ስለ ኤድስ የቀረበ አስደንጋጭ አኃዛዊ መረጃ!
ስለ ኤድስ የቀረበ አስደንጋጭ አኃዛዊ መረጃ!
በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ቲምቤካ በደቡባዊ አፍሪካ በአንድ ገጠራማ መንደር የምትኖር የ12 ዓመት ልጃገረድ ናት። ወላጆቿ በኤድስ የሞቱባት ሲሆን አሥር፣ ስድስትና አራት ዓመት ዕድሜ ያላቸው እህቶቿን የመርዳት ኃላፊነት በእርሷ ጫንቃ ላይ ወድቋል። አንዲት ዜና ዘጋቢ “እነዚህ ልጆች ቁራሽ ዳቦና ጥቂት ድንች . . . የሚጥሉላቸውን የጎረቤቶቻቸውን እጅ እያዩ ከመኖር በስተቀር ምንም የገቢ ምንጭ የላቸውም” በማለት ተናግራለች። የእነዚህ አራት የሙት ልጆች ፎቶ ግራፍ ሐምሌ 2000 በደርባን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ስለተካሄደው 13ኛው ዓለም አቀፍ የኤድስ ጉባኤ በዘገበው በአንድ የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ወጥቷል።
ወላጆቻቸውን በኤድስ ያጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆች የቲምቤካ እና የእህቶቿ ዓይነት ዕጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል። ጉባኤው ኤድስ የሚያስከትለውን አደጋ ለመቀነስ ኮንዶም በመጠቀም ኤድስን መከላከል እንደሚቻል ማስተማር፣ የኤድስ በሽተኞች አሁን ያለውን ከፍተኛ ወጪ የማይጠይቅ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግና ለኤድስ ክትባት ለማግኘት ለሚደረገው ምርምር ተጨማሪ በጀት መመደብ የመሳሰሉ ዘዴዎችን አንስቶ ተወያይቷል። እንዲሁም ሴቶች በተለይ ደግሞ ወጣት ልጃገረዶች ይበልጥ ለጥቃቱ የተጋለጡ የመሆናቸው ጉዳይም ተነስቷል።
ድንግል ከሆነች ልጅ ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸም በጾታ ግንኙነት ከሚተላለፍ በሽታ ያድናል የሚል አመለካከት ያላቸው ወንዶች ወላጆቻቸውን በኤድስ ባጡ ልጆች ላይ ዓይናቸውን መጣላቸው የሚያሳዝን ነው። ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ወንዶች አንዲት ሴት በመጀመሪያ ልጅ ወልዳ ካላዩ አያገቧትም። ስለሆነም ኮንዶም መጠቀም ለጋብቻም ሆነ ለእናትነት እንቅፋት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።
የሚያሳዝነው ብዙ ልጃገረዶች በኤድስ ስለ መያዝ አደጋ የሚያውቁት ነገር አለመኖሩ ነው። ሶዌታን የተባለ አንድ የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ “በዩኒሴፍ ጥናት መሠረት በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ከሚሆን ልጃገረዶች መካከል 51 በመቶ የሚሆኑት ጤነኛ መስሎ የሚታይ አንድ ሰው ኤች አይ ቪ ሊኖርበትና ወደ እነርሱ ሊያስተላልፍ እንደሚችል አያውቁም” በማለት የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በጉባኤው ላይ አቅርቦት የነበረውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል።
ለኤድስ መስፋፋት አስተዋጽዖ የሚያደርገው ሌላው ነገር በሴቶች ላይ የሚፈጸመው የጾታ ጥቃት ነው። በጉባኤው ላይ የተገኙት ራንጄኒ ሙኑሳሚ የተባሉ ሴት ለደቡብ አፍሪካው ሰንዴይ ታይምስ እንደሚከተለው ሲሉ ተናግረዋል:- “የወንድ ትምክህተኝነት መግለጫ የሆነው በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት የኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመግታትና ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት ትልቅ እንቅፋት ሆኗል። የወንድ ትምክህተኝነት ከሚገለጽባቸው እንደ አስገድዶ መድፈር፣ በሥጋ ዘመዳሞች መካከል የጾታ ግንኙነት መፈጸም፣ ሚስትን መደብደብ፣ ጾታዊ ጥቃት ከመሳሰሉት ድርጊቶች መካከል አንዱ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተው የግዳጅ ወሲብ ሲሆን ይህም በኤች አይ ቪ የመያዝን አጋጣሚ የሚያሰፋ ራሱን የቻለ አንድ ችግር ነው።”
በዚህ ርዕስ ሥር ያለው ሰንጠረዥ እንደሚያሳየው በጉባኤው ላይ የቀረበው አኃዛዊ መረጃ በጣም አስደንጋጭ ነው። በየዕለቱ በግምት 7, 000 ወጣቶችና 1, 000 ሕፃናት በኤች አይ ቪ ይያዛሉ። በ1999 ብቻ ከሳሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ 860, 000 የሚያክሉ ልጆች በኤድስ ምክንያት አስተማሪዎቻቸውን አጥተዋል።
የደቡብ አፍሪካ የሕክምና ምርምር ማዕከል ባደረገው ጥናት መሠረት በደቡብ አፍሪካ 4.2 ሚልዮን ሰዎች በኤች አይ ቪ የተያዙ ሲሆን ይህም ከ10 የአገሪቱ ዜጎች አንዱ ኤች አይ ቪ አለበት ማለት ነው። በአጎራባች አገሮች ያለው ሁኔታ ደግሞ ከዚህ የከፋ ነው። ዘ ናታል ዊትነስ ከዩ ኤስ ሥነ ሕዝብ ቢሮ ያገኘውን ግምታዊ አኃዝ ጠቅሶ እንደ ዘገበው “በኤድስ የተጠቁ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች በሚልዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው በኤድስ ሲሞቱባቸው የሕዝብ ብዛታቸው በፍጥነት ማሽቆልቆል የሚጀምር ሲሆን ከአሥር ዓመት በኋላ በእነዚህ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች አማካኝ በሕይወት የመቆያ ዘመን ወደ 30 ዓመት ዝቅ ይላል።”
ኤድስ ያስከተለው አሳዛኝ ሁኔታ የሰው ዘር መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ቀን” እንደሚከሰት አስቀድሞ በተናገረለት ‘አስጨናቂ ዘመን’ ውስጥ እንደሚኖር የሚጠቁም ተጨማሪ ማስረጃ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን የሚወድዱ ሰዎች ለኤድስና የሰውን ዘር በመቅሰፍ ላይ ላሉት ሌሎች ችግሮች ፍጹምና ዘላቂ መፍትሔ የሚገኙበትን ጊዜ በተስፋ ይጠባበቃሉ። በቅርቡ የአምላክ መንግሥት የምድር ጉዳዮችን የሚቆጣጠረውን አስተዳደር ይረከባል። ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ድህነትና እንግልት ጊዜ ያለፈባቸው ነገሮች ይሆናሉ። (መዝሙር 72:12-14፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) በምትኩ የምድር ነዋሪዎች ፍጹም ጤንነት ስለሚመለስላቸው አንዳቸውም ቢሆኑ “ታምሜአለሁ” አይሉም።—ኢሳይያስ 33:24
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በዓለም ዙሪያ በኤድስ ወላጆቻቸውን ያጡ 13,000,000 ሕፃናት አሉ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ግራፍ/ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
በ1999 መጨረሻ ላይ ኤች አይ ቪ/ኤድስ የነበረባቸው (ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 የሆኑ) ሰዎች ብዛት
ሰሜን አሜሪካ 890,000
የካሪቢያን አገሮች 350,000
ላቲን አሜሪካ 1,200,000
ምዕራብ አውሮፓ 520,000
ምሥራቅ እና መካከለኛው አውሮፓ 410,000
ሰሜን አፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ 210,000
ከሳሐራ በታች ያሉ አገሮች 23,400,000
ደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ እስያ 5,400,000
ምሥራቅ እስያ እና የፓስፊክ አገሮች 530,000
አውስትራልያ እና ኒው ዚላንድ 15,000
[ምንጭ]
ምንጭ:- UNAIDS
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ግራፍ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
በ1999 መጨረሻ ላይ በ16 የአፍሪካ አገሮች ኤች አይ ቪ/ኤድስ የነበረባቸው (ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 የሆኑ) ሰዎች ብዛት በፐርሰንት
1 ቦትስዋና 35.8%
2 ስዋዚላንድ 25.2
3 ዚምባብዌ 25.0
4 ሌሶቶ 23.5
5 ዛምቢያ 20.0
6 ደቡብ አፍሪካ 20.0
7 ናሚቢያ 19.5
8 ማላዊ 16.0
9 ኬንያ 14.0
10 የመካከለኛው አፍሪካ ሪ. 14.0
11 ሞዛምቢክ 13.2
12 ጅቡቲ 11.7
13 ቡሩንዲ 11.3
14 ሩዋንዳ 11.2
15 ኮት ዲቩዋር 10.7
16 ኢትዮጵያ 10.6
[ምንጭ]
ምንጭ:- UNAIDS
[ሥዕል]
ቲምቤካ ከእህቶቿ ጋር
[ምንጭ]
ፎቶ:- Brett Eloff