ግቦች በማውጣት መሰናክሎችን መወጣት
ግቦች በማውጣት መሰናክሎችን መወጣት
ዊልያም (ቢል) ማይነርስና ባለቤቱ ሮዝ የሚኖሩት በኒው ዮርክ ከተማ ለጋርዲያ አውሮፕላን ማረፊያ አጠገብ በሚገኝ አንድ አፓርተማ ውስጥ ነው። በሰባዎቹ ዓመታት ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኘውና ፍልቅልቅ እንግዳ ተቀባይ የሆነችው ሮዝ እንግዳዋን በደስታ ተቀበለች። እቤትዋ የገባ ሁሉ ከሳሎንዋ አቀማመጥና አጋጌጥ ደስተኛ ሴት መሆኗን በቀላሉ መገንዘብ ይችላል። በመተላለፊያው በር ላይ የሚገኙት አበባዎች አቀማመጥና ማራኪነት፣ በግድግዳዎቹ ላይ የተሰቀሉት የቀለም ቅብ ስዕሎች ማማር የደስታና የመኖር ፍላጎት ስሜት ያስተላልፋሉ።
ከሳሎኑ ቀጥሎ በሚገኘው ብሩሕ ክፍል ውስጥ የ77 ዓመቱ ቢል ጀርባው ከፍና ዝቅ ሊል በሚችል ፍራሽ ተደግፎ አልጋ ላይ ተኝቷል። ሊጠይቀው የመጣውን ሰው ሲመለከት ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ዓይኖቹ በራ አሉና ከንፈሮቹን በማላቀቅ ፈገግ አለ። ብድግ ብሎ እጁን ቢጨብጥና እቅፍ ቢያደርገው ደስ ይለው ነበር። ግን አይችልም። ቢል ከግራ ክንዱ በቀር ከአንገቱ በታች ሙሉ በሙሉ ሽባ ሆኗል።
ቢል ከ26 ዓመት ዕድሜው ጀምሮ የጤና እክል ተለይቶት ስለማያውቅ ላለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት ሕመሙን ተቋቁሞ እንዲኖር የረዳው ምን እንደሆነ ተጠየቀ። ቢልና ሮዝ እርስ በርስ ተያዩና ተሳሳቁ። ሮዝ “እዚህ ቤት ውስጥ ታማሚ ሰው አለ እንዴ?” ብላ ቤቱን በሳቅ ሞላችው። የቢልም ዓይኖች በደስታ ስሜት ተሞሉና ከሚስቱ ጋር መስማማቱን ራሱን በመነቅነቅ ገለጸ። “ሕመምተኛ ሰው የለብንም” አለ በጎርናናና በሚቆራረጥ ድምፅ። ሮዝና ቢል ሌሎች ቀልዶችን ተለዋወጡና ወዲያው ክፍሉ በሳቅ ተሞላ። በእርግጥ ሮዝና ቢል በ1945 መስከረም ወር ላይ ሲገናኙ የነበራቸው ፍቅር አሁንም ገና ሕያው እንደሆነ በግልጽ ይታያል። ቢል በድጋሚ “ወደ ቁም ነገሩ እንመለስና ምን ዓይነት መሰናክሎች አጋጥመውሃል? እነዚህንስ እንድትቋቋምና ለሕይወት ያለህን ብሩሕ አመለካከት ይዘህ እንድትቀጥል የረዳህ ምንድን ነው?” ተብሎ ተጠየቀ። ከትንሽ ጉትጎታ በኋላ ቢል ታሪኩን ለመናገር ተስማማ። ቀጥሎ የሰፈረው ንቁ! ከቢልና ከባለቤቱ ጋር ካደረጋቸው በርካታ ጭውውቶች የተውጣጣ ነው።
የመሰናክሎቹ አጀማመር
በጥቅምት ወር 1949 ቢል ሮዝን ካገባ ከሦስት ዓመት በኋላና ልጃቸው ቪኪ ከተወለደች ከሦስት ወር በኋላ በአውታረ ድምፁ ላይ የካንሰርነት ባሕርይ ያለው እብጠት እንደወጣበት ተነገረውና እብጠቱ ተቀዶ ወጣ። ከጥቂት ወራት በኋላ የቢል ሐኪም ሌላ መሰናክል እንደተከሰተ፣ ማለትም ካንሰሩ ሙሉ በሙሉ ወደ ማንቁርቱ እንደተዛመተ ነገረው። “ማንቁርቴ ሙሉ በሙሉ ተቆርጦ ካልወጣ ከሁለት ዓመት የበለጠ ዕድሜ እንደማይኖረኝ ተነገረኝ።”
የዚህ ቀዶ ሕክምና ውጤት ምን እንደሚሆን ለቢልና ሮዝ ተነገራቸው። ማንቁርት ወይም የድምፅ ሣጥን ከምላስ መነሻ አንስቶ እስከ ትንፋሽ ቧንቧ ይደርሳል። በማንቁርት ውስጥ ሁለት የድምፅ አውታሮች ይገኛሉ። ከሳንባ የሚወጣው አየር በእነዚህ አውታሮች በኩል በሚያልፍበት ጊዜ ይርገበገቡና በንግግር ጊዜ የሚሰማውን ድምፅ ይፈጥራሉ። ማንቁርት ተቆርጦ በሚወጣበት ጊዜ በአንገት በኩል አየር የሚያስገባ ቀዳዳ እንዲኖር ይደረጋል። ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ታካሚው በዚህ ቀዳዳ በኩል ይተነፍሳል። ድምፅ የማውጣት ችሎታ ግን አይኖረውም።
“ይህን ማብራሪያ ስሰማ ተቆጣሁ” ይላል ቢል። “ሕፃን ልጅ አለችን። ጥሩ ሥራ አለኝ፣ ስለ ወደፊቱ ሕይወታችን በጣም ብሩሕ ተስፋ ነበረን፤ አሁን ግን ተስፋ ያደረኩት ነገር ሁሉ መና ሆነ።” ይሁን እንጂ ማንቁርቱ ተቆርጦ ከወጣ የቢል ሕይወት ሊተርፍ ስለሚችል ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ ተስማማ። ቢል ታሪኩን በመቀጠል “ከቀዶ ሕክምናው በኋላ መዋጥ አቃተኝ። አንድ ቃል እንኳን መተንፈስ አልቻልኩም። ሙሉ በሙሉ ድዳ ሆንኩ” ይላል። ሮዝ ልትጠይቀው ስትሄድ ሐሳቡን የሚገልጸው ማስታወሻ ላይ በመጻፍ ብቻ ነበር። በጣም አስጨናቂ ጊዜ ነበር። ይህን መሰናክል ለመወጣት የሚያስችል አዲስ ግብ ማውጣት ነበረባቸው።
መናገር የተሳነውና ሥራ አጥ ሆነ
በማንቁርቱ ላይ የተደረገው ቀዶ ሕክምና ቢልን ድዳ ከማድረጉም በተጨማሪ ሥራ አጥ አደረገው። ይሠራ የነበረው የብረታ ብረት ቅርጽ ማውጫ ድርጅት ውስጥ ነበር። አሁን ግን መተንፈስ የሚችለው በአንገቱ ላይ በተበሳለት ቀዳዳ በኩል ብቻ ስለሆነ አቧራና ጭስ ቢገባበት በሳንባው ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል። ሌላ ሥራ ማግኘት ይኖርበታል። መናገር የተሳነው ቢል ሰዓት ሥራ ወደሚማርበት ትምህርት ቤት ገባ። “ከቀድሞ ሥራዬ ጋር ይመሳሰላል” ይላል ቢል። “የተለያዩ የማሽን ክፍሎች እንዴት እንደሚገጣጠሙ አውቃለሁ። ሰዓት በሚሠራበት ጊዜም የተለያዩ ክፍሎች ይገጣጠማሉ። ልዩነቱ ክፍሎቹ 20 ኪሎ የማይመዝኑ መሆናቸው ነው!” የሰዓት ሥራ ትምህርቱን እንደጨረሰ የሰዓት ሠሪነት ሥራ አገኘ። አንደኛውን ግብ አሳካ።
በዚሁ ጊዜ ቢል በጉሮሮ የመናገር ትምህርት መከታተል ጀመረ። በጉሮሮ ንግግር ድምፅ የሚፈጠረው በድምፅ አውታሮች ሳይሆን ምግብ ከአፍ ወደ ሆድ በሚያስተላልፈው ቧንቧ ማለትም በጉሮሮ ውስጥ በሚፈጠር እርግብግቢት ነው። በመጀመሪያ አየር ስቦ ወደ ጉሮሮ የገባውን አየር ወደ ምግብ ቧንቧው እንዴት መግፋት እንደሚችል ይማራል። ከዚያም አየሩን በመቆጣጠር ወደ ውጭ እንዴት እንደሚያስወጣ ይማራል። ይህም የጉሮሮ ግድግዳ እንዲርገበገብ ያደርጋል። በዚህ መንገድ የሚፈጠረውን ጎርናና ድምፅ በአፍና በከንፈር ቅላጼ እየሰጡ ንግግር ማሰማት ይቻላል።
“ካሁን በፊት የግሳት ድምፅ የማሰማው ከመጠን በላይ ከበላሁ ብቻ ነበር” ይላል ቢል ፈገግ እያለ። “አሁን ግን በተከታታይ ማግሳት ለመማር ተገደድኩ። በመጀመሪያ በአንድ ጊዜ አንድ ቃል ብቻ ማውጣት ተማርኩ። እንደዚህ ማለት ነው:- [ትንፋሽ ማስገባት፣ መዋጥ፣ ማግሳት] እንደ [ትንፋሽ ማስገባት፣ መዋጥ፣ ማግሳት] ምን [ትንፋሽ ማስገባት፣ መዋጥ፣ ማግሳት] ነህ? ቀላል አልነበረም። አስተማሪዬ ለማግሳት እንዲረዳኝ የመፍላት ባሕርይ ያለው ከዝንጅብል የሚሠራ መጠጥ በብዛት እንድጠጣ መከረኝ። ስለዚህ ሮዝ ከቪኪ ጋር ልትንሸራሸር ወጣ ስትል እየጠጣሁና እያገሳሁ እለማመድ ነበር። በከፍተኛ ትጋት ተለማመድኩ!”
ማንቁርታቸው ከወጣላቸው በሽተኞች መካከል 60
በመቶ የሚሆኑት በጉሮሮ መነጋገር መማር የማይችሉ ቢሆኑም ቢል ግን ዕድገት አደረገ። ለዚህ ትልቅ ግፊት የሰጠችው በዚህ ጊዜ ሁለት ዓመት የሞላት ቪኪ ነች። ቢል እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ቪኪ ታናግረኝና መልስ እንድሰጣት ዓይን ዓይኔን ታያለች። ግን አንድም ቃል ልተነፍስላት አልችልም። ደግማ ትናገራለች። ግን አሁንም መልስ የለም። ቪኪ በቁጣ ወደ ባለቤቴ ዘወር ትልና ‘አባባ እንዲያናግረኝ አድርጊው!’ ትላለች። ቃሎቿ ወደ ውስጤ ጠልቀው ገቡና መናገር መቻል አለብኝ ብዬ እንድቆርጥ አደረጉኝ።” በመጨረሻ ቢል ተሳካለትና ቪኪና ሮዝ እንዲሁም ሌሎች በጣም ተደሰቱ። ሌላውን ግብ አሳካ ማለት ነው።ሌላ መሰናክል ተደቀነበት
በ1951 መጨረሻ ቢልና ሮዝ ሌላ ጭንቅ ውስጥ ገቡ። ዶክተሮች ካንሠሩ ያገረሽ ይሆናል ብለው ስለሰጉ ቢል የጨረር ሕክምና እንዲወስድ መከሩትና በዚሁ ተስማማ። ሕክምናው እንዳለቀ ወደ ቀድሞ ኑሮው ለመመለስ ጓጉቶ ነበር። ሌላ ከፍተኛ የጤና መሰናክል ተጋርጦበት እንደነበረ አልጠረጠረም።
አንድ ዓመት ያህል አለፈ። ከዚያ በኋላ አንድ ቀን የቢል ጣቶች ደነዘዙ። ቀጥሎም ደረጃ መውጣት አቃተው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በእግሩ እየሄደ እንዳለ ወደቀና ዳግመኛ ቆሞ መሄድ ተሳነው። በተደረገለት ምርመራ ቢል የወሰደው የጨረር ሕክምና (ሕክምናው በዚያን ጊዜ እንደ አሁኑ አልተራቀቀም ነበር) በኅብለ ሰረሰሩ ላይ ጉዳት እንዳደረሰበት ታወቀ። ሁኔታው እየተባባሰ እንደሚሄድ ተነገረው። እንዲያውም አንደኛው ሐኪም በሕይወት የመቆየቱ ዕድል “በጣም የመነመነ” እንደሆነ ነገረው። ቢልና ሮዝ ክው ብለው ደነገጡ።
ቢሆንም ቢል ይህን መሰናክል ለመወጣት ሲል ሆስፒታል ገብቶ ለስድስት ወር የአካላዊ እንቅስቃሴ ሕክምና ወሰደ። ሕክምናው በአካላዊ ጤንነቱ ላይ ያመጣው ለውጥ ባይኖርም የሆስፒታል ቆይታው በሕይወቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትሏል። ይሖዋን ወደማወቅ እንዲደርስ አጋጣሚ ሰጥቶታል። ይህ የሆነው እንዴት ነው?
ለመሰናክሎች መንስኤ የሆነውን ነገር በማወቅ ብርታት ማግኘት
በእነዚህ ስድስት ወራት ውስጥ ቢል በአንድ አይሁዳውያን ሆስፒታል ውስጥ በሚገኝ ክፍል ውስጥ የኖረው ከ19 ሽባ የሆኑ ሰዎች ጋር ነበር። ሁሉም አክራሪ አይሁዳውያን ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ሁልጊዜ ከሰዓት በኋላ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይወያዩ ነበር። የባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን አባል የነበረው ቢል ከመስማት በቀር የሚያደርገው ነገር አልነበረም። ቢሆንም ካዳመጠው ውይይት ሁሉን የሚችለው አምላክ አንድ አካል እንደሆነና የሥላሴ ትምህርትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ለመገንዘብ ችሏል። በዚህ ምክንያት ከዚያ በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን አልሄደም። ይሁን እንጂ በሕይወቱ ያጋጠሙትን መሰናክሎች ለመወጣት መንፈሳዊ መመሪያ እንደሚያስፈልገው ተሰማው። “አምላክ እንዲረዳኝ መለመኔን ቀጠልኩ። ጸሎቴም መልስ አገኘ” ይላል ቢል።
በ1953 አንድ ቅዳሜ ቀን በአንድ ወቅት የቢል ጎረቤት የነበረው ሮይ ዳግላስ የደረሰበትን ሁሉ በመስማቱ ሊጠይቀው መጣ። ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ የሆነው ሮይ አብሮት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና ቢልን ጠየቀው። ቢልም ተስማማ። ቢል በመጽሐፍ ቅዱስና “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” * በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ያነበበው ነገር ዓይኑን ከፈተለት። የተማረውን ለሮዝ አካፈላትና እሷም አብራቸው ማጥናት ጀመረች። ሮዝ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “በቤተ ክርስቲያን ሕመም ከአምላክ የሚመጣ ቅጣት እንደሆነ ይነገረን ነበር። ይህ ግን እውነት አለመሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ተረዳን። ትልቅ ሸክም እንደወደቀልን ሆኖ ተሰማን።” ቢልም በማከል “የእኔን ሕመም ጨምሮ የማንኛውም ችግር ምክንያት ምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማወቅና ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ መገንዘባችን የደረሰብኝን ሁኔታ እንድንቀበል ረዳን” ሲል ገልጿል። በ1954 ቢልና ሮዝ አንድ ሌላ ግብ አሳኩ። ሁለቱም የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን ተጠመቁ።
ተጨማሪ ማስተካከያዎችን ማድረግ
በዚህ ጊዜ ቢል ሽባ የሆነው ሰውነቱ ሥራ መሥራት ከማይችልበት ደረጃ ላይ አደረሰው። መተዳደሪያ ለማግኘት ሲሉ ቢልና ሮዝ የሥራ ድርሻቸውን ተለዋወጡ። ቢል ቤት ውሎ ቪኪን ሲጠብቅ ሮዝ በሰዓት መሥሪያው ኩባንያ ሥራ ጀመረች። በዚህ ሥራዋ 35 ዓመት ያህል ቆይታለች!
“ሴት ልጃችንን መንከባከብ ከፍተኛ ደስታ ይሰጠኝ ነበር” ይላል ቢል። “ሕፃኗ ቪኪም ደስ ይላት ነበር። ላገኘችው ሁሉ በኩራት ‘አባባን እያስታመምኩት ነው’ ትል ነበር። ትምህርት ቤት ስትገባ ደግሞ የቤት ሥራዋን አሠራት ጀመር። ብዙ ጊዜ አብረን እንጫወታለን። ከዚህ በላይ ደግሞ ለቪኪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የምሰጥበት ግሩም አጋጣሚ አገኘሁ።”
ለቢልና ለቤተሰቡ የከፍተኛ ደስታ ምንጭ የሆነላቸው ሌላው ነገር ደግሞ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መገኘታቸው ነበር። ከቤቱ እስከ መንግሥት አዳራሹ እያነከሰ ለመድረስ አንድ ሰዓት ይፈጅበት ነበር። ቢሆንም አንድም ቀን ከስብሰባ ቀርቶ አያውቅም። በኋላም ቢልና ሮዝ ወደ ሌላ የከተማው ክፍል ከተዛወሩ በኋላ አነስ ያለ መኪና ገዙና ሮዝ መላውን ቤተሰብ ወደ አዳራሽ ማድረስ ጀመረች። ቢል መናገር የሚችለው በጣም አጭር ለሆነ ጊዜ ብቻ ቢሆንም በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት በተማሪነት መካፈል ጀመረ። “ንግግሬን በወረቀት ላይ እጽፍና ሌላ ወንድም ያቀርብልኛል። ከንግግሩ በኋላ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በንግግሩ ይዘት ላይ ምክር ይሰጠኛል” በማለት ቢል ይገልጻል።
በተጨማሪም ቢል በስብከቱ ሥራ በቋሚነት እንዲካፈል የተለያዩ የጉባኤ አባሎች ይረዱት ነበር። ቢል የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ሲሾም የቢልን ለአምላክ የማደር ባሕርይ ለተመለከቱ የጉባኤው አባሎች የሚያስገርም ነገር አልሆነባቸውም። እግሮቹ ሥራቸውን ሲያቆሙና ሽባነቱ ይበልጥ ሲዛመት ከቤት መውጣት ተሳነው። በመጨረሻም አልጋ ላይ ዋለ። ይህንንስ መሰናክል ይቋቋም ይሆን?
የሚያረካ የጊዜ ማሳለፊያ
“ሙሉ ቀን እቤት ስውል ጊዜዬን የማሳልፍበት ነገር ፈለግሁ” ይላል ቢል። “ሽባ ከመሆኔ በፊት ፎቶግራፍ ማንሳት ያስደስተኝ ነበር። ስለዚህም ከዚህ በፊት አንድም ሥዕል ስዬ ባላውቅም የቀለም ቅብ ሥዕል መሳል ለመሞከር አሰብኩ። ይሁን እንጂ ቀኝ እጄ በሙሉ እንዲሁም የግራ እጄ ሁለት ጣቶች ሽባ ሆነዋል። ያም ሆነ ይህ ሮዝ ስለ ሥዕል አሳሳል ዘዴዎች የሚያስተምሩ መጻሕፍት ገዛችልኝ። አጠናኋቸውና ግራኝ ባልሆንም እንኳ በግራ እጄ ለመሳል ተነሳሁ። አብዛኞቹ ሥዕሎቼ ለእሳት ተዳረጉ። በመጨረሻ ግን ችሎታ ማዳበር ጀመርኩ።”
በአሁኑ ጊዜ የቢልንና የሮዝን ቤት ግድግዳዎች ያስጌጡት የተዋቡ የቀለም ቅብ ሥዕሎች ቢል ካሰበው በላይ እንደተሳካለት ይመሰክራሉ። ቢል በማከል እንዲህ ይላል:- “ከአምስት ዓመት ገደማ በፊት ጀምሮ ግራ እጄ በጣም መንቀጥቀጥ በመጀመሩ የሥዕል ብሩሼን ጨርሶ ለመጣል ተገደድኩ። ይሁን እንጂ ይህ የጊዜ ማሳለፊያዬ ለበርካታ ዓመታት ብዙ እርካታ አምጥቶልኛል።”
አንድ የቀረ ግብ
ቢል እንዲህ በማለት ይተርካል:- “ጤናዬ መቃወስ ከጀመረ ከ50 ዓመት በላይ ሆኗል። አሁንም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ያጽናናኛል። በተለይ መዝሙርንና የኢዮብን መጽሐፍ ሳነብ በጣም እጽናናለሁ። እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎችን ማንበብ በጣም ያስደስተኛል። ከዚህም በላይ የጉባኤያችን አባሎችና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሲጠይቁኝና ተሞክሯቸውን ሲያካፍሉኝ በጣም እጽናናለሁ። በተጨማሪም ከመንግሥት አዳራሹ ጋር የሚያገናኝ የቴሌፎን መስመር ስለተዘጋጀልኝ ስብሰባዎችን አዳምጣለሁ። የትላልቅ ስብሰባ ፕሮግራሞች የተቀዱባቸው የቪዲዮ ክሮች ጭምር አገኛለሁ።
“አፍቃሪ የሆነች ሚስት በማግኘቴ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ባለፉት ዓመታት በሙሉ የቅርብ ባልንጀራዬ ሆናለች። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ የራሷን ቤተሰብ መሥርታ ይሖዋን በማገልገል ላይ በምትገኘው ልጃችን እጅግ እንደሰታለን። በይበልጥ ደግሞ ይሖዋ ወደ እሱ ተጠግቼ እንድኖር ስለረዳኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። አካሌና ድምፄ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በተዳከመበት በአሁኑ ጊዜ ‘አንታክትም፣ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል’ የሚሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ብዙ ጊዜ ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ። (2 ቆሮንቶስ 4:16) አዎን፣ አሁንም ግቤ በሕይወት እስከኖርኩ ድረስ በመንፈሳዊ ንቁ ሆኜ መቀጠል ነው።”
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.20 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመ። አሁን አይታተምም።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ከቀዶ ሕክምናው በኋላ መዋጥ አቃተኝ። አንድ ቃል እንኳን መተንፈስ አልቻልኩም። ሙሉ በሙሉ ድዳ ሆንኩ”
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቢልና ሮዝ በዛሬው ጊዜ