በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕልም ከአምላክ የሚመጣ መልእክት ነውን?

ሕልም ከአምላክ የሚመጣ መልእክት ነውን?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ሕልም ከአምላክ የሚመጣ መልእክት ነውን?

የልብስ ስፌት መኪና የፈለሰፈው ኤልያስ ሐው ንድፉን ያወጣው ባየው ሕልም ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ ይነገርለታል። የሙዚቃ ደራሲው ሞዛርት አብዛኞቹ የሙዚቃዎቹ ዜማዎች የመጡለት በሕልም እንደሆነ ተናግሯል። በተመሳሳይ ኬሚስቱ ፍሬደሪክ ኦገስት ኬኩሌ ፎን ሽትራዶኒትስ የቤንዚን ሞለኪውልን መዋቅር ያገኘው በሕልም እንደሆነ ተናግሯል። እንዲህ ዓይነት አባባሎች እንግዳ አይደሉም። በታሪክ ዘመናት በሙሉ በብዙ ኅብረተሰቦች ውስጥ ሕልም ከሌላ ዓለም የሚመጣ እንደሆነ ተደርጎ ሲታመን ቆይቷል። አንዳንድ ኅብረተሰቦች በሕልም ዓለምና በእውን ዓለም መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌለ ያምናሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕልም ወሳኝ የሆነ የመረጃ ምንጭ ማለትም መለኮታዊ መልእክት የሚተላለፍበት አንዱ መንገድ እንደሆነ የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎችን ይዟል። (መሳፍንት 7:​13, 14፤ 1 ነገሥት 3:​5) ለምሳሌ ያህል አምላክ አብርሃምን፣ ያዕቆብንና ዮሴፍን በሕልም አማካኝነት አነጋግሯቸዋል። (ዘፍጥረት 28:​10-19፤ 31:​10-13፤ 37:​5-11) የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር ትንቢት አዘል ሕልሞችን ከአምላክ ተቀብሏል። (ዳንኤል 2:​1, 28-45) ታዲያ በዛሬውም ጊዜ ቢሆን አንዳንድ ሕልሞች ከአምላክ የሚመጡ መልእክቶች ናቸው ብለን እንድናምን የሚያደርጉ አጥጋቢ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆን?

ከአምላክ የተላከ ሕልም

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው የምናገኛቸው አምላክ በመንፈሱ በኩል የገለጣቸው ሕልሞች ልዩ ለሆነ ዓላማ የተላኩ ነበሩ። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ሕልሙን ያየው ሰው የሕልሙ ትርጉም ወዲያው ላይገባው ይችላል። በብዙ ሁኔታዎች እንደታየው የሕልሙን ትርጉም ግልጽ ለማድረግ ‘ምሥጢርን የሚገልጠው አምላክ’ ራሱ የሕልሙን ፍቺ ይሰጣል። (ዳንኤል 2:​28, 29፤ አሞጽ 3:​7) ከአምላክ የሚላክ ሕልም በአብዛኛው በእንቅልፍ ልብ እንደሚታየው ያለ ቅዠት አይደለም።

አንዳንድ ጊዜ አምላክ ከዓላማው አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ቁልፍ ሚና ያላቸውን ሰዎች ለመጠበቅ በሕልም ተጠቅሟል። እንዲህ ዓይነቱ ሕልም የደረሳቸው የአምላክ አገልጋዮች ብቻ አልነበሩም። ለምሳሌ ያህል ሕፃኑን ኢየሱስን ለማየት የመጡት ኮከብ ቆጣሪዎች በእሱ በኩል እንዲያልፉ ወደነገራቸው ወደ ነፍሰ ገዳዩ ወደ ሄሮድስ አልተመለሱም። ለምን? ምክንያቱም በሕልም አማካኝነት ማስጠንቀቂያ ስለ ተሰጣቸው ነው። (ማቴዎስ 2:​7-12) ይህ ሁኔታ የኢየሱስ አሳዳጊ አባት የሆነው ዮሴፍ እርሱም በሕልም አማካኝነት በደረሰው መመሪያ መሠረት ቤተሰቡን ይዞ ወደ ግብፅ ለመሸሽ የሚያስችለው በቂ ጊዜ እንዲያገኝ አጋጣሚ ሰጥቶታል። ይህም የሕፃኑን የኢየሱስን ሕይወት ከሞት ለማትረፍ አስችሏል።​—⁠ማቴዎስ 2:​13-15

ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት አንድ ግብፃዊ ፈርዖን በአንድ በኩል መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች እና ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች በሌላ በኩል ደግሞ የደረቁ ሰባት እሸቶች እና ሥጋቸው የከሳ ሰባት ላሞች በሕልም አይቶ ነበር። ዮሴፍ በመለኮት ባገኘው እርዳታ ሕልሙን በትክክል ተርጉሞታል:- ግብፅ ሰባት የጥጋብ ዓመታት ካሳለፈች በኋላ ሰባት የረሃብ ዓመታት ይገጥማታል። ግብፃውያን ይህን ሁኔታ አስቀድመው ማወቃቸው ብዛት ያለው ሰብል እንዲያመርቱና እንዲያከማቹ አስችሏቸዋል። ይህም የአብርሃምን ዝርያዎች ከሞት ለመታደግና ወደ ግብፅ እንዲመጡ ለማድረግ እንደ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል።​—⁠ዘፍጥረት ምዕራፍ 41፤ 45:​5-8

በተመሳሳይም የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር ሕልም አይቶ ነበር። ሕልሙ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ የሚያሳድሩትን ወደፊት የሚነሱ የዓለም መንግሥታትን አነሳስና አወዳደቅ የሚተነብይ ነበር። (ዳንኤል 2:​31-34) ከጊዜ በኋላ ደግሞ በራሱ ላይ ስለሚደርሰው እብደትና ከዚያ በኋላም ወደ አእምሮው እንደሚመለስ የሚተነብይ ሌላ ሕልም አይቷል። ይህ ትንቢታዊ ሕልም አምላክ ፈቃዱን የሚያስፈጽምበትን የመሲሐዊውን መንግሥት መቋቋም የሚያመለክት ሰፊ ፍጻሜ ነበረው።​—⁠ዳንኤል 4:​10-37

ዛሬስ ሁኔታው ምን ይመስላል?

አዎን፣ አምላክ ለአንዳንድ ሰዎች በሕልም አማካኝነት መልእክት አስተላልፏል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ሁኔታ ሁልጊዜ ይደረግ እንዳልነበር ይጠቁማል። ሕልም መለኮታዊ መልእክት ለማስተላለፍ እንደ ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ አላገለገለም። በሕልም አማካኝነት ከአምላክ መልእክት ያልመጣላቸው በርካታ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ነበሩ። አምላክ ለሰዎች መልእክት ለማስተላለፍ በሕልም መጠቀሙ ቀይ ባሕርን ከከፈለበት ወቅት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ቀይ ባሕርን የከፈለው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ እናውቃለን፤ ሆኖም አምላክ ሕዝቡን ለማዳን ይህን ዘዴ በተደጋጋሚ ተጠቅሞበታል ማለት ግን አይደለም።​—⁠ዘጸአት 14:​21

ሐዋርያው ጳውሎስ እሱ በኖረበት ዘመን የአምላክ መንፈስ በአምላክ አገልጋዮች ላይ እጅግ አስደናቂ በሆኑ መንገዶች ይሠራ እንደነበር ገልጿል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፣ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፣ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፣ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፣ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፣ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፣ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፣ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፣ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል።” (1 ቆሮንቶስ 12:​8-10) ምንም እንኳ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተላከ ሕልም ተለይቶ ባይጠቀስም በርካታ ክርስቲያኖች በኢዩኤል 2:​28 ፍጻሜ መሠረት ከመንፈስ ስጦታዎች አንዱ የሆነው በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተላከ ሕልም እንደደረሳቸው ግልጽ ነው።​—⁠ሥራ 16:​9, 10

ይሁን እንጂ ሐዋርያው እነዚህን ልዩ ስጦታዎች በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል።” (1 ቆሮንቶስ 13:​8) ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ‘እንደሚሻሩ’ ከተነገረላቸው ስጦታዎች መካከል መለኮታዊ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ያገለግሉ የነበሩ ልዩ ልዩ መንገዶችንም ይጨምራል። ከሐዋርያት ሞት በኋላ አምላክ እነዚህን ልዩ ስጦታዎች ለአገልጋዮቹ መስጠቱን አቁሟል።

በዛሬው ጊዜ ባለሙያዎች የሕልምን ምንነት ለመገንዘብና ተግባራዊ ጠቀሜታ ያለው መሆን አለመሆኑን ለመረዳት አሁንም ድረስ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ የሚናገረው ምንም ነገር የለም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በሕልም አማካኝነት መለኮታዊ መልእክት ለማግኘት አጥብቀው ለሚሹ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። በዘካርያስ 10:​2 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ “ምዋርተኞችም . . . ሕልምንም የሚያዩ በሐሰት ተናግረዋል” ይላል። በተጨማሪም አምላክ ገድ ለማወቅ ጥረት ማድረግም ተገቢ አለመሆኑን ተናግሯል። (ዘዳግም 18:​10-12) ከእነዚህ የማስጠንቀቂያ ቃላት የተነሳ በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች በሕልም አማካኝነት መለኮታዊ መመሪያ እናገኛለን ብለው አይጠብቁም። ከዚህ ይልቅ ሕልምን በእንቅልፍ ወቅት የሚያጋጥም የተለመደ ክስተት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።