በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ካለፈው ታሪክ ምን ልንማር እንችላለን?

ካለፈው ታሪክ ምን ልንማር እንችላለን?

ካለፈው ታሪክ ምን ልንማር እንችላለን?

“ለታሪክ ተመራማሪዎች ውጤትን ከምክንያት ጋር ከማቀናጀት የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር የለም።”—ጄራልድ ሽላባክ፣ የታሪክ ረዳት ፕሮፌሰር

የታሪክ ተመራማሪዎች ብዙ ጊዜ አንዳንድ ክስተቶች እንዴትና ለምን እንደተፈጸሙ ይጠይቃሉ። ለምሳሌ ያህል ታሪክ የሮማ አጼያዊ መንግሥት እንደወደቀ ይነግረናል። ይሁን እንጂ ለምን ወደቀ? በምግባረ ብልሹነት ምክንያት ነው ወይስ ተድላ አሳዳጅ በመሆኑ? ግዛቱ ለማስተዳደር የማይቻልበት፣ ሠራዊቱ ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ነው? ወይስ የሮማ ጠላቶች በቁጥርም በኃይልም እየተጠናከሩ በመሄዳቸው?

አሁን በቅርቡ ደግሞ በአንድ ወቅት ለምዕራቡ ዓለም የሥጋት ምንጭ ሆኖ የቆየው የምሥራቅ አውሮፓ ኮምኒዝም በአንድ ጀንበር ተንኮታኮተ። ግን ለምን? ከዚህስ ምን ትምህርት ማግኘት ይቻላል? የታሪክ ሊቃውንት ምላሽ ለማግኘት የሚጣጣሩት እንደነዚህ ላሉት ጥያቄዎች ነው። ይሁን እንጂ መልስ ለማግኘት በሚጣጣሩበት ጊዜ በሚሰጡት ዳኝነት ላይ የግል ዝንባሌያቸውና ስሜታቸው ምን ያህል ተጽዕኖ ያሳድራል?

ታሪክ ሊታመን ይችላል?

የታሪክ ሊቃውንት ከሳይንስ ሰዎች ይልቅ የወንጀል መርማሪዎችን ይመስላሉ። የቀድሞ ዘመን መዝገቦችን ይመረምራሉ፣ ይፈትናሉ። ዓላማቸው ሐቁን ማግኘት ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ግባቸው በውል የሚታወቅ አይደለም። ይህም የሆነበት ምክንያት በከፊል ጥናታቸው ያተኮረው በሰዎች ላይ ሲሆን የታሪክ ሊቃውንት ደግሞ የሰዎችን አእምሮ፣ በተለይም የሞቱ ሰዎችን አእምሮ ለማንበብ አለመቻላቸው ነው። በተጨማሪም የታሪክ ሊቃውንት የየራሳቸው አስተሳሰብና መሠረተ ቢስ ጥላቻ ይኖራቸው ይሆናል። በዚህም ምክንያት ሥራቸው በአብዛኛው የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ የታሪክ አተረጓጎም ይሆናል።

እርግጥ አንድ ታሪክ ጸሐፊ የራሱ አስተያየትና አመለካከት ያለው መሆኑ ብቻውን የሥራውን ትክክለኛነት ላያዛባ ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆኑት በሳሙኤል፣ በነገሥትና በዜና መዋዕል ትረካዎች ውስጥ በአምስት የተለያዩ ግለሰቦች የተጻፉ አንድ ዓይነት ታሪካዊ ክንውኖች ይገኛሉ። ቢሆንም በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ግምት ውስጥ የሚገባ እርስ በርሱ የሚጋጭ ሐሳብ ወይም ስህተት እንደሌለ ማረጋገጥ ይቻላል። አራቱ ወንጌሎችም ተመሳሳይ ባሕርይ ይታይባቸዋል። እንዲያውም ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የየግላቸውን ጉድለትና በአላዋቂነት የሠሯቸውን ስህተቶች መዝግበዋል። ይህ በዓለማዊ የታሪክ ሥራዎች እምብዛም ያልተለመደ ነገር ነው።​—⁠ዘኁልቁ 20:​9-12፤ ዘዳግም 32:​48-52

ታሪክ ጸሐፊዎች ሊኖራቸው ከሚችለው መሠረተ ቢስ የሆነ ጥላቻ በተጨማሪ ታሪክ በምናነብበት ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርብን ሌላው አስፈላጊ ነገር የጸሐፊውን ዓላማና ፍላጎት ነው። ማይክል ስታንፎርድ ኤ ከምፓንየን ቱ ዘ ስተዲ ኦቭ ሂስትሪ በተባለው መጽሐፋቸው “በባለ ሥልጣኖች ወይም ሥልጣን ለማግኘት ይጣጣሩ በነበሩ ወይም የእነዚህ ወዳጆች በሆኑ ሰዎች የሚጻፉ ታሪኮችን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ይገባል” ብለዋል። በተጨማሪም የታሪክ ሥራዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብሔራዊ ስሜት ወይም የአርበኝነት ስሜት የሚቀሰቅሱ ከሆነ የትረካቸው ዓላማ በጣም አጠያያቂ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉ ሥራዎች አንዳንድ ጊዜ በትምህርት ቤት መማሪያ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው በእጅጉ ያሳዝናል። የአንድ አገር መንግሥት ያወጣው ድንጋጌ የታሪክ ትምህርት የሚሰጥበት ዓላማ “በሕዝቡ ልብ ውስጥ ያለውን የብሔረተኝነትና የአርበኝነት ስሜት ማጠናከር ነው። . . . ምክንያቱም የአርበኝነት ባሕርይ ከሚያሰርፁት አስፈላጊ ነገሮች አንዱ የአገሪቱን ቀደምት ታሪክ ማወቅ ነው” በማለት በይፋ አውጆአል።

የተበረዘ ታሪክ

ታሪክ ከመዛባት አልፎ የሚበረዝበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ትሩዝ ኢን ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ በቀድሞይቱ ሶቭየት ኅብረት “የትሮትስኪ ስም ከታሪክ መዛግብት በሙሉ እንዲፋቅ በመደረጉ የዚህ ኮሚሳር ሕልውና ጨርሶ ጠፍቷል።” ትሮትስኪ ማን ነበር? በሩስያ የቦልሼቪክ አብዮት መሪ ሲሆን ከሌኒን በስተቀር በሥልጣን የሚበልጠው አልነበረም። ሌኒን ከሞተ በኋላ ትሮትስኪ ከስታሊን ጋር ተጋጨና ከኮምኒስት ፓርቲ ተወገደ። በኋላም ተገደለ። አልፎ ተርፎም ስሙ ከሶቭየት ኢንሳይክሎፔድያዎች ተፋቀ። የሚያጋልጡ መጻሕፍትን እስከማቃጠል የሚደርሰው ይህን የመሰለ ታሪክን የማዛባት ድርጊት በብዙ አምባገነን መሪዎች የተለመደ ተግባር ሆኗል።

ይሁን እንጂ ታሪክን መበረዝ ቢያንስ ቢያንስ ከግብፅና ከአሦር መንግሥታት ዘመን አንስቶ የነበረ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ ድርጊት ነው። ኩሩዎቹና ትዕቢተኞቹ ፈርዖኖች፣ ነገሥታትና አፄዎች አንፀባራቂ ታሪክ ትተው ለማለፍ ይጣጣሩ ነበር። ስለዚህ ያገኟቸው የተሳኩ ውጤቶች አብዛኛውን ጊዜ ተጋንነው ሲተረኩ በጦርነት ድል እንደመነሣት ያሉት አሳፋሪና አዋራጅ ክስተቶች ተሸፋፍነው ይታለፋሉ ወይም እስከነጭራሹ እንዲሠረዙ ይደረግ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበው የእስራኤላውያን ታሪክ ግን ነገሥታቱም ሆኑ ተገዥዎቻቸው ያተረፉትን ዝናና የደረሰባቸውን ውድቀት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ አጣምሮ የያዘ ነው።

የታሪክ ሊቃውንት የጥንት ጽሑፎችን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡት እንዴት ነው? ጽሑፎቹን እንደ ጥንታዊ የታክስ መዝገቦች፣ የሕግ ሰነዶች፣ የባሪያ ሽያጭ ማስታወቂያዎች፣ የንግድና የግል ደብዳቤዎችና መዝገቦች፣ በሸክላ ፅላቶች ላይ የሠፈሩ ጽሑፎች፣ የመርከቦች መዛግብትና በመቃብሮች ውስጥ የተገኙ ዕቃዎች ከመሳሰሉት የታሪክ ማስረጃዎች ጋር በማወዳደር ነው። እንደነዚህ ያሉት ማስረጃዎች አብዛኛውን ጊዜ በኦፊሴላዊ ጽሑፎች ላይ ተጨማሪ ወይም የተለየ ብርሃን ይፈነጥቃሉ። የመረጃ ክፍተት ወይም አለመሟላት በሚኖርበት ጊዜ ጥሩ የታሪክ ጸሐፊዎች የራሳቸውን ግምታዊ ሐሳብ በማከል ክፍተቱን ለመሙላት ቢሞክሩም የመረጃ አለመሟላት መኖሩን በሐቀኝነት ያምናሉ። ያም ሆነ ይህ አስተዋይ አንባቢዎች ሚዛናዊ የሆነ የታሪክ አተረጓጎም ለማግኘት ከፈለጉ ከአንድ የበለጡ ጽሑፎችን ያነባሉ።

አንድ ታሪክ ጸሐፊ በርካታ ፈተናዎችን መወጣት የሚኖርበት ቢሆንም ሥራው ከፍተኛ ጠቀሜታ ሊያበረክት ይችላል። አንድ የታሪክ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “የዓለም ታሪክ ለመጻፍ አስቸጋሪ ቢሆንም . . . በጣም ጠቃሚያችን፣ እንዲያውም አስፈላጊያችን ነው።” ታሪክ የቀድሞውን ዘመን ለማየት የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ ስለ አሁኑ የሰው ልጅ ሁኔታ ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል። ለምሳሌ የጥንቶቹ ሕዝቦች ከዛሬዎቹ ያልተለየ ባሕርይ እንዳላቸው እንገነዘባለን። እነዚህ ተደጋጋሚ ባሕርያት በታሪክ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ታሪክ ራሱን ይደግማል የሚል አባባል የመጣው በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ ይህ አባባል ትክክል ነውን?

ታሪክ ራሱን ይደግማል?

የቀድሞውን ጊዜ መሠረት በማድረግ ስለመጪው ጊዜ በትክክል መተንበይ እንችላለን? አንዳንድ ክንውኖች ተደጋግመው ይከሰታሉ። ለምሳሌ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት ሄንሪ ኪሲንገር “ማንኛውም በምድር ላይ የተነሣ ሥልጣኔ በመጨረሻ ከመፈራረስ አልዳነም” ብለዋል። በመቀጠልም “ታሪክ ከሽፈው የቀሩ ጥረቶች፣ ሳይፈጸሙ የቀሩ ምኞቶች ጥርቅም ነው። . . . ስለዚህ የታሪክ ተመራማሪ የሆነ ሰው አሳዛኝ ሁኔታ መምጣቱ የማይቀር መሆኑን ተቀብሎ ለመኖር ይገደዳል” ብለዋል።

ታላላቅ መንግሥታት የወደቁበት መንገድ የተለያየ ነው። ባቢሎን በ539 ከዘአበ በሜዶናውያንና ፋርሳውያን እጅ የወደቀችው በአንድ ቀን ጀንበር ነበር። ግሪክ ታላቁ እስክንድር ከሞተ በኋላ በተለያዩ መንግሥታት ተከፋፍላ በመጨረሻ ለሮማ እጅዋን ሰጠች። የሮማ አወዳደቅ ግን አከራካሪ ሆኗል። ጄራልድ ሽላባክ የተባሉት የታሪክ ሊቅ “ሮማ የወደቀችው መቼ ነው? በእርግጥስ ወድቃለች?” ብለው ከጠየቁ በኋላ “ከ400 እስከ 600 እዘአ ባለው ጊዜ ውስጥ በምዕራብ አውሮፓ አንድ ዓይነት ለውጥ የተካሄደ ቢሆንም ብዙው ነገር እንዳለ ቀጥሏል” ብለዋል። * አንዳንድ የታሪክ ገጽታዎች ይደጋገሙ እንጂ ሌሎቹ እንደማይደጋገሙ ግልጽ ነው።

በተደጋጋሚ ከታዩት የታሪክ ገጽታዎች አንዱ የሰብዓዊ አገዛዞች ውድቀት ነው። በሁሉም ዘመናት ጥሩ መንግሥታት በራስ ወዳድነት፣ አርቆ ተመልካች ባለመሆን፣ በስግብግብነት፣ በምግባረ ብልሹነት፣ በወገናዊነትና በተለይም በሥልጣን ጥም ተሸንፈው ወድቀዋል። በዚህ ምክንያት የቀደመው ዘመን በጦር መሣሪያ እሽቅድድም፣ ውድቅ ሆነው በቀሩ ውሎች፣ በጦርነቶች፣ በኅብረተሰባዊ አለመረጋጋት፣ በዓመፅ፣ ፍትሐዊ ባልሆነ የሀብት ክፍፍልና ተንኮታኩተው በቀሩ ኢኮኖሚዎች የተሞላ ሆኗል።

ለምሳሌ ያህል ዘ ኮሎምቢያ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ወርልድ የተባለው መጽሐፍ ምዕራባዊው ሥልጣኔ በቀረው የዓለም ክፍል ላይ ስላሳደረው ተጽዕኖ የተናገረውን ተመልከት:- “ኮለምበስና ኮርቴዝ የምዕራብ አውሮፓን ሕዝቦች ሊያገኙ ስለሚችሉት አጋጣሚ ካነቋቸው በኋላ እነዚህ ሕዝቦች ምዕመናን፣ ትርፍና ዝና ለማግኘት የነበራቸው ጥማት ክፉኛ ተነሳሳ። በዚህም ምክንያት የምዕራቡ ሥልጣኔ በመላው የዓለም ክፍል ላይ ለማለት ይቻላል፣ የተስፋፋው በዋነኛነት በኃይል ነው። ፈጽሞ የማይቆርጥ የመስፋፋት ጥማት የተጠናወታቸው ወራሪዎች የተሻለ ጦር መሣሪያ ታጥቀው የቀረውን የዓለም ክፍል የታላላቆቹ የአውሮፓ መንግሥታት ቅጥያዎች እንዲሆኑ አስገደዱ። . . . በአጭሩ የእነዚህ አሕጉራት [አፍሪካ፣ እስያና አሜሪካ] ሕዝቦች የማያባራና አረመኔያዊ የሆነ ጭቆና ሰለባዎች ነበሩ።” “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” የሚሉት በመክብብ 8:​9 [NW ] ላይ የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው!

አንድ ጀርመናዊ ፈላስፋ ከታሪክ ሊገኝ የሚችለው ብቸኛ ትምህርት የሰው ልጆች ከታሪክ ምንም አለመማራቸው ነው እንዲል የገፋፋው ይህ አሳዛኝ የሆነ የታሪክ መዝገብ ሳይሆን አይቀርም። ኤርምያስ 10:​23 “የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” ይላል። በተለይ ይህ አካሄዳችንን በራሳችን ለማቅናት ያለመቻል ጉዳይ በዛሬው ጊዜ የምንኖረውን ሊያሳስበን ይገባል። ለምን? ምክንያቱም በቁጥርም ሆነ በመጠን ተወዳዳሪ በሌላቸው ችግሮች ተወጥረን ተይዘናል። ታዲያ እነዚህን ችግሮች መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

በዓይነታቸው አቻ ያልተገኘላቸው ችግሮች

በሰው ልጅ የታሪክ ዘመናት በሙሉ መላዋ ምድር በደን መራቆት፣ በአፈር መሸርሸር፣ በበረሃማነት መስፋፋት፣ በዕፅዋትና በእንስሳት ዝርያዎች መጥፋት፣ በከባቢ አየር የኦዞን ንጣፍ መመናመን፣ በብክለት፣ በምድር ሙቀት መጨመር፣ በውቅያኖሶች ነፍሳት እልቂትና በሕዝብ ብዛት ጥምር ኃይሎች በአንድ ጊዜ ተጠቅታ አታውቅም።

ኤ ግሪን ሂስትሪ ኦቭ ዘ ወርልድ የተባለው መጽሐፍ “በዘመናዊው ማኅበረሰብ ፊት የተደቀነው ሌላ ፈተና የለውጡ ፍጥነት ነው።” የወርልድ ዎች መጽሔት አዘጋጅ የሆኑት ኤድ አርዝ “ለጋራ ተሞክሯችን ፈጽሞ አዲስ ከሆነ ነገር ጋር ተፋጥጠን ስለምንገኝ ገሐድ የሆኑ ማስረጃዎች እያሉ እንኳን ይህ ነገር ሊታየን አልቻለም። ይህ ‘ነገር’ ለእኛ እስከ ዛሬ ተንከባክቦ ባቆየን ዓለም ላይ የደረሰ ከፍተኛ መጠን ያለው ባዮሎጂያዊና ፊዚካላዊ ለውጥ ውርጅብኝ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

የታሪክ ሊቅ የሆኑት ፓርደን ኢ ቲሊንግሃስት እነዚህና ከእነዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በማስመልከት ሲናገሩ “ማኅበረሰቡ እየተንቀሳቀሰ ያለበት አቅጣጫ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የተወሳሰበ ሲሆን ይህ አቅጣጫ የሚያስከትለው ውጤት አብዛኞቻችንን እጅግ የሚያስፈራ ሆኗል። የታሪክ ባለሙያዎች ግራ ለተጋባው የዘመናችን ሕዝብ ምን ዓይነት አመራር ሊሰጡ ይችላሉ? እምብዛም የሚሳካላቸው አይመስልም” ብለዋል።

የታሪክ ባለሙያዎች ምን እንደሚያደርጉ ወይም ምን ዓይነት ምክር እንደሚሰጡ ግራ ሊገባቸው ይችላል። ፈጣሪያችን ግን ግራ ሊገባው አይችልም። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመጨረሻው ቀን ዓለም “የሚያስጨንቅ ዘመን” እንደሚያጋጥማት ተንብዮአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) ይሁን እንጂ አምላክ በዚህ ብቻ ሳይወሰን የታሪክ ሊቃውንት የማይችሉትን ነገር አድርጓል። በሚቀጥለው ርዕስ እንደምናየው የመውጫውን መንገድ አመልክቷል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.16 ሽላባክ የሰጡት አስተያየት ነቢዩ ዳንኤል የሮማ መንግሥት ከራሱ በወጣ ተቀጽላ መንግሥት እንደሚተካ ከተናገረው ትንቢት ጋር ይስማማል። ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 4ንና 9ን ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በባለ ሥልጣኖች . . . የሚጻፉ ታሪኮችን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ይገባል።”—ማይክል ስታንፎርድ፣ ታሪክ ጸሐፊ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሠ ነገሥት ኔሮ

[ምንጭ]

Roma, Musei Capitolini

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በታሪክ ዘመናት ሁሉ “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው”

[ምንጮች]

ዘ ኮንከረርስ፣በፒየር ፍሪተል። የሚከተሉትን ይጨምራል (ከግራ ወደ ቀኝ):- ዳግማዊ ራምሲዝ፣ አቲላ፣ ሃኒባል፣ ታመርሌን፣ ጁሊየስ ቄሣር (መሃል ላይ)፣ ቀዳማዊ ናፖሊዮን፣ ታላቁ እስክንድር፣ ናቡከደነፆር እና ሻርለማኝ። ዘ ላይብረሪ ኦቭ ሂስቶሪክ ካራክተርስ ኤንድ ፌመስ ኢቬንትስ ከተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 3 የተወሰደ፣ 1895 አውሮፕላኖች:- USAF photo