በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የመጻሕፍት እጥረት ያጋጠመው አዲሱ የእስክንድርያ ቤተ መጻሕፍት

“በክርስቶስ ዘመን የነበረውን ሰብዓዊ እውቀት ሁሉ ይዞ እንደነበር የሚነገርለት” ታላቁ የእስክንድርያ ቤተ መጻሕፍት “በ47 ዓመተ ዓለም በእሳት ተቃጥሎ የነበረ ሲሆን በመጨረሻም በ7ኛው ዓመተ ምህረት ከናካቴው ጠፍቷል” ይላል ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል። ግብጽ ከሌሎች የአረብ መንግሥታትና ከተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት ባገኘችው እርዳታ የጥንቱን ቤተ መጻሕፍት ያስንቃል ብላ ያመነችበትን አዲስ ቤተ መጻሕፍት በእስክንድርያ አቋቁማለች። “የመጀመሪያዎቹ አራት ፎቆች ከምድር በታች ናቸው። በሚያንጸባርቅ የውኃ ገንዳ የተከበበው ይህ ቤተ መጻሕፍት 17 አሳንሰሮች፣ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያጸዱ መስኮቶችና እምብዛም በማይገኙት ጽሑፎች ላይ አንዲት ጠብታ ውኃ እንኳ ሳይተው እሳት የሚያጠፋ እጅግ የረቀቀ እሳት መከላከያ አለው።” ይሁን እንጂ ይላል ጆርናል በመቀጠል፣ “ቤተ መጻሕፍቱ አንድ ትልቅ ችግር ይኸውም የመጻሕፍት እጥረት አለበት።” ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ዓመታት ለፈጀው የግንባታ ሥራ በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ከፈሰሰ በኋላ “የአዲሱ ቤተ መጻሕፍት በጀት መጻሕፍት ለመግዛት የሚያስችል ባለመሆኑ የመጻሕፍት ቤቱ ኃላፊ የሆኑት . . . ሞሰን ዛራን በነፃ የሚሰጡ መጻሕፍት ለመለመን ተገድደዋል” ሲል ጋዜጣው ገልጿል። ዋና ዐቃቤ መጻሕፍት ለማግኘት የተደረገ ጥረት የለም፤ ምክንያቱም “ደሞዙን የመክፈል አቅም የለንም” ይላሉ ሚስተር ዛራን። አዲሱ ቤተ መጻሕፍት ለስምንት ሚልዮን ጥራዞች የሚሆን ቦታ አለው።

በተፈጥሮ የሚገኝ የቫይታሚን ሲ እንክብል

የጫካ ፍሬ በመባልም የሚታወቀው አዜሮል የተሰኘው ፍሬ ዲያሜትሩ ከሁለት ሳንቲ ሜትር አይበልጥም። ሆኖም የመምረርም የመጣፈጥም ጣዕም ያለው ይህ ፍሬ ከብርቱካን 50 ጊዜ፣ ከሎሚ ደግሞ 100 ጊዜ የበለጠ ቫይታሚን ሲ አለው። በፔሩ ታራፖቶ ውስጥ በሚገኘው የሳን ማርቲን የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ የተካሄዱ ጥናቶች እንዳመለከቱት 100 ግራም የሚመዝን ከፍተኛ የአሲድ መጠን ያለው የሎሚ የውስጥ አካል 44 ሚሊ ግራም አስኮርቢክ አሲድ የሚኖረው ሲሆን ተመሳሳይ መጠን ያለው አዜሮል ግን 4, 600 ሚሊ ግራም አስኮርቢክ አሲድ ይኖረዋል። አንድ ዐዋቂ ሰው በ“እንክብል” የተመሰሉትን አራት የአዜሮል ፍሬዎች በመብላት በቀን ውስጥ የሚያስፈልገውን የቫይታሚን ሲ መጠን ማሟላት ይችላል። ኤል ኮሜርስዮ የተባለው ጋዜጣ እንደሚለው ከሆነ “በቀላሉ የመበላሸት ባሕርይ ያለውን” የአዜሮል ፍሬ በኮካ ተክል ምትክ በማምረት ለገበያ ማቅረብ ይቻል እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ አንዳንድ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

መጥፎ የአፍ ጠረንና የሥራ ዕድል

የጥርስ ሐኪም የሆኑት አና ክሪስቲና ኮልቤ “[መጥፎ የአፍ ጠረን] በብዙ የሥራ መስኮች ጎጂ ተጽዕኖ ያሳድራል ቢባል ማጋነን አይሆንም” ሲሉ መናገራቸውን የብራዚል የንግድ መጽሔት የሆነው ኤዛሜ ጠቅሶ ዘግቧል። “አንዳንድ ጊዜ” ይላሉ የሥራ ቅጥር ኃላፊ የሆኑት ሌአንድሮ ሴርዴራ፣ “ሰዎች ዋናው ችግር ምን እንደሆነ እንኳ ሳይረዱ በየጊዜው ከሥራ ይፈናቀላሉ።” በብራዚል በሁለት ትልልቅ ከተሞች ውስጥ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ሃሊቶሲስ ወይም መጥፎ የአፍ ጠረን አለባቸው። ውጥረት እንዲሁም አሰር ያላቸውን ምግቦች በበቂ መጠን አለመመገብ ለዚህ ችግር ዋነኞቹ መንስኤዎች ናቸው። ዶክተር ኮልቤ ለእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የተጋለጡ ሰዎች ችግሩን ለማቃለል ጥቂት ቀናት ዕረፍት እንዲወስዱና ቅጠላ ቅጠሎች በብዛት እንዲመገቡ ምክራቸውን ለግሰዋል። ሃሊቶሲስ ያለባቸው ሠራተኞች እንዲህ ዓይነቱ ችግር ድንገት ሲገጥማቸው ጊዜያዊ እልባት ለማግኘት አነስተኛ መጠን ያለው ሃይድሮጅን ፐርኦክሳይድ ከውኃ ጋር ደባልቀው አፋቸውን ሊጉመጠመጡ ይችላሉ።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት

የዓለም የጤና ድርጅት (ደብሊው ኤች ኦ) 105 አገሮችን አስመልክቶ ያወጣው ዘገባ እንደሚለው ከሆነ በእነዚህ አገሮች ውስጥ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሰዎች አማካይ ቁጥር ከ1950 እስከ 1995 ባሉት ዓመታት ውስጥ 60 በመቶ ጨምሯል ሲል ለ ሞንድ የተሰኘው የፈረንሳይ ጋዜጣ ዘግቧል። የደብሊው ኤች ኦ የአእምሮ ጤና ዲፓርትመንት አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ሆሴ-ማሪያ ቤርቶሎቴ በ2000 አንድ ሚልዮን ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት እንደሚያጠፉና ሌሎች ከ10 እስከ 20 ሚልዮን የሚደርሱ ሰዎች ተመሳሳይ ሙከራ እንደሚያደርጉ ግምታዊ አስተያየት ሰጥተው ነበር። ይሁን እንጂ ትክክለኛው አኃዝ ከዚህ በጣም ሊበልጥ ይችላል። ዘገባው እንደሚለው በየዓመቱ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር በዓለም ዙሪያ በሚካሄዱ ጦርነቶች ከሚያልቁት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ይበልጣል። ከ15 እስከ 35 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች “ሕይወት መቀጠፍ በዋነኛነት ከሚጠቀሱት ሦስት ምክንያቶች አንዱ” የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት ነው ይላሉ ዶክተር ቤርቶሎቴ።

የግዳጅ ወሲብ ሰለባዎች በደቡብ አፍሪካ

“በደቡብ አፍሪካ በየዓመቱ 1 ሚልዮን የግዳጅ ወሲብ ይፈጸማል” ይላል ወርልድ ፕሬስ ሪቪው። ይህም በየ30 ሰኮንዱ አንድ የግዳጅ ወሲብ ይፈጸማል ማለት ነው። ጽሑፉ “ደቡብ አፍሪካ በነፍስ ግድያ ወንጀል በሚደመደም የግዳጅ ወሲብ ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ” እንደያዘች ይገልጻል። ቁጥሩ በሁለተኛ ተርታ ላይ በተቀመጠችው በዩናይትድ ስቴትስ ከተመዘገበው ቁጥር ጋር ሲነጻጸር 12 እጥፍ በልጦ ተገኝቷል። የሕዝብ ብዛቷ ከ40 ሚልዮን በማይበልጠው በደቡብ አፍሪካ እንዲህ ያለ ቁጥር መመዝገቡ እጅግ አስገራሚ ነው። ጽሑፉ አክሎ እንዲህ ይላል:- “በሌሎች አገሮች ሰዎች የግዳጅ ወሲብ ሊፈጽሙባችሁ፣ ሊዘርፏችሁ ወይም ሊገድሏችሁ ይችሉ ይሆናል። በደቡብ አፍሪካ ግን ሰዎች እንዲሁ በአጋጣሚ ስላገኟችሁ ብቻ ማለት ይቻላል፣ የግዳጅ ወሲብ ይፈጽሙባችሁና ይገድሏችኋል። ከየትኛውም የወንጀል ድርጊት ጋር በተያያዘ ማለት ይቻላል፣ የግዳጅ ወሲብ ይፈጸማል።” በተጨማሪም “የግዳጅ ወሲብ አዳዲስ የወንበዴዎች ቡድን አባላት መጀመሪያ ላይ መፈጸም ከሚጠበቅባቸው ድርጊቶች አንዱ ሆኗል።” የወንጀሉ ሰለባ የሆኑትን ሰዎች አስገድደው ከደፈሯቸው በኋላ ይገድሏቸዋል። ጽሑፉ በከፍተኛ መጠን በሕፃናት ላይ የሚፈጸመው በደልና ብዙዎች ሕይወትን እንደ ርካሽ ነገር መመልከታቸው ለዚህ ድርጊት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዳደረገ ጠቅሷል። ከዚህም ሌላ በ1998 በጆሃንስበርግ የተካሄደ አንድ ጥናት “ወጣት ወንዶች፣ ሴቶቹ ሆን ብለው እየደበቁት ነው እንጂ የግዳጅ ወሲብ ያስደስታቸዋል ብለው እንደሚያምኑና ከአንዲት ሴት ጋር ከወጣህ አስገድደህ ወሲብ የመፈጸም መብት አለህ ብለው እንደሚያስቡ አመልክቷል” ሲል መጽሔቱ ገልጿል።

አእምሮ በልብ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል

የአእምሮ ውጥረት ለሁለተኛ ጊዜ በልብ ድካም ለመጠቃት በር ይከፍታል ሲል ተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ሄልዝ ኤንድ ኒውትሪሽን ሌተር ገልጿል። ሆኖም “አእምሮ አንድ ሰው በልብ በሽታ እንዲያዝ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የሚጠቁሙ ማስረጃዎችም እየተበራከቱ መጥተዋል።” “ቁጡ የሆኑ ሰዎች በልብ ድካም የመጠቃታቸው ወይም በልብ በሽታ የመሞታቸው አጋጣሚ ከሌሎች ሰዎች ሦስት እጥፍ ገደማ እንደሚበልጥ” እና “ጥላቻ የሚያስከትላቸው ውጤቶች በአንጻራዊ ሁኔታ ቀደም ባለው የሕይወት ዘመናቸው ላይ መታየት እንደሚጀምሩ” በቅርቡ የተካሄዱ ጥናቶች አመልክተዋል። ውጥረት የልብ ጡንቻንና ልብን የሚመግቡትን በልብ ዙሪያ ያሉ የደም ሥሮች ይጎዳል። የመንፈስ ጭንቀት በልብ ድካም ወይም በሌላ የልብ በሽታ የመያዝን አጋጣሚ ከ70 በመቶ በላይ ሊያሳድገው ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ከፍተኛ ማኅበራዊ እገዛ ማለትም የቤተሰብና የጓደኞች ድጋፍ የሚያገኝ ከሆነ የመንፈስ ጭንቀቱ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ሊቀንስ ይችላል ይላሉ ተመራማሪዎች።

አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን ከልክ በላይ መጠቀም

“አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን ከልክ በላይ መጠቀምን በተመለከተ የጤና ባለ ሥልጣናት በተደጋጋሚ የሚሰጧቸው ማስጠንቀቂያዎች ሰሚ ጆሮ አላገኙም” ሲል ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት ገልጿል። “በዩናይትድ ስቴትስ በዘጠኝ ግዛቶች ውስጥ በ10, 000 ሰዎች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት 32 በመቶ የሚሆኑት አሁንም ድረስ አንቲባዮቲኮች ጉንፋንን ሊፈውሱ ይችላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው፣ 27 በመቶ የሚሆኑት አንድ ሰው ጉንፋን ሲይዘው አንቲባዮቲኮችን መውሰዱ ይበልጥ ከባድ ለሆነ ሕመም እንዳይጋለጥ ይረዳዋል ብለው እንደሚያስቡና 48 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የጉንፋን በሽታ ይዟቸው ሐኪም ዘንድ ከሄዱ አንቲባዮቲኮች ይታዘዙልናል ብለው እንደሚጠብቁ አመልክቷል።” ይሁን እንጂ አንቲባዮቲኮች እንደ ጉንፋን ላሉ በቫይረስ ለሚመጡ ኢንፌክሽኖች አያገለግሉም። አንቲባዮቲኮች የሚያገለግሉት በባክቴሪያ ለሚመጡ ኢንፌክሽኖች ብቻ ነው። አንቲባዮቲኮችን ከልክ በላይ መጠቀም መድኃኒቶችን መቋቋም ለሚችሉ በሽታዎች መፈጠር ትልቅ ድርሻ እንዳበረከተ ይታመናል። (የታኅሣሥ 22, 1998 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 28 ተመልከት።) የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ብራያን ስፕራት “ትክክለኛውን መልእክት ለሰዎች ማስጨበጥ የምንችልበት የተሻለ መንገድ መፈለግ ይኖርብናል” ብለዋል።

“የድንገተኛ ሀብት ድምረህመም”

“በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ የሚገኙ ሚልየነሮች ቁጥር ከ1997 ወዲህ 40 በመቶ ገደማ በመጨመር 2.5 ሚልዮን ደርሷል” ይላል የካናዳው ናሽናል ፖስት ጋዜጣ። በተጨማሪም ጋዜጣው በቴክኖሎጂ የመጠቀው ዓለም ብዙ ወጣቶችን በሀብት እያበለጸገ መሆኑን ገልጿል። ይሁን እንጂ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ስቲቨን ጎልድባርት እንዳሉት ከሆነ አንዳንዶች በድንገት ያገኙት ሀብት የሚያስከትልባቸውን ተጽእኖ መቋቋም አይችሉም። “ሕይወታቸውን ሊያበላሸው፣ ቤተሰባቸውን ሊያፈራርስና ጎጂ የሆነ ምግባር እንዲጠናወታቸው ሊያደርግ ይችላል። ገንዘብ ሁልጊዜ ሰላምና እርካታ አያስገኝም” ይላሉ ጎልድባርት። አንዳንድ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ በቴክኖሎጂ የመጠቀው ዓለም ከባድ የመንፈስ ጭንቀት፣ ድንገተኛ የሆነ የፍርሃትና የመሸበር ስሜት እንዲሁም የእንቅልፍ ማጣት ችግር የሚያስከትል “የድንገተኛ ሀብት ድምረህመም የተሰኘ አዲስ በሽታ” ፈጥሯል። ፖስት እንደጠቆመው “በቅርቡ በሀብት የበለጸጉ አንዳንድ ሰዎች ብዙ ገንዘብ በማካበታቸው የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማቸው ከመሆኑም በላይ መብቱ እንደሌላቸው ወይም ያካበቱት ሀብት እንደማይገባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል።” ሌሎቹ ደግሞ በጣም ተጠራጣሪ ይሆናሉ፤ በተጨማሪም ሌሎች መጠቀሚያ ያደርጉናል የሚል ስጋት ያድርባቸዋል። ዶክተር ጎልድባርት ደስታ የራቃቸው ቱጃሮች እንዲሁ ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች መዋጮ በማድረግ ብቻ ከመወሰን ይልቅ ወደ ማኅበረሰቡ ዘልቀው በመግባት በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ አበረታተዋል።

በለስላሳ መጠጦች ውስጥ ካፌይን የሚጨመረው ለምንድን ነው?

“ካፌይን ለስላሳ መጠጦችን የማያጣፍጥ ከሆነ ለምን ይጨመራል?” ሲል ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ጥያቄ አቅርቧል። “በባልቲሞር በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ሳይንቲስቶች ከ25 ዐዋቂዎች መካከል ካፌይን ያለውንና ካፌይን የሌለውን የኮላ መጠጥ መለየት የቻሉት ሁለቱ ብቻ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።” ሆኖም አሜሪካውያን በ1998 ከጠጧቸው 15 ቢልዮን ጣሳ የለስላሳ መጠጦች መካከል 70 በመቶዎቹ ካፌይን የተጨመረባቸው ነበሩ። ቀደም ሲል በተደረገ ጥናት ሳይኮፋርማኮሎጂስት ሮላንድ ግሪፍትስ እና ባልደረቦቻቸው “ቀደም ሲል ይጠጧቸው የነበሩትን ካፌይን ያላቸው ለስላሳ መጠጦች የተከለከሉ ልጆች ሱስ እንደያዛቸው የሚጠቁሙ ምልክቶች እንደታዩባቸው አረጋግጠዋል።” “በመጠኑ ሱስ የሚያስይዝ ንጥረ ነገር የሚጨምሩበት በመሆኑ ሰዎች ካፌይን ከሌላቸው ይልቅ ካፌይን ያላቸውን ለስላሳ መጠጦች በብዛት ይጠጣሉ” ሲሉ ግሪፍትስ ተናግረዋል።