በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቀሳፊ ማዕበል—የሚነገረው ነገርና እውነታው

ቀሳፊ ማዕበል—የሚነገረው ነገርና እውነታው

ቀሳፊ ማዕበል—የሚነገረው ነገርና እውነታው

ጀንበሯ ከጠለቀች ጥቂት ደቂቃዎች አልፈዋል። ሐምሌ 17, 1998 ዕለተ ዓርብ፣ ጸጥ ረጭ ባለው ምሽት በፓፑዋ ኒው ጊኒ ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻ የሚገኙት በርከት ያሉ ትናንሽ መንደሮች ነዋሪዎች የሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች 7.1 የደረሰ ድንገተኛ የምድር ነውጥ ባስከተለው ንዝረት ተደናገጡ። “ትልቁና ከፍተኛው ነውጥ” ይላል ሳይንቲፊክ አሜሪካን፣ “የባሕሩን ዳርቻ 30 ኪሎ ሜትር ያህል (19 ማይልስ ገደማ) ያናወጠ ከመሆኑም በላይ . . . በድንገት የውቅያኖሱን የታችኛ ወለል ቅርፅ ለወጠው። በዚህም ሳቢያ ለጥ ብሎ የተንሰራፋው የባሕሩ ገጽ ወደ ላይ በመውጣቱ እጅግ አስፈሪ የሆነ ሱናሚ ተፈጠረ።”

አንድ ሁኔታውን ይከታተል የነበረ ሰው ከርቀት የሚሰማ የነጎድጓድ ድምፅ እንደሰማና ባሕሩ ቀስ በቀስ ከተለመደው ዝቅተኛ የውኃ መጠን በታች እየቀነሰ ሲሄድ ድምፁ እየጠፋ እንደሄደ ተናግሯል። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የመጀመሪያውንና ሦስት ሜትር ከፍታ ያለውን ማዕበል ተመለከተ። ሮጦ ለማምለጥ ሲሞክር ማዕበሉ ቀደመው። ከመጀመሪያው የሚበልጥ ሁለተኛ ማዕበል ወጥቶ መንደሩን ከመጠራረጉም በላይ ሰውየውን በአቅራቢያ እስከሚገኘው ጫካ ድረስ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ይዞት ሄደ። “በዘንባባ ዛፎች ጫፍ ላይ ተንጠልጥለው የተገኙት ግባሶዎች ማዕበሉ እስከ 14 ሜትር [46 ጫማ] ከፍታ ድረስ ደርሶ እንደነበረ ያመለክታሉ” ሲል ሳይንስ ኒውስ ዘግቧል።

የዚያን ዕለት ምሽት የተነሱት ግዙፍ ማዕበሎች ቢያንስ ቢያንስ የ2, 500 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። አንድም የተረፈ ተማሪ አልነበረም ማለት ይቻላል፤ በመሆኑም አንድ የእንጨት መሰንጠቂያ ኩባንያ ለአዳዲስ ትምህርት ቤቶች መሥሪያ የሚሆን እንጨትና ጣውላ በእርዳታ መስጠቱ እንቆቅልሽ ነበር። ሁሉም ማለት ይቻላል፣ ከ230 የሚበልጡ ልጆች ሱናሚው ባስከተለው አደጋ ሕይወታቸው ጠፍቷል።

ሱናሚዎች ምንድን ናቸው?

ሱናሚ የጃፓናውያን ቃል ሲሆን “የወደብ ማዕበል” ማለት ነው። “እነዚህ ግዙፍ ማዕበሎች በተደጋጋሚ ጊዜያት በጃፓን ወደቦችና በባሕር ዳርቻዋ በሚገኙ መንደሮች ላይ ከፍተኛ ውድመት በማስከተላቸውና የብዙዎችን ሕይወት በመቅጠፋቸው ይህ ስያሜ ተስማሚ ነው” ይላል ሱናሚ! የተሰኘው መጽሐፍ። እነዚህ በድንገት የሚከሰቱ ማዕበሎች እጅግ አስፈሪ ኃይልና መጠን የሚኖራቸው ከምን የተነሳ ነው?

አንዳንድ ጊዜ ሱናሚዎች መውጃዊ ሞገድ (tidal wave) በመባል ይጠራሉ። ይሁን እንጂ መውጃዊ ሞገድ የሚለው መጠሪያ በትክክል የሚወክለው ማዕበል ብለን የምንጠራውን የባሕር ነውጥ ሲሆን ይህ ማዕበል በፀሐይና በጨረቃ የስበት ኃይል ሳቢያ የሚፈጠር ነው። በወጀብ ኃይል የሚነሱና አንዳንድ ጊዜ ከ25 ሜትር በላይ ከፍታ የሚኖራቸው ግዙፍ ማዕበሎች እንኳ ከሱናሚዎች ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም። ከእነዚህ መውጃዊ ሞገዶች በታች ጠልቀህ ብትገባ ወደ ታች እየጠለቅክ በሄድክ መጠን ኃይላቸው እየቀነሰ እንደሚሄድ ትገነዘባለህ። ከተወሰነ ጥልቀት በኋላ ያለው ውኃ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አይታይበትም። ሱናሚ ሲፈጠር የሚኖረው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ውኃው በብዙ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር ጥልቀት ቢኖረው እንኳ ሱናሚው ውቅያኖሱን ከላይኛው ገጹ አንስቶ እስከ ታችኛው ወለሉ ድረስ ያናውጠዋል!

ሱናሚ በአብዛኛው የሚፈጠረው በባሕሩ ወለል ውስጥ በሚካሄድ እጅግ ኃይለኛ የሆነ ስነ ምድራዊ እንቅስቃሴ ሳቢያ በመሆኑ ባሕሩን እስከ ወለሉ ድረስ ያናውጠዋል። በዚህም የተነሳ ሳይንቲስቶች አንዳንድ ጊዜ ሱናሚን እንቅጥቅጥ ሞገድ (seismic wave) በማለት ይጠሩታል። የባሕሩ ወለል ወደ ላይ በመነሳት ከላይ ያለውን የውኃ ዓምድ ይገፋዋል። በዚህ ጊዜ እስከ 25, 000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የውቅያኖስ ገጽ በትንሹ ወደ ላይ ከፍ ሊል ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የውቅያኖሱ ወለል ሊሰረጉድና በውቅያኖሱ ገጽ ላይ ለአጭር ጊዜ እንደ ጉድጓድ ያለ ክፍተት ሊፈጥር ይችላል።

በዚያም ሆነ በዚህ፣ የስበት ኃይል የታወከውን ውኃ ወዲያና ወዲህ ያናውጠዋል። ይህም ድንጋይ ኩሬ ውስጥ በሚያርፍበት ጊዜ የሚታዩትን ዓይነት አንድ ማዕከል ያላቸው የተያያዙ ማዕበሎች ያስከትላል። ይህ ክስተት ሱናሚ አንድ ነጠላ የሆነ አውዳሚ ማዕበል ነው የሚለውን በሰፊው የሚነገር ተረት ውድቅ ያደርገዋል። ከዚህ ይልቅ በአብዛኛው ሱናሚ ሲከሰት እንደ ፉርጎ የተቀጣጠሉ በርካታ ሞገዶች ይፈጠራሉ። በተጨማሪም ሱናሚ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች ወይም ከባሕር በታች በሚከሰት የመሬት መንሸራተት ሳቢያ ሊከሰት ይችላል።

በታሪክ ውስጥ ከታዩት እጅግ አውዳሚ የሆኑ ተከታታይ ሱናሚዎች አንዱ በነሐሴ ወር 1883 በኢንዶኔዥያ፣ ክራካቶ በደረሰው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሳቢያ የተከሰተው ነው። አንዳንዶቹ ማዕበሎች ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ ከባሕር ወለል በላይ እስከ 41 ሜትር ከፍታ ደርሰው የነበረ ሲሆን ወደ 300 የሚጠጉ በባሕር ዳርቻዎች የሚገኙ ከተሞችንና መንደሮችን ጠራርገው ወስደዋል። የሟቾቹ ቁጥር ከ40, 000 በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

የሱናሚ ጥንድ ባሕርያት

በነፋስ ኃይል የሚፈጠር ማዕበል በሰዓት ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ የማይጓዝ ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ ፍጥነቱ ከዚህ በጣም ያነሰ ነው። “በሌላ በኩል ግን የሱናሚ ማዕበል” ይላል ሱናሚ! የተሰኘው መጽሐፍ፣ “በውቅያኖስ ውስጥ ልክ እንደ አውሮፕላን በሰዓት እስከ 800 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ወይም ከዚያ በሚልቅ ፍጥነት ሊጓዝ ይችላል።” ይሁንና ከፍተኛ ፍጥነት ቢኖረውም ጥልቀት ባለው ውኃ ውስጥ አደገኛ ሁኔታ አያስከትልም። ለምን?

በመጀመሪያ ደረጃ በተንጣለለ ባሕር ላይ የሚነሳ አንድ ነጠላ ማዕበል ብዙውን ጊዜ ከፍታው ከሦስት ሜትር አይበልጥም። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በሁለት ማዕበሎች ጫፍና ጫፍ መካከል ያለው ርቀት በመቶ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር ሊሆን ይችላል። ይህም ብዙ እንዳያጋድል ያደርገዋል። በመሆኑም ሱናሚዎች ማንም ልብ ሳይላቸው በመርከቦች ሥር ሊያልፉ ይችላሉ። ከሃዋይ ደሴት የባሕር ዳርቻ ራቅ ብላ ትገኝ የነበረች የአንዲት መርከብ አዛዥ ሱናሚ በአጠገባቸው ማለፉን ያወቀው ኃይለኛ የሆነ ማዕበል በርቀት የሚገኘውን የባሕር ዳርቻ ሲመታ ነበር። በባሕር ላይ ያሉ መርከቦች ከአደጋ መጠበቅ ይችሉ ዘንድ ቢያንስ ቢያንስ 180 ሜትር ጥልቀት ወዳለው የባሕሩ ክፍል መጠጋት አለባቸው።

ሱናሚዎች ወደ የብስና ብዙም ጥልቀት ወደሌለው የውኃ አካል ሲቃረቡ ባሕርያቸው ይለወጣል። በዚህ ጊዜ ከባሕሩ ወለል ጋር የሚፈጠረው ሰበቃ የማዕበሉን ፍጥነት ይቀንሰዋል። እንዲህ ሲባል ግን ማዕበሉ ሙሉ በሙሉ ፍጥነቱን ይቀንሳል ማለት አይደለም። ምንጊዜም ከፊተኛው ይልቅ ከበስተኋላ ያለው ማዕበል ጥልቀት ስለሚኖረው የተሻለ ፍጥነት ይኖረዋል። በዚህም ሳቢያ ማዕበሉ ይታመቅና እየቀነሰ የመጣውን ፍጥነት ወደ ከፍታ ይለውጠዋል። በዚህ መካከል የማዕበል ፉርጎው አካል የሆኑት ከበስተኋላ ተከትለው የሚመጡ ማዕበሎች ይደርሱና ከፊት ባሉት ማዕበሎች ላይ ይቆለላሉ።

በመጨረሻ ሱናሚው ትልቅ የውኃ ክምር ሆኖ ከአንድ የባሕር ዳርቻ ጋር በመላተም የሚፈስስ ሲሆን ይህም አሸቃቢ ማዕበል በመባል ይታወቃል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ከተለመደው የውኃ ከፍታ በላይ በመውጣት በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ላይ እየጨመረ የሚሄድ የማዕበል ጎርፍ ይፈጥራል። ውኃው ከተለመደው የባሕር ከፍታ ከ50 ሜትር በላይ የሚያሻቅብ ሲሆን ግባሶ፣ ዓሣና አልፎ ተርፎም የዛጎል ስባሪዎች ይዞ በሺህ የሚቆጠሩ ሜትሮች በየብስ ላይ በመፍሰስ በፊቱ ያገኘውን ሁሉ እየጠራረገ ይሄዳል።

ምንጊዜም ሱናሚ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር ወደ ባሕሩ ዳርቻ እየጋለበ የሚመጣና መጠኑን የሚጨምር የውኃ ክምር ይታያል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። አንዳንድ ጊዜ የዚህ ተገላቢጦሽ የሆነ ነገር ሊከሰት ይችላል። ውኃው ወደ መሃል እየሸሸ እንዲሄድ የሚያደርግ ያልተለመደ ዓይነት ማዕበል ተከስቶ የባሕር ዳርቻዎች፣ ባሕረ ሰላጤዎችና ወደቦች ሊደርቁና ዓሦች ውኃ አልባ በሆነ አሸዋና ጭቃ ላይ ቀርተው ሲንደፋደፉ ሊታዩ ይችላሉ። መጀመሪያ ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች ወደ ባሕሩ ዳርቻ ቀድሞ በሚደርሰው የማዕበል ፉርጎው ክፍል ላይ የተመኩ ናቸው። ቀድሞ የሚደርሰው የማዕበሉ ክፍል ወደ ላይ የሚወጣ ወይም ወደ ታች የሰረጎደ ክፍተት የሚፈጥር ሊሆን ይችላል። *

የባሕር ዳርቻው ሲደርቅ

ጊዜው ኅዳር 7, 1837 ነው። ጸጥታ በሰፈነበት በዚያን ዕለት ምሽት አንድ ሰዓት ገደማ ላይ ማዊ ተብላ በምትጠራው የሃዋይ ደሴት ይላል ሱናሚ! የተሰኘው መጽሐፍ፣ ውኃው ከባሕሩ ዳርቻ በመሸሹ አለቶቹ አግጠው ከመውጣታቸውም በላይ ዓሦቹ ባዶ ሜዳ ላይ ተበትነው ቀሩ። በሁኔታው የተገረሙ በርካታ የደሴቲቱ ነዋሪዎች ዓሦቹን ለመልቀም ተሯሯጡ። ይሁን እንጂ ይበልጥ ንቁ የሆኑ ጥቂት ግለሰቦች ከቀደምት ተሞክሮዎች በመነሳት ምን ሁኔታ ሊከሰት እንዳለ በመገንዘባቸው ከፍ ወዳለ ቦታ ሮጡ። ብዙም ሳይቆይ እጅግ አስፈሪ የሆነ ማዕበል አካባቢውን በማጥለቅለቅ ነዋሪዎቹንና ከብቶቻቸውን ጨምሮ በመንደሩ የነበሩትን 26 የሣር ቤቶች በሙሉ ጠራርጎ 200 ሜትር ያህል ይዟቸው ከሄደ በኋላ አነስተኛ ሐይቅ ውስጥ ጨመራቸው።

በዚያው ዕለት ምሽት በሌላ ደሴት በአንድ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመካፈል በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድ የባሕር ዳርቻ ተሰባስበው ነበር። በዚያ ሥፍራም ውኃው በድንገት ሲሸሽ የተመለከቱ የማወቅ ጉጉት ያደረባቸው የሃዋይ ሰዎች ወደ ባሕሩ ዳርቻ ግር ብለው ሄዱ። ከዚያም በቅጽበት አንድ ግዙፍ ማዕበል ከተለመደው የውኃ ከፍታ በላይ 6 ሜትር ያህል ወደ ላይ በመነሳት አንድ ሁኔታውን የተመለከተ ሰው እንደገለጸው “ከፈረስ ግልቢያ ጋር በሚወዳደር ፍጥነት” ባሕር ዳርቻውን አጥለቀለቀው። ወደ ባሕሩ ተመልሶ በመግባት ላይ የነበረው ውኃ ጠንካራ ዋናተኞችን ሳይቀር ባሕሩ ውስጥ ከተታቸው። አንዳንዶቹ በጣም ከመዛላቸው የተነሳ ሰጠሙ።

ምን ያህል ጊዜ ይከሰታሉ?

“ከ1990 ወዲህ” ይላል ሳይንቲፊክ አሜሪካን፣ “10 ሱናሚዎች ከ4, 000 የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። በዓለም ዙሪያ በጠቅላላው 82 ሱናሚዎች የተመዘገቡ ሲሆን ይህም በታሪክ ውስጥ በአማካይ በየአሥርተ ዓመቱ ይከሰቱ ከነበሩት 57 ሱናሚዎች ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ልቆ ተገኝቷል።” ይሁን እንጂ ይህ ተከሰተ የተባለው ጭማሪ ሊታይ የቻለው በአብዛኛው የመረጃ ልውውጥ እየተሻሻለ በመምጣቱ ሲሆን ለሟቾቹ ቁጥር መጨመር በከፊል ምክንያት የሆነው በባሕር ዳርቻዎች የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር ማደጉ እንደሆነ መጽሔቱ አክሎ ገልጿል።

ፓስፊክ ውቅያኖስ በምድር ነውጥ ሳቢያ ለሚከሰት እንቅጥቃጤ በከፍተኛ ደረጃ የተጋለጠ በመሆኑ በዚህ ውቅያኖስ ውስጥ በርከት ያሉ ሱናሚዎች ሲፈጠሩ ይታያል። እንዲያውም “በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ አንድ አውዳሚ ሱናሚ ሳይከሰትበት ያለፈ አንድም ዓመት የለም” ይላል አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ። በተጨማሪም “ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከመሬት መንቀጥቀጥ ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች ሕይወታቸውን ካጡት ሰዎች መካከል 62 በመቶ የሚሆኑት ለሕልፈተ ሕይወት የተዳረጉት በሱናሚ ሳቢያ ነው” ሲል ይገልጻል።

አስቀድሞ መተንበይ ይቻላል?

ከ1948 እስከ 1998 በነበሩት ዓመታት በሃዋይ ከተላለፉት የሱናሚ ቅድመ ማስጠንቀቂያዎች ውስጥ 75 በመቶዎቹ የተሳሳቱ ማስጠንቀቂያዎች ነበሩ። ይህ ሁኔታ ሰዎች ለሚሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ቸልተኞች እንዲሆኑ ሊያደርግ እንደሚችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ እጅግ የተሻለ የመመርመሪያ ዘዴ ሥራ ላይ እየዋለ ይገኛል። በዚህ በተሻሻለው የመመርመሪያ ዘዴ ቁልፍ የሆነውን ሚና የሚጫወተው የውኃውን ግፊት መጠን የሚለካ ቦተም ፕሬዠር ሪኮርደር (ቢ ፒ አር) የተባለ መሣሪያ ሲሆን ከስያሜው መረዳት እንደሚቻለው በውቅያኖሱ ውስጥ በሺህዎች ከሚቆጠሩ ሜትሮች በታች በወለሉ ላይ ይተከላል።

ይህ የረቀቀ መሣሪያ ከአንድ ሴንቲ ሜትር የማይበልጥ ከፍታ ያለው ሱናሚ እንኳ ከላይ በሚያልፍበት ጊዜ የሚፈጠረውን የውኃ ግፊት ልዩነት የመመዝገብ ብቃት አለው። ቢ ፒ አር የተሰኘው ይህ መሣሪያ የድምፅ ሞገዶችን በመጠቀም ለየት ባለ መንገድ ወደተሠራው እንስፍ (buoy) ተብሎ ወደሚጠራው መሣሪያ መረጃ ያስተላልፋል። እንስፉ ደግሞ መረጃውን ወደ ሳተላይት ይልከዋል። ሳተላይቱ የደረሰውን መረጃ የሱናሚ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ወደሚሰጠው ማዕከል ያቀብላል። ሳይንቲስቶች ይህ ይበልጥ ትክክለኛ የሆነ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጫ ዘዴ የተሳሳቱ ማስጠንቀቂያዎችን በእጅጉ እንደሚያስቀር ጠንካራ እምነት አላቸው።

ሰዎች ከአደጋ እንዲጠበቁ በማድረግ ረገድ ከሁሉ የላቀውን ሚና የሚጫወተው ሕዝቡን ማስተማርና ግንዛቤው እያደገ እንዲሄድ ማድረግ ሳይሆን አይቀርም። ሰዎች ትኩረት የማይሰጡት ከሆነ ከሁሉ የተሻለው የቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጫ ዘዴም እንኳ ምንም ፋይዳ ላይኖረው ይችላል። ስለዚህ ለሱናሚ በተጋለጠ ዝቅተኛ የባሕር ዳርቻ አካባቢ የምትኖር ከሆነና የአካባቢው ባለ ሥልጣናት ሱናሚ እንደሚከሰት ማስጠንቀቂያ ከሰጡ ወይም መሬቱ እየተንቀጠቀጠ እንዳለ ከተሰማህ አሊያም ደግሞ ለየት ያለ ዓይነት ሞገድ ከተመለከትክ ወዲያውኑ ከፍ ወዳለ ቦታ መውጣት ይኖርብሃል። ሱናሚዎች በባሕር ውስጥ በአውሮፕላን ፍጥነት ሊጓዙ እንደሚችሉና ወደ ባሕር ዳርቻዎች በሚቀርቡበት ጊዜ መኪናዎች በአውራ ጎዳናዎች ላይ በሚበርሩበት ከፍተኛ ፍጥነት ሊጋልቡ እንደሚችሉ አትዘንጋ። ስለዚህ ማዕበሉን ካየኸው በኋላ ሮጠህ ማምለጥ የመቻልህ አጋጣሚ በጣም የመነመነ ነው። ይሁን እንጂ ራቅ ብለህ በባሕር ላይ በጀልባ እየተንሸራሸርክ ወይም ዓሣ እያጠመድክ እያለህ ሱናሚ በአጠገብህ ቢያልፍ የምትደናገጥበት ምክንያት አይኖርም። ጠረጴዛ ላይ ያስቀመጥከው የቡና ስኒ ወይም ወይን የያዘ ብርጭቆ እንኳ ከተቀመጠበት ንቅንቅ ማለቱ አጠራጣሪ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.16 ዲስከቨር የተሰኘው መጽሔት እንደሚለው ከሆነ በሁሉም ሞገዶች ላይ የሚታየው ክብ ወይም ሞላላ ቅርጽ የተከተለ የውኃ እንቅስቃሴም ውኃው እየራቀ እንዲሄድ ሊያደርግ ይችላል። በውቅያኖስ ውስጥ የሚዋኙ ሰዎች ማዕበል እነሱ ጋር ከመድረሱ በፊት ውኃው እንደሚጎትታቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ሱናሚዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ይህ ሁኔታ ጎላ ብሎ የሚታይ ሲሆን ይህም የመጀመሪያው ማዕበል ከመድረሱ በፊት የባሕር ዳርቻዎች ወይም ወደቦች እንዲደርቁ ያደርጋል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ብዙውን ጊዜ ሱናሚዎች የሚቀሰቀሱት በውቅያኖሱ ወለል ላይ በሚከሰት የምድር ነውጥ ሳቢያ ነው

መለያያ ስንጥቅ

መቀስቀስ

እየተባባሰ መሄድ

ማጥለቅለቅ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዘመናዊው ቴክኖሎጂ በውቅያኖስ ውስጥ በሚተከሉ መሣሪያዎች አማካኝነት ሱናሚዎች ከመከሰታቸው በፊት ለመተንበይ ይሞክራል

የሳተላይት ግንኙነት

እንስፍ

የውኃ ውስጥ የድምፅ መቀበያ

የድምፅ ሞገድ

የሱናሚ ጠቋሚ መሣሪያ

መልሕቅ

5, 000 ሜትር

[ምንጭ]

Karen Birchfield/NOAA/Pacific Marine Environmental Laboratory

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሱናሚ እያገላበጠ ወስዶ ከባድ መኪና ጎማ ውስጥ የወተፈው ጣውላ

[ምንጭ]

U.S. Geological Survey

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በአላስካ የሚገኘው የስኮች ኬፕ የባሕር ማማ በ1946 በሱናሚ ከመመታቱ በፊት (በስተግራ)

በኋላ የደረሰው አጠቃላይ ውድመት (ከላይ)

[ምንጭ]

U.S. Coast Guard photo

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

U.S. Department of the Interior