ወላጆቼ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሬ ለመጫወት እንዳልደረስኩ ቢነግሩኝስ?
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
ወላጆቼ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሬ ለመጫወት እንዳልደረስኩ ቢነግሩኝስ?
“አይ እማማ፣ አንቺኮ እንደድሮው እያሰብሽ ነው። አሁን ዘመኑ ተለውጧል። ሁሉም ሰው ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠረ ይጫወታል! እኔ ደግሞ ከአሁን በኋላ ሕፃን አይደለሁም።”—የ16 ዓመቷ ጄኒ *
ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ ለመጫወት አልደረሳችሁም መባል ሊያበሳጭ ይችላል። “መጽሐፍ ቅዱስን በመታዘዝ እናቴንና አባቴን ለማክበር እፈልጋለሁ” በማለት አንድ ወጣት ተናግሯል። “ሆኖም ወላጆቼ ትክክል አይመስሉኝም። ስለዚህ ጉዳይ ከእነርሱ ጋር እንዴት እንደምወያይ እንኳ አላውቅም።” እናንተም ልክ እንደዚህ ወጣት ወላጆቻችሁ ምክንያተ ቢሶችና ርኅራኄ የጎደላቸው እንደሆኑ ይሰማችሁ ይሆናል። ምናልባት ዓይናችሁን የጣላችሁበት (ወይም የጣላችሁባት) ልጅ ኖሮ (ኖራ) እርሱን ወይም እርሷን ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጉ ይሆናል። ወይም ምናልባት ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት ከእኩዮቻችን ጋር ለመመሳሰል ይረዳናል ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ሚሼል “ተጽእኖ አለ” በማለት ተናግራለች። “ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራችሁ ካልወጣችሁ ተማሪዎቹ የተለያችሁ እንደሆናችሁ አድርገው ይቆጥሯችኋል።”
አንድ የቤተሰብ አማካሪ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ ስለመጫወት እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “የዚህን ያህል ወላጆች በልጆቻቸው ዓይን ምክንያተ ቢስ ሆነው እንዲታዩ የሚያደርግ ጉዳይ የለም።” ይሁን እንጂ ወላጆቻችሁ ምክንያታዊ መስለው ስላልታዩ ብቻ በእርግጥ ምክንያታዊ አይደሉም ማለት ነውን? ደግሞም ወላጆቻችሁ በአምላክ ዘንድ እናንተን የማስተማር፣ የማሰልጠን፣ የመጠበቅና የመምራት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። (ዘዳግም 6:6, 7) ምናልባት ወላጆቻችሁ ስለ ደህንነታችሁ እንዲጨነቁ የሚያደርግ ምክንያት ስላላቸው ይሆን? አንዲት ወላጅ “አደጋ ሲያንዣብብ ይታየኛል፤ ደግሞ በጣም ያስፈራል” ስትል ተናግራለች። ጊዜው ሳይደርስ ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት ብዙ ወላጆችን የሚያሳስባቸው ለምንድን ነው?
አደገኛ ስሜቶች
“ወላጆቼ አንድን ሰው መውደድ ስህተት እንደሆነ አድርገው ለማቅረብ ይሞክራሉ” ስትል የ14 ዓመቷ ቤዝ አማርራለች። ይሁን እንጂ ወላጆቻችሁ ክርስቲያኖች ከሆኑ አምላክ ሁለቱንም ጾታዎች እርስ በእርሳቸው እንዲሳሳቡ አድርጎ እንደፈጠራቸው በሚገባ ያውቃሉ። (ዘፍጥረት 2:18-23) ይህ መሳሳብ ደግሞ ተፈጥሮአዊ እንደሆነና ፈጣሪያችን ‘ምድርን ለመሙላት’ ካለው ዓላማ ጋር እንደሚስማማ ይገነዘባሉ።—ዘፍጥረት 1:28
ከዚህም በተጨማሪ ወላጆቻችሁ ‘በአፍላ የጉርምስና እድሜ’ ላይ የሚሰማችሁ የጾታ ስሜት ምን ያህል ጠንካራ ሊሆን እንደሚችል ያውቃሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:36 NW ) እንዲሁም እነዚህን ስሜቶች በመቆጣጠር ረገድ ምንም ዓይነት ተሞክሮ እንደሌላችሁ ያውቃሉ። ከተቃራኒ ጾታ ጋር በአካል በመገናኘት፣ ስልክ በመደወል፣ ሌላው ቀርቶ ደብዳቤ በመጻፍ ወይም የኤሌክትሮኒክስ መልእክት በመለዋወጥ ረዥም ጊዜ ማሳለፍ ከጀመራችሁ በመካከላችሁ ያለው መሳሳብ እያደገ መሄዱ የማይቀር ነው። ‘ታዲያ ይህ ምን አለበት?’ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ይህንን ምኞት አግባብ ባለው መልኩ ዳር ማድረስ የምትችሉበት መንገድ አለ? እነዚህ ስሜቶች ምክንያታዊ መደምደሚያቸው ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ በሌላ አባባል ትዳር ለመመሥረትስ ተዘጋጅታችኋል? ለዚያ እንዳልተዘጋጃችሁ እሙን ነው።
በመሆኑም ያለጊዜው ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት አንዳንድ አደጋዎች አሉት። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:- “በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፣ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው?” (ምሳሌ 6:27) ብዙውን ጊዜ ያለጊዜው ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት ከጋብቻ በፊት የጾታ ብልግና ወደ መፈጸም ከመምራቱም ሌላ ወጣቶችን ከጋብቻ ውጭ ለሚፈጠር እርግዝና እንዲሁም በጾታ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች ሊያጋልጥ ይችላል። (1 ተሰሎንቄ 4:4-6) ለምሳሌ ወጣቷ ታሚ ወላጆቿ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራ እንዳትወጣ ሲከለክሏት ፍትሐዊ እንዳልሆኑ ተሰምቷት ነበር። ስለዚህ በትምህርት ቤት ከሚገኝ ልጅ ጋር በድብቅ ተቀጣጥራ መጫወት ጀመረች። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ታሚ አረገዘችና ሕይወቷ ተለወጠ። ታሚ “ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት የሚወራለትን ያህል አስደሳች አይደለም” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች።
ይሁን እንጂ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ተገቢ ያልሆነን ንክኪ ቢያስወግዱስ? ያም ቢሆን የፍቅር ስሜት ያለጊዜው እንዲቀሰቀስ ወይም እንዲነሳሳ የማድረጉን አደጋ አያስቀረውም። (መኃልየ መኃልይ 2:7) ከዓመታት በኋላ በሕጋዊ ጋብቻ አማካኝነት ብቻ ሊሟላ የሚችለውን የፍላጎት እሳት ማራገብ ለብስጭትና ለስቃይ ከመዳረግ በስተቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም።
ሌሎች ልታስቡባቸው የሚገቡ ነጥቦች:- ከአንድ የትዳር ጓደኛ ምን መጠበቅ እንዳለባችሁ ለማወቅ የሚያስችል የሕይወት ተሞክሮ አላችሁ? (ምሳሌ 1:4) በሌላ በኩል ደግሞ የምትወደዱና የምትፈቀሩ ባል ወይም ሚስት ለመሆን የሚያስፈልጉት ባህርያትና ችሎታዎች አሏችሁ? ዘላቂ ዝምድና ለመመሥረትና ይህንንም ዝምድና ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችለው ትዕግሥትና ቁርጠኝነት አላችሁ? በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚጀመሩ አብዛኞቹ የፍቅር ግንኙነቶች በሚያሳዝን ሁኔታ በአጭሩ የሚቀጩ መሆናቸው አያስደንቅም። ከእነዚህ ውስጥ ዘላቂ የሆነ ጋብቻ የሚመሠርቱት ጥቂቶች ናቸው።
የአሥራ ስምንት ዓመቷ ሞኒካ ያስተዋለችውን ነገር ጠቅለል አድርጋ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “ሁሉም የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ስለ ወንድ ጓደኞቻቸው ይነግሩኝ ነበር። ሆኖም ወይ በልጅነታቸው አግብተዋል አለዚያም ለትዳር ዝግጁ ስላልነበሩ ከወንድ ጓደኞቻቸው ጋር በሚያሳዝን ሁኔታ ተለያይተዋል።” ብራንደን የተባለ ወጣትም የሚከተለውን አስተውሏል:- “ግዴታ ውስጥ ለመግባት እንደማትችሉ ልባችሁ እያወቀው ተቀጣጥራችሁ መጫወት መጀመራችሁ የሚያስከትለው የኃላፊነት ስሜት በጣም ያስጨንቃል። ታዲያ የሌላውን ሰው ስሜት ሳትጎዱ ግንኙነቱን ማቋረጥ የምትችሉት እንዴት ነው?”
ወላጆቻችሁ ዕድሜያችሁ ደርሶ ጋብቻ መመሥረት እስክትችሉ ድረስ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ አለመጫወቱ ጥሩ እንደሆነ መወትወታቸው እንዲህ ያለው ስቃይና ብስጭት እንዳይደርስባችሁ ለማድረግ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን ሲሉም በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው “ከልብህ ኀዘንን አርቅ፣ ከሰውነትህም ክፉን ነገር አስወግድ” ከሚለው የመክብብ 11:10 ምክር ጋር መስማማታቸው ነው።
‘መስፋፋት’
ይህ ማለት ግን ጨርሶ ከተቃራኒ ጾታ ጋር መገናኘት የለባችሁም ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ቅርርባችሁ በአንድ ሰው ብቻ እንዲወሰን ለምን ታደርጋላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ሌላ ርዕሰ ጉዳይ አስመልክቶ ሲናገር “ተስፋፉ” በማለት ወዳጅነታችንን እንድናሰፋ ያበረታታናል። (2 ቆሮንቶስ 6:12, 13) ይህ ለወጣቶች ተስማሚ ምክር ነው። ይህንን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለው አንደኛው መንገድ ሁለቱንም ጾታዎች ካቀፈ ቡድን ጋር መቀራረብ ነው። “እንደዚያ ሲሆን ይበልጥ የሚያስደስት ይመስለኛል” ስትል ወጣቷ ታሚ ያስተዋለችውን ተናግራለች። “ብዙ ወዳጆች ማፍራት የተሻለ ነው።” ሞኒካም እንዲህ ብላለች:- “በቡድን መሆን የሚለው ሐሳብ በጣም ጥሩ ሐሳብ ነው። ምክንያቱም በቡድን ስትሆኑ የተለያየ ባሕርይ ካላቸው ሰዎች ጋር ከመተዋወቃችሁም በላይ እንዲህ ያለው አጋጣሚ ገና ያልተዋወቃችኋቸው ብዙ ሰዎች መኖራቸውን እንድትገነዘቡ ያደርጋችኋል።”
እንዲያውም ወላጆቻችሁ ከሌሎች ወጣቶች ጋር የሚያንጽ ጥሩ ጊዜ እንድታሳልፉ ዝግጅት ለማድረግ ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ። የሁለት ልጆች እናት የሆነችው አኒ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ቤታችን ልጆች የሚወዱት ቦታ እንዲሆን ለማድረግ ዘወትር እንጥራለን። ጓደኞቻቸው ቤት እንዲመጡ እንጋብዝላቸዋለን። የሚቀማመስ ነገር እናቀራርብላቸውና እንዲጫወቱ እንፈቅድላቸዋለን። ከዚህ የተነሣ ልጆቹ ለመደሰት የግድ ከቤት መውጣት እንዳለባቸው ሆኖ አይሰማቸውም።”
እርግጥ ከሌሎች ጋር በቡድን በምትሆኑበት ጊዜም እንኳ በአንድ ሰው ላይ ከልክ ያለፈ ትኩረት ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባችኋል። አንዳንድ ወጣቶች ሌሎች ሰዎች አብረዋቸው እስካሉ ድረስ በእርግጥ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥረው እየተጫወቱ እንዳልሆነ ሊሰማቸው ይችላል። እንደዚህ ብላችሁ በማሰብ ራሳችሁን አታታልሉ። (መዝሙር 36:2) ከጓደኞቻችሁ ጋር በተሰበሰባችሁ ቁጥር ሁልጊዜ ከአንድ ተመሳሳይ ሰው ጋር ብቻ የምትሆኑ ከሆነ ይህ ተቀጣጥሮ ከመጫወት ተለይቶ አይታይም። * ከተቃራኒ ጾታ ጋር ባላችሁ ግንኙነት ረገድ ጤናማ ውሳኔ ማድረግን ለመማር ጣሩ።—1 ጢሞቴዎስ 5:2
መጠበቅ የሚያስገኘው ጥቅም
ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ ለመጫወት አልደረሳችሁም ተብሎ ሲነገራችሁ አሜን ብሎ መቀበሉ ቀላል አይደለም። ይሁን እንጂ ወላጆቻችሁ እንዲህ የሚሏችሁ እናንተን ለመጉዳት ብለው አይደለም። እንዲያውም እናንተን ለመርዳትና ለመጠበቅ አቅማቸው የፈቀደላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው። ስለዚህ በራሳችሁ ልብ በመታመን የእነርሱን ምክር ከማጣጣል ይልቅ ለምን ካዳበሩት ልምድ ተጠቃሚ አትሆኑም? ለምሳሌ በሌላ ጊዜ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ባላችሁ ግንኙነት ረገድ ችግር ካጋጠማችሁ ለምን ምክር እንዲሰጧችሁ አትጠይቋቸውም? ምሳሌ 28:26 “በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ ነው” በማለት ያሳስበናል። ወጣቷ ኮኔ እንዲህ ብላለች:- “አንድ ወንድ ቢወደኝና ከእርሱ ጋር ተቀጣጥሬ እንድወጣ ተጽእኖ ቢደርስብኝ እንዲህ ያለውን ግፊት እንድቋቋመው የሚያስችለኝ ከእናቴ ጋር የማደርገው ውይይት ነው። በጓደኞቿና በቤተሰቦቻቸው ላይ የደረሰውን ነገር ትነግረኛለች። ይህ ደግሞ በጣም ጠቅሞኛል።”
ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራችሁ መጫወት ሳትጀምሩ ትንሽ መቆየታችሁ ስሜታዊ እድገት እንዳታደርጉ እንቅፋት የሚሆን ወይም ነጻነት የሚያሳጣ ነገር አይደለም። መጠናናትንና ጋብቻን በመሰሉ ትልልቅ ሰዎች ብቻ ሊሸከሟቸው በሚችሉ ኃላፊነቶች ውስጥ ስላልገባችሁ ‘በጉብዝናችሁ ወራት የመደሰት’ ነጻነት አላችሁ። (መክብብ 11:9) በተጨማሪም መቆየታችሁ ባሕርያችሁን፣ ጉልምስናችሁን እንዲሁም በጣም አስፈላጊ የሆነውን ነገር ማለትም መንፈሳዊነታችሁን እንድታዳብሩ ጊዜ ይሰጣችኋል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:26, 27) ሁኔታው አንድ ክርስቲያን ወጣት እንዳስቀመጠው ነው። “ከሌላ ሰው ጋር ቃል ኪዳን ከማድረግህ በፊት ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን ማድረግ አለብህ።”
ዕድሜያችሁ ከፍ እያለ ሲሄድና ማደጋችሁ ለሰው ሁሉ ግልጥ ሆኖ መታየት ሲጀምር ወላጆቻችሁም ለእናንተ ያላቸው አመለካከት እየተለወጠ ይሄዳል። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ ለመጫወት ዝግጁ ስትሆኑ የእነርሱ ድጋፍ ታክሎበት የምትፈልጉትን ማድረግ እንደምትችሉ ምንም ጥርጥር የለውም።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።
^ አን.17 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 232-3 ተመልከት።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ለአንድ ተቃራኒ ጾታ የተለየ ትኩረት መስጠት . . .
. . . አብዛኛውን ጊዜ የፍቅር ስሜቶች እንዲቀሰቀሱ ያደርጋል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቅርርባችሁን በአንድ ሰው ብቻ ከመወሰን ይልቅ ወዳጅነታችሁን አስፉ