በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መሄድ ይኖርብናልን?

ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መሄድ ይኖርብናልን?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መሄድ ይኖርብናልን?

“በፊት ወደ ቤተ ክርስቲያን እሄድ ነበር። አሁን ግን አቁሜአለሁ።” “የትኛውም ቦታ ሆነህ አምላክን ማምለክ ስለምትችል የግድ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የሚያስፈልግ አይመስለኝም።” “በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ አምናለሁ። ቤተ ክርስቲያን መሄድ ግን የሚያስፈልግ አይመስለኝም።” ሰዎች እንዲህ እያሉ ሲናገሩ ሰምተህ ታውቃለህ? ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ በተለይ በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ይህን የመሰለ ነገር ሲናገሩ ይሰማል። ከዚህ በፊት ቤተ ክርስቲያን መሄድ ያዘወትሩ የነበሩ ሰዎች አሁን እንደዚያ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ አይታያቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖታዊ ትምህርት በሚሰጥባቸው ስብሰባዎች ላይ ስለመገኘት ምን ይላል?

“ቸርች” እና “ቸርችስ” የሚሉት የእንግሊዝኛ ቃላት በኪንግ ጀምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ ከ110 ጊዜ በላይ ሰፍረው ይገኛሉ። ሌሎች ትርጉሞችም በእነዚህ ቃላት ይጠቀማሉ። በእንግሊዝኛ “ቸርች” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል፣ ቃል በቃል ሲተረጎም “ተሰብሰቡ የሚል ጥሪ ማቅረብ” ወይም በሌላ አባባል የተሰበሰቡ ሰዎች ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል ሥራ 7:​38 ሙሴ “በምድረ በዳ በማኅበሩ [“ቸርች፣” ኪንግ ጀምስ ቨርሽን ] ውስጥ” ማለትም በተሰበሰበው የእስራኤል ብሔር መካከል እንደነበር ይነግረናል። በሌላ ቦታም ቅዱሳን ጽሑፎች በኢየሩሳሌም የነበረውን የክርስቲያን ማኅበረሰብ ለማመልከት “በቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ” በማለት ይናገራሉ። (ሥራ 8:​1) ጳውሎስ በላከው በአንዱ ደብዳቤ ላይ ‘በፊልሞና ቤት ላለው ቤተ ክርስቲያን’ ማለትም በዚያ ለሚሰበሰበው ጉባኤ ሰላምታ ልኳል።​—⁠ፊልሞና 2

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም መሠረት “ቤተ ክርስቲያን” የሚለው ቃል የሚያመለክተው አምልኮ የሚፈጽሙ ሰዎችን ቡድን እንጂ አምልኮ የሚፈጸምበትን ሕንፃ አይደለም። ከዚህ ጋር በመስማማት በሁለተኛው መቶ ዘመን የሃይማኖት መምህር የነበረው የእስክንድርያው ክሌመንት “ቤተ ክርስቲያን ብዬ የምጠራው የተመረጠውን ጉባኤ እንጂ ቦታውን አይደለም” በማለት ጽፏል። የሆነ ሆኖ ክርስቲያኖች የሚያቀርቡት አምልኮ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ በአንድ ቦታ ወይም ሕንፃ መገኘት ይኖርባቸዋልን?

በእስራኤል ብሔር መካከል የነበረ አምልኮ

የሙሴ ሕግ አይሁዳውያን ወንዶች በሙሉ በሦስት ዓመታዊ በዓላት ለመካፈል በአንድ የተወሰነ ቦታ እንዲገኙ ያዝዝ ነበር። በርካታ ሴቶችና ልጆችም በእነዚህ በዓላት ላይ ይገኙ ነበር። (ዘዳግም 16:​16፤ ሉቃስ 2:​41-44) በአንዳንድ ወቅቶች ካህናትና ሌዋውያን ከአምላክ ሕግ ላይ የተወሰኑ ክፍሎችን በማንበብ የተሰበሰበውን ሕዝብ ያስተምሩ ነበር። ሕጉን ‘ያብራሩና ያስረዱ እንዲሁም ሕዝቡ እንዲያስተውለው ያደርጉ ነበር።’ (ነህምያ 8:​8) የሰንበት ዓመትን በማስመልከት አምላክ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቶ ነበር:- “ይሰሙና ይማሩ ዘንድ፣ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ይፈሩ ዘንድ፣ የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ ጠብቀው ያደርጉ ዘንድ ሕዝቡን ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናቶችንም በአገራችሁ ደጅ ያለውንም መጻተኛ ሰብስብ።”​—⁠ዘዳግም 31:​12

አንድ ሰው ለአምላክ መሥዋዕት ማቅረብና ከካህናቱ መመሪያ ማግኘት ይችል የነበረው ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ከሄደ ብቻ ነው። (ዘዳግም 12:​5-7፤ 2 ዜና መዋዕል 7:​12) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በእስራኤል አምልኮ የሚፈጸምባቸው ምኩራብ ተብለው የሚጠሩ ቤቶች ተቋቋሙ። በእነዚህ ቦታዎች ቅዱሳን ጽሑፎች ይነበባሉ እንዲሁም ጸሎት ይቀርባል። ሆኖም በዋነኛ ደረጃ አምልኮ የሚከናወነው ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ ከሰጠው ዘገባ ይህንን ለማየት ይቻላል። አረጋዊት ስለነበረችው ሃና ሲናገር “በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር” በማለት ጽፏል። (ሉቃስ 2:​36, 37) ለአምላክ ካደሩ ሰዎች ጋር በእውነተኛው አምልኮ መካፈል በሃና ሕይወት ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ነበረው። ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ሌሎች አይሁዳውያንም ተመሳሳይ ጎዳና ተከትለዋል።

ክርስቶስ ከሞተ በኋላ የነበረው እውነተኛ አምልኮ

ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ተከታዮቹ የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁም ሆነ አምልኳቸውን በቤተ መቅደስ ውስጥ እንዲያከናውኑ አይጠበቅባቸውም ነበር። (ገላትያ 3:​23-25) ሆኖም ለጸሎትና የአምላክን ቃል ለማጥናት አንድ ላይ መሰብሰባቸውን አላቆሙም። ያሸበረቁ ሕንፃዎች አልነበሯቸውም። ከዚያ ይልቅ የግል ቤቶችንና የሕዝብ የመሰብሰቢያ ቦታዎችን ይጠቀሙ ነበር። (ሥራ 2:​1, 2፤ 12:​12፤ 19:​9፤ ሮሜ 16:​4, 5) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የሚፈጸምባቸው ሳይሆኑ ቀለል ባለ መንገድ የሚካሄዱ ስብሰባዎች ነበሩ።

በስብሰባዎቻቸው ላይ ይማሯቸው የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥነ ምግባር ባሽቆለቆለበት በሮማ ግዛት ውስጥ እንደ አልማዝ የሚያበሩ ነበሩ። በስብሰባዎቻቸው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኙ አማኝ ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች “እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው” ብለው ለመናገር ይገደዱ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 14:​24, 25) አዎን፣ በእርግጥም አምላክ በመካከላቸው ነበር። “አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ይበረቱ ነበር፣ በቊጥርም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር።”​—⁠ሥራ 16:​5

በዚያን ወቅት የነበረ አንድ ክርስቲያን አምልኮውን በአረማውያን ቤተ መቅደሶች ውስጥ ወይም በተናጠል ቢያከናውን ኖሮ የአምላክን ሞገስ ማግኘት ይችል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ ግልጽ መመሪያ ይሰጣል። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ አምላኪዎች የብቸኛው እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ወይም ጉባኤ ማለትም የእውነተኛ አምላኪዎች “አንድ አካል” ክፍል መሆን ነበረባቸው። እነዚህ ደግሞ ክርስቲያን ተብለው ይጠሩ የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ናቸው።​—⁠ኤፌሶን 4:​4, 5፤ ሥራ 11:​26

ዛሬስ?

መጽሐፍ ቅዱስ አምልኳችንን በቤተ ክርስቲያን እንድናከናውን ከማበረታታት ይልቅ ከቤተ ክርስቲያን ማለትም “የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን” ከሆኑት “በመንፈስና በእውነት” የሚያመልኩ ሰዎች ጋር እንድናከናውን ያበረታታናል። (1 ጢሞቴዎስ 3:​15 የ1980 ትርጉም፤ ዮሐንስ 4:​24) አምላክ የሚቀበለው ሃይማኖታዊ ስብሰባ ሰዎች ‘በቅዱስ ኑሮ ለአምላክ ያደሩ ሆነው እንዲኖሩ’ ማስተማር ይገባዋል። (2 ጴጥሮስ 3:​11) በስብሰባው ላይ የሚገኙ ሁሉ ‘መልካሙንና ክፉውን ለመለየት’ የሚያስችል ጉልምስና ያላቸው ክርስቲያኖች እንዲሆኑ መርዳት አለበት።​—⁠ዕብራውያን 5:​14

የይሖዋ ምሥክሮች የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የተዉትን ምሳሌ ለመከተል ይጥራሉ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከ91, 400 የሚበልጡ ጉባኤዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና እርስ በእርስ ለመበረታታት በመንግሥት አዳራሾች፣ በግል ቤቶችና በሌሎች ቦታዎች አዘውትረው ይሰበሰባሉ። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ . . . መሰብሰባችንን አንተው” በማለት ከተናገረው ቃል ጋር የሚስማማ ተግባር ነው።​—⁠ዕብራውያን 10:​24, 25