በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ሃይማኖተኛ ሰዎች ረጅም ዕድሜ ይኖራሉን?

“በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች አዘውትሮ መካፈል ከተሻለ አካላዊ ጤናና ከረጅም ዕድሜ ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳለው ከ1977 አንስቶ ይህን ጉዳይ በማስመልከት የወጡት 42 የተለያዩ ጥናቶች አኃዛዊ ትንተና ያሳያል” ሲል ሳይንስ ኒውስ ይገልጻል። “ከአኃዛዊ መረጃዎች አንጻር ሲታይ በተለይ ሕዝባዊ በሆኑ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ከዕድሜ መርዘም ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳለው ሳይንቲስቶቹ ይናገራሉ።” ለአደጋ ከሚያጋልጡ ምግባሮች መራቅ፣ የሰከነ የትዳር ሕይወት፣ ከአቅም በላይ በሆኑ ጉዳዮች ከልክ በላይ አለመጨነቅ፣ የተሻለ ማኅበራዊ ግንኙነት፣ እንዲሁም አዎንታዊ ስሜትና አመለካከት ለዚህ እንደ ምክንያት ሆነው ተጠቅሰዋል። አንድ ዘገባ የሚከተለውን መደምደሚያ ሰጥቷል:- “አዘውትሮ በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ መገኘት . . . በተለይ ከሴቶች ዕድሜ መርዘም ጋር ዝምድና አለው። አዘውትረው በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ የሚገኙ ሰዎች . . . ከፍተኛ ማኅበራዊ ድጋፍ እንደሚያገኙ፣ ያለባቸው የመንፈስ ጭንቀት አነስተኛ እንደሆነና ለጤና ተስማሚ የሆነ ልማድ እንደሚከተሉ ተገልጿል።”

ዓሣ ነባሪን ፈላጊ ያሳጣ ብክለት

ብክለት ዓሣ ነባሪዎችን ከጥፋት ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ባልታሰበ መንገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል። በቅርቡ የተካሄዱ ምርመራዎች እንዳመለከቱት ከጃፓን የባሕር ዳርቻ ራቅ ባለ ቦታ ላይ የተያዙት ዓሣ ነባሪዎችና ዶልፊኖች በዲ ዲ ቲ፣ በዳይኦክሲን፣ በፒ ሲ ቢ ኤስ እና በሜተልሜርኩሪ በከፍተኛ ሁኔታ የተበከሉ ነበሩ። አንድ ምርመራ እንደጠቆመው ከሆነ 50 ግራም ብቻ የሚመዝን የተበከለ የዶልፊን ሥጋ መብላት በሰው ጤና ላይ ትልቅ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። አንዳንዶች እንደሚገምቱት ከሆነ እንዲህ ያሉት ዜናዎች የዓሣ ነባሪን ሥጋ ፈላጊ ሊያሳጡ ይችላሉ።

ሐዘንና የመንፈስ ጭንቀት

ከ70 እስከ 79 ዓመት ድረስ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት ባላቸውን ወይም ሚስታቸውን በሞት ያጡ አንዳንድ ሰዎች የትዳር ጓደኛቸውን ካጡ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶች እንደሚታዩባቸው አመልክቷል። በጥናቱ ላይ የተካፈሉት ሰዎች የትዳር ጓደኛቸውን በሞት አጥተው ያሳለፉትን የጊዜ ርዝመት መሠረት በማድረግ በስድስት ቡድኖች ተከፍለው ነበር። ቃለ ምልልሶቹም ሆኑ መጠይቆቹ የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶችን ለመመዘን የተዘጋጁ ነበሩ። ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ከሰጡት መካከል 38 በመቶዎቹ ወንዶች 62 በመቶዎቹ ደግሞ ሴቶች ነበሩ። የትዳር ጓደኛቸውን በቅርቡ በሞት ያጡ ሰዎች ያለባቸው የመንፈስ ጭንቀት ባለ ትዳር የሆኑና የዚህ ዓይነት ሐዘን ያልደረሰባቸው ሰዎች ካለባቸው የመንፈስ ጭንቀት ዘጠኝ እጅ እንደሚበልጥ ጥናቱ አመልክቷል።

ለመጠጥነት ሊውል ይችላል?

ዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ጥበቃ ድርጅት (ደብሊው ደብሊው ኤፍ) በፈረንሳይ ያለው የውኃ የጥራት ደረጃ “ምንም ዓይነት መፍትሔ ሊገኝለት ወደማይችል ደረጃ ላይ ከመድረሱ” በፊት “አንድ ዓይነት የመከላከያ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል” በማለት አስጠንቅቋል። ደብሊው ደብሊው ኤፍ እንደሚለው ከሆነ በፈረንሳይ ከምድር በታችና በምድር ገጽ ላይ የሚገኘው ውኃ በተባይ ማጥፊያዎችና በናይትሬት በመበከል ላይ ይገኛል። የናይትሬት ብክለቱ በአብዛኛው የሚከሰተው የአሳማና የከብቶች ፍግ ወደ ውኃው አካል በሚገባበት ጊዜ ነው። ዘገባው “በብሪታኒ ክልል የሚገኙት ስምንት ሚልዮን የሚሆኑ አሳማዎች ፍግ 24 ሚልዮን ሰዎች የሚኖሩባት ምንም ዓይነት የቆሻሻ ማስወገጃ የሌላት ከተማ ከሚኖራት ፍሳሽ ጋር ሊነጻጸር ይችላል!” ከዚህም ሌላ “መጠነ ሰፊ በሆኑ እርሻዎች ላይ የሚውለው ከፍተኛ መጠን ያለው ማዳበሪያ” የውኃ አካላት በናይትሬት እንዲበከሉ ያደርጋል ሲል ደብሊው ደብሊው ኤፍ ገልጿል። በተጨማሪም ከበቆሎ ምርት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ተባይ ማጥፊያዎች ጥቅም ላይ በመዋላቸው የተባይ ማጥፊያው መጠን ደንቡ ከሚፈቅደው ደረጃ ከ40 በመቶ በላይ ጨምሯል። ደብሊው ደብሊው ኤፍ ያወጣው ዘገባ ተፈጥሯዊ ማጣሪያዎች ሆነው የሚያገለግሉ ረግረጋማ መሬቶች እንዲዘጋጁና የእንጨት ግድቦች ዳግም እንዲሠሩ ሐሳብ አቅርቧል።

በአውሮፓ የሚፈጸም ከባድ ቅጣትና የጭካኔ ድርጊት

“ስደተኞችን በኃይል ከአገር ለማስወጣት በሚደረገው ጥረት ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት መዳረግ፣ በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ በተደረጉ ሰዎች ላይ የሚፈጸም ከባድ ቅጣት፣ ፖሊስ ሆን ብሎ የሚፈጽመው በደልና የዘርና የሃይማኖት ጭቆና” በአውሮፓ ከሚታዩት የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ይላል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው መግለጫ። “ምንም እንኳ በአውሮፓ የብዙዎቹ ሰዎች መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩ ቢሆንም ጥገኝነት የሚጠይቁ ሰዎችን እንዲሁም አናሳ ጎሳዎችንና ሃይማኖቶችን ጨምሮ አንዳንድ ሰዎች የሰብዓዊ መብቶችና የነፃነት መከታ ተደርጋ የምትታየውን አህጉር ገጽታ ፈጽሞ የሚጻረር ድርጊት እየተፈጸመባቸው ይገኛል” ይላል መግለጫው። “ይህን ሁኔታ ፖሊስ የሚፈጽመውን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት አስመልክቶ በተደጋጋሚ ጊዜያት በስፋት ከሚናፈሰው ወሬ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ከታላቋ ብሪታንያ አንስቶ እስከ አዘርባጃን ድረስ ሰዎች . . . በፖሊስ እጅ ጭካኔ የተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ የሆነ ወይም ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ በደል ተፈጽሞባቸዋል።” ድርጅቱ እንደሚለው ከሆነ ብዙውን ጊዜ ተጠያቂ የሆኑት ግለሰቦች ለፍርድ አይቀርቡም። ለዚህም የሚከተለውን ምሳሌ ይጠቅሳል:- “በሐምሌ [1999] የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከባድ ቅጣትንና አድልዎን አስመልክቶ ባካሄደው ችሎት ላይ ፈረንሳይ” ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ታስሮ ከቆየ አንድ ስደተኛ ጉዳይ ጋር በተያያዘ “ዓለም አቀፍ ደንቦችን እንደጣሰች አረጋግጧል።” “ተከሳሾቹ ፖሊሶች በዓመቱ መገባደጃ ላይም ከኃላፊነት ቦታቸው አልተነሱም ነበር” ሲል ዘገባው አክሎ ገልጿል።

ከተሞች የአየሩን ጠባይ እያዛቡት ነው

“በከተሞች ውስጥ የሚታየው ፈጣን ዕድገት ለየት ያሉ ‘የሙቀት ቀጣናዎች’ እያስከተለ በመሆኑ ከተሞቹ የራሳቸውን የአየር ጠባይ ሥርዓት በመፍጠር ላይ ናቸው” ሲል የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል። ከተሞቹ ቀን ላይ ሙቀቱን አምቀው ይይዙና ሌሊት መልሰው ወደ ጠፈር ይለቁታል። በመሆኑም እንደ ቤጂንግና አትላንታ ባሉ ከተሞች ያለው የሙቀት መጠን 5.5 ዲግሪ ሴልሸስ ወይም ከዚያ በላይ ጨምሯል። ታይምስ እንደዘገበው በአትላንታ ማዕከላዊ ክፍል የተመዘገበው የሙቀት መጠን በከተማዋ ዙሪያ ባሉት ገጠራማ ሥፍራዎች ከተመዘገበው የሙቀት መጠን በ22 ዲግሪ ሴልሸስ ይበልጣል። ባለፉት 19 ዓመታት በአትላንታ በዛፎች ተሸፍኖ የነበረ 150, 000 ሄክታር መሬት ተመንጥሮ መንገዶችና ቤቶች ተሠርተውበታል። የከተሞች መስፋፋት የአየር ብክለት ይጨምራል፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ነጓድጓዳማ ውሽንፍር ያስከትላል፣ እንዲሁም በእርሻ መሬቶች ላይ የሚኖረውን የፎቶሲንተሲስ ሂደት ያዳክማል። የብሔራዊ የበረራ ሳይንስና የጠፈር አስተዳደር ሳይንቲስት የሆኑት ዶክተር ማርክ ኢምሆፍ እነዚህ “የሙቀት ቀጣናዎች” የሚያስከትሉትን ሁኔታ በተመለከተ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “የሰው ልጅ ሕይወት ገፀምድሩ ባለው እህል የማምረት አቅም ላይ የተመካ ነው። ገፀምድሩ ፎቶሲንተሲስ የማካሄድ አቅሙ በከፍተኛ ሁኔታ ከተዳከመ ፕላኔቷ የሰውን ልጅ ሕይወት ደግፎ የማቆየት አቅሟ መቀነሱ አይቀርም።” አብዛኛውን ጊዜ እንደሚታየው ከተሞች እየተስፋፉ በሄዱ መጠን ለእርሻ እጅግ ተስማሚ የሆነው መሬት ለሌላ ዓላማ ይውላል።

“ራሱን በራሱ የሚያነጻው” ሎተስ

በምሥራቃውያን ሃይማኖቶች ለረጅም ዘመናት እንደ ቅዱስ ተደርጎ ሲታይ የኖረው ሎተስ የተሰኘው ተክል ሁልጊዜ ንጹሕ ሆኖ የሚታየው ለምንድን ነው? የጀርመን ሳይንቲስቶች የስነ ሕይወት ባለሙያዎችን ለብዙ ዘመናት ግራ ሲያጋባ ለኖረው ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል። “ውኃ ስለማያስገቡ የዕፅዋት ገጾች ከታወቀ ብዙ ዘመናት ተቆጥሯል” ይላሉ ሳይንቲስቶቹ ደብሊው ባርትሎት እና ሲ ናይንሁስ። “ይሁን እንጂ ራሳቸውን በራሳቸው የማንጻት ባሕርይ ያላቸው መሆኑን . . . ፈጽሞ ያስተዋለ አልነበረም።” ዘ ሰንዴይ ታይምስ ኦቭ ኢንዲያ እንደገለጸው “ከሎተስ ቅጠል ላይ የሚወርዱት የውኃ ጠብታዎች በካይ የሆኑ ቅንጣቶችን ይዘው በመውረድ ገጹን በተሟላ ሁኔታ ያጸዱታል።” ይህ የሚሆነው ገጹ ለስላሳ በመሆኑ አይደለም። በአጉሊ መነፅር ሲታይ ቅጠሉ “አበጥ ያሉ ነገሮች ያሉትና በሸንተረር የተሞላ” እንዲሁም “የግማሽ ክብ ወይም የጉልላት ዓይነት ቅርፅ የያዘ ውኃ የማያሰርግ” ሸካራ ገጽ ያለው ነው። ከዚህ በተጨማሪ ተክሉ የተሸፈነበት ውኃ የማያስገባ እንደ ሰም ያለ ንጥረ ነገር ለተክሉ ንጽሕና የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ተመራማሪዎቹ ይህ “የሎተስ ተክል ባሕርይ” ውኃና የቆሻሻ ቅንጣቶች በተክሉ ላይ ተጣብቀው እንዳይቀሩ በከፍተኛ ደረጃ የሚከላከል እንደሆነ ከመጠቆማቸውም በላይ ተክሉ መጥፎ አካባቢያዊ ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜም እንኳ ዳግመኛ ሰም ማመንጨት እንደሚችል አክለው ገልጸዋል። ይህ ሁኔታ ይላሉ ተመራማሪዎቹ፣ ሎተስ ያለው ተፈጥሯዊ ብቃት ውኃ ከማያሰርጉ ሠው ሠራሽ ቀለሞችም ሆነ የንጽሕና መገልገያ ኬሚካሎች የላቀ እንዲሆን ያደርገዋል።

በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣ ሕገወጥ ንግድ

ሰዎችን እንደ ሸቀጥ መነገድ “በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣ ሕገወጥ ንግድ ሆኗል” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአደገኛ መድኃኒቶች ቁጥጥርና የወንጀል መከላከያ ቢሮ ዋና ኃላፊ የሆኑት ፒኖ አርላኪ ተናግረዋል። ሚስተር አርላኪ እንዳሉት ከሆነ ወደ 200 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን ሕገወጥ ንግድ በሚያካሂዱ ግለሰቦች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ ይገመታል። የባሪያ ንግድ ይካሄድ በነበረባቸው 400 ዓመታት 11.5 ሚልዮን ሰዎች ከአፍሪካ የተጋዙ ሲሆን ባለፈው አሥርተ ዓመት ብቻ ከደቡብ ምሥራቅ እስያ የተወሰዱት ሴቶችና ሕፃናት ግን ከ30 ሚልዮን በላይ ይሆናሉ። አብዛኞቹ በፋብሪካዎች ውስጥ ጉልበታቸው ይበዘበዛል አለዚያም ለወሲባዊ ዓላማ መጠቀሚያ ይሆናሉ። ሚስተር አላርኪ በአሁኑ ጊዜ የፀረ ባርነት ሕግ የሌላቸው አገሮች እነዚህን ሕጎች መልሰው ሥራ ላይ እንዲያውሉ ሐሳብ አቅርበዋል።

የሕንድ ሕዝብ ብዛት ከአንድ ቢልዮን አለፈ

የሕንድ ሕዝብ ብዛት ግንቦት 11, 2000 ላይ አንድ ቢልዮን እንደደረሰ ተነግሯል። ይሁን እንጂ “በየቀኑ 42, 000 ሕፃናት በሚወለዱበትና የሕክምና መረጃዎች በተሟላ ሁኔታ በማይጠናቀሩበት አገር የሕዝቡ ብዛት 1 ቢልዮን የደረሰበትን ጊዜ በትክክል ማወቅ በጣም ከባድ ነው” ሲል አሶስዬትድ ፕሬስ ገልጿል። ምንም እንኳ በእህል ምርትና በትምህርት ረገድ ከፍተኛ እመርታዎች የታዩ ቢሆንም በሕዝቡ ቁጥር ማደግ የተነሳ ረሃብና መሃይምነት እየተስፋፋ ሄዷል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በድህነት በመማቀቅ ላይ ቢሆኑም እንኳ አንድ ሕፃን ሲወለድ ወደፊት ሠርቶ ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር በማሟላት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ደሞዝተኛ እንደሚሆን ተደርጎ ይታያል።