በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታሪክ ሊታመን ይገባል?

ታሪክ ሊታመን ይገባል?

ታሪክ ሊታመን ይገባል?

“የታሪክ እውቀት . . . ከመወለዳችን ከብዙ ዓመታት በፊት የነበረውና ከሞትንም በኋላ ለረዥም ዘመናት የሚዘልቀው ማኅበረሰብ ክፍል መሆናችን እንዲሰማን ያደርጋል።”—ኤ ከምፓኒየን ቱ ዘ ስተዲ ኦቭ ሂስትሪ፣ በማይክል ስታንፎርድ።

ያለፈውን ታሪክ አለማወቅ የማስታወስ ችሎታ የማጣት ያህል ነው። ታሪክ ባይኖር አንተነትህ፣ ቤተሰብህ፣ ነገድህ፣ የገዛ አገርህ ሳይቀር ምንም ዓይነት ሥርና የቀድሞ ሕልውና የሌለው ይሆንብሃል። የአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት መሠረትና ትርጉም የሌለው ይሆናል።

ታሪክ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ ተዝቆ የማያልቅ ትምህርት ምንጭ ነው። ሌሎች በወደቁበት ጉድጓድ ውስጥ ከመውደቅ እንድናለን። አንድ ፈላስፋ እንዳረጋገጡት ያለፈውን ጊዜ የሚዘነጉ ሕዝቦች ያለፈውን ስህተት መድገማቸው አይቀርም። ያለፈውን ታሪክ ማወቅ ስለ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች፣ አስደናቂ ስለሆኑ ግኝቶችና ስሜትን ስለሚማርኩ ሕዝቦች ያለንን ግንዛቤ ከማስፋቱም በላይ ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለማየት ያስችለናል።

ይሁን እንጂ ታሪክ የሚተርከው ከረዥም ዘመናት በፊት ስለነበሩ ሕዝቦችና ስለተፈጸሙ ሁኔታዎች በመሆኑ ሊታመን የሚችል መሆኑንና አለመሆኑን እንዴት ለማወቅ እንችላለን? ከታሪክ ጠቃሚ ትምህርት ለማግኘት ከፈለግን ታሪኩ በሐቅ ላይ የተመሠረተ መሆን እንደሚገባው ግልጽ ነው። ሐቁን ወይም እውነቱን ካወቅን ደግሞ የማይዋጥልን እንኳን ቢሆን ልንቀበለው ይገባል። የቀደመው ጊዜ እንደ ቁልቋል ዛፍ ሊሆንብን ይችላል። የቁልቋል ዛፍ ውበቱ ማራኪ ቢሆንም እሾህም ስላለው ሊወጋ ይችላል። ልክ እንደዚሁም ያለፈው ጊዜ ታሪክ መንፈስን በእጅጉ ለያነሳሳ ቢችልም ስሜትን ሊጎዳም ይችላል።

በሚቀጥሉት ርዕሶች የምናነባቸውን ነገሮች ትክክለኛነት ለማመዛዘን የሚረዱ አንዳንድ የታሪክ ገፅታዎችን እንመለከታለን። በተጨማሪም እውነተኛ ታሪክ አንድን አስተዋይ አንባቢ እንዴት ሊጠቅም እንደሚችል እንመለከታለን።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከታሪክ ምን ዓይነት ትምህርት ሊገኝ ይችላል?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንግሥት ነፈርቲቲ

[በገጽ 3 ላይ የሚገኙ የሥዕሎቹ ምንጮች]

ነፈርቲቲ:- Ägyptisches Museum der Staatlichen Museen Preußischer Kulturbesitz, Berlin

ከታች:- Photograph taken by courtesy of the British Museum