በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ባሕር ዛፍ ምን ያህል ጠቃሚ ነው?

ባሕር ዛፍ ምን ያህል ጠቃሚ ነው?

ባሕር ዛፍ ምን ያህል ጠቃሚ ነው?

አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

አንዳንዶቹ በጣም ግዙፍ ከመሆናቸው የተነሳ (ከ90 ሜትር የሚበልጥ ቁመት አላቸው) በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ረጃጅም ከሚባሉት ዛፎች መካከል የሚመደቡ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ አጫጭርና የተጠማዘዙ ከመሆናቸው የተነሳ መሬት ለመንካት የተጎነበሱ ይመስላሉ። ቅጠሎቻቸው እጅግ አስደናቂ የፍጥረት ሥራ የተንጸባረቀባቸው ሲሆኑ አበቦቻቸው ዓይን የሚማርኩ ናቸው። ከዚህ ቀደም የዚህን ዛፍ የተወሰነ አካል በሆነ መንገድ ሳትጠቀምበት አትቀርም።

አንዳንዶቹ አልፓይን አሽ እና ታዝሜኒያን ኦክ እንደሚሉት ያሉ የራሳቸው የሆነ የተለየ ስያሜ ያላቸው ቢሆንም አብዛኞቹ የሙጫ ዛፍ በሚለው ስያሜ ይታወቃሉ። ይሁን እንጂ እውነተኛው ሙጫ ከካርቦሃይድሬት የሚሠራ በውኃ ውስጥ የሚሟሟ ንጥረ ነገር ሲሆን የትኛውም ባሕር ዛፍ ይህን ሙጫ አያወጣም። ስለዚህ የሙጫ ዛፍ የሚለው መጠሪያ የተሳሳተ ስያሜ ነው። ዛፎቹ ዩካሊፕተስ የሚለው መጠሪያቸው ይበልጥ በትክክል ለይቶ የሚያሳውቃቸው ሲሆን ከ600 የሚልቁ አውስትራሊያ በቀል የሆኑ የዚህ ዛፍ ዝርያዎች አሉ።

ዩካሊፕተስ (ባሕር ዛፍ) በሰሜን አውስትራሊያ በሚገኘው ሞቃታማ የሐሩር ክልልና ራቅ ብለው በሚገኙ ደረቅ የሆኑ የአውስትራሊያ ገጠራማ ሜዳዎች በብዛት ያድጋል። ይሁን እንጂ የአንታርክቲክ ነፋስ በሚያይልበት ደቡባዊ ታዝሜኒያ እና በባሕር ዳርቻዎች በሚገኙት ጭጋግ የዋጣቸው ሰንሰለታማ ተራሮችም ላይ ይበቅላል። በየቦታው በብዛት የሚታዩ በመሆኑ አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን አገር አሳሽና ሊቀ ስነ እንስሳ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቶ ነበር:- “በሄድንበት ሁሉ ማለቂያ ከሌላቸው የሙጫ ዛፎች ሌላ ምንም ማየት አልቻልንም። ብዙ ኪሎ ሜትሮች ተጉዘንም እንኳ የምናየው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው።”

በ19ኛው መቶ ዘመን የአውሮፓ ሰፋሪዎች በብዛት ወደ አውስትራሊያ ከፈለሱበት ጊዜ አንስቶ ባሕር ዛፍ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ተካሂዶበታል። ዛፉ የእድገት ፀር ተደርጎ በመታየቱ 300, 000 ካሬ ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍኑ የሚገመቱ ባሕር ዛፎች ከሥራቸው ተመንግለዋል። ይሁን እንጂ ይህን ጠቃሚ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ትኩረት የነፈገው ሁሉም ሰው አልነበረም። በ19ኛው መቶ ዘመን የባሕር ዛፍ ዝርያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ማግኘት ጀመሩ።

ንጉሠ ነገሥትና ዶክተር

በ1880ዎቹ ዓመታት በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በመባል የምትታወቀው የአቢሲኒያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ዳግማዊ ምኒልክ ደረቅ በሆነችው በአዲሷ ዋና ከተማቸው በአዲስ አበባ ለጥላነትና ለማገዶነት የሚያገለግሉ ዛፎች ለመትከል ፈለጉ። ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ ለተካሄደበት ለዚህ አካባቢ ተስማሚ የሆነ አፍሪካ በቀል ዛፍ ማግኘት አልተቻለም። በመሆኑም የንጉሠ ነገሥቱ ጠበብት ቢያንስ ቢያንስ በአገራቸው ያለውን ሐሩር ተቋቁሞ ማደግ የሚችል ዛፍ በሌሎች ቦታዎች ማፈላለግ ያዙ። “አዲስ አበባ” የሚለው የከተማዋ መጠሪያ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ ሚና ለመጫወት የበቃውንና ከባሕር ማዶ የመጣውን ባሕር ዛፍ ከፍ አድርገው በመመልከት ያወጡት ስያሜ ሊሆን ይችላል።

ባለንበት የታሪክ ዘመን ባሕር ዛፍን ወደ ሌላ አገር ያፈለሰው ሌላው ሰው ዶክተር ኤድሙንዶ ናቫሮ ዴ አንድራዲ ነው። በከፍተኛ ፍጥነት እየተመናመነ ያለውን የብራዚል ደን መልሶ ለመተካት ቆርጦ በመነሳት በ1910 ከአውስትራሊያ ባሕር ዛፍ ማስገባት ጀመረ። ወደ 38 ሚልዮን የሚጠጉ ባሕር ዛፎች እንዲተከሉ አድርጓል። በዛሬው ጊዜ በብራዚል ከሁለት ቢልዮን የሚበልጡ ባሕር ዛፎች በመልማት ላይ ይገኛሉ።

ስለዚህም ብራዚል ከራሷ አገር በቀል የሆኑ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች በተጨማሪ ከአውስትራሊያ ውጪ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ባሕር ዛፎች የሚገኙባት አገር ለመሆን በቅታለች። ይህ ልማት የብራዚልን ኢኮኖሚ በእጅጉ በማጎልበቱ ዶክተር ናቫሮ ይህን በጣም ጠቃሚ የሆነ እሴት ወደ አገሩ በማስገባት ላበረከተው የላቀ አገልግሎት ልዩ ሜዳይ ተሸልሟል።

የሕይወት ዛፍ

እንደ ማሊ ያሉ አንዳንድ የባሕር ዛፍ ዝርያዎች ደርቆ ከተ​ሰነጣጠቀው መሬት ውስጥ ማግ​ኘት የቻሉትን ያህል ውኃ በመውሰድ ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ በሥሮቻቸው ውስጥ ያከማቻሉ። የአውስትራሊያ አቦርጂኖችና የጥንት አገር አሳሾች ራቅ ብለው በሚገኙ ደረቅ የአውስትራሊያ ክልሎች ውስጥ እነዚህን ከመሬት በታች የሚገኙ የውኃ ጠርሙሶች በመጠቀም ሕይወታቸውን ማቆየት ችለዋል። ከላይ የሚገኙት ረጃጅም ሥሮች ተቆፍረው ይወጡና በአጭር በአጭሩ ይቆረጣሉ። ከዚያም በአንደኛው ጫፍ በኩል በአፍ ተይዞ ሲነፋ ነጣ ያለ ቡናማ ቀለም ያለው ፈሳሽ ሊወጣ ይችላል። ለመጠጣት የሚያጓጓ ዓይነት ባይሆንም እንኳ 9 ሜትር ርዝማኔ ካለው ሥር ውስጥ 1.5 ሊትር የሚሆን ሕይወት አድን ውኃ ሊገኝ ይችላል።

ሌሎች የባሕር ዛፍ ዝርያዎች ረግረጋማ በሆኑ ሥፍራዎች የሚያድጉ ሲሆኑ በውኃ የራሰውን አፈር ሁሉ እየመጠጡ በደንብ ተመችቷቸው ይኖራሉ። ይህን የተገነዘቡ ኢጣሊያውያን ረግረጋማ ቦታ የሚመቻቸውን ባሕር ዛፎች በመጠቀም በአንድ ወቅት የወባ መራቢያ የነበሩትን የፖንታይን ረግረጋማ ቦታዎች ማድረቅ ችለዋል። በአሁኑ ጊዜ ይህ አካባቢ እጅግ ጠቃሚ የሆነ የእርሻ መሬት ለመሆን በቅቷል።

በአፍሪካ፣ በሰሜንና ደቡብ አሜሪካ፣ በእስያና በአውሮፓ የሚገኙ ከ50 በላይ የሚሆኑ አገሮች በንግዱ መስክም ሆነ ለአካባቢ ውበት በመስጠት ረገድ የሚያበረክተውን ጥቅም በመገንዘብ ባሕር ዛፍ አልምተዋል። የቤት ቁሳቁሶችን የሚሠሩ ሰዎች ቀላ ያለና ብርቱካንማ ቀለም ያላቸውን የባሕር ዛፍ እንጨቶች ከፍ ያለ ግምት ይሰጧቸዋል። አንድ ጹሑፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የባሕር ዛፍ እንጨት ረጅም ዕድሜ ካላቸውና እጅግ ከባድና ጠንካራ ከሆኑ የእንጨት ዓይነቶች መካከል የሚመደብ ነው። የእንጨቱ የጥራት ደረጃ ከዛፉ ፈጣን ዕድገት ጋር ተዳምሮ . . . ይህ የዛፍ ዝርያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የላቀ ጠቀሜታ ያለው የምርጥ እንጨት መገኛ እንዲሆን አድርጎታል።”

ውኃ ብዙም የማያሰርጉ የዚህ ዛፍ ዝርያዎች መርከቦችን፣ የወደብ መድረኮችን፣ የስልክ እንጨቶችን፣ አጥሮችንና የመሳሰሉትን ለመሥራት ያገለግላሉ። ከዚህም በተጨማሪ የሎው ቦክስ እና አይረንባርክ የሚባሉት ዝርያዎች የሚያፈሯቸው ማራኪ የሆኑ የሚያጣብቁ ፍሬዎች ጣፋጭ የአበባ ወለላ የሚያወጡ ሲሆን ንቦች ይህን የአበባ ወለላ በጣም ጣፋጭ ወደሆነ ማር ይለውጡታል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አውስትራሊያ 4.5 ሚልዮን ቶን የሚመዝን የባሕር ዛፍ ሰጋቱራ ወደ ውጪ የላከች ሲሆን ይህም በየዓመቱ 250 ሚልዮን ዶላር ገቢ ያስገኝላታል።

ኪኖ፣ ዘይትና ታኒን

ከባሕር ዛፍ ቅርፊትና እንጨት ውስጥ የሚወጣ ኪኖ የሚባል እንደ ደም የቀላ ሙጫ የሚመስል ንጥረ ነገር አለ። አንዳንዶቹ የኪኖ ዓይነቶች እንጨትን ሺፕወርም ተብሎ ከሚጠራው ትል ለመጠበቅ ያገለግላሉ። በተጨማሪም ኪኖ የደም መፍሰስን ለማስቆም የሚረዳ መድኃኒት ለመሥራት ያገለግላል። የባሕር ዛፍ ሌሎች ዝርያዎች ቅርፊታቸው ታኒን የሚያወጣ ሲሆን ይህም ቆዳ ለማልፋትና ጨርቆችን ለማቅለም ያገለግላል።

ቅጠሎቹ እጅግ አስደናቂ የሆነ ንድፍ ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ በጣም ጠቃሚ የሆነ ዘይት የያዙ ናቸው። በዛለ እጅ ላይ እንዳሉ ጣቶች ጫፎቻቸው ወደ ዛፉ ሥር ተቆልምመውና ተንጠልጥለው ይታያሉ። ይህ ቅርጻቸው እንደ ትልቅ ማንቆርቆሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ ይረዳቸዋል። የቅጠሎቹ ገጽ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ተን ካከማቸ በኋላ ጠንካራ በሆኑት ጫፎች በኩል ከታች ወዳለው ሥራተ ሥር ያንጠባጥበዋል።

ቅጠሎቹን በእንፋሎት በማስመታትና የማንጠር ሂደት (distilling process) በመጠቀም ኃይለኛና መንፈስን የሚያድስ መዓዛ ያለው የባሕር ዛፍ ዘይት ከቅጠሎቹ ላይ እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል። ዘይቱ በስፋት የሚሠራበት ሲሆን እንደ ሽቶ፣ ሳሙና፣ መድኃኒት፣ ጣፋጭ ምግብና የጽዳት መገልገያዎች ላሉ ነገሮች ያገለግላል። ከዚህም በተጨማሪ በዛፉ ቅጠሎች ላይ ያለው ዘይት እየተነነ አየሩን የፀሐይ ብርሃንን አቅጣጫ በሚያስቀይሩ ብናኝ ጠብታዎች በመሙላት የባሕር ዛፍ ጫካውን ለየት ያለ ሰማያዊ ቀለም ያለብሰዋል። በሲድኒ ከተማ ምዕራባዊ ጫፍ የሚገኙት ሰማያዊ ተራሮች ይህን ያልተለመደ ዓይነት ስያሜ ሊያገኙ የቻሉት በዚህ ክስተት ሳቢያ ነው።

ለየት ያለ አመጋገብ ያላቸው እንስሳት መኖሪያ

ኮኣላ በባሕር ዛፍ ጫካ ነዋሪነቷ በእጅጉ የምትታወቅ የተድበለበለችና በፀጉር የተሸፈነች ደስ የምትል እንስሳ ነች። ይህች ለየት ያለ አመጋገብ ያላት እፀበል እንስሳ ወደ 12 ገደማ የሚጠጉ የተለያዩ ዓይነት የባሕር ዛፍ ቅጠሎችን ጫፎች መመገብ ትመርጣለች። እንዲህ ያለው ለየት ያለ አመጋገብ አብዛኞቹን እንስሳት ሊገድላቸው የሚችል ሲሆን ለኮኣላ ግን ተስማሚ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው?

ይህ ሊሆን የቻለው ኮኣላ ከአንድ እስከ ሁለት ሜትር የሚደርስ ርዝማኔ ያለውን ትርፍ አንጀቷን ጨምሮ የተለየ ንድፍ ያለው ስርአተ እንሽርሽረት ስላላት ነው። በአንጻሩ የሰው ትርፍ አንጀት ርዝማኔው ከስምንት እስከ አሥራ አምስት ሴንቲ ሜትር ብቻ ነው። ኮኣላ ያላት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ትርፍ አንጀት ከምትመገባቸው የባሕር ዛፍ ቅጠሎች ፕሮቲኑን፣ ካርቦሃይድሬቱንና ስቡን በሙሉ ለይታ እንድታወጣ ይረዳታል።

ከሚበርሩ ኦፖሰሞች መካከል በትልቅነቷ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የምትይዘውና በአውስትራሊያ የምትኖረው ብዙም የማትታወቅ እንስሳ እንደ ኮኣላ የባሕር ዛፍ ቅጠሎችን ትመገባለች። ይህች ባለ ፀጉር ኪሴ (marsupial) የቤት ድመትን ታክላለች። ወደ 40 ሴንቲ ሜትር የሚጠጋ በተመሰቃቀለ ፀጉር የተሸፈነ ጭራና በፊትና በኋላ እግሯ መካከል የተዘረጋ የሚርገበገብ ቆዳ አላት። ኦፖሰም እነዚህን በሥጋ የተሸፈኑ ክንፎች በመጠቀም ከአንድ ቅርንጫፍ ዘልላ እስከ 100 ሜትር በመንሳፈፍና አየር ላይ እንዳለች 90 ዲግሪ በመታጠፍ ሌላ ቅርንጫፍ ትይዛለች።

የዱር እሳትና ማቆጥቆጥ

የዱር እሳት የአውስትራሊያን የባሕር ዛፍ ጫካ እየተፈታተነው ይገኛል። ሆኖም ዛፎቹ ራሳቸውን መታደግ በሚችሉበት መንገድ የተፈጠሩ ናቸው። እንዴት?

ከዛፉ ቅርፊት በታች ግንዱና ቅርንጫፎቹ ላይ እድገት ያላደረጉ ቀንበጦች ይገኛሉ። ዛፉ ቅርፊቱና ቅጠሎቹ ተቃጥለው መለመላውን ሲቀር እነዚህ ቀንበጦች ያቆጠቁጣሉ። በእሳት የከሰለውን ግንድ በአዳዲስ አረንጓዴ ቅጠሎች ይሸፍኑታል። በዚህ መንገድ ዛፉ ዳግመኛ ይለመልማል። ከዚህም በላይ በመሬት ውስጥ ተቀብረው የቆዩ የዛፉ ዘሮች ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለውን አጋጣሚ በመጠቀም ያጎነቁሉና ያድጋሉ።

አድናቆት ሊቸረው የሚገባ ዛፍ

ከባሕር ዛፍ በተሠራ መድኃኒት የጉሮሮህን ሕመም አስታግሰህ ወይም በባሕር ዛፍ ማር የተሠራ ጣፋጭ ነገር አጣጥመህ በልተህ ታውቃለህ? በባሕር ዛፍ እንጨት በተሠራ ጀልባ ተጉዘህ ወይም በዚህ ዛፍ እንጨት በተሠራ ቤት ኖረህ አለዚያም ደግሞ በባሕር ዛፍ ማገዶ በተቀጣጠለ እሳት ሞቀህ ታውቃለህ? በዚህ በጣም አስደናቂ የሆነ ዛፍ ልትጠቀም የምትችልባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። እንግዲያው ወደፊት በአካልም ይሁን በፎቶግራፍ በፀጉር የተሸፈነች ኮኣላ የመመልከት አጋጣሚ ካገኘህ የኮኣላ መኖሪያ የሆነው ይህ ዛፍ ያለውን አስደናቂ ንድፍ ለማስታወስ ሞክር።

በእርግጥም ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጠውና በጣም ጠንካራ የሆነው ይህ ዛፍ በርካታ ጥቅሞች ያበረክታል።

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባሕር ዛፎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ረጃጅም ከሚባሉት ዛፎች መካከል የሚመደቡ ናቸው

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንቦች የባሕር ዛፍን አበባ ወለላ በመጠቀም በጣም ጣፋጭ የሆነ ማር ይሠራሉ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የባሕር ዛፍ እንጨት “ረጅም ዕድሜ ካላቸውና እጅግ ከባድና ጠንካራ ከሆኑ የእንጨት ዓይነቶች መካከል የሚመደብ ነው”

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኮኣላዎችና (በስተግራ) በራሪ ኦፖሰሞች (ከላይ) የባሕር ዛፍ ቅጠሎችን ይመገባሉ

[ምንጭ]

© Alan Root/Okapia/PR

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Geoff Law/The Wilderness Society

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጮች]

Courtesy of the Mount Annan Botanic Gardens