በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ሕፃናትና ውሾች

ኤል ዩኒቨርሳል የተሰኘው የሜክሲኮ ሲቲ ጋዜጣ እንዳወጣው ዘገባ ከሆነ ብቻቸውን ከውሻ ጋር የተተዉ ሕፃናት የመነከስ ዕጣ ሊገጥማቸው ይችላል። “ምንጊዜም ማለት ይቻላል፣ ትንኮሳውን የሚያካሂደው ሕፃኑ ሲሆን ውሻው ራሱን ለመከላከል ሲል ጥቃት ይሰነዝራል” ይላል ዘገባው። አንድ የሜክሲኮ ሆስፒታል ባለፉት አምስት ዓመታት በውሻ ለተነከሱ 426 ልጆች ሕክምና ሰጥቷል። ከእነዚህ ልጆች መካከል 12 በመቶ የሚሆኑት ዘለቄታዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይም መልካቸው ተበላሽቷል። ዘገባው ወላጆች ውሻን በተመለከተ ሊከተሏቸው የሚገቡትን መሠረታዊ ደንቦች ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ አጥብቆ ያሳስባል:- መጫወቻዎቻቸውን፣ ቤታቸውንና መመገቢያ ዕቃዎቻቸውን አትንኩ፣ እየበላ ወይም ተኝቶ ወዳለ ውሻ አትቅረቡ፣ ጭራውን አትጎትቱ ወይም ላዩ ላይ ተቀምጣችሁ ልትጋልቡ አትሞክሩ።

በጃፓን የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሰዎች

በርካታ ጃፓናውያን እንደሚሉት ከሆነ ኢኮኖሚው ተስፋ ሰጪ የሆነ ለውጥ ሊያሳይ ባለመቻሉ ሳይሆን አይቀርም፣ “ጃፓን የተደናገረች” እና “ግራ የተጋባች ትመስላለች።” በዚህም ሳቢያ “በርካታ ሰዎች ለአሥርተ ዓመት የዘለቀ የራስን ሕይወት የማጥፋት እርምጃ ሲወስዱ ቆይተዋል” ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። “ኀፍረት በእጅጉ በሚያሸማቅቀው ኅብረተሰብ ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር የገጠማቸው በርካታ ወንዶች ተስፋ ከመቁረጣቸውም በላይ ቀኑን ሙሉ ከቤት ርቀው ሲንቀዋለሉ በመዋል ጥሩ ሥራ እንዳላቸው በማስመሰል ለመኖር ተገድደዋል።” አንዳንዶቹ በጭንቀት ስለሚዋጡና ኀፍረት ስለሚይዛቸው ሕይወታቸውን ለማጥፋት ይነሳሉ። “ተስፋ የሚፈነጥቅ ነገር የለም” ሲሉ ዶክተር ዩኪኦ ሳይቶ ተናግረዋል። “ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚያልሙት ነገር የለም። ሁሉም ነገር እያሽቆለቆለ የሚሄድ ይመስላል። . . . የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት እንደ ወረርሽኝ ተስፋፍቷል።” የባቡር ሐዲድ ውስጥ በመግባት የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። አንድ የባቡር ኩባንያ የራሱን ሕይወት ለማጥፋት የተነሳሳውን ሰው ሐሳብ ለማስለወጥ ሊረዳ ይችላል ብሎ በማሰብ የባቡር ሐዲድ አውራ ጎዳናዎችን አቋርጦ የሚሄድባቸውን ቦታዎች ደማቅ አረንጓዴ ቀለም ከመቀባቱም በላይ ዘሎ ባቡሩ ሥር ለመውደቅ ያሰበን ሰው ቆም ብሎ እንዲያስብ ለማድረግ ከሐዲዶቹ ጎንና ጎን በሚገኙት ከፍ ያሉ ቦታዎች ላይ መስተዋቶች ተክሏል። በተጨማሪም ግለሰቡ ከሌሎች እይታ መሰወር እንዳይችል ኩባንያው የዛፍ ቅርንጫፎችን ከርክሟል። ይሁን እንጂ ኢኮኖሚያዊው ሁኔታ ካልተሻሻለ እነዚህ ጥረቶች መና ሊቀሩ እንደሚችሉ ጠበብት ይናገራሉ።

ጭቅጭቅና ትዳር

በሎስ አንጀለስ የሚገኘው የካሊፎርንያ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ በሆኑት በአንድሩው ክሪስተንሰን የተካሄደ አንድ አዲስ ጥናት እንዳመለከተው “ለዘብተኛ የሆኑና በመካከላቸው ያሉትን ልዩነቶች ተቀብለው የመኖር ባሕርይ የሚንጸባረቅባቸው የትዳር ጓደኛሞች ይበልጥ ስኬታማ የሆነ ትዳር ይኖራቸዋል” ሲል ታይም መጽሔት ገልጿል። በሌላው በኩል ግን ጭቅጭቅ ብዙውን ጊዜ ሌላ ውዝግብ ከመፍጠር በስተቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም።

በቂ እንቅልፍ ማግኘት

“ኅብረተሰባችን በቂ እንቅልፍ የማያገኝ ከመሆኑ የተነሳ ለአደጋ ተጋልጧል” ሲሉ የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ስታንሊ ኮረን ተናግረዋል። በስሪ ማይል ደሴት ለደረሰው የኑክሊየር አደጋና ለኤክሰን ቫልዲዝ የነዳጅ ዘይት መፍሰስ አደጋ በከፊል ምክንያት የሆነው ነገር በቂ እንቅልፍ አለማግኘት ነው። በሰሜን አሜሪካ በእንቅልፍ ድብታ ምክንያት በየዓመቱ ከ100, 000 በላይ የሚሆኑ የመኪና አደጋዎች ይደርሳሉ ሲል መክሊንዝ የተሰኘው የካናዳ መጽሔት ዘግቧል። በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የእንቅልፍ ስፔሽያሊስት የሆኑት ዶክተር ዊልያም ደሜንት “ሰዎች ምን ያህል እንቅልፍ ማግኘት እንዳለባቸው አይገነዘቡም” ሲሉ ጠበቅ አድርገው ተናግረዋል። ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት የሚከተሉትን ነገሮች ማድረጉ ጠቃሚ ነው:- እራትህን ቢያንስ ቢያንስ ወደ አልጋ ከመሄድህ ከሦስት ሰዓት በፊት ብላ። በየቀኑ የምትተኛበትና የምትነሳበት ቋሚ ሰዓት ይኑርህ። መኝታ ክፍልህ ውስጥ ቴሌቪዥን ወይም ኮምፒውተር አታስቀምጥ። ከካፌይን፣ ከአልኮልና ከትምባሆ ተቆጠብ። ስትተኛ እግርህን እንዲሞቅህ የእግር ሹራብ አድርግ። ከመተኛትህ በፊት ሞቅ ባለ ውኃ ሰውነትህን ታጠብ። በየዕለቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ። ሆኖም ይህን የምታደርገው ልትተኛ ስትል መሆን የለበትም። በመጨረሻም “እንቅልፍ አልወስድ ካለህ ተነስተህ የሆነ ነገር አድርግ። ድካም ሲሰማህ ተመልሰህ ተኛ፤ ከዚያም በተለመደው ሰዓት ተነሳ” ይላል መክሊንዝ።

ወጥ ቤትን በንጽሕና መያዝ

ሥራ በሚበዛበት ወጥ ቤት ውስጥ ተሸሽገው የሚኖሩትን በሽታ አማጭ ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች “ለመከላከል [ተራ] በረኪናን የመሰለ ነገር የለም” ይላል ቫንኩቨር ሰን የተሰኘው የካናዳ ጋዜጣ። ዘገባው የሚከተሉትን ሐሳቦች ለግሷል:- በየዕለቱ ሠላሳ ሚሊ ሊትር በረኪና ለብ ባለ (በጣም መሞቅ የለበትም) አራት ሊትር ውኃ ቀላቅለህ አዘጋጅ። ውኃው በጣም የሞቀ ከሆነ በረኪናውን ያተንነዋል። ይህን በረኪና የተቀላቀለበት ውኃ በመጠቀም በንጹሕ ጨርቅ ወጥ ቤቱ ውስጥ የሚገኙ ገጾችን ወልውል። ገጾቹን አየሩ ራሱ እንዲያደርቃቸው አድርግ። በረኪናው እስኪደርቅ ድረስ በሚኖረው ጊዜ ውስጥ ብዙ ዘአካላትን መግደል ይችላል። የመመገቢያ ዕቃዎችን ሳሙና ባለው ሙቅ ውኃ ካጠብክ በኋላ በረኪና በተቀላቀለበት ውኃ ውስጥ ለጥቂት ደቂቃዎች በመዘፍዘፍ ከጀርሞች እንዲጠራ አድርግ። ዕቃዎቹ ከደረቁ በኋላ ላያቸው ላይ የሚቀር የኬሚካል ርዝራዥ አይኖርም። በየዕለቱ በወጥ ቤት ውስጥ የሚገኙ ስፖንጆችን፣ የዕቃ ማጠቢያ ጨርቆችንና መፈተጊያ ብሩሾችን ማጠብና በበረኪና መዘፍዘፍ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ምግብ እንዳትበክል እጆችህን በደንብ መታጠብ በተለይ ደግሞ ጥፍሮች ሥር ያሉትን ቦታዎች በሚገባ ማጽዳት ይኖርብሃል።

ጠጥተህ አትዋኝ

በቅርብ ዓመት ውስጥ በጀርመን ውኃ ውስጥ ሰጥመው ሕይወታቸው ያለፈው አብዛኞቹ ሰዎች “ከልክ በላይ አልኮል ጠጥተው” እንደነበር የጀርመን ሕይወት አድን ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ክላውስ ቪልኬንስ ተናግረዋል። አፖቴከን ኡምሻው የተሰኘው የጤና የዜና መጽሔት እንዳለው ከሆነ በ1998 በጀርመን ወንዞች፣ ጅረቶችና ሐይቆች ውስጥ 477 የመስጠም አደጋዎች ተከስተዋል። አልኮል ሰውነት በደንብ እንዳይታዘዝ ሊያደርግና የሰውነትን የጡንቻ እንቅስቃሴ ሊያስተጓጉል የሚችል ከመሆኑም በላይ ከልክ በላይ በችሎታህ እንድትተማመን ሊያደርግህ ስለሚችል አልኮል ጠጥቶ መዋኘት አደገኛ ነው። በመሆኑም ሕይወት አድን የሆኑ ሠራተኞች ‘ጠጥተህ አትዋኝ!’ ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ኤድስና ግብርና በዛምቢያ

በዛምቢያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ያለው ኤድስ በግብርናው ምርት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። በግብርናው ዘርፍ ትልቅ ሚና ከሚጫወቱት ነገሮች አንዱ ገበሬዎችና ረዳቶቻቸው የሚያውሉት ጉልበት ነው ሲል ዛምቢያ ዴይሊ ሜይል የተሰኘው ጋዜጣ ገልጿል። ይሁን እንጂ ኤድስ ይህን የሰው ኃይል እያመናመነው ይገኛል። “ገበሬዎች ሲሞቱ በእርሻው ሥራ ላይ የሚሰማራው የሰው ኃይል ስለሚቀንስ የምርቱ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ያሽቆለቁላል። ይህም ቤተሰብ በቂ ምግብ እንዳያገኝ የሚያደርግ በመሆኑ ድህነት በእጅጉ እየተባባሰ ይሄዳል” ይላል ዴይሊ ሜይል ያወጣው ዘገባ። በዛምቢያ የማንሳ አውራጃ አስተዳዳሪ የሆኑት ዳንኤል ምቢፓ መፍትሔው ገበሬዎች በትዳር ጓደኞቻቸው ተወስነው መኖራቸው እንደሆነ ጠቁመዋል። “ጥሩ ሥነ ምግባርን በማበረታታት ኤድስን መቆጣጠር ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።

ሦስት አፅቄዎችን ለመግደል መቀጠር

በሕንድ የሚገኘው የኡታር ፕራዴሽ ግዛት የደን ጥበቃ መምሪያ ሆፕሎ የተሰኘው አንድ ኢንች የሚደርስ ክንፍ ያለው ሦስት አፅቄ በግምት 650, 000 የሚሆን ሳል የተሰኘ ዛፍ የሚገኝበትን ደን እንዳያጠፋ ለመከላከል ሦስት አፅቄዎችን የማጥፋት ዘመቻ ጀምሯል ሲል ዘ ታይምስ ኦቭ ኢንዲያ ዘግቧል። ሦስት አፅቄዎቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱ የዚህን ዛፍ ዝርያ ሕልውና አደጋ ላይ ጥሎታል። ሦስት አፅቄዎቹ ቅርፊቱንና ግንዱን ስለሚቦረቡሩ ዛፉን ያደርቁታል። የደን ጥበቃ መምሪያው ሦስት አፅቄዎቹን ለመያዝ “የዛፍ ወጥመድ” በመጠቀም ላይ ይገኛል። ገና በማደግ ላይ ካሉ ትንንሽ የሳል ዛፎች ላይ የተወሰዱ ቅርፊቶች ሦስት አፅቄዎቹ በሚገኙባቸው ቦታዎች ይበተናሉ። ከእነዚህ ቅርፊቶች የሚወጣው የሚያጣብቅ ፈሳሽ ነገር ሦስት አፅቄዎቹን የሚስብ ከመሆኑም በላይ ያሰክራቸዋል። በመሆኑም በቀላሉ ይያዛሉ። በአካባቢው የሚኖሩ ልጆች ሦስት አፅቄዎቹን እየያዙ እንዲገድሉ የሚቀጠሩ ሲሆን ለአንድ ሦስት አፅቄ 75 ፓይሳ (ሁለት ሳንቲም ገደማ) ይከፈላቸዋል።

ጡረታ መውጣት በስሜት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

ቀደም ብሎ ጡረታ መውጣት አንዳንድ ጥቅሞች ሊኖሩት ቢችልም ከባድ የስሜት ቀውስ ሊያስከትል ይችላል። ቀደም ሲል የመንግሥት ሠራተኞች የነበሩ ሰዎች ‘እርካታ እንደሌላቸው፣ ብስጩ እንደሆኑ፣ ስጋት እንደሚሰማቸው፣ የግል ስብዕናቸውን እንደሚያጡ፣ የመንፈስ ጭንቀት እንደሚያድርባቸውና ሕይወታቸው እንዳበቃለት ሆኖ እንደሚሰማቸው’ በም​ሬት ሲናገሩ ይደመጣል ሲል የብራዚሉ ዲያሪዮ ደ ፐርነምቡኮ ዘግቧል። አረጋውያንን የሚያጠቁ በሽታዎች ባለሙያ የሆኑት ጊዶ ሻሽኒክ እንዳሉት ከሆነ “ቀደም ብለው ጡረታ የሚወጡ ወንዶች የመጠጥ፣ ሴቶቹ ደግሞ የመድኃኒት ጥገኛ መሆናቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም።” ጡረታ ለመውጣት የሚያስቡ ሰዎች “ሊወጡት የማይችሉት ዕዳ ውስጥ እንዳይዘፈቁ አስቀድመው ከዕዳ ነፃ መሆን፣ ችሎታን ከተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ መጠቀምና ምክር መጠየቅ” ይኖርባቸዋል ሲሉ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ግራሰ ሳንቶስ ተና​ግረዋል።

ሊጠፉ የተቃረቡ ቋንቋዎች

ሜክሲኮ በአሜሪካ ከሚገኙ አገሮች ሁሉ ይበልጥ አገር በቀል የሆኑ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባት አገር ናት። በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን አሁንም ድረስ በርካታ አገር በቀል ቋንቋዎች ከሚነገሩባቸው ከሕንድና ከቻይና ቀጥሎ በሦስተኛነት ደረጃ የምትጠቀስ አገር ናት። ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ብዙዎቹ በመክሰም ላይ መሆናቸውን ዘ ኒውስ የተሰኘ በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየታተመ የሚወጣ የሜክሲኮ ጋዜጣ ዘግቧል። የባሕልና የኪነ ጥበብ ምክር ቤት ዲሬክተር የሆኑት ራፋኤል ቶቫር ኢ ዴ ቴሬሳ በ19ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ በሜክሲኮ ይነገሩ ከነበሩት 100 የማይሞሉ የአገሬው ቋንቋዎች ውስጥ 62 ብቻ ቀርተዋል። ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ደግሞ 16ቱ ከ1, 000 ባነሱ ሰዎች የሚነገሩ ናቸው። አንዱ አሳሳቢ ጉዳይ ቋንቋዎች እየከሰሙ በሚሄዱበት ጊዜ ለዕፅዋት የተሰጡ አገር በቀል ስያሜዎች አብረው የሚጠፉ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ስለ ባሕላዊ የሕክምና ዘዴዎቻቸው ያላቸው እውቀት እየተዳፈነ እንዲሄድ ያደርጋል።