይም ዘይቶችን በጋለ ምድጃ ላይ ጥደህ ጥለህ አትሂድ። ቤት ማሞቂያ መሣሪያዎችን አደጋ ሊያስከትል የሚችል ቦታ ላይ እንዳታስቀምጥ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል። ቤትህ አጠገብ የተቀመጡ ጋዝ የተሞሉ ሲሊንደሮች ካሉ እሳት ሊያቀጣጥሉ የሚችሉትን ማስተንፈሻ ክፍክዶች (safety valves) ከቤትህ በተቃራኒ አቅጣጫ አዙረህ ማስቀመጥ ይኖርብሃል። ትክክለኛ መጠን ያላቸውን የኤሌክትሪክ ባልቦላዎች (fuses) ተጠቀም። የተጎዱ የኤሌክትሪክ ገመዶችን ለውጥ።

በቤት ውስጥ እሳት ቢነሳ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች አስቀድመህ ልምምድ ለማድረግ አስበህ ታውቃለህ? እንዲህ ዓይነቱ ልምምድ ሕይወትን ሊታደግ ይችላል። እሳት ቢነሳ ቤተሰቡ በቀንም ሆነ በማታ በቀላሉ ሊገኝ በሚችል አንድ ግልጽ ቦታ ላይ እንዲሰባሰብ አድርግ። በተጨማሪም ኃላፊነት ስጥ:- ሕፃናትን ወይም የአካል ጉዳተኛ የሆኑትን የሚያወጣቸው ማን ነው? ለእሳት አደጋ መከላከያ ጣቢያ የሚያሳውቀው ማን ነው? አዎን፣ እንዲህ ዓይነቱ ልምምድ ወዲያውኑ በደመ ነፍስ ትክክለኛውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሥልጠና የሚሰጥ በመሆኑ ሕይወትን ሊታደግ ይችላል።

የከፋ ነገር ቢከሰት

ንብረት ሊተካ ይችላል፤ ሕይወት ግን ሊተካ አይችልም። የተነሳውን እሳት ካላጠፋሁ ብለህ ሕይወትህን አደጋ ላይ መጣል የለብህም። ይሁን እንጂ ከአደጋ ነፃ ሆነህ እሳቱን መዋጋት እንደምትችል ሆኖ ከተሰማህ ማምለጥ በምትችልበት ቦታ ላይ ሆነህ እሳቱን መከላከል ትችላለህ። ሆኖም ያለህ የእሳት ማጥፊያ ትክክለኛው ዓይነት መሆኑን ከተጠራጠርክ ወይም እሳቱን ሊቋቋመው እንደማይችል ሆኖ ከተሰማህ ወዲያውኑ ወጥተህ ለእሳት አደጋ መከላከያ ጣቢያ ማሳወቅ ይኖርብሃል።

በተጨማሪም ከእሳት ይልቅ ጭስ በተለይ ደግሞ ሰው ሠራሽ ከሆኑ ነገሮች የሚወጣ መርዘኛ ጭስ ብዙ ሰዎችን ሊገድል እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብሃል። ከሁለት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሕልፈተ ሕይወት ሊዳርግ ይችላል! ስለዚህ እየተቃጠለ ካለ ሕንፃ በምትወጣበት ጊዜ በተቻለ መጠን ወደ ታች አጎንብስ። በወለሉ አካባቢ የሚኖረው አየር ቀዝቀዝ ያለ ከመሆኑም በላይ ብዙ ጭስ አይኖረውም። ከቻልክ ረጠብ ባለ ጨርቅ አፍህን ሸፍን። በር ከመክፈትህ በፊት በመዳፍህ ጀርባ ንካው። በሩ ግሎ ከሆነ ከበሩ በስተኋላ እሳት አለ ማለት ነው፤ ስለዚህ ሌላ መውጪያ መፈለግ ይኖርብሃል። ስትወጣ በሮቹን በሙሉ ከበስተኋላህ ዝጋ። ይህ እሳቱ ብዙ ኦክሲጅን እንዳያገኝ ለማድረግ ይረዳል። እሳት በሚነሳበት ጊዜ አሳንሰር መጠቀም በጣም አደገኛ ነው። እዚያው አስሮ ሊያስቀርህና ወደ ምድጃነት ሊቀየር ይችላል!

እንግዲያው ለቤትህ፣ ለመኪናህ ወይም ለድርጅትህ እሳት ማጥፊያ ለመግዛት ካሰብክ በጉዳዩ ላይ በአካባቢህ ከሚገኙ የእሳት አደጋ መከላከያ ጣቢያ ባለሥልጣናት ጋር መወያየትህ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ይበልጥ ዝርዝር የሆኑት ጉዳዮች ከአገር ወደ አገር ሊለያዩ የሚችሉ ከመሆኑም በላይ ሁሉንም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ማካተት አይቻልም።

ያም ሆነ ይህ ከእንግዲህ ከእነዚህ ድምፅ አልባ የሆኑ ትናንሽ ዘብ ጠባቂዎች አንዱን ስትመለከት ቆም ብለህ በደንብ ለመተዋወቅ ሞክር። ማን ያውቃል፣ አንድ ቀን ትልቅ ውለታ ይውልልህ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.18 እሳት ማጥፊያ ብርድ ልብስ በአገርህ በብዛት የሚሠራበት ከሆነ አጠቃቀሙን በትክክል ጠንቅቀህ ማወቅ ይኖርብሃል። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የእሳት አደጋ መከላከያ ማኅበር እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እሳት ማጥፊያ ብርድ ልብሶች በሁለተኛ ደረጃ ሊታዩ የሚገባቸው ነገሮች መሆናቸው . . . መዘንጋት የለበትም። ልንጠቀምባቸው የሚገባው በቅርብ የሚገኙ ከሆነ ብቻ ነው። . . . የእሳት ማጥፊያ ብርድ ልብሱን በተሳሳተ መንገድ በመጠቀማችን የተነሳ ብርድ ልብሱ ጭሱን ወደ ፊታችን የሚለቀው ከሆነ ወይም እሳቱ ከጠፋ በኋላ ብርድ ልብሱ ካልተነሳ ጭሱና እሳቱ የሚያስከትሉትን ጉዳት የከፋ ሊያደርገው ይችላል።”

[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች/ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

እሳት

ነዳጅ

ሙቀት

ኦክሲጅን

[ሥዕሎች]

መደብ ኤ

መደብ ቢ

[ምንጭ]

Chubb Fire Safety

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ልብስህ በእሳት ከተያያዘ አትሩጥ

1. ባለህበት ቁም

2. መሬት ላይ ተኛ

3. ተንከባለል

[ምንጭ]

© Coastal Training Technologies Corp. Reproduced by Permission

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቤት ውስጥ የሚነሳን እሳት ለማጥፋት የሚያገለግሉ በርካታ ሁለገብ እሳት ማጥፊያዎች አሉ

[ምንጭ]

ከላይ ያለው ሥዕል:- Reprinted with permission from NFPA 10 - 1998, Portable Fire Extinguishers, Copyright © 1998, National Fire Protection Association, Quincy, Massachusetts 02269. This reprinted material is not the complete and official position of the NFPA on the referenced subject which is represented only by the standard in its entirety.